Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መጥኔ!

እነሆ መንገድ! ከቄራ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። ከፊሉ በተንቧቸንበት ጎዳና ላይ ሲሮጥ፣ ከፊሉ ጉልበት ሳይከዳው ኑሮ ከብልኃቱ አልገናኝ ብሎት በጉብዝናው ወራት እያዘገመ ይጓዛል። ሩቅ ማሰብ፣ ነገን ማብሰልሰል፣ የዛሬን ሰላምና እርጋታ ያውካል። መንገድ ነውና ሰው መሆን በዘመናት ሒደት ሊፈታ ያልቻለ ታላቅ ሚስጥር ነውና ሕፃን አዋቂው ‘የዛሬ መንገዴ የት ያደርሰኝ ይሆን?’ ብሎ ሲርበተበት ገጹ ላይ ይነበባል። በመኖር ብዙ ያስተዋሉ፣ ያሳለፉ፣ ክፉና ደግ እይታቸውን የለጠጠው አዛውንቶችና ጎልማሶች ጭንቀትና ሐሳብ የሚያጠወልጋቸውን ወጣቶች እያዩ ትናንትናቸው ውስጥ የተልከሰከሱ ሀቆችን በመገረም እያሰሉ ወዲያ ወዲህ ይላሉ። ያለፉበትን ጎዳና ሌላ ትውልድ፣ ሌላ አዲስ ፍጥረት በገዛ ራሱ ተሞክሮ እየዳሰሰ ሲያጣጥመው ሲያዩ የሕይወት እንቆቅልሽ በዕድሜ ብዛት ጭምር የማይፈታ መሆኑን የሚገነዘቡ ይመስላሉ። መጪ ሂያጁን፣ መተላለፊያ ሰርጡን ሳይቀር ላጠና የሚመዘው ዕውቀት አያጣም። ከሚስተዋለው ትዕይንት በስተጀርባ የሚዘውረን ኃይል ሊሰጠን ያልሳሳው ነገር ቢኖር በትዝብት የሚሰባሰብ የመረጃ ዕውቀት ሳይሆን አይቀርም። ጎዳናው በተመላላሹ የሐሳብ መጉላላት ተደበላልቋል። ይህ የሰው ልጅ መባዘን መስከኛው መቼ ይሆን? መልሱ የማይገደውን መጠየቅ ይቻላል!

‹‹ምንድነው? ቶሎ ቶሎ ግቡ እንጂ! የቡፌ ሠልፍ አስመሰላችሁት እኮ! ሰዓት የለንም!›› ሾፌራችን ይንጨረጨራል። ‹‹ስንቸኩል ስድብ! ስንሰክን ተረብ! ምን እንሁን እሺ!›› አንዲት መለሎ ለወዳጇ ሾፌሩን ታማለታለች። ሁላችንም እንድንሰማት ድምጿን ታጎላለች። ‹‹ኧረ ቀስ በይ እባክሽ አንቺ ሴት። ዓይን ውስጥ መግባት ስትወጂ?›› ትላለች ወዳጅዋ ተሳቃ። ‹‹አይ አንቺ ይኼ ሁሉ ሰው ዓይን ስላለው ብቻ የሚያይ ይመስልሻል? እንደዚያማ ቢሆን ምነው በአደባባይ ቀማኛውና ጉቦኛው ሲበዛ የሚጮህ ሰው የጠፋ?›› ትላትና ጥርሷን ትነክሳለች። ‹‹ቢሆንም ዝምታን የመሰለ ነገር የለም። እግዜር ከሚሰጠን ይልቅ ዝምታ የሚሰጠን ዕድሜ ነው ተሽሎ የተገኘው፤›› ወዳጇ ትመልሳለች። ‹‹እኮ ዝምታ? ምነው ለእኔ ነፈገኝ ታዲያ? እ? አንድም ሲያደኸየኝና ሲያመኝ ኖረ። ባል ተብዬ ከቀን ቀን ይሻለዋል እያልኩ ዝም ብዬ ብኖር ይኼው በላዬ ላይ ቤቴን በዕዳ አሸጠው። ይኼን ያህል ዘመን ተለጉሜ ዛሬ መሳቂያ ሆንኩ። ተይኝ እስኪ! ሰው ዕድሜ ልኩን ሰው ሳይሆን ይኖራል?›› አለቻትና ወዲያው መሀል መቀመጫ ላይ ገብተው አጠገብ ላጠገብ ተቀመጡ።

‹‹ጉድ ነው ዘንድሮ! አሁን ይህቺ ሴት አዕምሮዋ ጤነኛ ነው ትላለህ? በቁሙ የሚሞተውና በጤናው የሚያብደው እኮ በዛ፤›› ብሎ ደግሞ ጋዜጣ የያዘ ወጣት ዞሮ ያናግረኛል። ወዲያ ወያላው ‹‹ተንቀራፈፋችሁ›› እያለ ሾፌሩን ተከትሎ ይወርድብናል። ‹‹ደርሰው የጊዜ ጠበቃ ሲመስሉ እውነት አይመስልም? አስመሳይ ሁላ…›› ይላል የጋቢናውን በር የሚከፍት ጎልማሳ። ‹‹መተው ነው እንጂ በስንቱ ተቃጥለን እንችለዋለን? የፖለቲከኛውን፣ የአገልግሎት ሰጪውን፣ የአላፊ አግዳሚው የታይታ አመል ከቆጠርንማ ማበዳችን ነው፤›› ስትል ደግሞ ጎልማሳውን አስቀድማ ጋቢና የምትንጠላጠል ወይዘሮ ትናገራለች። ያም ያም የመሰለውን እየተናገረ ይሳፈራል። በተለያየ ዕቅድና ጉዳይ አንድ አቅጣጫ ያገናኘን መንገደኞች፣ ባገኘናት ዕድል ሁሉ ለመተንፈስ እንሽቀዳደማለን። የእሽቅድምድም ዓለም!  

ጉዟችን ተጀምሯል። ከሾፌሩ ጀርባ አሁንም አሁንም ከንፈሩን የሚነክስ ጎልማሳና ሻሽ ያሰረች የቤት እመቤት ተሰይመዋል። ሦስተኛው መቀመጫ ላይ ከተሠለፉ ጀምረው ስልካቸው ላይ የተተከሉ ወጣቶች ተቀምጠዋል። መጨረሻ ወንበር እኔን ጨምሮ ጋዜጣ ይዞ የነበረው ወጣት ጋዜጣውን በትኖ እያነበበ፣ ከሴት ልጃቸው ጋር ጣራው እስኪበሳ የሚስቁ ተጫዋች አዛውንት በስተቀኝ ተቀምጠው መንገዱ ሲወዘውዘን እየተወዘወዝን፣ ሲያነጥረን እየነጠርን እንጓዛለን። ወያላው፣ ‹‹ሒሳብ ወጣ ወጣ! በቅድሚያ ግን በዶላርና በዩሮ የማንቀበል መሆናችንን እናስታውቃለን፤›› ይላል። ‹‹ፈርሞ መሄድስ ይቻላል?›› ትለዋለች ቤቴ በዕዳ ተሸጠ ብላ ነገር ዓለሙን ንቃ በነፃነት ያሻትን የምትናገረው ሴት። ‹‹መፈረምና ማፅደቅ የአፍሪካ መሪዎች ተግባር እንጂ፣ መቼም ቢሆን የሒሳብ አሰባሰባችን ሥልት ሆኖ አያውቅም። ጨዋታው በ ‘ካሽ’ ብቻ ነው፤›› ይላል ወያላው እየሳቀ። ‹‹ሥልጣን ቢኖረኝ ኖሮ አንተን ነበር አፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ንግግር እድታደርግ የምጋብዝህ፤›› ስትለው ወያላው እየሳቀ አንገቱን ያቀረቅራል።

አጠገቤ የተሰየሙት አዛውንት ጣልቃ ገቡ። ‹‹መሪዎቹ ራሳቸው መቼ ተናግረው አበቁና ነው ተመሪዎቹ የሚናገሩት? አፍሪካ በትምህርትና በዕውቀት እንጂ በንግግር የምትነቃ ይመስል ቢሉት አይታክታቸውም። የታከታቸውም ዓለም እየታዘባቸው እንቅልፋቸውን ይቀጫሉ። ዕድሜ ልካችንን አንድ ዓይነት መልክና አቋም እያየን ዲሞክራሲያዊት አፍሪካን ዕውን እናደርጋለን ይሉናል። እኛ ተውን እንጂ አድርጉልን አላልን። ፈረደብን እኮ!›› እያሉ ሳለ ከበድ ያለ ሳል ንግግራቸውን አቋረጣቸው። ወዲያ ደግሞ ሻሽ ያሰረቸው የቤት እመቤት ጎልማሳውን ጠጋ ብላ፣ ‹‹እኔንስ ገላግለውኛል። ይኼው ሦስት ረባሽ ልጆቼን አደብ የማስገዛቸው በአፍሪካ መሪዎችና በተወካዮች ምክር ቤት አፍዛዥ ቴሌቪዥን ነው፤›› አለችው። ጎልማሳው ግራ ገብቶት ‹‹አልገባኝም?›› ሲላት፣ ‹‹አንድ ጥፋት ሲያጠፉ ሦስቱንም ቴሌቪዥን ፊት አስቀምጥና ቀድቼ የማስቀምጣቸውን የአባላቱን አልያም የተመራጮችን ስብሰባ መክፈት ነው። አምስት ደቂቃ ሳይቆዩ በያሉበት ሲፈነገሉ የእኔ ሥራ ጋቢ መደረብ ብቻ ይሆናል። አልዘየድኩም ታዲያ?›› ትለዋለች። አምርሬያለሁ ብሎ ከሚያሾፍብን በላይ አሾፍኩ ብሎ የሚያመረው ባሰ እንዴ?

ጉዟችን እንደቀጠለ ነው። አብዛኛዎቹ ተሳፋሪዎች ክፉኛ ሲተቹት የምንሰማው የኅብረቱ መሪዎች ስብሰባ ሌላ ስብሰባ ያደራጅ ይዟል። ‹‹‘የራሷ ሲያርባት የሰው ታማስላለች’ አሉ። ኧረ ስለፈጠራችሁ! እኛ ራሳችንን መምራት ያቃተን ሰዎች ነን። በምን አቅማችን ነው አሁን እኛ አገር የሚመሩ ሰዎችን የምናማው? ምናለበት የቄሳሩን ሸክም ለቄሳር ትታችሁ ስለራሳችን ሸክም ብናስብ?›› ጋቢና የተሰየመችው ወይዘሮ አስገመገመች። ‹‹እንዴ እንዴት ነው ነገሩ? ጊዜው የምርጫ ሆኖ ነው ስለመሪዎቻችን ለምን እናወራለን የሚባለው? ሸክማችንስ ቢሆን የማን ዕዳ መሰለሽ?›› ብሎ ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠው ጎልማሳ መለሰላት። ‹‹ወይ ዕዳ ከሜዳ አለ ያገሬ ሰው። እስኪ ስለዕዳ አታውሩ እባካችሁ ራሴን ያመኛል!›› ስትል ነገር ዓለሙ የተሳከረባት መሀል መቀመጫ የተቀመጠች ሴት ጣልቃ ትገባለች። አዛውንቱ፣ ‹‹አቤት የዘንድሮ ምላስ! ምናለበት ነነዌ እንኳ እስክታልፍ ከነገር ብንታቀብ?›› ብለው ሳይጨርሱ ሞባይላቸው ላይ እንዳቀረቀሩ ወጣቶቹ ‹‹ወራጅ!›› ብለው ታክሲዋን አስቆሟት። በመነቋቆር የተለከፈው መንገደኛ ትችቱን ሊያወርድባቸው እስኪወርዱ ይቁነጠነጣል። ወርደው መንቀሳቀስ ከመጀመራችን፣ ‹‹እኔ የምፈራው ትንሽ ቆይተን በፌስቡክና በኢሜል ‘ወራጅ’ እንዳንል ነው፤›› ብሎ ጎልማሳው ጀመረው። ‹‹ቴክኖሎጂ በላይ በላይ ሰው ከራሱ እንዳይተያይ ያለችው ዘፋኙዋ ምን አይታ ይመስልሃል?›› ሲል ከጋቢና ይመልስለታል። ‹‹በግንባር መግባባት ያቃተን እስኪ አሁን በፌስቡክ ማኅበር ተባብረን እንዘልቃለን ትላለህ?›› የሚለኝ ደግሞ አጠገቤ የተቀመጠው ወጣት ነው። ይኼን ሲል አዛውንቱ ሰምተው ኖሮ፣ ‹‹ተወኝ እስኪ! እንዲያው ጨዋታችን ሁሉ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ! ተውማ አታናግረኝ ፆም ነው፤›› ብለው እጃቸውን አፋቸው ላይ ይጭናሉ። ልጃቸው ይኼን ጊዜ፣ ‹‹አባዬ በዚህ አያያዝህ ከሥጋ ሐሳብና ሥራ ነው ወይስ ከዴሞክራሲያዊ መብትህ ነው ለመፆም የምትታገለው?›› አለቻቸው። አዛውንቱ ከመመለስ ይልቅ ዓይን ዓይኗን እያዩ ፈገግ አሉ። እኛም የቆጡን ልናወርድ የብብታችንን የምንጥለውን እያሰብን ሳቅን። ሌላ ምን ይባላል?

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ጥቂት ቀደም ብሎ ሦስተኛው ረድፍ ላይ ማውራት የማይቦዝኑ ወጣቶችን ወያላው ተክቷል። የቀደምነው ተሰለቻችተን ነው መሰል ዝምታችን ያስፈራል። ሁለቱ በስሜት የሚጫወቱትን እናዳምጣለን። ‹‹እኔ እኮ የሰላምና የዴሞክራሲ ቱርፋት ነው የሚባለው የልማት ሥራ ሁሉ ለምን እንደ ችሮታ እንደሚታሰብብን ነው የማይገባኝ። ‘አገር ምድሩ አስፓልት በአስፓልት ሆነ’ እህ? ‘እኛ ባንሆን ኖሮ አዳሜ አቧራሽን እያቦነንሽ የዛሬ መቶ ዓመትም በመሠረተ ልማት ባላለፈልሽ ነበር’ ዓይነት ፕሮፓጋንዳ ሲያስጨንቀን ይሰነብታል። ‘በምግብ ዋስትና ራሳችንን ችለናል’ በተባለ ማግሥት፣ እርስ በርስ የተገዳደልንበት የጦርነት ቪዲዮ በቴሌቪዢን ሲደጋገም ይሰነብታል። ‘የገደልንም እኛ የሞትንም እኛ። ልማቱም የጋራ ውድቀቱም የጋራ’ የሚለን ሰው እኮ ነው የናፈቀን። መቼ ይሆን ያ ቀን?›› ሲል ጥግ ላይ የተቀመጠው ደግሞ፣ ‹‹መቼ ነውን’ አሁን ደውዬ በ ‘ኤፍ ኤም’ እጋብዝሃለሁ። መቼም ሐሳብ ከማዋጣት ዘፈን መጋበዝ የሚቀልበት አገር ሆኗል፤›› ይለዋል።

‹‹ታዲያስ ገንዘባችን ብቻ መሰለህ ዋጋ ያጣው? እኛም ነን እኮ፤›› ይላል ጥግ ያለው መልሶ። ‹‹ኧረ ተረጋጉ መብራት እንዳትጥሱ!›› ሲሉ ደግሞ አዛውንቱ አጠገቤ የተቀመጠው ወጣት፣ ‹‹ሰው ተገኘ እያለ ይኼን የተወጋ መጠጥ ይልፍ ይልፍና ማታ በሞቅታ የጀመረውን ፈንጂ መርገጥ ቀንም ይቀጥለዋል። እንዲያው ምን ይሻላል?›› ይለኛል። ወዲያው ታክሲያችን ጥጓን ያዘችና ቆመች። ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ በሩን በረገደው። ተራችንን እየጠበቅን ሁላችንም እስክንወርድ አላስችል ያለው ወያላ፣ ‹‹ዛሬ ሰው ምን ሆኗል? ሥራ ያለን ሰዎች እኮ ነን አፍጥኑት እንጂ!›› ብሎ ሲያበቃ፣ ‹‹እዚህ እዚያ ተፍ ተፍ ብለን ባኖርናችሁ ደግሞ ትጀነኑብናላችሁ?›› አለን በግልምጫ። ይኼኔ ያቺ ሰማይ የተደፋባት ሴት አንገቱን አንቃ፣ ‹‹ችሮታ ሌላ ግዴታ ሌላ!›› ብላ ጮኸችበት። ለመገላገል ጊዜ የነበረው መሀል ገብቶ ወያላውን አስጣለው። ሌሎቻችን ወደ ቀጣይ ጉዟችን ተበታተንን። ግራ ተጋብተው ግራ የሚያጋቡን ሲበዙ ምን ይባላል? መጥኔ ነዋ! መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት