Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበጠቅላላ ጉባኤ የፀደቀው የቀይ መስቀል ማሻሻያ ቻርተር ለመንግሥት ይቀርባል

በጠቅላላ ጉባኤ የፀደቀው የቀይ መስቀል ማሻሻያ ቻርተር ለመንግሥት ይቀርባል

ቀን:

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ማቋቋሚያ ቻርተርን ለማሻሻል የተዘጋጀው ረቂቅ ፀደቀ፡፡ ረቂቁ የፀደቀው ጥር 24 ቀን 2007 ዓ.ም. በተካሄደው የማኅበሩ 17ኛ አገር አቀፍ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነው፡፡ የቻርተሩ ማሻሻያ ሐተታና ረቂቅ ላይ፣ ሰፋ ያለ ውይይት ከተካሄደ በኋላ ነው፡፡

ማኅበሩ ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሠራበት የቆየውን ቻርተር ማሻሻል ያስፈለገው በተለያየ ምክንያት ነው፡፡ በጦርነትና በአደጋ ምክንያት በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰው ስቃይ መልኩን እየቀየረ መምጣቱና ከፍተኛ የሆነ የአደጋ ተጋላጭነት በመከሰቱና የዚህንም አደጋ ውጤት ለመቀነስ የሚደረገው እንቅስቃሴ እየሰፋ ብሎም ውስብስብ እየሆነና ከፍተኛ አቅም እየጠየቀ መምጣት ከምክንያቹ መካከል ናቸው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በሰብአዊ አገልግሎት ድጋፍ ላይ የሚሳተፉ ብዛት ያላቸው የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተፈጥረዋል፡፡ ስለሆነም ከእነዚህ አዳዲስ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ጋር ማኅበሩ ራሱን ፈትሾና አስተካክሎ መሄድ ማኅበሩ የሚሠራበትን ቻርተር መፈተሽና ከጊዜው የሰብዓዊ አገልግሎት ፍላጐት ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ለጉባኤው ከቀረበው የቻርተር ማሻሻያ ሐተታና ረቂቅ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ስለዚህም የማኅበሩ ቻርተር በሥራ ላይ በቆየባቸው ዓመታት ውስጥ ሕጉ በሥራ ላይ ሲውል ያሉበትን ክፍተቶችና ችግሮችን በማጥናት ከ2002 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ የማሻሻያ ሥራ ሲከናወን ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ማቋቋሚያ እንዲሁም የሌሎች አገሮች የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ እንቅስቃሴ አካላትን መተዳደሪያ ቻርተርና ሌሎች ሕጎችን መፈተሽ ቻርተሩን ለማሻሻል ከተሠሩ ሥራዎች መካከል አንዱ ነበር፡፡

በቻርተሩ ከተካተቱ የማሻሻያ ሐሳቦች መካከል ማንም ሰው ከማኅበሩ ፈቃድ ሳያገኝ ዓርማውን መያዝም ሆነ በማንኛውም ሁኔታ መጠቀምና መገልገል እንደማይችል፣ የዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ በኅብረተሰቡ ዘንድ በስፋት እንዲታወቅ ማድረግ፣ ለሕጉ ተግባራዊነት መንግሥት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ማገዝና መደገፍ የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ማኅበሩ የእህት ማኅበራትን ጨምሮ ከአገር ውስጥና ውጪ ድርጅቶች ጋር የሚያደርጋቸውን የሥራ ግንኙነትና ስምምነቶች ቦርዱ አጠቃላይ መመርያዎችንና አቅጣጫዎችን እያስቀመጠ ዋና ጸሐፊው እንዲፈፅም ያደርጋል፡፡ ማኅበሩ ዓላማውን ለማስፈጸም ከውጭ በግዥም ሆነ በስጦታ በሚያስመጣቸው ዕቃዎች ከጉምሩክ ቀረጥና በገቢ ዕቃዎች ላይ ከሚጣል ታክሶች ነፃ ይሆናል የሚሉ ነጥቦችም ተሻሽለው ከተካተቱት ሐሳቦች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ቻርተሩ የሚሻሻለው ጉባኤተኞቹ ያፀደቁት ረቂቅ ወይም የማሻሻያ ሐሳብ ለመንግሥት ቀርቦ ሲፀድቅ ነው፡፡ በሚሻሻለውም ቻርተር መሠረት ምርጫና የሥራ ድልድል እስከሚደረግ ድረስ በሥራ ላይ ያሉ የማኅበሩ ተመራጮች ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ ታውቋል፡፡

በኢሊሌ ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ በተከናወነው በዚሁ ጉባኤ ላይ  የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የበላይ ጠባቂው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ማኅበሩ ሰብአዊ አገልግሎቱን አጠናክሮ ለመቀጠል በሚያካሂደው እንቅስቃሴ ላይ መንግሥት በገንዘብና በቁሳቁስ በማገዝ ከጐኑ እንደሚቆም ገልጸዋል፡፡

የማኅበሩ ቦርድ ተወካይ ተባባሪ ፕሮፌሰር ወንድወሰን ታምራት፣ ማኅበሩ የሚያሠራውን ሕንፃ በሚመለከት ‹‹የፍልውኃ ሁለገብ የሕንፃ ግንባታ ፕሮጀክትን በተመለከተ ከሚድሮክ ኮንስትራክሽን ጋር በተገባው ውል መሠረት ርክክብ ተፈጽሞ በአሁኑ ወቅት የግንባታው የመሬት ቁፋሮ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

ለሕንፃው ግንባታ ታስቦ የተዘጋጀውን የገቢ ማስገኛ ለማገዝ አምና በሁሉም ክልሎች የተጀመረው የአንድ ብር ለሰብአዊነት የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራ በያዝነው በጀት ዓመትም ተጠናክሮ እየተካሄደ እንደሚገኝ ከዚህም እንቅስቃሴም እስካሁን ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ለማግኘት ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከሐምሌ 1 ቀን 1927 ዓ.ም. ጀምሮ በአገሪቱ ብቸኛ የቀይ መስቀል ማኅበር በመሆን በጦርነት፣ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋዎች ለተጐዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገቢውን ዕርዳታና ድጋፍ ሲሰጥ የቆየ ድርጅት ነው፡፡ ሥራውንም ለማከናወን በ1927 ዓ.ም. ከወጣው አዋጅ በተጨማሪ በ1940፣ በ1962፣ በ1973፣ በ1982 ዓ.ም. በመንግሥት የተፈቀዱ ቻርተሮችን እንደ ሕጋዊ መሠረት ሲጠቀም መቆየቱ ይታወቃል፡፡    

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...