Wednesday, December 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ለቀላል ባቡር መሠረተ ልማቱ ከፍተኛ እንክብካቤና ጥበቃ ያስፈልገዋል

  ባለፈው እሑድ በይፋ የሙከራ ሥራ የጀመረው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት አካል የሆነው፣ ከቃሊቲ ዴፖ እስከ መስቀል አደባባይ ያለው መስመር የዜጎችን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡ አጠቃላዩ የከተማ ባቡር ፕሮጀክት የግንባታ ወጪ 474 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ለኦፕሬሽንና ተያያዥ ሥራዎች 118 ሚሊዮን ዶላር ይወጣበታል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት የተከሰከሰበት መሠረተ ልማት በመሆኑ፣ እንክብካቤና ጥበቃ ያስፈልገዋል፡፡

  የቀላል ባቡር ፕሮጀክቱ የሙከራ ጊዜ የዛሬ ሦስት ወራት አካባቢ ሲጠናቀቅ መደበኛው የትራንስፖርት አገልግሎት ይቀጥላል፡፡ አዲስ አበባን ከሰሜን ወደ ደቡብ፣ እንዲሁም ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የሚያካልለው ይህ የቀላል ባቡር አገልግሎት በአግባቡ እንዲሠራ ከተፈለገ የመንግሥት፣ በየደረጃው ያሉ አስፈጻሚ አካላት፣ ባለድርሻ አካላትና ተገልጋዩ ሕዝብ የመንከባከብና የመጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

  እንደሚታወቀው ይህ መሠረተ ልማት የተገነባው ከቻይና በተገኘ ብድር ነው፡፡ ይህ ብድር ተመልሶ የሌሎች መሠረተ ልማቶች ግንባታ እንዲቀጥል አስተማማኝ ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ቀላል ባቡሩ በሚያልፍባቸው መስመሮች ውስጥ የሚገኙ የኤሌክትሪክና የስልክ መስመሮች፣ የባቡር ሐዲዶች፣ በግራና ቀኝ የተሠሩ መከለያዎችና ሌሎች ንብረቶች ከፍተኛ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በመንገድ መሠረተ ልማቶች፣ በኤሌክትሪክና በስልክ መስመሮች፣ እንዲሁም በውኃና መሰል የተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ የሚፈጸሙ ዝርፊያዎች እንዳይኖሩ ከወዲሁ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ የባቡር ፕሮጀክቱ የወጣበትን ወጪ መልሶ ለሌሎች መሠረተ ልማቶች የሚሆን ገቢ ማመንጨት ስላለበት ከወዲሁ ይህ በከፍተኛ ደረጃ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

  ማንኛውም ዜጋ የአገር ሀብት የሆነውን ይህንን ፕሮጀክት ልክ እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በማየት ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል፡፡ ለአገራችን አዲስ የሆነው የከተማ ባቡር አገልግሎት ያለምንም መስተጓጎል ሥራውን ሲያቀላጥፍ የሚጠቀመው፣ ታክሲ ጥበቃ በፀሐይና በውርጭ የሚደበደበው ሕዝብ ነው፡፡ በአንድ የጉዞ መስመር 15 ሺሕ ያህል ተገልጋዮችን ማስተናገድ የሚችለው ይህ የባቡር አገልግሎት እንዳይታወክ ከተፈለገ ዜጎች እንደ ራሳቸው ንብረት መንከባከብ ይኖርባቸዋል፡፡

  የባቡር አገልግሎቱን ሊያውክ ይችላል ተብሎ የሚገመተው ትልቁ ችግር የንፅህና መጓደል ነው፡፡ በተለያዩ የሕዝብ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚታየው የንፅህና ጉድለት በባቡር ተገልጋዮች ላይ ችግር ይፈጥራል፡፡ ይህ ዘመናዊ የባቡር አገልግሎት ምቾቱ ተጠብቆ ተገልጋዮችን ማርካት የሚችለው የፅዳት እንከኖች ሲወገዱ ነው፡፡ በሠለጠነው ዓለም እንደሚታየው በተለይ የከተማ ባቡሮች እጅግ ንፁህና ውብ ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያትም ምቾት አላቸው፡፡ እኛ ለንፅህና መጓደል ምክንያት ከሆንን የባቡሩን የአገልግሎት ዕድሜ በማሳጠር ወደተለመደው የትራንስፖርት ችግር እንገባለን፡፡ የባቡር አገልግሎቱ ዝቅተኛና ከፍተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ሊያስተናግድ ስለሚችል ለንፅህና ትልቅ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡ አገሪቱን የሚጎበኙ የውጭ ዜጎችንም ታሳቢ ሲደረግ ንፅህና ከፍተኛ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡

  በባቡር አገልግሎቱ ላይ ሌሎች ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ሕገወጥ ተግባራት ናቸው፡፡ በባቡር ላይ ዘረፋ መፈጸም፣ ሰዎችን በማስገደድ የማይፈልጉትን ተግባር ማድረግ (ፆታዊ ጥቃትና ሌሎች ተግባራት) እና የባቡሩን የውስጥ ንብረቶች መዝረፍና ማበላሸትን ያጠቃልላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሕገወጥ ተግባራት በሕግ የሚያስጠይቁ ከመሆናቸውም በተጨማሪ፣ የባቡሩን አገልግሎት የሚያደናቅፉ በመሆናቸው ለተጨማሪ ቅጣት ይዳርጋሉ፡፡ የባቡር አገልግሎቱ ቀልጣፋና አስደሳች መስተንግዶ እንዲኖረው የሚፈለግ ከሆነ ሕገወጦች መደበቂያ እንዳያደርጉት ከፍተኛ ክትትል መደረግ አለበት፡፡ ይህ በተለይ ከፌርማታዎች ጀምሮ መነሻና መድረሻ ተርሚናሎችን እንዲሁም በጉዞ ላይ የሚከሰቱ ድርጊቶችን ሳይቀር የሚያጠቃልል ነው፡፡

  የባቡር አገልግሎቱ ደኅንነቱ ተጠብቆ ተሳፋሪዎች የሚመች መስተንግዶ እንዲያገኙ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ከፍተኛ ተግባር ይጠብቀዋል፡፡ በመገናኛ ብዙኃንና በተለያዩ ዘዴዎች ኅብረተሰቡ ይህንን የአገር ሀብት እንዴት መጠበቅ እንዳለበት ተከታታይ የሆነ ግንዛቤ ማስጨበጥ ይኖርበታል፡፡ ከፍተኛ የአገር ሀብት የፈሰሰባቸው መሠረተ ልማቶች ጤናቸው ተጠብቆ ዘለግ ላለ ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ሲፈለግ፣ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ሕዝብ ሀብቱን በንቃት እንዲጠብቅ ከፍተኛ የውትወታና የጉትጎታ ሥራ መከናወን አለበት፡፡ እያንዳንዱን ጥቃቅን ግድፈት ለመከታተልና ለማረም የሚያስችል ግንዛቤ እንዲኖር ካልተደረገ፣ በአገር ሀብት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ይደርሳል፡፡ በሌሎች መሠረተ ልማቶች ላይ ሲፈጸም የነበረውን አሳዛኝ ድርጊት ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

  በእንክብካቤና በጥበቃ ጉድለት የአገር ሀብት ከወደመ በኋላ ጣት ከመቀሳሰር ይልቅ፣ ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ታሳቢ አድርጎ በንቃት መንቀሳቀስ የግድ ነው፡፡ አዲስ አበባን ከሠለጠኑ ከተሞች ተርታ ያሠልፋታል የተባለለት ይህ ትልቅ የሕዝብ ሀብት ከፍተኛ የሆነ እንክብካቤና ጥበቃ ያስፈልገዋል!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ለካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ስድስት የቦርድ አባላት ተሾሙ

  ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቦርድ ሰብሳቢ ሆነዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

  በሙስና የተጠረጠሩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው

  ብሔራዊ ፀረ ሙስና ኮሚቴ በክልሎችም ሊቋቋም ነው በቅርቡ ተቋቁሞ ወደ...

  የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚመራና የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ተቋም የመመሥረት ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ

  የኢንሹራንስ (መድን) ዘርፍን የመቆጣጠርና የመከታተል ኃላፊነት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...

  በትግራይና ሌሎች አካባቢዎች ከጦርነት ጋር ባልተያያዘ ጉዳት የደረሰባቸው ደንበኞች ካሳ እንዲጠይቁ ዕድል ሊሰጥ ነው

  በሰሜን ኢትዮጵያ ከነበረው ጦርነት ጋር ባልተያያዘ ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸው...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...

  ዘንድሮ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን በበይነ መረብ ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩ ተገለጸ

  በሁሉም መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሐ ግብሮች የሚመረቁ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ምሁራንና ልሂቃን ከአስተዋዩ ሕዝብ ታሪክ ተማሩ!

  አገራዊ ምክክሩን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ የኢትዮጵያን የትናንት ትውልዶችና የዛሬውን ይዘት መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ ያለፉት ዘመናት ትውልዶች ለአገራቸው የነበራቸው ቀናዒነት የፈለቀበት...

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...