Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአብዛኛዎቹ የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አባላት ሰማያዊ ፓርቲን ተቀላቀሉ

አብዛኛዎቹ የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አባላት ሰማያዊ ፓርቲን ተቀላቀሉ

ቀን:

ባለፈው ሳምንት የተላለፈውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔን ተከትሎ ዕውቅና የተነፈገው የአንድነት ፓርቲ የአቶ በላይ ፍቃዱ ቡድን አብዛኛው አባላት፣ ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀላቸውን የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት አስታወቁ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ይህን ያስታወቁት ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በፓርቲው ጽሕፈት ቤት ተገኝተው ፎረም የሞሉ የአንድነት አባላትን በተቀበሉበት ወቅት ነው፡፡

ፓርቲውን መቀላቀላቸው ካስታወቁት የቀድሞው አንድነት አመራርና አባላት መካከል አቶ አበበ አካሉ የቀድሞው አፈ ጉባዔ፣ አቶ ፀጋዬ አላምረው የቀድሞው ምክትል አፈ ጉባዔ፣ አቶ ነገሠ ተፈረደኝ የቀድሞው የአዲስ አበባ ሰብሳቢና አቶ ስንታየሁ ቸኮል የቀድሞው የአዲስ አበባ ሥራ አስፈጻሚና የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ ይገኙበታል፡፡

‹‹በግል መጡ የሚለው ነገር የሆነው ለሕግ ቴክኒካሊቲ ነው እንጂ፣ ብዙዎቹ የአንድነት አባላት እስከ ታች መዋቅር ድረስ በፍጥነት ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ተገናኝተው እየሠሩ ነው፤›› በማለት ኢንጂነር ይልቃል አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹በአብዛኛው የአንድነት መዋቅር በየክፍለ ሀገሩ ለዕጩዎች ምዝገባ በምንቀሳቀስበት ወቅት በጐንደር፣ በደሴ፣ በጐጃም እንዲሁም በሲዳማና በአርባ ምንጭ አብዛኛው የፓርቲው አባላት ተባባሪ ሆነው በግልጽ ከሰማያዊ ጋር እየሠሩ ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ ‹‹እኛ በሌለንበት ቦታ ላይ የሰማያዊ ፓርቲን ፎርም ሞልተው በዕጩነት ቀርበዋል፤›› በማለት የፓርቲው ፕሬዚዳንት አክለው አስረድተዋል፡፡

ቀደም ሲል የአንድነት ፓርቲ አፈ ጉባዔ የነበሩት አቶ አበበ አካሉ በበኩላቸው፣ ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ የተገኘነው የተወሰንን አንድ ዓይነት ዓላማና አስተሳሰብ ያለን ወገኖች፣ ቀደም ሲል በነበረው አንድነት ውስጥ በኃላፊነት ላይ የነበርንና አባላት ነን፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሰማያዊ ፓርቲና አንድነት የፕሮግራምና የደንብ መቀራረብና ተመሳሳይ የሆነ የትግል እንቅስቃሴም ስላለን ሰማያዊ ፓርቲን ለመቀላቀል ወስነናል፤›› በማለት ፓርቲውን የተቀላቀሉበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አቶ አበበ፣ ‹‹ምርጫ ቦርድ በቅርቡ የወሰነው ውሳኔ እስከዛሬ ስናደርገው የነበረውን ሰላማዊ ትግል በረዶ ስላፈሰሰበት፣ የትግሉ እንቅስቃሴ ደግሞ በየትኛውም መመዘኛ የማያቋርጥና የሚቀጥል መሆኑ ይገባናል የሚል ደረጃ ላይ በመድረሳችን ነው ፓርቲውን የተቀላቀልነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

የቀድሞ አንድነት የአዲስ አበባ ሰብሳቢ አቶ ነገሠ ተፈረደኝ፣ ‹‹በምናደርገው ትግል ለአገራችን ይበጃታል ብለን የምናምነው ሰላማዊ ትግል ብቻ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ሰላማዊ ትግልን መርጠን ዕውቅና ወዳለው ወደ ሰማያዊ ፓርቲ የመጣነው፤›› በማለት ፓርቲውን የተቀላቀሉበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም፣ ‹‹የበላይ ቡድን የተባለው በአንድ ወገን ዕውቅና ቢያጣም፣ በሰላማዊ ትግሉ ደግሞ ተሰባስበን ሰላማዊ ትግል ከሚያነሱ ኃይሎች ጋር መቆም ስላለብን፣ ሰማያዊን ለመቀላቀል ዛሬ በጽሕፈት ቤቱ ተገኝተን ፎርም ሞልተናል፤›› ብለዋል፡፡

ወደ ሰማያዊ ፓርቲ መምጣት ቁርጠኝነት ይጠይቃል ያሉት ደግሞ የቀድሞው አንድነት ፓርቲ ምክትል አፈ ጉባዔ አቶ ፀጋዬ አላምረው ሲሆኑ፣ ‹‹አለመታሰር የሚፈልግ ኃይል ሰማያዊ ፓርቲን ይቀላቀላል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይህ እምነታችን ደግሞ ፓርቲውን እንድንቀላቀል አድርጐናል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

‹‹በፓርቲው የተለያዩ መዋቅሮች ላይ ያሉ ተቋማት ምርጫችሁን አሳውቁን ወደ የት ነው የምንሄደው የሚል መልዕክት እያስተላለፉ ነው፡፡ ይህን መልዕክት ደግሞ ዛሬ እኛ አስተላልፈንላቸዋል፤›› ሲሉ ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀል ምላሽ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

‹‹ስለዚህ ሰማያዊ ፓርቲ ከአሁን በኋላ የአንድነትን ተቋም የመቀበልና የመሸከም አቅም ኖሮት፣ ይህንን አዳብሮ ትግሉን ወደፊት መምራት የሚችል አቅም አለው የሚል እምነት ነው ያለን፤›› በማለት አቶ ፀጋዬ ገልጸዋል፡፡

‹‹ከዚህ አንፃር ሰማያዊን መርጠናል፡፡ ይህን የመረጥነው ደግሞ እያንዳንዱ የአንድነት ተቋም ይህንን ተቀብሎ ከነገ ጀምሮ የአባልነት ፎርም እየሞላ ሰማያዊን ይቀላቀላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤›› በማለት አስተያየታቸውን አጠናቀዋል፡፡

በምርጫ ቦርድ የጊዜ ሠሌዳ መሠረት የዕጩዎች ምዝገባ ጥር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ይጠናቀቅ ነበር፡፡ ቦርዱ በፌስቡክ ገጹ ላይ ለአንድ ሳምንት መራዘሙን አስታውቋል፡፡ ይህ ቢሆንም ግን የጊዜው መጠናቀቅ ብዙም ችግር እንደማይፈጥርባቸውና አሁን ፓርቲውን የተቀላቀሉትን የአንድነት አባላትን በማሳተፍ የዕጩዎች ምዝገባ ሊከናወን እንደሚችል ኢንጂነር ይልቃል አስረድተዋል፡፡

ለዚህ የሚያቀርቡት ምክንያት ደግሞ፣ ‹‹የሰማያዊ ፓርቲ ሙሉ አባል ለመሆን የአንድ ቀን የሥራ አስፈጻሚ ውሳኔ ነው የሚፈልገው፡፡ ከዚህ አንፃር ከአንድነት የሚመጡ አባላት የዕጩነት ጊዜ ሳያስፈልጋቸው በሙሉ አባልነት ለመቀበል ወስነናል፡፡ ስለዚህ የሰማያዊ ሙሉ አባል ከሆኑ በኋላ ደግሞ የመምረጥም ሆነ የመመረጥ ሕጋዊ መብታቸው የተረጋገጠ ነው፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...