[ክቡር ሚኒስትር ሰሞኑን የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ስለነበር ወደ ቤት የሚገቡት እያመሹ ነው፡፡ በተደጋጋሚ በማምሸታቸውም ባለቤታቸው ደስ አላላቸውም፡፡ እንደለመዱት አምሽተው ሲገቡ ባለቤታቸው ሳይተኙ ጠበቋቸው]
- የት ነበርክ?
- ማለት?
- የተጠየቅከውን ብቻ መልስ፡፡
- ምን እያልሽ ነው ሴትዮ?
- የት ነው ያመሸኸው?
- ሥራ ላይ ነበርኩ፡፡
- የምን ሥራ ነው እስከ እኩለ ሌሊት?
- ስብሰባ እንዳለ ታውቂያለሽ አይደል?
- እስከዚህ ሰዓት ግን ስብሰባ የለም፡፡
- እሱማ የለም፡፡
- እኮ ታዲያ የት አመሸህ?
- እንግዶቹን ይዘን ዞር ዞር ማለት አለብን፡፡
- የምን እንግዳ?
- ከአፍሪካ አገሮች የመጡትን መሪዎች ነዋ፡፡
- ታዲያ ይኼ ያንተ ሥራ ነው?
- ለእኔም አስቢልኝ እስቲ?
- ምንድነው የማስብልህ?
- እኔም እኮ ትንሽ መዝናናት ያምረኛል፡፡
- እኔስ አያምረኝም?
- አንቺማ ሁሌም እንደተዝናናሽ ነው፡፡
- እኮ እኔና አንተ ለምን አብረን አንዝናናም?
- ማለት?
- ስታመሽ ለምን አትጠራኝም?
- ማን? አንቺን?
- አዎና፡፡
- መሪዎች እኮ ናቸው፡፡
- ቢሆኑስ?
- መዝናናት እኮ ስልሽ ዝም ብሎ መዝናናት አይደለም፡፡
- ታዲያ ምንድነው?
- የሥራ መዝናናት ነው፡፡
- ምን ማለት ነው?
- እየሠራሽ በዚያው ትዝናኚያለሽ፡፡
- እኮ እንዴት?
- ያው አገሪቷን መሸጥ አለብን፡፡
- ቀን ለምን አትሸጧትም?
- ቀን ለሕዝቡ እንሸጣለን፣ ማታ ደግሞ ለመሪዎቹ፡፡
- አሁን እኔ ልሙት ምንድነው የምትሸጡት?
- በቃ የሚሠራውን ሥራ እናሳያቸዋለን፡፡
- ድንቄም ሥራ፡፡
- ምን አልሽ አንቺ?
- ለመሆኑ ምን እየሠራችሁ ነው?
- ስንት ነገር አለ?
- እኮ ምን?
- ባቡር፣ ግድብ፣ መንገድ ኧረ ስንቱ?
- አልቀረብህም፡፡
- እንዴት?
- አሁን አገር ለመሸጥ ማምሸት ምን ያስፈልጋል ነው የእኔ ጥያቄ፡፡
- እሱማ ቀንም እንሸጣለን፡፡
- ከአሁን በኋላ ይኼ ማምሸት አይፈቀድም፡፡
- አገሪቷ አትሸጥ ነው የምትይኝ?
- አገሪቷም ትሸጥ፡፡
- ታዲያ ሳላመሽ እንዴት እሸጣለሁ?
- ቀን ሽጣት፡፡
- ይሻላል?
- አዎን፡፡
- ማታስ?
- ማታ ቀን ስለሸጥከው ለእኔ ታጫውተኛለህ፡፡
- እሺ፡፡
- በል አሁን እንተኛ፡፡
- እሺ ደህና እደሪ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ በጠዋት ቢሮአቸው ሲገቡ አማካሪያቸውን አገኙትና ቢሮ ገብተው ማውራት ጀመሩ]
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ሆንክ?
- አይ ዓይንዎት ቀልቷል፡፡
- ማታ አምሽቼ ነው፡፡
- አመመዎት እንዴ?
- ኧረ በፍጹም ትንሽ የእንቅልፍ ማነስ ነው፡፡
- ስብሰባ ነበር እንዴ?
- ስብሰባ እንኳን አልነበረም፡፡
- እንዴት አመሹ? ብዬ ነው፡፡
- ያው እንግዶቹን ይዘን ወዲህ ወዲያ ስንል ነው፡፡
- ኦ…. ትንሽ ወሳሰዱ?
- መቼ ይቀራል ብለህ ነው?
- አሁን ገባኝ፡፡
- ምን አዲስ ነገር አለ?
- ስለምን?
- ስለፖለቲካው ነዋ፡፡
- ኧረ ብዙ ነገር አለ፡፡
- እና ምን ተባለ ደግሞ?
- ሰው ደስተኛ አይደለም፡፡
- በምኑ?
- በምርጫ ቦርድ ውሳኔ፡፡
- ለምንድነው ደስተኛ ያልሆነው?
- ውሳኔው ክፍተት አለበት እየተባለ ነው፡፡
- እኮ የምን ክፍተት?
- በርካታ ሊመለሱ የሚገባቸው ጥያቄዎች አሉ፡፡
- እሱ የቦርዱ ሥራ ነው፡፡
- አውቃለሁ ግን…
- የምን ግን ነው?
- የፖለቲካው ምኅዳር እኮ እየጠበበ ነው፡፡
- ቢጠብ ታዲያ ምን ችግር አለው?
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- አሁን እንዲያውም ፋሽኑ ጠበብ ያለ ነገር ነው፡፡
- እ…
- ምንድነው እ… የምትለው?
- ይኼ እኮ ከእኛ ዓላማ ጋ ይቃረናል፡፡
- እንዴት ነው የሚቃረነው?
- ሁሌም ቢሆን የፖለቲካው ምኅዳር ይስፋ ነው እኮ የምንለው?
- አሁንም ቢሆን እኮ ሰፊ ነው፡፡
- እኮ እንዴት?
- ወረቀት ላይ ከሰፋ ይበቃል፡፡
- እ…
- በተግባር ግን መጥበብ አለበት፡፡
- አልገባኝም፡፡
- ሰው ሰፊ ነገር እንዳይሰለቸው ነው፡፡
- ለምን ይሰለቸዋል?
- ያው ምርጫ ቦርድም ሆደ ሰፊ ነኝ ይላል፣ እኛም የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፊ ይሁን እንላለን፣ ስለዚህ ሰው ሰፊ ነገር እንዳይበዛበት ነው፡፡
- እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- እውነቴን ነው እንጂ፡፡
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር እየተተቸን ነው እኮ፡፡
- ማነው የሚተቸን?
- ሕዝቡ ነዋ፡፡
- ምን ብሎ?
- እንዲያውም ምን እንደተባለ ያውቃሉ?
- ምን ተባለ?
- ቦርዱ ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ ዕውቅና የሰጠው በጨረታ ይመስላል ሲባል ሰምቼያለሁ፡፡
- እንዴት በጨረታ?
- በቃ በርካታ ጥያቄዎች ሳይመለሱ ያን ውሳኔ መስጠቱ ነው እንደዚያ ያስባለው፡፡
- እሱን ቦርዱ ራሱ ይመልስ፤ እኛ አያገባንም፡፡
- እንደዚያማ ማለት አንችልም፡፡
- ለምን አንችልም?
- በአገሪቷ ውስጥ የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲሰፋ እኛ ትልቁም ሚና መጫወት አለብን፡፡
- እሱንማ አውቃለሁ፡፡
- ደግሞ ለሕዝቡም ማሰብ አለብን፡፡
- እኔም እኮ የምልህ ይኼንን ነው፡፡
- እንዴት?
- ለሕዝቡ የሚበጀውን ፓርቲ እናውቃለን፡፡
- እ…
- ማን ለአገር እንደሚሠራ? ማን እንደሚጠቅም? እናውቃለን፡፡
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- ለአገር ለሚጠቅሙት ነው የተፈረደው፡፡
- እኛን ማነው ፈራጅ ያደረገን?
- ለሕዝቡ የሚጠቅመውን እናውቃለን እያልኩህ?
- ቢሆንም እኛ ሥልጣን የለንም፡፡
- የምን ሥልጣን?
- የመፍረድ ነዋ፡፡
- ለምን?
- እኛው ዳኛ፣ እኛው ከሳሽ፣ እኛው ተከሳሽ፣ እኛው ፈራጅ መሆን እንዴት እንችላለን?
- ታዲያ ምን ይደረግ?
- ሕዝቡ ነዋ መፍረድ ያለበት፡፡
- ለሕዝቡ የሚጠቅመውንማ እኛ እናውቃለን፡፡
- እ…
- የምን እ… ነው?
- ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ያልተጠየከውን አትቀባጥር፡፡
- እኔ እኮ አንድ ነገር አልገባ ብሎኝ ነው፡፡
- ምንድነው ያልገባህ?
- ከፊታችን እኮ ምርጫ አለ፡፡
- ቢኖርስ?
- ለምን ይካሄዳል?
- ምን እያልክ ነው?
- በቃ አያስፈልግማ፡፡
- የሕዝቡ ብቸኛ መሣሪያ እኮ ምርጫ ነው፡፡
- እሱንማ አውቃለሁ፡፡
- የገነባነው ዴሞክራሲ ይፍረስ እያልክ ነው?
- ኧረ በፍጹም፡፡
- ታዲያ ምርጫ እንዴት ይቅር ትላለህ?
- ለሕዝቡ እኛ ካወቅንለት ምን ያደርጋል?
- ምኑ?
- ምርጫው ነዋ፡፡
- ቢሆንም ያስፈልጋል፡፡
- እሱንማ አውቃለሁ፡፡
- ካወቅህ ለምን ትጠይቃለህ?
- ግራ ገብቶኝ፡፡
- ግራ አይግባህ፡፡
- ወይ የፓርቲ ስማችን ይቀየራ?
- ምን ተብሎ?
- እኛው ለእኛው!