ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኅብረተሰቡን በሩጫ በማሳተፍ የተለያዩ መልዕክቶች ማስተላለፍና እግረ መንገዱንም ከሚገኘው ገቢ ለተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማዋል እየተዘወተረ ይገኛል፡፡ ለዚህ ትልቁን ድርሻ እየወሰዱ የሚገኙት ደግሞ በአትሌቲክሱ ስፖርት ለዕውቅና የበቁ አትሌቶች ናቸው፡፡ እየተከናወኑ ከሚገኙ ተመሳሳይ ውድድሮች በባሕር ዳር ከተማ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በየዓመቱ የሚደረገው የባሕር ዳር ከተማ የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ይጠቀሳል፡፡ ሩጫው የፊታችን እሑድ እንደሚደረግ የውድድሩ አዘጋጅ አትሌት መልካሙ ተገኝ ይናገራል፡፡ አትሌቱ ከባህር ዳሩ ውድድር በተጨማሪ የካቲት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ደሴ ከተማ ላይ የአምስት ኪሎ ሜትር ውድድር በማዘጋጀት፣ ከዝግጅቱ የሚገኘውን ገቢ ለወሎ ተርሸሪ ሆስፒታል ግንባታ ለማዋል ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል፣ ደረጀ ጠገናው አነጋግሮታል፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት አትሌትም የአትሌቲክስ ማናጀርም ነህ፤ ይቻላል?
አትሌት መልካሙ፡- እንደሚችል አምኜ እየሠራሁበት ነው፡፡ ምክንያቱም ለዚህ የአትሌቲክስ ስፖርት የበቃሁት አስቤበት ሳይሆን በአጋጣሚ ነው፡፡ ዋናው ነገር አጋጣሚ የፈጠረልህን ዕድል መጠቀም መቻል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ለዚህ መነሻ የሆነህ ይኖራል?
አትሌት መልካሙ፡- አጋጣሚው እንደ ተሞክሮ ወይም መነሻ ካልተባለ በስተቀር የምጠቅሰውና የተጠቀምኩበት የለም፡፡ ምክንያቱም ትውልዴና ዕድገቴ ጎንደር አምባ ጊዮርጊስ ወረዳ ነው፡፡ በወቅቱ ከሐምሌ 5 እስከ መስከረም 30 ባለው ጊዜ ውስጥ ለኔም ሆነ ለቤተሰቦቼ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ እታመም ነበር፡፡ በሕክምና ደረጃም ከዘመናዊ እስከ ባህላዊና ፀበልን ጨምሮ ሞክሬ መፍትሔ ሊያስገኝልኝ አልቻለም ነበር፡፡ በጊዜው እኔም ሆንኩ ቤተሰቦቼ ብቸኛ መፍትሔ አድርገን የወሰድነው አገሩን ጥሎ መውጣት (ስደት) በመሆኑ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡
ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ ነገሮች በጠበከው መልኩ ሆነውልህ ነበር?
መልካሙ፡- እጅግ ከባድ ነበር፡፡ ምክንያቱም ዘመድም ሆነ የማውቀው ሰው አልነበረኝም፡፡ የነበረኝ አማራጭ የሚደርስብኝን ሁሉ ተቋቁሜ መዋልና ማደር በጀመርኩ በጥቂት ቀናት ውስጥ በወቅቱ ቴሌኮሙዩኒኬሸን በሚባል መሥሪያ ቤት በቀን ሠራተኝነት ሥራ አገኘሁ፡፡ በሥራ ላይ እያለሁ ብዙም ሳልገፋበት ታመምኩ፡፡ ወደ ሕክምና ስሄድ ‹‹ብርድ ነው›› ተባልኩ፡፡ ጠዋት ጠዋት የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለብኝ ጭምር ተነገረኝ፡፡ የተሰጠኝን መድኃኒት ሳልጠቀምበት ጠዋትና ማታ መስቀል አደባባይ ስሮጥበት በሽታውም ተወኝ፣ ሩጫውንም ቀጠልኩበት፡፡ በአካባቢው አትሌቶች በርከት ብለው ልምምድ ይሠሩ ስለነበር አብሬያቸው መሥራት ጀመርኩ፡፡ ከቀናት በኋላ ግን የአባቱን ስም ለጊዜው የዘነጋሁት አቶ ወንድወሰን በሚባል ግለሰብ የተቋቋመ ኮንፎርሜሸን ለሚባለው ክለብ በየወሩ 100 ብር እንደሚከፈለኝ ተነግሮኝ በክለብ ደረጃ ታቅፌ መሥራት ጀመርኩ፡፡ በክለቡ ብዙም ሳልቆም በግለሰቦች አማካይነት እንደተቋቋመ ለሚነገርለት በአይሻ ክለብ ተይዤ መሥራት ጀመርኩ፡፡ ክለቡ አትሌቶችን አዲስ አበባ ላይ እያሠለጠነ ለተለያዩ አገሮች እንዲሮጡ የሚልክ ስለነበረ እኔም ጠንክሬ ከሠራሁ ለጂቡቲ በ10,000 ሜትር እንደምሮጥ ነግረውኝ በአገር ውስጥ ማጣሪያ ውድድር ላይ ሁለተኛ ብወጣም መሄድ እንደማልፈልግ ነግሬያቸው ቀረሁ፡፡ ክለቡም በነበረው መቀጠል አልቻለም ነበር፡፡ ቆይቶ ግን ክለቡ መፍረስ እንደሌለበት፣ በጊዜው አሠልጣኝ ከነበረ አንድ ሰው ጋር በመነጋገር ክለቡንም እንደገና ለማቋቋም ፈቃድ ለማግኘት የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠይቀን፣ ማሟላት ያለብንን ነገር አሟልተን አይሻ የተባለው ክለብ እንዲቋቋም ተደረገ፡፡ አሠልጣኝ ሻምበል እሸቱ ቱራ እንዲሆኑ ተደርጎ እኔም በአትሌትነት ቀጠልኩ፡፡ ቆይተን ግን እኔ ጥሩ ነበርኩ ብዬ ነው የማምነው፣ ሆኖም አሠልጣኙና የክለቡ ባለቤት መቀነስ እንዳለብን ተነግሮን ከክለቡ ተቀነስኩ፡፡
ሪፖርተር፡- አትሌቲክሱን ተውከው?
አትሌት መልካሙ፡- እንደማልተወው አቋም ወስጄ የሚገጥመኝ የገንዘብ ችግር ለመፍታት መጀመሪያ ካፍቴሪያ ተቀጠርኩ፡፡ በሆነ ቀን ሁሌም በካፍቴሪያው የሚጠቀሙ ፍቃዱ ተስፋዬ የተባሉ ሰው ወደ ካፍቴሪያው ይመጣሉ፡፡ ታዘዝኳቸው፣ ያቀረብኩላቸው ግን እሳቸው ካዘዙኝ ውጪ ኮካ ኮላና ወይን ነበር፡፡ ተናደው ሰውዬ እኔ ያዘዝኩህ ማኪያቶ እንጂ ይህን አይደለም ካሉኝ በኋላ፣ ግን ለምንድ ነው እንዲህ ያደረከው ሲሉኝ እያንዳንዱን ነገር አስረዳኋቸው፡፡ ሥራዬም አትሌት እንደነበረና አሁን ደግሞ እንደተቀነስኩ ነገርኳቸው፡፡ ከዚያም የካፍቴሪያውን ማናጀር አስጠርተው በእኔ ምትክ አስተናጋጅ እንዲቀጥር፣ እኔ ወደ ቀድሞ የአትሌቲክስ ሙያየ መመለስ እንደምችልና ለዚያም እገዛቸው እንደማይለየኝ ነግረውኝ አድራሻቸውን ሰጥተውኝ ተለያየን፡፡ በአጋጣሚ ካፍቴሪያው የተገናኘነው ሰኞ ቀን ነበር፡፡ በማግሥቱ ጠዋት ቀጠሮ በያዝንበት ቦታ ተገናኝተን ቀደም ሲል ልምምድ ወደ ምሥራበት ሱሉልታ በራሳቸው ተሽከርካሪ ተያይዘን ሄድን፡፡ እሳቸው የሚያውቁት የአትሌቲክስ አሠልጣኝ ስለነበር ለእሱም ያለሁበትንም ሁኔታ አስረድተው እሱም በዚያው ሰዓት የምወዳደርበትን ኪሎ ሜትር ጠይቆኝ ከነገርኩት በኋላ፣ አሥር ኪሎ ሜትሩን እስከ 31 ደቂቃ ድረስ መጨረስ ካልቻልኩ እንደማያዋጣኝ ነግሮኝ ሁለቱም በመኪና እየተከታተሉኝ 29 ደቂቃ፣ 05 አጠናቀቅኩ፡፡ ከዚያም ወደ ከተማ ተመልሰን ለዝግጅት የሚያስፈልገኝን ቱታና ጫማ አሟልተውልኝ በየወሩ ደግሞ 600 ብር እንደሚሰጡኝ ተስማምተን ለአንድ ዓመት ያህል በዚህ መልኩ ቀጠልኩ፡፡ የመጀመሪያዬ የሆነውን ማራቶን በህንድ ፑኔ ከተማ ላይ በማራቶን ተወዳድሬ አራተኛ ወጣሁ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የአውሮፕላን ትኬት ሳይቀር አሟልተውልኝ ነው ወደ ውድድሩ ሥፍራ ያመራሁት፡፡ ከዚያ ሲቀጥል በጣሊያንና በአፍሪካ ኮንጎ ብራዚል ውድድሮችን አድርጌ አሁን ለምገኝበት ደረጃ እንድበቃ ያስቻለኝን ገንዘብ ማግኘት ቻልኩ፡፡
ሪፖርተር፡- በመጀመርያው ውድድርህ ምን ያህል ገንዘብ አገኘህ?
መልካሙ፡- 80,000 ብር
ሪፖርተር፡- በአትሌቲክስ ገፋህበት?
መልካሙ፡- ባደረግኳቸው የተለያዩ ውድድሮች ገንዘብ ካገኘሁ በኋላ ከአትሌቲክሱ ጎን ለጎን ማናጀር በመሆን ልክ እንደ እኔ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ያሉ አትሌቶች ስላሉ፣ እነሱን መርዳት የምችልበትን ሁኔታ ነው ያመቻቸሁት፡፡ ያንን ለማድረግ ደግሞ የግድ ማናጀር ወይም የማናጀር ተወካይ መሆን እንዳለብኝ ስላመንኩ፣ የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የማናጀርነት ፈቃድ እንዲሰጠኝ ጠይቄ ተሰጠኝ፡፡ ከዚያም ከዓለም አቀፍ የውድድር ማናጀሮች ጋር በመጻጻፍ ረዳት የሌላቸው አትሌቶች ውድድር እንዲያገኙ ዕድል መፍጠር ጀመርኩ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ወደ 68 የሚጠጉ አትሌቶች በስሬ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም በላይ የራሴ ክለብና የተሟላ ሰርቪስም አለኝ፡፡
ሪፖርተር፡- የክለብህ ስም ማን ይባላል?
መልካሙ፡- ቅዱስ ያሬድ አትሌቲክስ ክለብ፡፡ በክለቡ በአሁኑ ወቅት 48 ወንድና ሴቶች አትሌቶች ይገኛሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ብዙዎቹ በአገሪቱ የሚገኙ የአትሌት ማናጀሮች በአውሮፓና በሌሎችም አገሮች ለሚገኙ የአትሌት ማናጀሮች ተወካይ በመሆን እየሠሩ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ፌዴሬሽኑ የሰጠህ ፈቃድ ደረጃው እንዴት ይገለጻል?
መልካሙ፡- ውድድር ከሚያዘጋጁ ድርጅቶች ጋር ቀጥታ ግንኙነት በማድረግ የተለያዩ ውድድሮች ላይ አትሌቶች በመላክ እንዲወዳደሩ አደርጋለሁ፡፡ ለዚህ ፌዴሬሽኑ የሰጠኝ ፈቃድ በቂ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን የማናጀር ተወካዮች ዓይነት ሥራ የምሠራበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ እየሠራሁበት ያለውን የማናጀር ፈቃድ በአይኤኤኤፍ ሙሉ ዕውቅና ያለው እንዲሆን ጥረት እያደረግኩ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በሕይወትህ እጅግ አስገራሚ ውጣ ውረዶችን አሳልፈሃል፡፡ ከዚህ አኳያ ሩጫ በአንተ እንዴት ይገለጻል?
መልካሙ፡- ማለት የምፈልገው ተፈትኖ የሚመጣ እንጀራ ይጣፍጣል፡፡ ከሁሉም በላይ በአትሌቲክሱም ቢሆን እንዲህ አሁን እንደምነግርህ ቀላል አልነበረም፡፡ ተስፋ አስቆራጭና አድካሚ ስፖርት ነው፡፡ ምክንያቱም ለማንኛውም ውድድር ከበቂ በላይ ብቁ ነኝ ብለህ ለውድድር ስትቀርብ ባላሰብከውና ባልጠበከው መልኩ የሕመም ስሜት ይሰማሃል፡፡ ሮጠኸም የማይሳካልህ ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ግን ፅናቱ ያለው ሰው ካሰበው ለመድረስ የሚያግደው ነገር እንደሌለ የእኔ ተሞክሮ ምስክር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አገሪቱ የሯጮችን ምድር ተብላ ብትታወቅም ብዙ አትሌቶች ያሰቡትን ሳያሳኩ ይቀራሉ፡፡ ከዚህ አኳያ የምትለው ይኖርሃል?
አትሌት መልካሙ፡- ጽናት ከሌለህ በአትሌቲክሱ ብቻ ሳይሆን፣ በሌላውም ሴክተር ተመሳሳይ ዕጣ ነው የሚገጥምህ፡፡
ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል ከሩጫውና ከማናጀርነቱ ጎን ለጎን ተጨማሪ ሥራ እንደምታከናውን ተናግረሃል?
መልካሙ፡- ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ የባሕር ዳር ከተማ አሥር ኪሎ ሜትር ሩጫ በሚል ስያሜ ኅብረተሰቡን የሚያሳትፍ ውድድር ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ ለማከናወን ዝግጅት እያጠናቀቅሁ ነው፡፡ የአትሌቲክስ ስፖርት በተለይም በአሁኑ ሰዓት ከመዝናኛነቱ አልፎ ትልቅ የኢንቨስትመንት አማራጨ እየሆነ ነው፡፡ ይህንን የባሕር ዳር ከተማና አካባቢው ኅብረተሰብ ተገንዝቦ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥ ለማስቻልም ነው፡፡ ሌላው የክልሉን ገጽታ ለማስተዋወቅ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ ከተለያዩ አካላት መልዕክቶች ይደርሱኛል፡፡ ይህን ውድድር ስጀምር ምንም እገዛ የሚያደርግልኝ ሰው አልነበረም፣ መኪናዬን ሸጨ ነው ውድድሩን የጀመርኩት፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ የመጀመርያው ውድድር ከጠበቅኩት በላይ ተሳታፊ ተመዝግቦ ውድድሩ ተከናወነ፡፡ በ2005 ዓ.ም. ደግሞ ወደ 4,500 ተሳታፊ ከፍ አለ፡፡ በ2006 ዓ.ም. ላይ 10,000 ሰው አሳተፍኩ፡፡ የፊታችን እሑድ ሊደረግ ምዝገባው እየተከናወነ የሚገኘው የባሕር ዳር ከተማ ሩጫ በዕቅድ ደረጃ የያዝኩት 15,000 ተሳታፊ ነው፡፡ ይህን ቃለ መጠይቅ እስካደረኩበት ድረስ ምን ያህል እንደተመዘገበ አዲስ አበባ በመሆኔ ምክንያት መረጃው ተሟልቶ አልደረሰኝም፡፡ እዚህ ላይ ሳልገልጽ የማላልፈው ውድድሩን ስጀምር ጀምሮ የመሮጫ ቲሸርቶችን በማሳተምና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የሞሃ ለስላሳ መጠጦች አክሲዮን ማኅበርና ዓባይ ባንክ ትልቅ እገዛ አድርገውልኛል፡፡ በቀጣይም ከጎኔ እንደሚሆኑ አረጋግጠውልኛል፡፡ በዚህም የባሕር ዳር ከተማ ሩጫ ከታላቁ ሩጫ ቀጥሎ ሁለተኛው ሕዝባዊ የሩጫ መድረክ ሆኖ እንዲቀጥል ዕቅድ አለኝ፡፡
ሪፖርተር፡- በውድድሩ የሚገኘውን ገቢ ለወሎ ተርሸሪ ሆስፒታል ግንባታ የሚውል እንደሆነ ተነግሯል?
አትሌት መልካሙ፡- እሱ የባሕር ዳሩን ሩጫ አይመለከትም፡፡ የካቲት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ደሴ ከተማ ላይ አምስት ኪሎ ሜትር ተመሳሳይ የሩጫ ውድድር ይደረጋል፡፡ ከዚያ የሚገኘው ገቢ ሙሉ ለሙሉ ለሆስፒታሉ ግንባታ የሚውል ነው የሚሆነው፡፡ ሐሳቡም የመጣው ከወሎ ተርሸሪ ሆስፒታል የግንባታ ኮሚቴ ነው፡፡ ዝግጀቱም ተጀምሯል፡፡