የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሪሴፕ ታይፕ ኤርዶጋን፣ በጥር አጋማሽ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቆዳ ላይ የተሣለ ምስላቸውን አበርክተውላቸው ነበር፡፡
ፎቶ በመስፍን ሰሎሞን
*********
ዝቅ ብሎ ከፍ ማለት
ሰው ውስጡ ለመልካም፣ የተሰበረ’ለት
ያኔ ተገንብቷል፣ ጠንክሮ እንደ አለት
ጥበቡን ላገኘ፣ በ’ርግጥ ላስተዋለ
ዝቅ በማለት ውስጥ፣ ከፍ ማለት አለ
ታምራት መቻል ‹‹እንደ ባቢሎኖች›› (2007)
* * *
‹‹ጉድ በል ብራዚል››
‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም›› እንዲሉ፤ መሰንበቻውን ከጉድም ጉድ የተሰማው ከላቲን አሜሪካዊቷ ብራዚል ነው፡፡ በዓመታዊው የወይዘሪት አማዞን የቁንጅና ውድድር ያልተለመደ እንግዳ ክስተት ተፈጥሮ ነበር፡፡
ፎክስ ኒውስ ላቲኖ በድረ ገጹ እንደዘገበው፣ የብራዚል የቁንጅና ውድድር ያበቃው በመሸነፏና ሁለተኛ በመውጣቷ የተበሳጨችው ተወዳዳሪ አሸናፊዋ የድሏን አመልካች አክሊል (ቲያራ) በራሷ ላይ እየተደረገላት ሳለ ከጀርባዋ በመምጣት መንጭቃ መውሰዷና በመሬት ላይም መወርወሯ ነበር፡፡
በሰሜናዊቷ ብራዚል ማናውስ ከተማ የተከናወነውን የቁንጅና ውድድር የ20 ዓመቷ ካሮሊና ቶሌዶ በማሸነፍ ‹‹የወይዘሪት አማዞን 2015›› አክሊልን መድፋቷ ያልተዋጠላት የ2013 የግሎብ ኢንተርናሽናል የቁንጅና ውድድር አሸናፊዋ ሼስላኔ ሃያላ፣ ቶሌዶ አክሊሉን ‹‹ገዛችው›› እንጂ አላሸነፈችም ብላለች፡፡
ወይዘሪት አማዞን ቶሌዶ፣ ሪቫኑ ተጠልቆላትና ቲያራው እየተደፋላት ሳለ ሃያላ ከፀጉሯ ላይ መንጭቃ በመወርወር መድረኩን የለቀቀችው ለታዳሚው ሰላምታ በመስጠት ነበር፡፡ የወይዘሪት አማዞን አሸናፊ ዘንድሮ በብሔራዊ ደረጃ በሚካሄደው የወይዘሪት ብራዚል ውድድር ጠቅላይ ግዛቷን ትወክላለች፡፡
* * *
ጠቢባኑ እንዲህ አሉ
አንዱን ሰው ማን ገሰጸህ ብለው ጠየቁት፡፡ እሱም መልሶ የሰነፎችን ስንፍና አይቼ ራቅሁ ከዚህም የተነሳ ተገሰጽኩ አለ፡፡
ዲዮጋንስ አንድ ሰነፍ ሰው በደንጊያ ላይ ተቀምጦ አየና፣ ደንጊያው በደንጊያ ላይ ተቀምጧል አለ፡፡
አፍላጦንን ሰው ጠላቱን በምን መንገድ ሊቀበለው ይችላል ብለው ጠየቁት፡፡ እሱም አብዝቶ ጥሩ ነገር ያደረጉለት እንደሆነ ነው ብሎ መለሰ፡፡
ከጠቢባን አንዱን እንዲህ ብለው ጠየቁት፣ የሚጠቅምና የሚያስተክዝ ምንድነው፡፡ እሱም የክፉ ሰዎች ሞት ነው ብሎ መለሰ፡፡
ዲዮጋንስን ሞት እንዴት ናት ብለው ጠየቁት፡፡ እሱም ሀብታሞችን የምታስደነግጥ በድሆች ዘንድ ግን የምትፈለግ ናት አላቸው፡፡
ዲዮጋንስ አንድ መልከ መልካም ሰው ሲዋሽ አየው፤ እሱም ቤቱ ያማረ ሆኖ የሚኖርበት ግን ክፉ ነው አለ፡፡
አንድ አዋቂ ወደ ሌላ አዋቂ መኖሪያ ሄዶ እንዲህ ብሎ ጠየቀው፡፡ ብቻህን ስትኖር እንዴት አይሰለችህም አለው፡፡ እሱም መልሶ እንዲህ አለው፡፡ እኔ እኮ ብቻዬን አይደለሁም፡፡ ከብዙ አዋቂ ሰዎች ጋር ነኝ ከእነሱም ጋር እነጋገራለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ እጁን ዘርግቶ ካጠገቡ ብዙ መጻሕፍት አወጣና ይህ ሊባኖስ ሕያው ነው፡፡ አብቅራጥም ይገስጻል፡፡ ሶቅራጥም ያስተምራል፡፡ አፍላጦንም ይናገራል፡፡ አርስጣጣሊስ ምሳሌ ይመስላል፡፡ ሕርምስም ምላሽ ይሰጣል፡፡ ፎርፎዬስ ይመክራል፡፡ ጐርጐርዮስ ይናገራል፡፡ ዳዊት ያስተምራል፡፡ ጳውሎስ ይሰብካል፡፡ ወንጌል ያበስራል፡፡ ከእነዚህ ሁሉ መካከል ከፈለግኩት ከእኔ ጋር ይጫወታል አለው፡፡
(በ17ኛው ክፍለ ዘመን የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት ከዓረብኛ የተረጐሙትና ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ ‹‹አጭር የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ›› ውስጥ የጠቀሱት፡፡)
* * *
ሹመት
ካለጨበጨቡ
ወይ ካልቸበቸቡ
ወይም ካልሰረቱ
ወይ ካላሰረቱ
ወይ ካላሳበቱ
ማ ለማ ይሰጣል ከዚያ ከሱረቱ
መንግሥቱ ለማ
ቀበሮውና ሚዛኑ
ከብዙ ዓመታት በፊት ሁለት ጦጣዎች አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ምግብ ፍለጋ ወጥተው የሚበሉት ነገር አገኙ፡፡ ሆኖም በምግቡ ላይ መጣላት ጀመሩ፡፡
ስለዚህ “ወደ ቀበሮው ዘንድ ሄደን እርሱ ይገላግለን፡፡” ብለው ወደ ቀበሮው ሄዱ፡፡ ቀበሮውም ጉዳዩን በጥሞና ካዳመጠ በኋላ “ምግቡን ሁለት እኩል ቦታ ማካፈል ስላለብኝ ሚዛን መጠቀም አለብኝ፡፡ ነገር ግን አሁን ሚዛን በእጄ የለም፡፡ ዛሬ ጠዋት ሚዛኑን ለአንበሳው ስላዋስኩት ወደ አንበሳው ሄደን ምግቡን እናካፍለው፡፡” አለ፡፡
እንደደረሱም ቀበሮው አንበሳውን ተጣርቶ ጉዳዩን ነገረው፡፡ እንዲህም አለው “አንበሳ ሆይ! እነዚህን ጦጣዎች አስታርቃቸው፡፡” ይህንንም ብሎ ቀበሮው ወደ አንበሳው ዋሻ ሳይገባ ተመልሶ ሄደ፡፡ ጦጣዎቹም የተውትን ምግብ አንስቶ ራሱ በላው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለም ሁለቱ ጦጣዎች ችግራቸውን ለአንበሳው መንገር ጀመሩ፡፡ ነገር ግን አንበሳው እነርሱን መብላት እንጂ መዳኘት አልፈለገም ነበርና በላቸው፡፡
- በዩሱፍ አድም ማንደሬ የተተረከ የሶማሌ ተረት
* * *
‹‹ስፖርት ለጤንነት››
ሰሞኑን አዲስ አበባ የአፍሪካ መሪዎችን ለኅብረቱ ጉባኤ አስተናግዳ ነበር፡፡ ርእሰ ብሔሮችና የመንግሥታት መሪዎች ወደ ከተማይቱ መዝለቃቸውን ተከትሎ በሚተላለፉባቸው አውራ ጐዳናዎች መንገዱ ለትራፊክ ዝግ ይሆን ነበር፡፡ አንዱ የሚተላለፉበት መስመርም በብሔራዊ ቴአትር ወደ ሜክሲኮ የሚያመራው ነው፡፡
ባለፈው ቅዳሜ 7፡30 ሰዓት ግድም ብሔራዊ ባንክ ፊት ለፊት ባለው አንድነት አደባባይ እንግዶች እንደሚያልፉ በመታወቁ በየአቅጣጫው የሚመጡት ተሽከርካሪዎች እንዲቆሙ ሲደረግ ነበር፡፡ በምዕራብ አቅጣጫ ከአምስተኛ አካባቢ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል እየተሽከረከረ ይመጣ የነበረው አውቶቡስ ከመጣበት ፍጥነት አኳያ ለመቆም ያደረገው ጥረት ሳይሳካለት ወደ ሰሜን አቅጣጫ ተገልብጧል፡፡ አውቶቡሱ ለትምህርት ቤቶች ስፖርት ውድድር ሲያመሩ የነበሩ ተማሪዎችን የያዘ ሲሆን ጉዳት ሳይደርስባቸው በአካባቢው በነበረ ተሽከርካሪዎችን በሚያነሳ ተሽከርካሪ ተነስቷል፡፡ አውቶቡሱ በፊት ገጹ መስታወት ላይ ‹‹ስፖርት ለጤንነት››፣ ‹‹የቂርቆስ…›› የሚሉና ሌሎች ጥቅሶች ተለጥፎበታል፡፡
(ፎቶ በአዜ በየነ ከአዲስ አበባ)
*********
በድንጋይ ተወግራ የተረፈችው ሶርያዊት
አይኤስአይኤስ የተባለው አክራሪና ጽንፈኛ ቡድን ሶርያ ውስጥ በተቆጣጠራት ራካ ከተማ ስትጎለምት ተደርሶባታል ያላትን አንዲት ሴት በድንጋይ ተወግራ እንድትገደል ይወስናል፡፡ በትዕዛዙ መሠረት ሴቲቱ ብትወገርም ሕይወቷ ሳያልፍ ይቀራል፡፡
ተርኪሽ ዊክሊ፣ መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገውና የሶርያ ኦብዘርቫቶሪ ፎር ሒውማን ራይትስ የተባለው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ይህችው ሶርያዊት አል ፍሪዶስ በተባለው ጎዳና ላይ ነበር እንድትገደል የተወሰነው፡፡
የአይኤስአይኤስ አማፅያንም ሴትየዋ በተፈጸመባት የድንጋይ ውርጅብኝ ሞታለች የሚል እምነት አድሮባቸው እንደነበር ጋዜጣው ጠቁሞ፣ ሴትዬይቱ ከወደቀችበት ተነስታ ለማምለጥ ስትሞክር አንደኛው አማፂ ተኩሶ ሊገድላት ቢሞክርም በስፍራው የነበረው የሸሪያው ዳኛ ሴትየዋ ፍርዷን ስለተቀበለች እንዳይተኩስባት፣ እንዳትያዝና ወደፈለገችው እንድትሄድ መወሰኑን አስረድቷል፡፡
******
“ምድር ቤቱን ስጠው አላችሁኝ ሰጠሁት”
እነሆ ሁለት ቂሳ ባጭሩ አብዱልቃዱር ጅላሊ ከባግዳድ ነው የመጡት ይባላል፡፡ እሮብ በስማቸው የሚከበርላቸው፡፡
ለአያሌ ዓመታት ሲያገለግሉዋቸው የኖሩትን ሁለት ተከታዮቻቸውን የሚያሰናብቱበት ጊዜ ደረሰ፡፡ የትኛውን ወዴት እንደሚልኩትና እዚያስ ምን እየሰራህ ትተዳደራለህ እንደሚሉት ለማወቅ በሌላ አባባልም የሁለቱን ዋጋ ወይም ክብደት ለመመዘን እንዲህ አደረጉ፡፡ ለሁለቱም አንድ ዶሮ ሰጡዋቸውና “ለየብቻችሁ ሂዱና ዶሮዋል እኔ በሌለሁበት ስፍራ አርዳችሁ አምጡልኝ አሉዋቸው፡፡ ተቀብለው ቢላ ቢላቸውን ይዘው ሄዱ፡፡
አንደኛው ሄዶ ዶሮዋን አርዶ መጣ፡፡ ሁለተኛው ግን ቆይቶ ዶሮዋን ሳያርዳት ይዟት ተመለሰ፡፡ “ምነው አላረድካት” ቢሉት “እርስዎ የሌሉበት ቦታ አጣሁ” አላቸው፡፡ (ሌላውን ለአንባቢ እንተዋለን፡፡)
አንድ ነክናካ (ነፍናፋ) ሼህ ፎቅ ቤታቸው ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡ ደርጉ መጣና የቤታቸውን ፎቁን ተወረሱና የቀበሌ ባለሥልጣን ገባበት፡፡ ለሳቸው ምድር ቤቱን ተውላቸው፡፡
እሳቸውም ቤቴን አስመልሱልኝ፤ ልወረስ አይገባኝም እያሉ ቀበሌ ጽህፈት ቤት እየተመላለሱ ሊቀ መንበሩን አሰለቹት፡፡ ማመልከቻ ይጻፉ ሲላቸው “እኔ ምኑን አውቄ እጽፈዋለሁ? አንተው ፃፍ ፃፍ አርግና እንደሚሆን አርገህ አስመልስልኝ፡፡
እሱም አላስመለሰላቸውም እሳቸውም መመላለሳቸውንም አልተው፡፡ በመጨረሻም “ወይም ፎቁን እርስዎ ይውሰዱትና ምድር ቤቱን ለሱ ይስጡት” አላቸው፡፡ “እንዲያ ካላችሁኝ መልካም!” ብለውት ሄዱ፡፡
በነጋታው ጧት ፎቃቸው ውስጥ ይኖር የነበረው ባለሥልጣን ሞቶ ተገኘ፡፡ ሊቀ መንበሩ መጥቶ “ምን ተደረገ እነ ሼህ?” ቢላቸው “ምድር ቤቱን ስጠው አላችሁኝ፤ ምድር ቤቱን ሰጠሁት” አሉት፡፡
- ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ‹‹አንድ ሺ ከአንድ ሌሊቶች›› (1987)