Sunday, September 25, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህልበሙዚቃ የተግባቡት ‹‹ቋንቋ››ዎች

  በሙዚቃ የተግባቡት ‹‹ቋንቋ››ዎች

  ቀን:

  ሦስት ኢትዮጵያውያንና አሜሪካዊት ሙዚቀኛ የተካተቱበት ባንድ ‹‹ቋንቋ›› ይባላል፡፡ አባላቱ ከሳምንታት በፊት በትሮፒካል ጋርደን በተካሔደው ሰላም ፌስቲቫል ላይ ያቀረቡት ሙዚቃ በክራር፣ ከበሮና ቫዮሊን የተቀናበረ ነበር፡፡

  የኢትዮጵያን ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ከቫዮሊን ጋር በማጣመር በመሣሪያ ብቻ የተቀነባበረ ሙዚቃ ያስደመጠው ባንዱ፣ የቫዮሊን ተጫዋች ኬታ ሆስታተር፣ ቤዝ ክራር ተጫዋች ዳዊት ሥዩም፣ ክራር ተጫዋች መሰለ አስማማውና ከበሮ ተጫዋች ሳምሶን ሰንደቁን የያዘ ነው፡፡

  ክራር ተጫዋቹ መሰለ ከቋንቋ ባንድ በተጨማሪ በበርካታ ባህላዊ ሙዚቃ አልበሞች ላይ ተሳትፏል፡፡ ከሀብተሚካኤል ደምሴ እና ዓለማየሁ ፋንታ ጋር በጥምረት የሠራቸውም ይጠቀሳሉ፡፡ ኬታ አሜሪካ ውስጥ ‹‹ደቦ›› የተባለና በኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ ላይ ዋነኛ ትኩረቱን ያደረገ ባንድ አባል ነበረች፡፡ ቫዮሊን እንደመሰንቆ ያለ ድምፅ እንዲያወጣ አድርጋ በመጫወት የምትታወቅ ሲሆን፣ በባህላዊ ሙዚቃ ዙሪያ ለዓመታት ሠርታለች፡፡ ቤዝ ክራር ተጫዋቹ ዳዊት በ2005 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ወክሎ በናይል ፕሮጀክት ተሳትፎ ነበር፡፡ በቴአትር ቤቶች እና በሌላም ስፍራ በባህላዊ ሙዚቃ የሚታወቀው ዳዊት ከብዙ ሙዚቀኞች ጋር ተጣምሮ ሠርቷል፡፡

  ኬታ እንደምትለው፣ ባንዱን ለመመሥረት ስታቅድ በቅርበት የምታውቃቸውን ባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች ለማካተት ፍላጐት ነበራት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በመጣችባቸው አጋጣሚዎች ከመሰለ ጋር በተደጋጋሚ ተጣምረው ሠርተዋል፡፡ ከሳምሶንና ዳዊት ጋር የተገናኘችው በፈንድቃና ሌሎች አዝማሪ ቤቶች ነበር፡፡ አራቱም አዲስ ዓይነት ሙዚቃ ለመሥራት በመፈለጋቸው ስብስቡን ፈጥረዋል፡፡ ባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃ መሣሪያ ለመቀየጥ ያላቸው ተመሳሳይ ፍላጐት አብሮነታቸውን አጠንክሮታል፡፡ ለኬታ፣ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከተለያዩ ዘመናዊ መሣሪያዎች ጋር በማጣመር መሥራት አስደሳች ውጤት ያለው ተሞክሮ ነው፡፡

  ቋንቋ ባንድ በብዛት የሚጫወተው በሙዚቃ መሣሪያ የተቀነባበረ ሙዚቃ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ድምፃውያን ቢጋብዙም የሙዚቃ መሣሪያዎቹ ጐልተው እንዲደመጡ በሚል አዘውትረው ያለ ድምፃዊ ይጫወታሉ፡፡ ኬታ እንደምትለው፣ ብዙ ጊዜ ድምፃውያን በባንድ ከታጀቡ ተመልካች ሙሉ ትኩረቱን ወደ ድምፃውያኑ ያደርጋል፡፡

  የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች ተነጥለው መሥራታቸው ሥራቸው እንዲደመጡ ያደርጋል ትላለች፡፡ አንዳንዴ አባላቱ ሙዚቃቸውን ለማጀብ ይዘፍናሉ፤ አንዳንዴም ሌላ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች ይጋብዛሉ፡፡ ኬታ ግን ድምፃውያን ሳይኖሩ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች የበለጠ እንደሚደመጡ በአጽንኦት ትናገራለች፡፡

   ቋንቋ ባንድ ከተመሠረተ አራት ዓመቱ ሲሆን፣ አሜሪካ ውስጥ ፕሮዲውስ የተደረገ አንድ አልበም አሳትመዋል፡፡ አልበሙ በድረ ገጽ ላይ የተለቀቀ ሲሆን፣ በቅርብ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚከፋፈል አባላቱ ይናገራሉ፡፡

  አልበሙ በአሜሪካ ውስጥ ጥሩ ተደማጭነት እንዳገኘ ነው አባላቱ የሚናገሩት፡፡ ሙዚቃው ከተለመደው በተለየ ዘዬ መሠራቱ ተወዳጅ እንዳደረገውም እምነታቸው ነው፡፡ ቀጣይ አልበማቸውን ለማሳተም በዝግጅት ላይ ያሉት አባላቱ፣ የመጀመሪያ አልበማቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ባይለቀቅም አድማጭ ለሙዚቃቸው ያለውን በጐ አመለካከት በተለያዩ መድረኮች ከተሰጣቸው ምላሽ እንደተገነዘቡ ይገልጻሉ፡፡

  ከዚህ ቀደም ጉራማይሌ፣ ሌስካልና ቺላክስን በመሰሉ መዝናኛዎች እንዲሁም በአኬሻና ሰላም ፌስቲቫል ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ መሰለ እንደሚለው፣ እስከዛሬ ለሙዚቃቸው ያገኙት ምላሽ አበረታች የሚባል ነው፡፡ ባህላዊና ዘመናዊ መሣሪያዎችን በማዋሀድ የሚያስደምጧቸው ኤክስፐርመንታል ሙዚቃዎች ከአድማጭ በተጨማሪ ከሙዚቃ ባለሙያዎች አወንታዊ ምላሽ እንዳገኙ ይገልጻል፡፡

  በባንዱ ሙዚቀኞች ከሚሠሩ ቅንብሮች ውጪ የአንጋፋ ሙዚቀኞችን ነባር ሥራዎች በራሳቸው ቅንብሮች ያዘጋጃሉ፡፡ ቡድኑ በኢምፕሮቫይዜሽንና ኤክስፐርመንታል ሙዚቃ ላይ ማተኮሩ ልዩ ልዩ ጥዑመ ዜማዎችን ለመሥራት እንዳስቻለው አባላቱ ይናገራሉ፡፡

  ዳዊት እንደሚለው፣ ባህላዊ ሙዚቃን ከዘመናዊ ጋር ማዋሀዳቸው በርካታ ዓለም አቀፍ ሙዚቀኞችን ስቧል፡፡ ጊታር፣ ሳክስፎን፣ ፐርከሽን፣ ኪቦርድንና ሌሎችም የሙዚቃ መሣሪያዎችን የሚጫወቱና ከቋንቋ ጋር በጋራ የሠሩ የውጭ ሙዚቀኞችን ይጠቅሳል፡፡ ከኢትየጵያ ማሲንቆ ተጨዋቹን እንድሪስ ሀሰንና የሬጌ ሙዚቃ የሚጫወቱትን ኢምፔሪያል ማጂስቲክ ባንድ ያነሳል፡፡ እንደ ሙዚቀኛው ገለጻ፣ ብዙዎች የኢትዮጵያን ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ከዘመናዊ ጋር ለማዋሀድ ሲደፍሩ ባይታይም፣ የሌሎች የአፍሪካ አገሮችን ሙዚቃ ዓለም አቀፍ ተደማጭ ለማድረግ አግዟል፡፡

  የማሊ ሙዚቃ ባህላዊ ይዘቱን እንደያዘ በዓለም መሰማት እንደቻለው ለኢትዮጵያ ሙዚቃም ጥሩ መንገድ የሚከፍት ይሆናል ይላል፡፡ ኬታ ከቀደመው ጊዜ አንፃር ‹‹ኢትዮጲክስ››ና ኢትዮ ጃዝን በመሰሉ ሥራዎች የኢትዮጵያ ሙዚቃ እየታወቀ መጥቷል ትላለች፡፡ በሀሳቡ የሚስማማው መሰለ፣ ከውጭ ሙዚቀኞች ጋር ኮንሠርትና ፌስቲቫል ማቅረብ ለሙዚቃው ዕድገት እንደሚያግዝ ያምናል፡፡

  ባንዱ የራሱ መለማመጃ ቦታ አለማግኘቱና አድማጮች ቋሚ ዘፋኝ እንዲኖሯቸው መወትወታቸውን እንደ ችግር ያነሱታል ይህም የፈጠራ ሥራቸውን የሚገድብ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እንደ ኬቲ፣ በገንዘብ በኩል የባንዱ ሥራ ከክፍያው አንፃር ተመጣጣኝ አይባልም፡፡ ዝግጅት ሲኖራቸው ጥራት ያለው ሳውንድ ሲስተም አለማግኘታቸውንም ትጠቅሳለች፡፡ ዳዊትም ጥሩ ሳውንድ ሲስተም አለመኖሩ ሙዚቃቸው በጥራት እንዳይደመጥ እንደሚያደርግ ይናገራል፡፡

  መሰለ በበኩሉ የሙዚቃ ሥራቸውን መስመር የሚያስይዝ ማናጀር ቢኖር አሁን ካላቸው በበለጠ ሥራቸውን በብዙ መድረክ ለማቅረብ ያስችላቸዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ እየተዘዋወሩ ለመሥራት ስፖንሰር የሚያደርጉ ተቋሞች እንደሚያስፈልጉ፣ ሙዚቃውን የሚደግፉ ተቋሞች መበራከት እንዳለባቸውና የተሻለ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያስረዳል፡፡

  መሰለ ፌስቲቫሎች ሙዚቀኞችን በማገናኘትና የኢትዮጵያን ሙዚቃ በሌሎች አገሮችም ታዋቂ ለማድረግ እንደሚያግዙ ይናገራል፡፡ በግለሰቦች የሚዘጋጁት በቂ ስላልሆኑ መንግሥት እጁን ቢያስገባበትና ድጋፍ ቢያደርግ ለውጥ ይመጣል ይላል፡፡ ዳዊትም የመሰለን ሀሳብ ይጋራል፡፡ ከጐረቤት የአፍሪካ አገሮች አንፃር የኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ደካማ ነው ይላል፡፡ ኮንሠርቶችና ፌስቲቫሎች ቋንቋን ለመሰሉ ባንዶችና ወጣት ሙዚቀኞች ልምድ ለመቅሰም ያስችላል፡፡

  ‹‹ሙዚቃ የዓለም መግባቢያ ቋንቋ ነው፤›› የሚለውን ብሒል አባላቱ በተደጋጋሚ ይጠቅሳሉ፡፡ መጠሪያቸውም ይህን የሚያንፀባርቅና የተነሱለትን ዓላማ የሚያሳይ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከተለያየ ሀገር ቢመጡም በሙዚቃ ቋንቋ ተግባብተው ሙዚቃ መሥራታቸው መጠሪያቸውን እንደሚገልጽ መሰለ ያስረዳል፡፡

  መሰለ በሙዚቃቸው ለውጥ እንደሚያመጡ ያምናል፡፡ ሌሎች ሙዚቀኞች እየሠሩ ካሉት የተለየ አማራጭ ማቅረብን እንደ ግባቸው ይወስደዋል፡፡ ዳዊት ‹‹ሙዚቃችን የሰውን ስሜት የሚያንፀባርቅ ነው›› ይላል፡፡ በማንኛውም ዓይነት የሙዚቃ መሣሪያ የየትኛውንም አገር ሙዚቃ በመጫወት ትስስር መፍጠር መቻል ግባቸው እንደሆነም ይናገራል፡፡

  ኬታ የሰው ልጅ በዕድሜ፣ በፆታ፣ በዘር፣ በሃይማኖት ሳይከፋፈል የሚያዳምጠው ሙዚቃ ማቅረብ ዋነኛ ዓላማቸው መሆኑን ታስረዳለች፡፡ ሁሉንም በማማከል ረገድ በመሣሪያ ብቻ የተቀነባበረ ሙዚቃ በመሥራት ግባቸውን እንደሚመቱ ትናገራለች፡፡ ‹‹ቋንቋ››ዎች ከወራት በኋላ ሁለተኛ አልበማቸው እንደሚወጣ ይናገራሉ፡፡

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...