Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበርካቶች በደስታ የተዋጡበት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የመጨረሻ ምዕራፍ ተጀመረ

በርካቶች በደስታ የተዋጡበት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የመጨረሻ ምዕራፍ ተጀመረ

ቀን:

‹‹በተስፋ ስንጠብቀው የነበረ ቀን ነው›› ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም

የባቡር ትራፊክ አስተዳደር ሕግ እየተዘጋጀ ነው

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ወደ ትራንስፖርት አገልግሎት ለመግባት የሚያስችለው የመጨረሻ ምዕራፍ የሙከራ አገልግሎት ጥር 24 ቀን 2007 ዓ.ም. በይፋ ተጀመረ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዚህ ፕሮግራም ላይ አራት ትራሞች (ቀላል ባቡሮች) አገልግሎት ላይ የዋሉ ሲሆን፣ በሙከራ ፕሮግራሙ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ቀዳማዊ እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን፣ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሯ ወ/ሮ አስቴር ማሞ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ የባቡር ኮርፖሬሽን ቦርድ ሊቀመንበርና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይና ሌሎች በርካታ ሚኒስትሮችና የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ታዋቂ ሰዎች ተገኝተዋል፡፡

የሙከራ ፕሮግራሙ በይፋ ከመጀመሩ በፊት ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ይህ ቀን በተስፋ ስንጠብቀው የነበረ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ቀን እስኪደርስ በተስፋና በትዕግሥት የገጠማቸውን ችግር ሁሉ ላሳለፉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከፍተኛ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ ወር መጨረሻ ላይ ሁሉ ነገሩ ተጠናቆ ለትራንስፖርት አገልግሎት ዝግጁ መሆን ቢኖርበትም፣ ይሁን እንጂ የተወሰነ መጓተት እንዳሳየ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ የተፈጠረው መጓተት በእንደዚህ ዓይነት ግዙፍና ምንም ዓይነት ልምድ በሌለበት አገር ውስጥ ሲታይ ግን ኢምንት ነው ብለዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን እንደ ናይጄርያ ያሉ አገሮች ከሰባት ዓመት በፊት መሰል ፕሮጀክት ጀምረው እስከዛሬ አለማጠናቀቃቸውንና የኢትዮጵያን ተሞክሮ ለመመልከትም፣ ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

በወቅቱ ንግግር ካደረጉት የመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል የአዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ከተቆረቆረች 127 ዓመታት ያስቆጠረችው አዲስ አበባ፣ በዘመናት ቅብብሎሽ በርካታ ማኅበራዊ ችግሮች ተተብትባ መቆየቷን አውስተዋል፡፡

ከተማዋ በአሁኑ ወቅት በሁለንተናዊ መልኩ እያስመዘገበች ያለው ለውጥ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የዘመናዊ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት መሠረተ ልማትና አገልግሎት ባለቤት በመሆን የአፍሪካ መዲናነቷን ይበልጥ የሚያጐላ፣ እንዲሁም አንድ ትልቅ የታሪክ አሻራ ነው ብለዋል፡፡

ይህ የባቡር ትራንስፖርት ከሦስት ወራት በኋላ እንደሚጀመር የተገለጸ ሲሆን፣ አገልግሎቱ ተግባራዊ ሲሆንም ሆነ በአሁኑ የሙከራ ወቅት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለጥንቃቄ ቅድሚያ እንዲሰጡ በሁሉም ኃላፊዎች ጥሪ ቀርቧል፡፡

በእግረኛ መሸጋገሪያዎች ብቻ እግረኞች እንዲጠቀሙ፣ የተዘረጋውን መሠረተ ልማት ኅብረተሰቡ ንብረቴ ነው ብሎ ዘብ እንዲቆም፣ ትራንስፖርቱ ሲጀመርም በየአካባቢው ከሚኖሩ የትራፊክ ፖሊሶች ጋር እንዲተባበርና የትራፊክ መብራት ምልክቶችን በጥንቃቄ እንዲያስተውል ጥያቄ ቀርቧል፡፡

በአሁኑ ወቅት የባቡር ትራፊክ አስተዳደር ሕግ ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ በመውሰድ እየተዘጋጀ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የባቡር ኮርፖሬሽን ቦርድ ሊቀመንበር ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ በበኩላቸው፣ ከአዲስ አበባው ቀላል ባቡር ፕሮጀክት በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ-ጂቡቲ የባቡር መስመር ዝርጋታ በመፋጠን ላይ መሆኑንና በቀጣዩ ዓመት እንደሚጠናቀቅ፣ እንዲሁም ከአዋሽ-ወልዲያ-መቀሌ ያለው የባቡር ፕሮጀክት ግንባታ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡

የቀላል ባቡር ሙከራ አገልግሎቱ ከቃሊቲ መስቀል አደባባይ ባለው መስመር ላይ የተጀመረ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ባቡር ላይም ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተሳፍረው በሞባይል ስልኮቻቸው ፎቶግራፍ ሲነሱ ተስተውለዋል፡፡

በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ባቡሩ በሚያልፍበት ቦታ ሁሉ በመውጣት ደስታቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...