Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የፋይናንስ ተቋማትና የገዥው ባንክ መመርያ ሁለት ገጽታ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ከጥቂት ዓመታት በፊት የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዋጅ መሻሻሉ ይታወሳል፡፡ አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገበትን  ምክንያቶች በዝርዝር ቀርቦም ነበር፡፡ የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት ውስጣዊና ውጫዊ እንቅስቃሴ በመፈተሽ ጭምር እንዲሻሻል መደረጉም ይታወሳል፡፡ የማሻሻያ አዋጁ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የበለጠ ለመቆጣጠር የሚያስችለው ስለመሆኑም ያሳያል፡፡ የማሻሻያ አዋጁ በተሰናዳበት ወቅት ገዥው ባንክ፣ የፋይናንስ ተቋማትን ጤናማነት ለማረጋገጥ መከናወን ይገባቸዋል ያላቸውን ጉዳዮች በተለያየ መንገድ አስቀምጧቸዋል፡፡

  የፋይናንስ ተቋማት ለምን ቁጥጥር ይደረግባቸዋል ለሚለው መጠይቅ ምላሽ ናቸው የተባሉ አንኳር ነጥቦች ተቀምጠዋል፡፡ ሰፋ ያሉ ማብራሪያዎችም ስለ አስፈላጊነቱ እንዲያትቱ ተቀምጠው ነበር፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ‹‹ባንኮች የቱንም ያህል ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል ቢደረግባቸውም ሊወድቁ ይችላሉ፡፡ የባንኮች መውደቅ ገንዘብ አስቀማጮች በባንክ ያላቸውን ገንዘብ እንዲያወጡ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንድ ባንክ ሲወድቅ የዚያ ባንክ አስቀማጮች ገንዘባቸውን ያጡ መሆኑን የሌላ ባንክ አስቀማጮች ሲረዱ፣ እነዚህ ችግሮች የሌሉበት ባንክ አስቀማቀጮችም ገንዘባቸውን ከባንኮች ለማውጣት ሊሠለፉ ይችላሉ፡፡ ይህ የተከሰተ እንደሆነ አገሪቱ አጠቃላይ ወደ ሆነ የባንክ ሥርዓት ቀውስ ልታመራ ትችላለች፤›› የሚለው ገዥ ሐሳብ ይገኝበታል፡፡

   እንዲህ ዓይነት ማብራሪያዎች የባንክ ኢንዱስትሪው መሠረታዊ ሥጋቶች በመሆናቸው፣ ብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ መመርያዎችን ሊያወጣ ይችላል የሚለውን እምነት አጠናክሯል፡፡ ከከፍተኛ ባለአክሲዮኖችና ከቦርድ አመራር ተግባራት ጋር በተያያዘም አዳዲስ መመርያዎች ተግባራዊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁሞም ነበር፡፡

  ሰሞኑንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአገሪቱ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት የሥራ አመራር ሥልት ምን መሆን እንዳለበት የሚያመላክትና አስገዳጅ ሆኖ ለማገልገል ያስችላል ያለውን አዲስ መመርያ ለማውጣት በዝግጅት ላይ ስለመሆኑ መገለጹም ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡

  ‹‹ኮርፖሬት ገቨርናንስ››ን ወይም የተቋማት አስተዳደር ሊባል ይችላል፣ ይህንን የሚመለከተው አዲሱ መመርያ ቀደም ብሎ በብሔራዊ ባንክ  የማሻሻያ አዋጅ ውስጥ በተለያየ መልክ የተገለጸ ነበር፡፡ አዋጁ የመቆጣጠሪያ ሥልቶችን ለመፍጠርና ለማጠናከር የአዋጁን መንፈስ ተከትለው ሊወጡ የሚችሉ መመርያዎች እንደሚኖሩ የሚገልጽ በመሆኑ፣ ይህም መመርያ ይህንኑ መንፈስ ተከትሎ የሚወጣ ነው ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት በበላይነት የሚቆጣጠረው ባንኩ በየጊዜው የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱ መመርያዎችን ሳያወጣ የቆየ ሲሆን፣ በርካቶቹ መመርያዎች ብዙ ክርክር ሲያስነሱ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ መመርያዎቹ ገዥ ስለሚሆኑ ተቀብሎ ተግባራዊ ከማድረግ ውጪ የተለየ አማራጭ ባለመኖሩ ሲሠራባቸው ቆይተዋል፡፡ በቅርቡ ተግባራዊ ይሆናል የተባለው የኮርፖሬት ገቨርናንስን የሚመለከተው መመርያ ግን የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት የጠራ የአሠራር ሥልት ተከትለው እንዲሠሩ የሚያመላክት በመሆኑ፣ እንደከዚህ ቀደሞቹ መመርያዎች የጠነከረ ትችት የሚቀርብበት እንዳልሆነ ያነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያዎችና ባለአክሲዮኖች ይገልጻሉ፡፡

  ብሔራዊ ባንክ በበላይነት የሚቆጣጠራቸው የባንክ፣ የመንድና የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የሚስተዋለውን የሥራ አመራር አወቃቀር ተመርኩዞ ለማውጣት ያዘጋጀው አዲስ መመርያ ትኩረት፣ በተቋማቱ ውስጥ ሁለንተናዊና የተሳሰረ የሥራ አመራር ሥልት እንዲዘረጋ የሚያስችል ነው በሚለው ሐሳብም ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ የመመርያው መንፈስ የፋይናንስ ተቋማትን የበለጠ ሊያጠናክር ይችላል የሚል እምነት ያላቸው ወገኖች የመኖራቸውን ያህል፣ በአንፃሩ ግን የመመርያው አንዳንድ አንቀጾች ባንኮች የራሳቸውን የአሠራር ስልት ተከትለው እንዳይሠሩ የሚያደርግ ነው የሚል አስተያየት እየሰነዘሩ ነው፡፡  

  የኮርፖሬት ገቨርናንስ መመርያው ከዚህ በፊት ያልነበሩ ይዘቶችን አካቷል፡፡ በተለይ በባንኮች አሠራር ላይ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ አሠራራቸው በመመርያ ውስጥ በተቀመጠው መሠረት እንዲሆን የሚደነግግ ነው፡፡ የተቋማቱ የበላይ ኃላፊዎች የአመራረጥ፣ የትምህርትና የልምድ ስብጥር፣ የአገልግሎት ዘመንና የጥቅማ ጥቅም ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ መሥራት ያለባቸው በዚህ መንገድ ነው የሚል ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ በአዲሱ የኮርፖሬት ገቨርናንስ መመርያው፣ የተቋማቱን የቦርድ ስብሰባ ሥርዓትን የተመለከተው ጉዳይ ጠንከር ያሉ አንቀጾችንም የያዘ ነው፡፡

  የፋይናንስ ተቋማት የቦርድ ዳይሬክተሮች የስብሰባ ሥነ ምግባሮችን የሚያንፀባርቁ አዳዲስ ደንቦችን አውጥተው መተግበር ያለባቸው ስለመሆኑም መመርያው ያሳስባል፡፡ የሁሉም የፋይናንስ ተቋማት የቦርድ ስብሰባቸውን ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ መካሄድ ይኖርባቸዋል ይላል፡፡ ይህም የቦርድ አባላት ከዚህ በፊት ያካሂዱ የነበረው ስብስባ በዚህ ደንብ መሠረት ቀን እንዲቆረጥለት አድርጓል፡፡ ከዚህ በፊት የቦርድ ስብሰባዎችን በተመለከተ በፋይናንስ ተቋማቱ ዙሪያ አንድ ወጥ የሆነ አካሄድ የሌላቸው ቢሆንም፣ ይህ መመርያ ግን በተመሳሳይ መንገድ እንዲያከናውኑ የሚደነግግ ነው፡፡ ከቦርድ ስብሰባ ክንውን ጋር በተያያዘ መተግበር አለባቸው ያላቸውንም ነጥቦች አስቀምጧል፡፡ ከስብሰባ ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ በተቋማቱ መተግበር አለባቸው ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ የተቋማቱ ቦርዶች በየጊዜው የሚያካሄድባቸው ስብሰባዎች በግልጽ መታወቅና አጀንዳውም ቀድሞ እንዲደርሳቸው ማድረግ የሚገባ መሆኑን ነው፡፡ የቦርዱ ሊቀመንበርና ዋና ጸሐፊ ለቦርዱ አባላቶች ይህንን የማሳወቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡  በተጨማሪም ሁሉም የቦርድ ዳይሬክተሮች የስብሰባውን ይዘት የተመለከተ መደበኛ ማስታወሻዎችን ጨምሮ የስብሰባውን አጀንዳ ሰብስበው ቢያንስ ከሦስት ቀናት በፊት ማሳወቅ ይኖርባቸዋል፡፡

  የቦርድ ሰብሳቢዎችና የቦርድ አባላት ስብሰባዎች ላይ ካልተገኙ መወሰድ ስላለበት ዕርምጃም መመርያው ያስቀመጣቸው ነጥቦች አሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ የፋይናስ ተቋማቱ የቦርድ ሊቀመንበር በአንድ በጀት ዓመት ውስጥ በሚካሄዱ የቦርድ ስብሰባዎች 75 በመቶ በሚሆኑት ላይ መገኘት የሚኖርበት መሆኑን መደንገጉ አንዱ ነው፡፡ አንድ የቦርድ ሊቀመንበር ከዚህ ደንብ ውጪ በስብሳበዎች ያልተገለጸ ከሆነ ያልተገኘበት ምክንያት  በባለክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ቀርቦ በቂና አሳማኝ ሆኖ ካልተገኘ፣ ከቦርድ ሰብሳቢነቱ ሊያሰርዘው እንደሚችልም ያሳስባል፡፡

  መመርያው የቦርድ አባላቶች የጥቅማ ጥቅም ክፍያን በተመለከተ ከዚህ በፊት ያልተለመደና ጠንከር ያለ አንቀጽ ስለመካተቱም ያነጋገርናቸው አንዳንድ የባንክ ባለሙያዎች ይጠቅሳሉ፡፡ እንደባለሙያዎቹ ማብራርያ፣ ከዚህ ቀደም የባንክ ቦርድ አባላት ክፍያ በንግድ ሕጉ መሠረት ተድርጎ የሚሠራበት ነበር ይላሉ፡፡ ይህም ባንኩ ወይም ኢንሹራንስ ኩባንያው ከዓመታዊ ከጠቅላላ ትርፉ ላይ በመቶኛ ተሰልቶ ለቦርድ አባላት ይከፈል ነበር፡፡ ይህ አሠራር ከጥቂት ዓመታት በፊት የቦርድ አባላት ክፍያ በ50 ሺሕ ብር እንዲገደብ ብሔራዊ ባንክ መመርያ በማውጣቱ፣ የሁሉም ተቋማት ቦርድ ዳይሬክተሮች ከፍተኛ ክፍያ 50 ሺሕ ብር ሆኗል፡፡ ይወጣል ተብሎ በሚጠበቀው መመርያ ላይ የቦርድ አባላት ክፍያ መጠን በ50 ሺሕ ብሩ የሚፀና መሆኑን የሚመለከት ቢሆንም፣ የ50 ሺሕ ብሩ ክፍያ ተፈጻሚ የሚሆነው ግን የቦርድ አባላቶች በስብሰባዎች ላይ የተገኙበትን ጊዜ መሠረት ባደረገ መልኩ መካፈል እንዳለበት ይገልጻል፡፡ አንድ የቦርድ አባል በበጀት ዓመቱ ውስጥ መካሄድ ካለባቸው በ12 ስብሰባዎች ውስጥ በአራቱ ላይ የተገኘ ከሆነ ከጠቅላላው ክፍያ (50 ሺሕ ብር) ውስጥ የሚደርሰው ከ25 በመቶ በታች ሊሆን ይገባል በማለት ለቦርድ አባላት ክፍያ የሚሰጠው በተሰበሰቡበት የስብሰባ መጠን ተሰልቶ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡

  ይህ ውሳኔ የቦርድ አባላት ሊያገኙ የሚችሉትን ጥቅም ቀስ በቀስ የሸረሸረ ነው የሚል አስተያየት የሚሰነዝሩ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ግን በአንዳንድ ባንኮች ውስጥ የነበረውን ‹‹ፉክቻ›› ሊያስቀር ይችላል የሚል እምነት ያሳደረ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ክፍያው እንዲህ መሸራረፉ ሊሠሩ የሚችሉ ሰዎችን ያሳጣል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡

  ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ከጠቅላላ የባንኩ ትርፍና እስከ አምስት በመቶ የሚሆነው ለቦርድ አባላት እንዲከፈል ይፈቀድ ነበር፡፡ ሁሉም ባንኮች በመቶኛ የሚያስቀምጡት መጠን የተለያየ ቢሆንም፣ ክፍያቸው ዓመታዊ ትርፍን መሠረት ያደረገ ነበር፡፡ በዚህ ዓይነት በሚፈጸመው ክፍያ ትላልቅ ባንኮችን በቦርድ አባልነት የሚያገለግሉ አባላት ከ300 ሺሕ ብር በላይ ዓመታዊ ክፍያ ያገኙበት ወቅትም ነበር፡፡ በኋላ ግን ብሔራዊ ባንክ ክፍያው በ50 ሺሕ ብር እንዲወሰን በማድረጉ የቀድሞውን አሠራር አስቀርቷል፡፡

  ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው መመርያ የቦርድ አባላት ኃላፊነቶች ምን እንደሆኑም ያስቀምጣል፡፡ የፋይናንስ ተቋማቱ የቦርድ አሠራር ይዘተን በተመለከተ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን የሚያሳይና የባለአክሲዮኖችን ግንኙነትን በተመለከተ የጠራ ፖሊሲ መንደፍ የሚኖርበት ስለመሆኑ ይደነግጋል፡፡ ከዚህም ሌላ ቢያንስ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸምን የመገምገም አሠራርን መከተል የሚኖርበትና ያለፉትን የአሠራር ስህተቶች ከሥር የመፈተሽ ዓላማ ይዞ ግልጽ በሆነ መንገድ በኩባንያዎች ግብ፣ ስትራቴጂና የአፈጻጸም ብቃት ዙሪያ መወያየት የሚያስችል ስልት እንዲኖርም ይጠቁማል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁሉም የፋይናንስ ተቋማት ስትራቴጂዎችን፣ ፖሊሲዎችን፣ መመርያዎችንና አካሄዶችን ዓመታዊ የቢዝነስ ፕላንና በጀትን የመከለስና የማፅደቅ ስልትን መከላከል የሚያስችል ነው፡፡ ቦርዱ ከዚህ በተጨማሪ የተቋማቱን ማኔጅመንት አፈጻጸም ብቃት የመከታተል ኃላፊነቱን በመወጣት፣ በመመርያው የተቀመጡ ቁልፍ የብቃት ማሳያዎችን (Key Performance Indicator) መከተል እንደሚኖርበትም መመርያው ይጠቁማል፡፡

  በሌላ በኩል ስልቶችን በመንደፍ በኩባንያ ሁለንተናዊ የኃላፊነትና የተጠያቂነት መስመር ተግባራዊ እንዲሆን በማድረግ መላውን ኩባንያ ፈትሾ አዋጪ የአወቃቀር ስልትን ተግባራዊ ማድረግ የቦርዱ ኃላፊነት ሲሆን፣ ቦርዱ በመመርያ ውስጥ በዝርዝር የተጠቀሱ የሥነ ምግባር ደንቦችን፣ በቦርዱና በከፍተኛ የማኔጅመንት ኃላፊዎች እንዲተገበር የማስፈጸም ግዴታ አለበት፡፡

  በዚሁ መሠረት የቦርዱ ሊቀመንበርና ጸሐፊ የጠቅላላ ጉባዔውን ቃለ ጉባዔ በ15 ቀን ውስጥ ለብሔራዊ ባንክ የመስጠት ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ በብሔራዊ ባንክ የኮርፖሬት ገቨርናንስ መመርያ መሠረት የተቋማቱ ቦርድና ከፍተኛ የአመራር ኃላፊዎች በአጠቃላይ ለባለአክሲዮኖች፣ ለቆጣቢዎችና ለባለድርሻ አካላት ግልጽነትን የሚያሳይ ሒደት መከተል የሚኖርባቸው ሲሆን፣ በዚህም ሚስጥራዊነት እንዳይኖር የተለያዩ ነጥቦችን በማስቀመጥ አሳይቷል፡፡ ይህም እንደ የብድር አወሳሰንና አሰጣጦች ግልጽ እንዲሆኑ ያሳስባል፡፡ በዚህም መሠረት ከውጭ ምንዛሪ ዝውውር ጋር በተያያዘ የሚከናውኑ ዝርዝር ሒደቶችም በአምስት ቀናት ውስጥ ለብሔራዊ ባንክ ማሳወቅ ይኖባቸዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የገንዘብ ዝውውሮቹ የተፈጸመለት አካልን ስም፣ የዝውውር ዓይነትና መጠን ማሳወቅ የሚኖባቸው ሲሆን፣ በተለይ የዝውውሩን ይዘቶች በተመለከተ ቢያንስ ቢያንስ በየሩብ ዓመቱ ማሳወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህ በማዕከላዊ ባንክ ሕግና በተቋማቱ ፖሊሲና ደንብ መፈጸማቸውን ማሳየት እንደሚኖርባቸውም ተመልክቷል፡፡  

  የተቋማቱ ግምታዊ የሒደት ሪፖርት ጽሑፍና አስተያየት በኩባንያዎቹ ድረ ገጽ ላይ መጫን ያለባቸውና ሲሆን፣ ይህም የአፈጻጸም ሒቶች ሕግን፣ መመርያን ደንብን የተከተለ መሆን ይኖርበታል ብሏል፡፡

  የፋይናንስ ተቋማቱ የአፈጻጸም ብቃታቸውን የተመለከተ መረጃ በዋነኛነት ሰፊ ሥርጭት ባላቸው ጋዜጣዎች ላይ መግለጽ ይኖባቸዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ ዓመታዊ የኦዲት ሪፖርታቸውንም በጋዜጣ የማሳተም ግዴታ አለባቸው፡፡

  ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው መመርያ ውስጥ አነስተኛ አክሲዮን ያላቸው ባለአክሲዮኖች በቦርድ ውስጥ እንዲካተቱ፣ ራሱን የቻለ የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከምርጫው ሦስት ወር በፊት እንዲቋቋም የሚሉና ሌሎችንም መተግበር ይገባቸዋል ያላቸውን አሠራሮች አካትቷል፡፡ በእነዚህ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ በቋሚነት ወይም በኮንትራት የሚሠሩ ሠራተኞች በቦርድ ውስጥ መቀመጫ ማግኘት የማይችሉ ስለመሆኑም ይገልጻል፡፡ የቦርድ አባል ብድር እንዳይወስድም ይከለክላል፡፡

  ዘርዘር ብለው የተገለጹ የሥነ ምግባር ደንቦችን ተግባራዊ እንዲሆኑ ያመለከተ ሲሆን፣ በተለይ የቦርድና የማኔጅመንት ከፍተኛ ኃላፊዎች ደንቦችን ሚስጥር ጠብቆ የመያዝና ኃላፊነታቸውን ተጠቅመው ራሳቸውን ወይም ሌላ ወገን ከሕግና ደንብ ውጪ መፈጸም የማይቻል መሆኑን አመልክተዋል፡፡    

  ብሔራዊ ባንክ ይህንን መመርያ የማይከተሉ ኩባንያዎች ላይ የገንዘብና የአስተዳደራዊ ቅጣቶችን የሚጥል ሲሆን፣ በዚህ ደንብ ዙሪያ ከፋይናንስ ተቋማት አመራሮች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ ተቋማቱም የየራሳቸውን አስተያየት ሲሰጡበት ቆይተዋል፡፡ ይህ መመርያ በቅርቡ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ መመርያው በአገሪቱ ውስጥ ያሉ 19 ባንኮች፣ 17 ኢንሹራንስ ኩባንያዎችና 32 ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን የሚመለከት ነው፡፡

   

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች