Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርብልህ መሆን ቢያቅት ሞኝነትን ምን አመጣው?

ብልህ መሆን ቢያቅት ሞኝነትን ምን አመጣው?

ቀን:

በታምራት መስፍን

‹‹ብልህ ከሌሎች ስህተት ሲማር ሞኝ ግን ከራሱ ስህተትም አይማርም›› የሚለው አባባል ዋዘኛ አይደለም፡፡ ኒኮሎ ማኪያቬሊ የተባለው የጣሊያን የታሪክ፣ የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ፣ የፍልስፍናና የሥነ ጽሑፍ ሰው በዘመነ ተሃድሶ ስመ ገናና ነበር፡፡ ይህ የዘመናዊው የፖለቲካ ሳይንስ ቀማሪና የብልጠት መሐንዲስ ፖለቲከኞች ብልህ ካልሆኑ ዋጋ የላቸውም በማለቱም ይታወቃል፡፡

“The Prince” በተባለው እጅግ ዝነኛ በሆነ መጽሐፉ ፖለቲከኞች እንዴት መሰሪና ከሚገባው በላይ ጠንካራ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝቧል፡፡ ‹‹ማኪያቬሊዝም›› ተብሎ የሚታወቅበት ይህ መሰሪ ጽሑፉ እጅግ በጣም ብዙ አንባቢያን ያፈራ ሲሆን፣ ማኪያቬሊ ለሥልጣን ትንቅንቅ በሚደረግ ትግል ጭካኔንና ኢሞራላዊ ድርጊቶችን አቀንቅኗል፡፡ ብዙዎች ማኪያቬሊን የጭካኔና የኃይለኝነት ሰባኪ አድርገው ሲነቅፉት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጭካኔንና ስግብግብነትን ወደጎን በማድረግ ብዙዎቹ የብልጠት ምክሮቹን ይቀበላሉ፡፡ በዘመናችን በዓለም ዙሪያ ያሉ ፖለቲከኞች የኒኮሎ ማኪያቬሊን አስተምህሮዎች ደግመው ደጋግመው ይጠቀሙባቸዋል፡፡ ማኬያቬሊ ከክፋቱ በተጨማሪ ጠቃሚ ነገሮችም አሉት ለማለት ነው፡፡ ራስን ከችግሮች ለመታደግ፡፡

ወደ አገራችን ፖለቲከኞች ስንመጣ ለበርካታ ዓመታት አንድ ዓይነት ነገር ግን የሚደጋገሙ ችግሮች ይታያሉ፡፡ የችግሮቹ ተመሳሳይነት በሁሉም የፖለቲካ ቡድኖችና ግለሰቦች የሚታወቁ ቢሆንም፣ ለችግሮቹ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ እንዲባባሱ እየተደረገ ከችግር አዙሪትና አረንቋ ውስጥ መውጣት አልተቻለም፡፡ የእኔ ትውልድ አባላት በተለይም የመኢሶንና የኢሕአፓ ፖለቲከኞች በቀላሉ ሊፈታ የሚችለውን ችግራቸውን አባብሰው እንዴት በደርግ ተቀርጥፈው እንደተበሉ አንዘነጋውም፡፡ በዚያን ዘመን የማርክሲስት ርዕዮት እንከተላለን የሚሉ ሁለቱ የፖለቲካ ቡድኖች ደርግን የሚያህል የጋራ ጠላት ተባብረው እንደመጣል፣ እልህ ተጋብተው በቆሰቆሱት እሳት አንድ ትውልድ አስበልተዋል፡፡ ዛሬም ረመጡ ይለመጥጣል፡፡

ባለፉት 24 ዓመታት በአገራችን የፖለቲካ አየር ውስጥ የሞላው ብልጠት የጎደለው አደረጃጀትና የቅራኔ አፈታት ሥልት አለመኖር ስንቶቹን የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደበተናቸው እናውቃለን፡፡ ብልጠትና ብልኃት ያልተቀላቀሉበት የእልህ ፖለቲካ ጥላቻና ክፋትን እየዘራ ብዙዎችን ተስፋ አስቆርጧል፡፡ ለስደት ዳርጓል፡፡ የፖለቲካ ልሂቃኑ ከተለመደው የፖለቲካ ዚቅ ውስጥ መውጣት እያቃታቸው ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ በ1993 ዓ.ም. ዋነኛ አባል ድርጅቱ ሕወሓት ለሁለት ሲሰነጠቅ፣ ድርጅቱን ለማዳን የተኬደበት መንገድ መሥራች አባላቱን እስከማባረር የደረሰ ነበር፡፡ ድርጅቱ በወቅቱ በዚህ መንገድ ከውድቀት ተረፈ ተብሎ ብዙ ቢዘመርም፣ የተለያዩ ጸሐፊዎችና ውስጥ አዋቂዎች እንደነገሩን አካሄዱ በሙሉ ኢዴሞክራሲያዊ ነበር፡፡

በወቅቱ እነ አቶ መለስ ዜናዊ ድርጅቱ የመበስበስ አደጋ እንዳጋጠመው አምነው ለተሃድሶ መነሳታቸውን ቢያውጁም፣ ያ ተሃድሶ የሚባለው ነገር ምን ይዞ መጣ? ብለን ስንጠይቅ ምላሹ የፖለቲካ ምኅዳሩን ማጣበብና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን መድፈቅ ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ጊዜ የተበረገደው የዴሞክራሲ በር የተሃድሶው ውጤት ነው ብለው የሚከራከሩ ቢኖሩም፣ ከዚያ በኋላ የነበረውን ለሚታዘብ ደግሞ ከደፈቃ ውጪ ምንም አይታየውም፡፡ የኢሕአዴግ ከመጠን ያለፈ ጫናና ከእኔ በቀር ማንም የለም የሚለው አባባል የመጣው በማኪያቬላዊ መንገድ ነው፡፡ ከመጠን ያለፈ ብልጠትና መሰሪነት ያለበት፡፡

በምርጫ 97 የት ይደርሳል የተባለው ቅንጅት በኢሕአዴግና በራሱ የውስጥ ችግሮች ተጠልፎ ወድቆ፣ የአመራር አባላቱ እስር ቤት ሲገቡ ሁሉም ነገር ጨላለመ፡፡ እነሱ ከእስር ቤት ወጥተው በየፊናቸው ሲበታተኑ ለለውጥ የተነሳው ኃይል ከሰመ፡፡ ለዴሞክራሲ የተደረገው ሰላማዊ ትግል ውኃ በላው፡፡ ሌላው ቀርቶ ልዩነትን አቻችሎ በሠለጠነ መንገድ ሰላማዊውን ትግል ወደ ሐዲዱ መመለስ ሲቻል፣ ያ የተለመደው ብልጠት የጎደለው አካሄድ ተጀመረ፡፡ ለዘመናት ከውስጣችን አልወጣው ያለው ክፋትና እልህ ተተካ፡፡ ከዚያም በውስጥ መባላት ተጀመረ፡፡

አንድነት ፓርቲ የቅንጅት ወራሽ መሆኑን አውጆ በዝነኛዋ ብርቱካን ሚደቅሳ ፕሬዚዳንትነት ሲመሠረት፣ የቅንጅትን ያህል ባይሆን እንኳ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር (Landscape) ውስጥ ብርቱ ተፎካካሪ መሆን እንደሚችል ታምኖበት ነበር፡፡ ብርቱካን በውጭ አገር ‹‹ይቅርታ ጠይቀን አይደለም የተፈታነው›› ብለሻል ተብላ እንድታስተባበል ስትጠየቅ ‹‹ቃሌ ነው›› በማለቷ ዳግም ለእስር ስትዳረግ፣ እነኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው አመራሩን ተረከቡ፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የመጣው ችኩቻ ነበር፡፡ ውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ በአግባቡ ሊፈታው ይገባ የነበረ ነገር ግን ገንፍሎ አደባባይ የወጣ ሽኩቻ፡፡

በፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም የሚመራው ‹‹መርህ ይከበር›› ያለው የፓርቲ አባላት ስብስብ ጥያቄ ሲያነሳ፣ በአግባቡ ምላሽ የሚሰጥ አካል በመጥፋቱ ቅራኔው ጦዘ፡፡ በሚዲያ ተራገበ፡፡ ቅራኔው መለስተኛና በፓርቲው ደንብ መሠረት መፈታት ሲገባው፣ ይባስ ብሎ ባምቢስ አካባቢ ኃይል የተቀላቀለበት ድብድብ ታየ፡፡ የአካል ጉዳት ደረሰ፡፡ ፖሊስ ጣልቃ ገብቶ ባያበርደው ኖሮ ሕይወት ይጠፋ ነበር፡፡ አንድ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት በውስጡ ቅሬታ ሲነሳ የሚፈታበት ሥልት ባለመኖሩ ብዙዎችን አበሳጨ፡፡ ድርጅቱን የመሠረቱት አባላት ራሳቸውን አገለሉ፡፡ ፓርቲው ከነችግሩ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ የተመሠረተው በዚህ ቡድን ውስጥ በነበሩ ሰዎች እንደነበረ ልብ ይሏል፡፡ ምርጫ 2002 እንደዚያ ጨፍጋጋ የሆነው አንድም በአንድነት ፓርቲ ውስጥ የነበረው ሽኩቻ ውጤት ነው ቢባል የተጋነነ አይመስለኝም፡፡ ቢያንስ በፓርቲው መመሥረት ነቃ ነቃ ብለው የነበሩ ወገኖች በተፈጠረው ችግር አዝነው ተስፋ ቆርጠዋል፡፡ ይህም የብልኃት ማነስ ውጤት ነው፡፡

ያ ሁሉ ጊዜ አልፎ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በፕሬዚዳንትነት ለተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ራሳቸውን ገለል አድርገው የነበሩት ኢንጂነር ግዛቸው እንደገና መጡ፡፡ በምርጫ ተወዳድረውም ተፎካካሪያቸውን በከፍተኛ ድምፅ በልጠው በማሸነፍ ሥልጣኑን ተረከቡ፡፡ ‹‹ወደ አንድነት የመጣሁት የቀረኝ ሥራ ስላለ ነው›› ብለው ሥራቸውን ቀጠሉ፡፡ በዚህ ጊዜ አንድነት ፓርቲ በርካታ አባላትን እያፈራ መጣ፡፡ ሌላው ቀርቶ ከኢሕአዴግ ጎራ አፈንግጠው የወጡ ሳይቀሩ ተቀላቀሉት፡፡ በሥልጣንም ተንበሸበሹ፡፡ ፓርቲው ውስጥ ሰርጎ ገቦች በብዛት እየገቡ ነው እየተባለ ሐሜቱ ጦፈ፡፡ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ራሱን ያዘጋጀው ደግሞ መታተሩን ቀጠለ፡፡ ቅራኔ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ ምንም እንዳልተፈጠረ ወይም ምንም እንደማያመጣ ተቆጥሮ ዝም ተባለ፡፡ ከብልኃት ይልቅ ሞኝነት አየለ፡፡

በአንድ ባልታሰበ ቀን ኢንጂነር ግዛቸው ‹‹ዳያስፖራው ሊያሠራኝ አልቻለም›› ብለው በተፅዕኖ ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን ሲያውጁ ግራ መጋባት ተፈጠረ፡፡ ድርጅቱን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ እንመራለን ያሉ ወገኖች ግን ተተኪውን ፕሬዚዳንት አስመርጠው ሥራ ሲጀምሩ፣ ሌላ ወገን የቀድሞውን የእነፕሮፌሰር መስፍን መፈክር አንግቦ ‹‹መርህ ይከበር›› ብሎ ተነሳ፡፡ ችግር ሲፈጠር መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ በፌስቡክ የአሽሙርና የሥላቅ ዘመቻ የሚጀምሩ ወገኖች በዙ፡፡ አፈንግጠው የወጡት ሰዎች ችግራቸው ምንድነው ብሎ አጠያይቆ ለመፍትሔ ከመሯሯጥ ይልቅ ‹‹የጠላት ተላላኪ›› ተብለው የበለጠ እንዲገፉ ተደረገ፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው›› በሚለው ብሒል መኢሶን ኢሕአፓን በደርግ አስበልቶ ራሱ መበላቱ አይዘነጋም፡፡ ዛሬም በጠላትነት ወይም በከሃዲነት የተፈረጀው ወገን ‹‹ጠላት›› ሠፈር ቢገኝ አይደንቅም፡፡ ብልኃት በሌለበት ሞኝነት ይገናልና፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ የሆነውም ይኼው ነው፡፡

ሌላው ቀርቶ የአንድነት ፓርቲ አባላት ጎራ ለይተው በቴሌቪዥን ሲጨቃጨቁ የአንዳንዶች ንግግር ያበግን ነበር፡፡ ከይቅርታ ጋር የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ በቴሌቪዥን ሳያቸው ከመልዕክታቸው ይልቅ ስሜታዊነት ገኖባቸዋል፡፡ አላስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሲነታረኩ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ የማያቸው ጽሑፎች በጣም ያሳስቡኛል፡፡ እልህ የተሞላባቸው ናቸው፡፡ ብልጠት ይጎድላቸዋል፡፡ ስድብና ዘለፋ ከፖለቲከኛ አይጠበቅም፡፡ በተለይ ፓርቲውን ቀምተው ወሰዱ የተባሉት ግለሰብ ላይ የጻፉዋቸው ነገሮች ከእሳቸው ሰብዕና ጋር አይመጣጠኑም፡፡ አቶ ግርማ የበሰሉ ጎልማሳ የፖለቲካ ሰው ይመስሉኝ ነበር፡፡ አሁን ግን ራሴን ተጠራጠርኩ፡፡ አንድነት ፓርቲ ተጠልፎ ሲወድቅ ችግሩ የማን ነው? ብሎ እንደገና ውስጥን መፈተሽ ካልተቻለ አሳሳቢ ነው፡፡ ሁልጊዜም ባለጋራን ለውድቀት ተጠያቂ ማድረግ ብቻ ጥሩ አይደለም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ነኝ የሚል ፓርቲ ውስጡን ሳያጠራ አደባባይ ሲወጣ ችግር ነው፡፡ የስም ዴሞክራሲ ለማንም አይበጅምና፡፡ ኢሕአዴግ በስመ ዴሞክራሲ ግራ የሚያጋባን አንሶ ሌሎች ሲደገሙበት ያናድዳል፡፡

ለነገሩ የአንድነት ፓርቲን እንደማሳያ ለመጠቀም ሞከርኩ እንጂ የመኢአድ ጉዳይም የባሰበት ነው፡፡ ለዓመታት የዘለቀው የውስጥ ትርምስ በውጭ ጫና እየተሳበበ መኢአድን ለመንቀሳቀስ እንዳላስቻለው ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ መኢአድ አለ ወይ? እስኪባል ድረስ ደብዝዟል፡፡ የአባላት ድርጅት ሳይሆን የግለሰብ ኩባንያ ያህል እስከመቆጠር የደረሰው በእኔ ወይም በእናንተ በአንባቢያን ሳይሆን እርስ በርስ በሚተጋተጉት ወገኖች ጭምር ነው፡፡ የውስጥ ችግርን ለመፍታት ያለመቻል አባዜና ብልኃት አልባነት ሰሞኑን ያመጣበትን ፈተና አይተናል፡፡ ውስጡ የደፈረሰ የፖለቲካ ድርጅት ሆኗል፡፡ ይህም ጠልፎ የመጣል አባዜ ውጤት ነው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎችን እጅግ በጣም በተጣበበው ምኅዳር ውስጥ ለመሥራት ሲነሱ፣ ከሚቃወሙት ኢሕአዴግ በላይ ብልጠት ጎድሎአቸዋል፡፡ ጫናው ቢበረታም፣ ውክቢያውና እንግልቱ ቢበዛም፣ ለሰላማዊ የፖለትካ ተሳትፎው (Political Engagement) መከፈል ያለበት መስዋዕትነት አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በብልኃት የታጀበ እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው፡፡ እስካሁን የተመጣበት የፖለቲካ አወቃቀርና አሠራር (Format) መቀየር ይኖርበታል፡፡ ግጭትና መጠላለፍን እያስቀደመ የሚጓዝ ፖለቲካ ውጤቱ ጥሩ አልሆን ካለ፣ ዘመኑን የሚወጥን ብልኃት ይዞ መነሳት ይበጃል፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ አበቃለት እያሉ የሚያወሩ ወፈፌዎችን ምክር ትቶ ሕጋዊውን መንገድ ይዞ መጓዝና በአዲስ አስተሳሰብ መነሳት የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡ ውስጥን ሳያፀዱና ራስን በቅጡ ሳይመለከቱ ሰበብ መደርደር ይበቃል፡፡

ግትርነት፣ ክፋትና ራስ ወዳድነት የተቀላቀሉበት የፖለቲከኞቻችን ጉዞ በብልኃት ወይም በጥበብ ካልተተካ ሁሌም ‹‹ውኃ ቢወቅጡት እንቦጭ›› ከሚል ጨዋታ አይወጣም፡፡ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አደባባይ ከመውጣታቸው በፊት ውስጠ ዴሞክራሲ ሥርዓታቸውን ቢገመግሙ ይመረጣል፡፡ ያለፈው ትውልድ የተጓዘበትን ጠማማ መንገድ እየተከተሉ መጓዝ ‹‹የዝንጀሮ መንገድ ቢከተሉት ገደል›› ነው የሚሆነው፡፡ ወጣት አብዮተኞችን ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ የነገ ተተኪዎችን ከፖለቲካው ተሳትፎ ያርቃል፡፡ ዘመኑ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተካነ በመሆኑ የፓርቲ አባላት በአንድ ጉዳይ ላይ ደስተኝነት ሳይሰማቸው ሲቀር ‹‹የራስህ ጉዳይ›› ማለት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ከፓርቲ ህልውና በላይ የዳያስፖራው ገንዘብ መነታረኪያ ሆኖ ገመናን አደባባይ ላይ እንደ ብቅል ሲያሰጣ ያሸማቅቃል፡፡ ሰላማዊው የፖለቲካ ትግል ተገፍቶ የትም እንደማይደረስ፣ ጦርነት አውጀው ከሰሜን አሜሪካ በኢንተርኔት አስቂኝ ትግል ከጀመሩት ተስፋ ቢሶች አይተነዋል፡፡ ትግሉ አስቸጋሪ ጉዞው እልህ አስጨራሽ ቢሆንም፣ ዴሞክራሲያዊ ሆኖ በትጋት መነሳት የግድ ነው፡፡ ዘመኑ ጉልበትን ሳይሆን ብልኃትን ነው የሚጠይቀው፡፡ ለዚህም ነው ብልህ መሆን ሲያቅት ሞኝነት ለምን? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳው፡፡

ኒኮሎ ማኪያቬሊ ከሚነገሩለት ጥቅሶች መካከል አንዱ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹አንበሳ ራሱን ከወጥመድ ሊከላከል አይችልም፡፡ ቀበሮም ራሱን ከተኩላዎች መጠበቅ ይሳነዋል፡፡ ወጥመዶችን ለማወቅ ቀበሮ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ተኩላዎችን ለማስፈራራት ደግሞ አንበሳ መሆን ያሻል፡፡›› እንግዲህ እንዲህ እያሰቡ ነው ፖለቲካ መመራት ያለበት፡፡ የዋህነት አይሠራም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...