Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየአፍሪካ አገሮች ትብብር ላይ ጥያቄ ያስነሳው ኢቦላ

የአፍሪካ አገሮች ትብብር ላይ ጥያቄ ያስነሳው ኢቦላ

ቀን:

በዘንድሮው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ አጀንዳ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል የኢቦላ ወረርሽኝ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ነበር፡፡ ወረርሽኙ በተከሰተ በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ሥርጭቱን ለመግታት የተደረጉ እንቅስቃሴዎች አነስተኛ መሆን በእጅጉ መተቸቱን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ለተከሰተው ወረርሽኝ የሰጠው ምላሽ የዘገየ መሆን ችግሩን እንዳባባሰውም ተጠቁሟል፡፡ ኅብረቱ ጉዳዩን በሚመለከት ስብሰባ ያደረገውም ቫይረሱ ከታየ ከአሥር ወራት፤ የዓለም የጤና ሥጋት እንደሆነ ከታወጀ አንድ ወር በኋላ መሆኑ ለችግሩ ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠው ያሳያል ተብሏል፡፡

ወረርሽኙን ባለበት ለመቆጣጠር ከመሞከር ይልቅ እንዳይዛመት በሚል አንዳንድ አገሮች ድንበራቸውን መዝጋታቸው፣ በረራ መከልከላቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ዕርምጃ በወረርሽኙ የተጠቁት አገሮችን ጊኒ፣ ላይቤሪያና ሴራሊዮን እንዳገለለና እንዳሳዘነ በስብሰባው ላይ ተገልጿል፡፡

- Advertisement -

የሴራሊዮኑ ፕሬዚዳንት ኧርነስት ባይ ኮሮማ በበኩላቸው ወረርሽኙን ለመግታት ጋምቢያ ያደረገችላቸውን የ500,000 ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አድንቀው ሌሎች ጐረቤቶችን ወቅሰዋል፡፡ ‹‹እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች ከጐናችን የቆሙ አገሮችንና እውነተኛ አፍሪካዊነትን ያሳዩ አገሮችን አንረሳም፤›› ብለዋል፡፡ በቀጣይም ሁሉም አፍሪካዊ አገሮች፣ ድርጅቶች፣ ኢኮዋስና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወረርሽኙን ለማጥፋት በሚያደርጉት ጥረት እንደ ጋምቢያ ከጐናቸው እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሴራሊዮን ከፍተኛ ባለሥልጣን ኢብራሒም ቤን ካርቦ ከሳምንት በፊት ደቡብ አፍሪካ በአንድ በኩል ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪ ስትለግስ በሌላ በኩል ሴራሊዮናውያን ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ዕግድ መጣሏ እንዳስደነገጣቸው ገልጸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በወረርሽኙ የተጠቁ ግለሰቦችን ከመርዳት ይልቅ ማግለል መሆኑን ብዙዎች ይገልጻሉ፡፡ ዕርምጃውም አሳፋሪ መሆኑን አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ጠቁመዋል፡፡

ወረርሽኙ ለ9,000 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው አገሮችና ባለድርሻ አካላት የቤት ሥራቸውን ባለመሥራታቸው እንደሆነ የኔልሰን ማንዴላ ባለቤት ግሬስ ማሼል ገልጸዋል፡፡ ‹‹ወረርሽኙን ለመግታት የተሰጠው ምላሽ አነስተኛ መሆን ለሰው ልጅ ሕይወት የተሰጠውን አነስተኛ ግምት ያሳያል፤›› ሲሉ የአፍሪካ ኅብረት በጉዳዩ ያሳየውን ቸልተኝነት ኮንነዋል፡፡

‹‹በአህጉራዊ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በብሔራዊ የተሰጠው ምላሽ የዘገየ ነበር፤›› በማለት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ከተባበሩት መንግሥታት ዳይሬክተርና ከዓለም ባንክ ጋር ከጥቂት ወራት በፊት ባደረጉት ስብሰባ ላይ ገልጸው ነበር፡፡ ኅብረቱም የሚጠበቀበትን ያህል እንዳልሠራ አምነዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ከአፍሪካ ልማት ባንክና ከቢዝነስ መሪዎች ጋር በወረርሽኙ የተጠቁ ሰዎችን ለመንከባከብና ሥርጭቱን ለመቀነስ ባለፈው ኅዳር በአፍሪካ ኅብረት የገንዘብ ማሰባሰብ ፕሮግራም  28 ሚሊዮን ዶላር ቃል ተገብቶ ነበር፡፡

በጉባኤው ከተነሱ ነጥቦች መካከልም በወረርሽኙ የተጠቁ አገሮች ላይ የደረሰውን የኢኮኖሚ ድቀት ለማስተካከል ‹‹ሶሊዳሪቲ ፈንድ›› እና የአፍሪካ በሽታ የመከላከል ማዕከል ማቋቋም ዋነኞቹ ነበሩ፡፡ እስካሁን በተደረገ ርብርብ ምንም እንኳ የዘገየ ቢሆንም ውጤት ለማስመዝገብ መቻሉን የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡ ሒደቱንም ‹‹ሥርጭቱን ከማዘግየት ሥራ ወደ መግታት ተቀይሯል፤›› ሲል አስታውቋል፡፡

‹‹አሁን ማየት ያለብን በኢቦላ ወረርሽኝ ምክንያት የተጐዳውን ኢኮኖሚና የገንዘብ አቅማችንን እንዴት መጠገን እንችላለን የሚለውን ነው፤›› ሲሉ የጊኒው ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ ባለፈው ሳምንት ገልጸው ነበር፡፡   

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...