Monday, October 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሦስቱ መሥሪያ ቤቶች በደመወዝ ጭማሪው ላይ ያደረጉት እንቅስቃሴ በተግባር ሲመዘን

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለፈው በጀት ዓመት ትልልቅ መነጋገሪያ ሆነው ካለፉ ክስተቶች መካከል የደመወዝ ጭማሪ ዋናው ነበር፡፡ ለመንግሥት ሠራተኛው ማኅበረሰብ ይደረጋል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የደመወዝ ጭማሪ ብዙ አነጋገሮ፣ የዋጋ ንረትንም አስከትሎ ማለፉን መንግሥት ያምናል፡፡ ማመን ብቻም ሳይሆን ‹‹ኢኮኖሚያዊ መሠረት የላቸውም›› ባላቸው የዋጋ ጭማሪዎች ላይ ዕርምጃ እወስዳለሁ በማለት በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሲያሰማ ከርሟል፡፡

በአዲስ አበባና በክልሎች የችርቻሮ ሱቆች ላይ የተወሰዱት ዕርምጃዎች ይታወሳሉ፡፡ በዋጋ ጭማሪው ላይ የተሳተፉት ግን ትልልቅ አስመጪዎችና ትልልቅ ፋብሪካዎች እንደነበሩ መንግሥት ከሰጠው መግለጫ ለመታዘብ ተችሏል፡፡ እርግጥ አምራቾቹን በማወያየት ዋጋ እንዲያስተካክሉ ማድረጉን፣ እንዲያተካክሉ ማግባባቱንና አሻፈረኝ ሲሉ ያንገራግሩ በነበሩት ላይም ማስጠንቀቂያ በማውጣት እንዲታቀቡ ለማድረግ መቻሉን የገለጸው መስከረም በባተ ሰሞን ነበር፡፡

የንግድና የሸማቾች ጉዳይ ከሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መካከል በመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ጭማሪ አሳበው ዋጋ አንረዋል ያላቸውን አካላት በማነጋገር፣ ሲያስፈልግም በማስጠንቀቅና ዕርምጃ በመውሰድ ሥራ ተጠምዶ እንደነበር ቀድሞ የገለጸው የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ነበር፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መርከቡ ዘለቀ በዓመቱ መጀመሪያ በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት፣ ካነሷቸው ነጥቦች መካከል በተለይ በሐምሌ ወር 2006 ዓ.ም. የተደረገውን የደመወዝ ጭማሪ ምክንያት በማድረግ የተደረጉ የዋጋ ጭማሪዎችን የዳሰሰ ነበር፡፡ የዋጋ ጭማሪውን ለማርገብ ዕርምጃዎች መወሰዳቸውን አስታውሰዋል፡፡

የደመወዝ ጭማሪውን መነሻ አድርገው ምንም ዓይነት ‹‹የኢኮኖሚ ምክንያት ሳይኖር›› የዋጋ ጭማሪ በማድረግ በተለይ በምግብና ምግብ ነክ በሆኑ ሸቀጦች ላይ የታየው የዋጋ ለውጥ ችግር ፈጥሮ እንደነበር አቶ መርከቡ ያስታውሳሉ፡፡ በተለይ አገር ውስጥ በሚመረቱና በሚፈበረኩ ፈሳሽ የምግብ ዘይቶች፣ የታሸጉ ውኃዎች፣ ዱቄት፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ሩዝ ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ የተጋነነ እንደነበር ገልጸው ነበር፡፡ የግል ትምህርት ቤቶችና የግል ጤና ተቋማት ላይ የታየው የዋጋ ለውጥ ጎልቶ መታየቱንም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ይህንን ጡዘት ያረግባል ተብሎ አብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ የነበረ ሲሆን፣ ይኸው ኮሚቴ ምርመራ በማካሄድ የዋጋ ንረቱን ለማርገብ ሲንቀሳቀስ ነበር፡፡ ዋጋ ጨምረዋል ከተባሉ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ጋር ውይይት ተደርጎም የጨመሩትን ዋጋ እንዲያስተካክሉ መደረጉን ገልጸው ነበር፡፡ አቶ መርከቡ የዋጋ ንረቱ በፍላጎትና በአቅርቦት ላይ ወይም በእሳቸው አገላለጽ ምንም ዓይነት ኢኮኖሚዊ ክስተቶች ሳይኖሩ የተደረገ ከመሆኑ በላይ፣ የደመወዝ ጭማሪ የተደረገው ከአገሪቱ ሕዝቦች አንድ ከመቶውን ብቻ ለሚወክለው የመንግሥት ሠራተኛ በመሆኑ፣ ይህ ክፍል አገልግሎት ሰጪ እንጂ አምራች ባለመሆኑ የጎላ የፍላጎት ጭማሪ እንደማይከሰት እየታወቀ ዋጋ መጨመሩ አግባብ አለመሆኑን ባለሥልጣኑ ሲያስታውቅ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

 የዋጋ ጭማሪውን ሊያነሳሱ የሚችሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ሳይከሰቱ፣ የዓለም የገበያ ሁኔታ በነተረጋጋበት መልኩ የተደረገው የምግብና ምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ የታየው ጭማሪ አግባብ ባለመሆኑ፣ ዋጋው ወደነበረበት መጠን እንዲመለስና እንዲስተካከል ለማድረግ መሞከሩን ዋና ዳይሬክተሩ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በመሆኑም የአገር ውስጥ የምግብ ሸቀጥ አምራቾች ዋጋ እንዲያተካክሉ በተነገራቸው መሠረት አስተኮ ምግብ ኮምፕሌክስ፣ ያምሮት ምግብ ኮምፕሌክስ፣ ጀማነሽ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ድሬዳዋ ፉድ ኮምፕሌክስ የመሳሰሉትን ጨምሮ ትልልቅ የምግብ ሸቀጥ አምራች ፋብሪካዎች ዋጋ እንደሚያተካክሉና ከወደመዝ ጭማሪ በፊት የነበራቸውን የመሸጫ ዋጋና ያስተካከሉትን ዋጋ ጭምር ለመንግሥት ማሳወቃቸውን፣ በችርቻሮ ከመሸጥ ጀምሮ በኅብረት ሆነው ለሚመጡ ሸማቾች ከጅምላ መሸጫ ዋጋ ቀንሰው ለማቅረብ ፍላጎት እንዳላቸው በዋና ዳይሬክተሩ መግለጫ ተመልክቷል፡፡ ቢራ ፋብሪካዎች፣ የታሸገ ውኃ አምራቾች ወዘተ ዋጋ እንዲያተካክሉ ጥሪ ተደርጎላቸው አስተካክለዋል፤ ያንገራገሩም ነበሩ ተብሏል፡፡

በአዲስ አበባ 1671 የግል ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ሲሆን አብዛኞቹ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል፣ ያሳዩት የዋጋ ጭማሪም ከፍተኛ እንደነበርና በርካቶችም ዋጋ ለመቀነስ አንገራግረው እንደነበር አቶ መርከቡ አስታውሰዋል፡፡ ጥናት ተደርጎም በየዓመቱና በየመንፈቁ ዋጋ የሚጨምሩ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ መታወቁንም ተናግረዋል፡፡ በርካታ ትምህርት ቤቶች የዋጋ ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ተገኝተዋል፡፡ በሕግ ይጠየቃሉ ተብሎ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ በተለይ 24 ትምህርት ቤቶች ትልቅ ችግር አለባቸው ተብሎ ተለይተው እንደነበርም አይዘነጋም፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ዕርምጃዎች

ምንም እንኳ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን፣ በዚህ መልኩ መንቀሳቀሱን ቢገልጽም፣ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮም ሆነ የንግድ ሚኒስቴር ያደረጉትን እንቅስቃሴ በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥተው ነበር፡፡ በጥቅምት ወር የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በምክትል ኃላፊው አቶ ገመቺስ መላኩ አማካይነት በሰጠው መግለጫ፣ የሦስት ወራት ሪፖርቱ ውስጥ ካካተታቸው ነጥቦች መካከል የግብይትና ገበያ የማረጋጋት ሥራዎች ይጠቀሳሉ፡፡

ንግድ ቢሮው በገበያ ማረጋጋት መስክ አከናወንኳቸው ካላቸው ተግባራት መካከል የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪን ሰበብ በማድረግ የተደረጉ የዋጋ ጭማሪዎችን አትቷል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ያላቸውንና የሌላቸውን የዋጋ ጭማሪዎች በመለየት፣ የዋና ዋና የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች የጅምላና ችርቻሮ ዋጋን በመከታተል መረጃ መስጠቱን ያስታወቀው ንግድ ቢሮው፣ ሕገወጦችን በማስጠንቀቅና እምቢ ያሉትን በመቅጣት (በብዛት በማሸግ) ዕርምጃ መውሰዱን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ከዚህ ባሻገር በፌደራልና በከተማው አስተዳደር መሥሪያ ቤቶች ለሚሠሩ የመንግሥት ሠራተኞች በየመሥሪያ ቤቶቻቸው ሸቀጦችን እንዲገኙ በማድረግ የዋጋ ንረቱን ለመግታት እንደሞከረ አቶ ገመቺስ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ይህም ብቻ አይደለም፡፡ እስከ መስከረም መጨረሻ በነበረው የሩብ ዓመት ውስጥ ጥሬ ስንዴ 334,600 ኩንታል፣ የስንዴ ዱቄት 244 ሺሕ ኩንታል፣ ስኳር 259,196 ኩንታል ለከተማው ነዋሪ፣ በተለያዩ ተቋማት በኩል ማከፋፈሉን አቶ ገመቺስ አስታውቀዋል፡፡ ይህ ግን በታሰበው ወይም በታቀደው ልክ የሆነ እንዳልነበር ልብ ይሏል፡፡ ለአብነት ለአዲስ አበባ ይከፋፈላል ተብሎ የታሰበው የጥሬ ስንዴ ዱቄት መጠን ግማሽ ሚሊዮን ኩንታል ነበር፡፡ የስንዴ ዱቄት መጠኑ ደግሞ 462 ሺሕ ኩንታል ሲሆን የስኳር መጠን 306 ሺሕ ኩንታል ይሆናል ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡ የአቅርቦቱ መጠን ከዕቅዱ ጋር ሳይጣጣም ቀረ፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በፓልም ዘይት ረገድ ካሰበው በላይ አቅርቦት በገበያው ውስጥ መኖሩን ይፋ ማድረጉም አይዘነጋም፡፡ 10.5 ሚሊዮን ሊትር ፓልም ዘይት ለማቅረብ አቅዶ 13.3 ሚሊዮን ሊትር ገደማ በማቅረብ ተሳክቶልኛል ብሏል፡፡

ንግድ ሚኒስቴር ምን አለ?

ንግድ ሚኒስቴርም ተመሳሳይ ይዘት ያለውን፣ የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡ ሚኒስትር ከበደ ጫኔ የመንግሥት ሠራተኞችን የደመወዝ ጭማሪ ምክንያት በማድረግ ተፈጥሯል ስለተባለው የዋጋ ንረት፣ ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት መሥሪያ ቤቶች ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው ሪፖርት አሰምተዋል፡፡ ‹‹የመንግሥት ሠራተኞችን ደመወዝ መጨመርን ሰበብ በማድረግ ያለበቂ ምክንያት በሸቀጦች ላይ ዋጋ በጨመሩ አምራች ድርጅቶች፣ አስመጪዎችና ቸርቻሪ ነጋዴዎችን በተደጋጋሚ በማወያየት የማስተካከያ ዕርምጃ በመውሰድ ለመቆጣጠር ጥረቶች ተደርገዋል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር የመንግሥት ዋጋ ተመን የሚመለከታቸው መሠረታዊ የሚባሉትን ፍጆታ ሸቀጦች በሚመለከት ሪፖርታቸው እንዳመለከተው፣ 2.5 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ዱቄት በተመረጡ ፋብሪካዎች ተፈጭቶ፣ ለዳቦ ጋጋሪዎች እንዲሰራጭ ታቅዶ ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ 2.2 ሚሊዮን ኩንታል መሰራጨቱን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡ ከሦስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስኳር ለማሰራጨት ታስቦ እንደነበር ሆኖም የ1.8 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ መሳካቱን ተናግረዋል፡፡ እንደ አዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ሁሉ በንግድ ሚኒስቴርም ስኬታማ የተባለው የዘይት ስርጭት ነው፡፡ 135.7 ሚሊዮን ሊትር ይሰራጫል ተብሎ የተሠራጨው ግን 145 ሚሊዮን ሊትር መሰራጨቱን (ለጅንአድ ግን 160.5 ሚሊዮን ሊትር ቀርቦለታል) በሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡

ይህ ሁሉ ቢባልም ግን በአገሪቱ የሚታየው የዋጋ ንረት እንደቀጠለ ነው፡፡ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የታኅሣሥ ወር 2007 ዓ.ም. የአገር አቀፍና የክልሎች የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክሶች (የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ማለት ሸማቾች ለተወሰኑ ዕቃዎችና አገልግሎቶች የከፈሉትን አማካይ የዋጋ ለውጥ ለመለካት የሚያገለግል ተቋሚ አኃዝ ነው ሲል ኤጀንሲው መፍቻ አስቀምጧል) የሚጠቁሙት የዋጋ ግሽበት መመዝገቡን ነው፡፡

በታኅሣሥ ወር 2007 ዓ.ም. የተመዘገበው የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ አገራዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት አኳያ በ7.4 ከመቶ ጭማሪ አሳይቷል ያለው የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ሪፖርት፣ በታኅሣሥ ወር የታየው የምግብ ዋጋ የ12 ወራት ተንከባላይ ግሽበትም 5.4 ከመቶ መድረሱን ይጠቁማል፡፡ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበትም በ9.6 ከመቶ ጭማሪ ታይቶባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል የታኅሣሥ ወር የ2007 ዓ.ም. የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር ጋር ሲነፃፀርም በ7.1 ከመቶ ጭማሪ በማሳየት የዋጋ ግሽበት ማስከተሉ ታውቋል፡፡ ንግድ ሚኒስቴርን ሆነ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የዋጋ ግሽበትን በሚመከት በሪፖርታቸው ያካተቱት ነገር አልታየም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች