Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምሴቶችን ያንበረከኩ አመለካከቶች

ሴቶችን ያንበረከኩ አመለካከቶች

ቀን:

በፆታ እኩልነት ላይ የሚያጠነጥነው የቤጂንግ የትግበራ መርሐ ግብር ከፀደቀ 20 ዓመታት፣ የሚሊኒየሙ የልማት ግብ መተግበር ከጀመረ 15 ዓመታት፣ በአፍሪካ የሚገኙ ሴቶችን መብት ለማስጠበቅ የሚያስችለውን ፕሮቶኮል አፍሪካ ከተቀላቀለች አሥር ዓመታት፣ እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት እ.ኤ.አ. ከ2010 እስከ 2020 የሴቶች ዓመት ብሎ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ መሥራት ከጀመረ አምስት ዓመታትን ቢያስቆጥሩም፣ ለአፍሪካ ሴቶች መብታቸው ተከብሮ የመኖር በር ገና አልተከፈተም፡፡

በአፍሪካ ሴት ወጣቶችና እናቶች ዛሬም በወንዶች ይገረፋሉ፣ ይረገጣሉ፣ ይናቃሉ፣ አይችሉም ተብለው ይፈረጃሉ፡፡ የፖለቲካና የትምህርት ተሳትፏቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ የቱንም ያህል ቢማሩም አብዛኛዎቹ ከወንዶች ጥገኝነትና ረገጣ አልተላቀቁም፡፡ ይልቁንም ወንዶች በሴቶች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት በአፍሪካ መድኃኒት ያልተገኘለት ወረርሽኝ ሆኗል፡፡

በሴት ወጣቶችና እናቶች ላይ የከፋ ጭካኔ መፈጸም፣ አቅዶ መደብደብ፣ ሴቶችን ያለማብቃት እንዲሁም የፆታ እኩልነት ክፍተቶች አልቀነሱም፡፡ በተቃራኒው በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ከመስፋፋት ባለፈም እንደ ተቋም መሠረት ጥሎ ሥር ሰዷል፡፡

ጥር 22 እና 23 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ ባስተናገደችው 24ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ፣ ‹‹ይር ኦፍ ውሜንስ ኢምፓወርመንት ኤንድ ዴቨሎፕመንት ኢን አፍሪካ›› በሚል ጭብጥ የቀረበ ሲሆን፣ በጉባዔው ላይ የቀረበ ስኮር ካርድና ፋክት ሽት እንዳመለከተው፣ በአፍሪካ አብዛኞቹ ወንዶች የሴቶችን ሕይወት ከባድ አድርገውታል፡፡

እንደ መረጃው ከሆነ፣ ባለፈው ሩብ ዓመት በአፍሪካ ከ25 በመቶ እስከ 75 በመቶ የሚሆኑና በ15 እና በ49 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣት ወንዶችና አባቶች ሴቶች ምግብ ሲያበስሉ ካረረባቸው፣ ከወንዶቹ ጋር ከተከራከሩ ወይም መልስ ከሰጡ፣ ለባሎቻቸው ሳይነግሩ ከቤት ከወጡ፣ ልጆች በደንብ ካልተንከባከቡ፣ ወይም የወሲብ ጥያቄን ካልተቀበሉ መመታት አለባቸው ብለው ያምናሉ፡፡ ሴቶች በተጠቀሱት ምክንያት መመታት አለባቸው ብለው የሚያምኑ አብዛኞቹ ወንዶች፣ ከ54 የአፍሪካ አገሮች በተለይ በ25ቱ ውስጥ ተንሰራፍተው ይገኛሉ፡፡    

ሴቶች በተጠቀሱት ምክንያቶች መመታት አለባቸው ብለው የሚስማሙና ትክክል ነው ብለው የሚያምኑ ከ15 እስከ 49 የዕድሜ ክልል የሚገኙ ወንዶች በመቶኛ ሲሰሉ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ 75 በመቶ፣ ጊኒ 66 በመቶ፣ ኮንጐ 62 በመቶ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ 52 በመቶ፣ ዛምቢያ 49 በመቶ፣ ሌሴቶ 48 በመቶ፣ ማዳጋስካር 46 በመቶ፣ ኢትዮጵያ 45 በመቶ፣ ኤርትራ 45 በመቶ፣  ብሩንዲ 44 በመቶ፣ ኬንያ 44 በመቶ፣ ኡጋንዳ 44 በመቶ፣ እንዲሁም ኮትዲቯዋር 42 በመቶ ናቸው፡፡

በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት እንዲሁ እንደሚቀጥል የሚያመለክተው ደግሞ፣ በወጣትነት የዕድሜ ክልል የሚገኙ ወንዶች በጐልማሳነት እንደሚገኙት ሁሉ በሴቶች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት እያቆጠቆጠና ሥር እየሰደደ መሆኑ ነው፡፡ ከ50 በመቶ ያላነሱ ወጣት ወንደችም ሴቶች መመታት አለባቸው የሚለውን አመለካከትና ድርጊት ትክክል ነው ብለው ያምናሉ፡፡  

በአፍሪካ በሚገኙ ስምንት አገሮች ውስጥ ከ15 እስከ 19 የዕድሜ ክልል ከሚገኙት ወንዶች ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ፆታዊ ጥቃት ትክክል ነው ብለው የተቀበሉ ናቸው፡፡ እንደ መረጃው ከሆነ፣ በዚህ የዕድሜ ክልል ከሚገኙ ወንዶች መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ 87 በመቶ፣ ብሩንዲ 56 በመቶ፣ ኬንያ 54 በመቶ፣ ሌሴቶ 54 በመቶ፣ ኡጋንዳ 52 በመቶ፣ ኮትዲቫዋር 51 በመቶ እንዲሁም ኢትዮጵያ 51 በመቶ የጥቃቱን ትክክለኛነት የሚቀበሉ ናቸው፡፡

መገረዝ፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ መደፈር፣ መደበደብ፣ መሰደብ፣ ለረዥም ሰዓታት በቤትና በውጭ ሥራ መጠመድ ከሚያሳድሩት ተፅዕኖ ባለፈ ሴቶች በማኅበረሰቡ ያላቸው ቦታና የሚሰጣቸው ግምት እንዲሁም የሚገለጹበት መንገድ፣ ሴቶቹ ራሳቸው ሁኔታው ትክክል ነው ብለው እንዲያምኑና እንዲቀበሉ አድርጓቸዋል፡፡

መረጃ ከተወሰደባቸው 42 የአፍሪካ አገሮች ከ15 እስከ 49 የዕድሜ ክልል ከሚገኙ ሴቶች ከ25 በመቶ እስከ 92 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ምግብ ሲያበስሉ ካሳረሩ፣ ከባሎቻቸው ጋር ከተከራከሩ፣ ሳያስፈቅዱ ወይም ሳይናገሩ ከቤት ከወጡ፣ ልጆችን ካልተንከባከቡና የወሲብ ጥያቄን ካልተቀበሉ መመታት አለባቸው ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡

መረጃ በተሰበሰበባቸው 45 አገሮች ውስጥ በሚኖሩ ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት ትክክለኛ ነው ብለው የተናገሩ ሴቶች ቁጥር በመቶኛ ሲሰላ ዝቅተኛውን ሥፍራ የሚይዘው የማላዊ ብቻ ነው፡፡ በማላዊ ዳሰሳ ከተደረገባቸው ወጣት ሴቶች 16 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው የሴቶችን ጥቃት ትክክለኛ ነው ብለው የተናገሩት፡፡

በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአፍሪካ ሴቶች በራሳቸው ላይ የሚደርስን ጥቃት ትክክል ነው ብለው እንዲቀበሉ፣ መንግሥታት ለሴቶች ጥቃት የሚሰጡት ምላሽ አናሳ መሆን በችግሩ ሰለባዎች ላይ የፈጠረው አሉታዊ የማኅበረሰብ አቀባበል ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡ በሌላም በኩል ያለዕድሜ ጋብቻና የግዳጅ ጋብቻ፣ የሴቶች ሕገ መንግሥታዊ መብት አለመከበር፣ ሰብዓዊ መብታቸው መጣስ፣ የሴቶች የዜግነት መብት አደጋ ላይ መውደቅ አፍሪካ ላለመችው ቀጣይነት ያለው ዕድገት አደጋ ነው፡፡

የአፍሪካ አገሮች የወጣት ሴቶችንና የእናቶችን የዜግነት መብት ማስጠበቅ አለመቻላቸው፣ ሴቶች ለከፋ ጥቃት እንዲጋለጡ አድርጓል፡፡ ሴቶችን ለጥቃት ማጋለጡ ደግሞ በሴቶች ትምህርት፣ በኤችአይቪ/ኤድስ፣ በሥነ ተዋልዶ፣ በወሊድ፣ በሕፃናት ጤና፣ በማህፀን ካንሰር፣ በአዕምሮ ሕመምና በሌሎች ሕመሞች የኢኮኖሚ አቅም ለመገንባት፣ የፖለቲካ ተሳትፎና አጠቃላይ የድህነት ቅነሳን አስመልክቶ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለተቀመጡት የልማት ግቦች ቦታ አለመስጠት ነው፡፡

በሴቶች ላይ የሚደርስ የከፋ ጥቃት ዛሬ የተጀመረ አይደለም፡፡ ሥር እየሰደደ መሆኑን በማመላከት ችግሩን ለመቅረፍ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሕፃናት መርጃ ድርጅት፣ ዩኤንኤፍፒኤ፣ ዩኤን ውሜን፣ እንዲሁም ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት በተለያዩ ጊዜያት ችግሩ ትኩረት እንዲሰጠው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ዲፕሎማሲያዊ የሆነው አካሄድ ለውጥ ማምጣት አልቻለም፡፡ ይልቁንም ሴቶች ለከፋ ጥቃት እየተጋለጡ ይገኛሉ፡፡ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በህንድና በሌሎች አገሮች ሴቶች ከሚደርስባቸው ድብደባ በከፋ በቡድንና በነጠላ ይደፈራሉ፡፡ በቤት ውስጥ ሠራተኝነትን በአሠሪዎቻቸው የከፋ በደል ይደርስባቸዋል፡፡  

አፍሪካ 99 በመቶ የሚሆኑ ሴቶችና ወንዶች ዜጐቿ፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ትክክል ነው ብለው እስኪቀበሉ መጠበቅ እንደሌለባት መረጃው ያሳያል፡፡ በአፍሪካ በግጭት ውስጥ በሚገኙ አገሮች የሚኖሩ ሴቶች ከሚደርስባቸው የወሲብ ጥቃትና የታገቱ ሴቶችን ለትዳር ከመሸጥ ባለፈ፣ ሰላም አለባቸው በሚባሉት አገሮች በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ብሷል፣ ተስፋፍቷል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአፍሪካ የሴቶችን መብት ለማስከበር፣ ከጥቃት ለመከላከልና የኢኮኖሚው ተጠቃሚ ለማድረግ በየኮንፍረንሱ የፀደቁ ዲክላሬሽኖች ተግባራዊ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡   

በመሆኑም የአፍሪካ አገሮች በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለመታደግ ወንዶች ትክክል ነው ብለው የተቀበሉትን ሴቶችን የማጥቃት ልማድ ተቀባይነት ማሳጣትና ሴቶችም ያላቸውን ተመሳሳይ አመለካከት መለወጥ እንዳለባቸው፣ ለሕግ አስፈጻሚው አካል ሥልጠናና ትምህርት መስጠትና በፆታ እኩልነትና በሴቶች መብቶች ዙርያ የማሻሻያ ሐሳቦች መካተት የግድ ነው እየተባለ ነው፡፡

ለመከላከያ ሠራዊቶች አስቸኳይ የሆነ የፆታ እኩልነትና የሴቶች ሰብዓዊ መብት ትምህርት መስጠት፣ በተለይ በግጭት ቀጣናዎች በሴቶች ላይ የሚደርስ የወሲብ ጥቃትን ለመቀነስ ያስችላል የሚል አስተያየትም ተሰጥቷል፡፡

በሕጐችና በፍትሕ ዙሪያ ክለሳ ማካሄድ፣ በመገናኛ ብዙኃን ሴቶች የሚተረኩበት፣ የሚታዩበትና የሚዘገቡበትን አሉታዊ አካሄድ መቀነስና ማጥፋት፣ በሴቶች መደበኛ ትምህርት ላይ ያለውን ኢንቨስትመንት ማሳደግ፣ ነፃ ብሔራዊ የፆታ እኩልነት፣ እንዲሁም የሴቶች መብት ኮሚሽን መመሥረት እንደ መፍትሔ ከተቀመጡ ሐሳቦች መካከል ይገኙበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...