Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር በእጥፍ ሊያሳድግ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ጊዜ የሚያንቀሳቅሳቸው 80 አውሮፕላኖች ሲኖሩት፣ በነደፈው የ15 ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መሠረት የአውሮፕላኖቹን ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2025 ደግሞ 150 እንደሚያደርስ ተገለጸ፡፡

አየር መንገዱ አዲስ ያስገባው ቦይንግ 787-8 ድሪምላይነር ዘመናዊ አውሮፕላን ባለፈው እሑድ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በደረሰበት ወቅት በተደረገው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም፣ አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት የ80 ዘመናዊ አውሮፕላኖች ባለቤት መሆኑን ጠቅሰው እ.ኤ.አ. በ2025 ይህን ቁጥር በእጥፍ እንደሚያሳድግ ተናግረዋል፡፡

አቶ ተወልደ ድሪምላይነርን የዘመኑ ምርጥ አውሮፕላን ሲሉ ያሞካሹት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሥር ድሪምላይነር አውሮፕላኖች እንዳሉትና በደንበኞች ዘንድም የተወደዱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ባለፈው እሑድ የገባው አዲሱ ድሪምላይነር 270 መቀመጫዎች ሲኖሩት ሁለት የጄኔራል ኤሌክትሪክ ሞተሮች ተገጥመውለታል፣ ከበፊቶቹ ለየት የሚለው የቢዝነስ ክላስ መቀመጫዎች እንደ አልጋ ሙሉ ለሙሉ መዘርጋት መቻላቸውና በዓይነቱ አዲስ የሆኑ የመዝናኛ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት መሆኑ ነው፡፡

አዲሱ ድሪምላይነር በዋሽንግተን ስቴት ሲያትል ከተማ ኤቨሬት አካባቢ ከሚገኘው የቦይንግ አውሮፕላን ማምረቻ 16 ሰዓታት የፈጀ ቀጥታ በረራ በማድረግ ከቀኑ 6፡30 ሰዓት ላይ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ተደርጐለታል፡፡ አውሮፕላኑን ያበረሩት ሁለት ኢትዮጵያዊያን ካፒቴኖችና ሁለት ረዳት አብራሪዎች ናቸው፡፡

አውሮፕላኑ እግረ መንገዱን 1,814 ኪሎ ግራም ክብደት ያላቸው መድኃኒቶችና የሕክምና መሣሪያዎች በኢትዮጵያና በሶማሊያ ለሚገኙ ሆስፒታሎች በነፃ አጓጉዟል፡፡

በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ላይ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የአየር መንገዱ ቦርድ አባላት፣ የቢዝነስ ክላስ ደንበኞችና ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት፣ የቦይንግና የጄኔራል ኤሌክትሪክ ኩባንያ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡ አምባሳደር ፓትሪሺያ ሃስላክ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምርጥ የአፍሪካ አየር መንገድ መሆኑን አስታውቀው፣ የድሪምላይነር አውሮፕላንን ገዝቶ በመጠቀም ከጃፓን በመቀጠል ሁለተኛ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ሌሎች ዘመናዊ የቦይንግ አውሮፕላኖች ወደ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

አየር መንገዱ በነደፈው በራዕይ 2025 የዕድገት መርሐ ግብር የተቀመጡ ግቦች በሙሉ በማሳካት ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ መርሐ ግብሩ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ አምስት ዓመት እንደሆነው ያስታወሱት አቶ ተወልደ፣ በአውሮፕላን ብዛትና አዳዲስ መዳረሻዎችን በመክፈት ረገድ በዕቅዱ ከተቀመጠው ቁጥር በላይ መኬዱን ተናግረዋል፡፡

አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት ለ80 አውሮፕላኖቹ በአምስት አኅጉሮች 84 መዳረሻዎች አሉት፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 50 ያህሉ አፍሪካ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አየር መንገዱ ቦይንግ 787፣ 777፣ 767፣ 757፣ 737፣ ኤምዲ 11 እና ቦምባርዲየር ኪው 400 አውሮፕላኖች ባለቤት ነው፡፡ በተጨማሪም 14 ኤርባስ 350-900 ጨምሮ በአጠቃላይ 43 አዲስ አውሮፕላኖች እንዲሠራለት ትዕዛዝ ሰጥቶ ለመረከብ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡

ባለፈው እሑድ የገባው አዲሱ ድሪምላይነር አውሮፕላን ለአሥር ዓመት ኪራይ የተወሰደው አይኤልኤፍሲ ከተባለ ድርጅት ሲሆን፣ ተጨማሪ ሁለት ተመሳሳይ አውሮፕላኖች በየካቲትና በሚያዚያ ወር ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ቀደም ሲል አየር መንገዱ ያስገባቸው አሥር ድሪምላይነር አውሮፕላኖች በግዥ መሆናቸው ይታወሳል፡፡ አየር መንገዱ ተጨማሪ ድሪምላይነር አውሮፕላኖች ለመግዛት ቢፈልግም፣ ከቦይንግ ኩባንያ ወረፋ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ በመሆኑም ሦስት ድሪምላይነር አውሮፕላኖችን ለረዥም ጊዜ ለመከራየት ተገዷል፡፡  

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች