Sunday, November 27, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናጦማሪያንና ጋዜጠኞች ሰብሳቢ ዳኛው እንዲነሱ ጠየቁ

  ጦማሪያንና ጋዜጠኞች ሰብሳቢ ዳኛው እንዲነሱ ጠየቁ

  ቀን:

  በሽብርተኝነት ወንጀል የተከሰሱት ጦማሪያንና ጋዜጠኞች፣ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ19ኛ ወንጀል ችሎት ሰብሳቢ (የመሀል) ዳኛ አቶ ሸለመ በቀለ እንዲነሱላቸው አቤቱታ አስገቡ፡፡

  ችሎቱ ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ተሰይሞ የነበረው የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ቢሆንም፣ ተከሳሾቹ በጠበቃቸው አቶ አመሐ መኮንን አማካይነት ባስገቡት አቤቱታ፣ ‹‹ዳኛው ላለፉት ስድስት ወራት በነበረው ክርክር የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብታችንን አላስጠበቁልንም፤›› በሚል እንዲነሱላቸው ጠይቀዋል፡፡

  ‹‹በተለያየ ጊዜም ሐሳባችንን ለመግለጽ ስንሞክር ክልከላ አድርገውብናል፡፡ አሁን ደግሞ ችሎቱ ራሱ የሰጠውን ትዕዛዝ ራሱ ሽሮ ፈጽሞ ልንረዳው በማንችለውና የመከላከል መብታችንን በሚያጣብ ክስ ክርክሩን እንድንቀጥል ሲበይን፣ የችሎቱ ሰብሳቢ ወሳኝ ሚና እንደነበራቸው ተሰምቶናል፤›› ሲሉ ተከሳሾቹ በአስገቡት አቤቱታ ገልጸዋል፡፡

  ተከሳሾቹ ላስገቡት አቤቱታ አንደኛው መሠረት ፍርድ ቤቱ ለሁለተኛ ጊዜ ክስ እንዲሻሻል ለዓቃቤ ሕግ ዕድል መስጠቱና እንዲያም ሆኖ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት ያልተሻሻለ ሆኖ ሳለ ተቀባይነት ማግኘቱ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ጥር 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ባሳለፈው ብይን ከዚህ ቀደም እንዲያሻሽል ካዘዛቸው አራት ክሶች ውስጥ ሦስቱን ሲቀበል፣ የተጠርጣሪዎችን የሥራ ክፍፍል በተመለከተ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ውድቅ አድርጎ ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

  ተከሳሾቹ ፍርድ ቤቱ ክሱን ሰርዞ ነፃ ሊያደርጋቸው ሲገባ ዓቃቤ ሕግ ክሱን እንዲያሻሽል ድጋሚ ዕድል መስጠቱን በአቤቱታቸው ተቃውመዋል፡፡ ‹‹በዚህ ሁኔታ የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ ሸለመ በቀለ ተከሳሾች የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብታችን እንዲከበር እንደ ሰብሳቢ ዳኛ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሳይወጡ ቀርተዋል፤›› ሲሉ በአቤቱታቸው ገልጸዋል፡፡

  በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀፅ 27 (1/ሠ) እና 28 መሠረት ‹‹ትክክለኛ ፍትሕ አይሰጥም የሚል በቂ ምክንያት ሲኖር›› የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ ከችሎቱ እንዲነሱ መጠየቅ እንደሚቻል ይደነግጋል፡፡

  ማመልከቻው ውሳኔ የሚያገኘው ማመልከቻ የቀረበበት ዳኛ በሌለበት በቀሩት ዳኞች እንደሚሆን ሕጉ ይደነግጋል፡፡ የሚሰጠው ውሳኔም የመጨረሻና ይግባኝ የማይባልበት ነው፡፡

  ማመልከቻው በቂ ምክንያት ሳይኖር የቀረ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ማመልከቻውን ውድቅ አድርጎ፣ በአመልካቹ ላይ እስከ የአምስት መቶ ብር መቀጫ እንደሚጥልበት ተደንግጓል፡፡

  ፍርድ ቤቱ በማመልከቻው ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለጥር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዟል፡፡ በተሻሻለው የዓቃቤ ሕግ ክስ መሠረት ተከሳሾች በፀረ ሽብር ሕጉ አንቀጽ 3(2 እና 4) ላይ የተቀመጡትን በመተላለፍ ነው የተከሰሱት፡፡ እነዚህም የኅብረተሰቡን ወይም የኅብረተሰቡን ክፍል ደኅንነት ወይም ጤና ለከፍተኛ አደጋ ማጋለጥና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ ናቸው፡፡

  በዚህ ክስ አሥር ተከሳሾች ሲኖሩ ዘጠኙ የዋስትና መብት ተከልክለው ለዘጠኝ ወራት ያህል በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ነው፡፡ አንደኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ ጉዳይዋ በሌለችበት እየታየ ነው፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...