Monday, March 4, 2024

ከአገሮች ምርጫ እስከ ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ብዙ የተባለበት የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

እ.ኤ.አ. ከ1963 ጀምሮ የአኅጉሪቱ ዋና ከተማ ሆና የቆየችው አዲስ አበባ ካለፈው ሁለት ሳምንታት ጀምሮ ከአፍሪካ አገሮች የመጡ እንግዶቿን በማስተናገድ ሥራ በዝቶባት ነበር የከረመችው፡፡

ከጥር 22 እስከ 23 ቀን 2007 ዓ.ም. የ34 አገሮች መሪዎችና የአገር ተወካዮች በተገኙበት 24ተኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የተካሄደ ሲሆን፣ ሰፊው የስብሰባው አካል ግን የጀመረው ከአንድ ሳምንት ቀድሞ ከጥር 15 ጀምሮ ነበር፡፡

ለሳምንት በተካሄደው የኅብረቱ ጉባዔ ከ2,500 በላይ የሚሆኑ ከአኅጉሪቱና ከአኅኑሪቱ ውጪ የተገኙ እንግዶች በአዲስ አበባ ተገኝተዋል፡፡ የዚህ ዓመታዊ ጉባዔ ዋናው አካል የሆነውና ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው በሁለቱ መጨረሻ ቀናት የሚካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ነው፡፡

ጉባዔውም በቀደመው ዓመት ላይ ውሳኔ በተሰጣቸውና ለዓመቱ በታቀዱ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት፣ በመገምገምና የውሳኔ ሐሳቦችን በማሳለፍ ለመጪው ዓመት መተግበር በሚኖራቸው ጉዳዮች ላይ ዕቅድ በማውጣት የሚከናወን ነው፡፡

የዘንድሮውም የመሪዎቹ ጉባዔ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጉባዔ ላይ ታቅዶ በነበረው የአፍሪካ ሴቶችን በልማት ስለማጎልበት እና ‹‹ልማት ለ2063›› ላይ በዋናነት እንዲወያይ ታቅዶለት ነበር፡፡

በዕቅዱ መሠረት የተተገበሩ ጉዳዮችንና በጠቃላይ የታዩ ደካማና ጠንካራ ጉዳዮች የመገምገሙ ሒደት እንዳለ ሆኖ፣ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ የዘንድሮውም ጉባዔ ከዋናው አጀንዳ ውጪ ያሉ ጉዳዮች እንዲስተናገዱ አስገድዶ ነበር፡፡

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር በምዕራቡ የአኅጉሪቱ ክፍሎች የተከሰተው የኢቦላ በሽታ አስደንጋጭ ክስተት፣ በመካከለኛው የሰሐራ ክፍል የታየው የድርቅ አደጋ፣ ከናይጄሪያ ጀምሮ እስከ ካሜሩን የዘለቀው ደም አፍሳሹ የቦኮ ሐራም የሽብር መስፋፋት፣ እንዲሁም በደቡብ ሱዳንና በሌሎች አገሮች የተስተዋሉ ግጭቶችና ተዛማጅ ጉዳዮች  በዘንድሮው ጉባዔ ሰፊውን ጊዜ ወስደዋል፡፡

በተለይ የኢቦላ ወረርሽኝና የጽንፈኛው ቡድን የቦኮ ሐራም ጉዳይ የኅብረቱ አባል አገሮችን፣ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተወካዮችን በጋራ ያሳሰቡና አፋጣኝ መፍትሔ ሊበጅላቸው እንደሚገባ ውሳኔ የተላለፈባቸው ጉልህ ጉዳዮች ነበሩ፡፡

የኅብረቱ ኮሚሽነር ዶ/ር ንኮ ሳዛና ድላሚኒ ዙማ በመክፈቻ ንግግራቸው፣ ‹‹ለሕዝባችን የጤናና  የንፅህና አገልግሎትን ለማስፋፋት መዋዕለ ንዋይ ልናፈስ ይገባናል፤›› በማለት አሳሳቢውን የኢቦላ ወረርሽኝ እንዲሁም የኤችአይቪኤድስንና ወባን ማሸነፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ኮሚሽነሯ በምዕራብ አፍሪካ በተለይም በሴራሊዮን፣ በጊኒና በላይቤሪያ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሕልፈት ምክንያት የሆነውን የኢቦላ ወረርሸኝ ለመከላከል በኅብረቱ ሥር በተቋቋመው ድርጅት አማካይነት አጋርነታቸውን ያሳዩ አገሮችን በማመስገን፣ እስካሁን በመረዳዳቱ ላይ ተሳትፎ የሌላቸውን አገሮች እንዲቀላቀሉ ጥሪ አድርገዋል፡፡

በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወረርሽኙን ለመመከት እየተደረገ ካለው ጥረት ባሻገር፣ በችግሩ ተጠቂ የሆኑት ሦስቱ የምዕራብ አፍሪካ አገሮች እየተጎዳ ያለው ኢኮኖሚያቸውን እንዲያገግም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለባቸው ዕዳ እንዲሰረዝላቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን በበኩላቸው፣ በየትኛውም አገር የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝ መቆጣጣር ካልተቻለ ማንኛውም አገር ዋስትና እንደማይኖረው በመግለጽ፣ በጋራ መቆጣጠር አለብን ሲሉ በመሪዎች ስብሰባ ላይ ተናግረዋል፡፡

በሁለቱ ቀን የመሪዎች ስብሰባ ላይ በአባል አገሮች መሪዎች የጋራ አቋም እንደተደረሰበት የተገለጸበት የቦኮ ሐራም ነውጥና የሽብርተኝነት ጥቃት ሌላው ዓብይ አጀንዳ ነበር፡፡

በኅብረቱ ሥር በሚገኘው የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት አክራሪውን ቡድን ለመዋጋት ከአምስት የምዕራብ አፍሪካ አገሮች የተወጣጣ 7,500 ጠንካራ ጦር በናይጄሪያና በከፊል ወደ ካሜሩን ለማሰማራት ያቀረበው ረቂቅ ሐሳብ፣ የመሪዎቹን ድጋፍ አግኝቶ በጉባዔው መጨረሻ ላይ ፀድቋል፡፡ የቦኮ ሐራም አስጊነት ‹‹አስፈሪ ደረጃ›› ላይ መድረሱን ኮሚሽነሯ ለመሪዎች ገልጸዋል፡፡

‹‹ቦኮ ሐራም በተወሰኑ አገሮች ብቻ ሳይሆን በሁሉም ላይ ትልቅ ሥጋት እየፈጠረ ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹የጋራ ጥረታችን እንደገና በማደስ ልንዋጋው ይገባል፤›› በማለት የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

ይኼው ጉባዔ የአኅጉሪቱ መሪዎች የሚሰባሰቡበት ከመሆኑ አንፃር ብዛት ያላቸው ፖለቲከኞች፣ ዲፕሎማቶች፣ የለጋሽ አገሮች ተወካዮች፣ የሲቪል ማኅበራትና ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ይታደሙበታል፡፡ የ54 አባል አገሮችም በጋራ በሚመለከታቸው ጉዳዮች ላይ ትልልቅ ውሳኔ ያስተላልፉበታል፡፡ በየአገሮቹ የፖለቲካ መሪዎችና በተለያዩ ተቋማት ብዙ መልዕክቶች የሚተላለፍበት መድረክ በመሆኑ፣ ከምንም በላይ ትልቁን ቦታ በመያዝ ተወዳዳሪ እንደሌለውም አያከራክርም፡፡

በዚሁ በዘንድሮም ጉባዔ ላይ ከተላለፉት መልዕክቶችና የብዙዎችን ቀልብ ከያዙት አንዱ ባን ኪ ሙን ለመሪዎች በይፋ ያስተላለፉት መልዕክት ሳይጠቀስ አያልፍም፡፡

በተለይ ጥቂት የማይባሉ የአኅጉሪቱ አገሮች በዚሁ በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት ምርጫ የሚያካሂዱበት ከመሆኑ አንፃር፣ መሪዎች በምርጫ ወቅት የሚንፀባረቀውን የዜጎቻቸውን ፍላጎት ወደ ጎን በመተው ሥልጣን ላይ ‹‹ሙጭጭ›› ማለት እንደማይገባቸው፣ የሥልጣን ዘመናቸውን ሊገድቡ እንደሚገባ ሽንቆጥ የሚያደርግ መልዕክታቸውን በግልጽ አስተላልፈዋል፡፡

‹‹በመላው ዓለም የሚገኙ ሕዝቦች የሥልጣን ዘመናቸው መጠናቀቁ እየታወቀ ሥልጣን ለማስረከብ ፈቃደኝነት በማያሳዩ መሪዎች ላይ ሥጋታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡ እኔም በበኩሌ ይኼንን ሥጋት እጋራዋለሁ፡፡ ዴሞክራሲያዊ ባልሆነ መንገድ የሚደረግ የመንግሥት ለውጥንም ሆነ ከሕግ ታቃርኖ ባለው መንገድ ሥልጣንን በመቆናጠጥ መጠቀም በፍጹም አያስፈልግም፤›› ሲሉ ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም፣ ‹‹በአፍሪካም ሆነ በመላው ዓለም ላላችሁ መሪዎች ሁሉ ሕዝባችሁን እንድትሰሙ አሳስባለሁ፡፡ ዘመናዊ መሪዎች የዜጎቻቸውን ምኞትና ፍላጎት በምንም መንገድ ወደ ጎን ሊሉ አይችሉም፤›› ሲሉ አበክረው አስረድተዋል፡፡

ከዋና ጸሐፊው ጠንከር ያለ መልዕክት በኋላ የኅብረቱ አባል አገር መሪዎች ዚምባቡዌን ከነፃነቷ ጀምሮ ላለፉት 34 ዓመታት የሚመሩዋትን የ90 ዓመት አዛውንቱን ፕሬዚዳንት ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ ለአንድ ዓመት የኅብረቱ ሊቀመንበር ሆነው እንዲያገለግሉ በመሉ ድምፅ መርጠዋቸዋል፡፡

በአፍሪካ በርከት ያሉ መሪዎች በሥልጣን ላይ ረዘም ላሉ አመታት መቆየታቸው የተለመደ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ከተለያዩ አቅጣጫዎች ትችቶች ይጎርፋሉ፡፡

በመሆኑም ከ20 እስከ 40 ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆዩ መሪዎች በተደጋጋሚ በትችች ስማቸው ይነሳል፡፡ የካሜሩን ፖል ቢያ ለ39 ዓመታት፣ መሐመድ አብዱላዚዚ (ሰሃራዊ ሪፐብሊክ) ለ38 ዓመታት፣ ቲኦዶር ኦቢያንጎ (ኢኳቶሪያል ጊኒ) ለ35 ዓመታት፣ ጆሴ ኤድዋርዶ (አንጎላ) ለ35 ዓመታት፣ ሮበርት ሙጋቤ (ዚምባብዌ) ለ34 ዓመታት፣ እንዲሁም የኡጋንዳው ዩዌሪ ሙሴቬኒ ለ29 ዓመታት በሥልጣን ላይ የሚገኙ ቀዳሚ ስድስት መሪዎች ለአብነት ይነሳሉ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሕዝባዊ ዓመፅ የተወገዱት የሊቢያው ሙአመር ጋዳፊ ለ41 ዓመታት ሥልጣን ላይ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡

ከዚሁ በአፍሪካ ከሚካሄዱት ከምርጫዎች ጋር በተያያዘ ከጉባዔው ጎን ለጎን አስተያየት ከሰጡት ውስጥ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ይገኙበታል፡፡ ኃላፊዋ ለአገር ውስጥና ለውጭ የሚዲያ ሰዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የሚካሄዱትን ሕዝባዊ ምርጫዎች አገራቸው በቅርበት እንደምትከታተልና የሕዝቦችን ፍላጎት መሠረት ባደረገ ሁኔታ እንዲካሄድ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዚህ ዓመት ይካሄዳሉ ተብለው ከሚጠበቁት ምርጫዎች ከወዲሁ ትኩረት ከተሰጣቸው አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ ናይጄሪያ፣ ብሩንዲና ታንዛኒያ ይገኙበታል፡፡ ከእነዚህ አገሮች ውስጥ በተለይ ከቦኮ ሐራም የሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ ትችቶች ከብዙ አቅጣጫ እየወረደባቸው ያሉት የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን  ይፈተኑበታል የተባለው የናይጄሪያው ምርጫ፣ የአሜሪካን ትኩረት መሳቡን ግሪንፊልድ ገልጸዋል፡፡    

‹‹ናይጄሪያንና ኢትዮጵያን ጨምሮ በደርዘን የሚቆጠሩ አገሮች ምርጫቸውን እንደሚያከናውኑ ይጠበቃል፡፡ አገሮች የሕዝብን አመኔታ ማስከበር የሚችል ምርጫ እንዲያደርጉ የአሜሪካ መንግሥት ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በቅርበት ሆኖ እገዛ ያደርጋል፡፡ በምርጫው የሚሳተፉ ሁሉም አካላት የሕዝቦቻቸውን ውሳኔና ፍላጎት በማክበር ሊፈጠር የሚችለውን ብጥብጥና ጉዳት ለማስወገድ ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው፤›› ያሉት ምክትል ኃላፊዋ፣ በተለይ የናይጄሪያውን አገራቸው ካላት ጥቅም አንፃር የተለየ ትኩረት እንደምትሰጠው ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሚጠበቀውን የግንቦቱን ምርጫ አስመልክቶም፣ ‹‹በኢትዮጵያም ላይም ያለው የአሜሪካ አቋም ተመሳሳይ  ነው፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ጥር 23 ቀን 2007 ዓ.ም. ማምሻውን የተጠናቀቀው የመሪዎቹ ጉባዔ በርከት ባሉ ጉዳዮች ላይ ከመከረ በኋላ ብዙ ውሳኔዎችንም አሳልፏል፡፡ በተለይ በታሪኩ ትልቅ የተባለለትና እስከ እ.ኤ.አ. 2063 ድረስ የተባለለት የ50 ዓመት አኅጉራዊ ዕቅድ ለኅብረቱ እንደ ስኬት ተቆጥሯል፡፡ ውሳኔውን ተከትሎ የኅብረቱ ኮሚሽነር ደስታቸውን ከቃላት አልፈው በጭፈራ (በዳንስ) እስከማንፀባረቅ ደርሰዋል፡፡

ነገር ግን በጉባዔውም ወቅት ሆነ መጠናቀቁ ከተበሰረም በኋላም በአነጋጋሪነቱ የቀጠለው ጉዳይ ግን የሙጋቤ ለሊቀመንበርነቱ የመመረጣቸው ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹አፍሪካዊ ታጋይነትና ቆራጥነት›› እንዳለባቸውና በሌላ በኩል ‹‹አወዛጋቢ አምባገነን›› በመባል የሚታወቁት የሙጋቤ ጉዳይን አስመልከቶ ጥያቄዎች መነሳታቸውን ቀጥለዋል፡፡  ከምዕራባውያን መንግሥታት ጋር የከረረ ቁርሾ እንዳላቸው እየታወቀ መመረጣቸው ሰፊ የዘገባ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ በተለይ የአሜሪካ መንግሥትና የአውሮፓ ኅብረት በዚምባቡዌው መሪ ላይ ከዓመታት በፊት የጉዞ ማዕቀብ የጣሉባቸው በመሆኑ፣ በምርጫው ምዕራባውያን ደስተኛ እንዳልሆኑ ዘገባዎችም እየጠቆሙ ይገኛሉ፡፡

ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ ዚምባቡዌን በመምራት የሚታወቁት ሙጋቤ በሊቀመንበርነት መምረጣቸውን የአሜሪካ መንግሥት እንዴት እንደሚያየው የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊዋ፣ ‹‹የኅብረቱ አባላት በራሳቸው የመረጡዋቸው በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ የአሜሪካ መንግሥት ምንም አስተያየት መስጠት አይፈልግም፤›› ሲሉ መልሰዋል፡፡

የአሜሪካ መንግሥትም ሆነ የአውሮፓ ኅብረት ለአፍሪካ ኅብረት ካላቸው አጋርነትና ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶች አንፃር ለሚቀጥሉት አንድ ዓመት የሚኖራቸው ግንኙነት እንዴት ሊቀጥል እንደሚችል ለጊዜው ያልተመለሰ ጥያቄ ሆኗል፡፡ በዋናነት በሚቀጥለው መስከረም ወር መጨረሻ በኒውዮርክ የሚጠበቀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ የአፍሪካ ኅብረት ውክልናና ሊቀመንበሩ የሚኖራቸው ተሳትፎ ትኩረት መሳቡ አይቀርም፡፡ በተለይ ደግሞ የመንግሥታቱ ድርጅት እ.ኤ.አ. እስከ  2015 ድረስ የተተገበረው የሚሊኒየም ግብ መጠናቀቂያና ሌላ እሱን የሚተካ አዲስ ዕቅድ ቦታ ሊሰጠው ከመቻሉ አንፃር፣ የሙጋቤ በሊቀመንበርነት መመረጥን መነጋገርያ ካደረጉ  ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ የጉዞ ማዕቀቡ እንደሚነሳላቸው ወይም ፀንቶ መቆየቱ ለጊዜው ባይታወቅም፣ ሙጋቤ ካላቸው አቋምና የምዕራባውያን የበላይነት ስሜት አንፃር ለጊዜው የተለየ ነገር ይዞ ይመጣል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

ሙጋቤም በበኩላቸው አሁንም ቢሆን እጅ የመስጠትም ሆነ መለሳለስ እንደሌላቸው የሚያሳይ አቋማቸውን ሹመታቸውን ሲቀበሉ ባደረጉት ንግግር አስተጋብተውታል፡፡ ከ50 ዓመታት በፊት የቀድሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት ከተመሠረተበት አንስቶ እስከ አልጋ ወራሹ የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት ያለውን ጊዜ በማውሳት፣ ‹‹አፍሪካ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ረዥም ርቀት ተጉዛለች›› ብለው፣ በቀጥታ ‹‹ቅኝ ገዢዎችና ኢምፔሪያሊስት›› ያሉቸውን ምዕራባውያንን በነገር ጎሸም አድርገዋል፡፡ ‹‹አፍሪካ ወዳጅ የሚሆኗትን ሁሉ ስትፈልግ ነበር፡፡ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች በወዳጅነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን ቅኝ ገዢዎችና ኢምፔሪያሊስቶች መቼም ቢሆን በአፍሪካ ውስጥ ቦታ ኖሯቸው አያውቅም፤›› በማለት ለብዙ ጊዜ የሚታወቁበትን የፀረ ምዕራባውያን አቋማቸውን በይፋ ደግመውታል፡፡

ፕሬዚዳንት ሙጋቤ በተደጋጋሚ በሚታወቁበት ሌላው አቋማቸው የአፍሪካ የተፈጥሮ ሀብትና ማዕድን የአፍሪካውያንን ብቻ መሆኑን በመጠቆም፣ ከውጭ ‹‹አቆርቋዦች›› መጠበቅ እንደሚገባው አስምረው ገልጸዋል፡፡

‹‹የአፍሪካ ሀብት የአፍሪካውያን እንጂ የሌላ የማንም ሊሆን አይገባውም፡፡ ምናልባት ራሳችን የጋበዝናቸው የውጭ ወዳጆቻችን የሀብቱ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ቅኝ ገዢዎችና ኢምፔሪያሊስቶች ግን ከዚህ በላይ ምንም አይኖራቸውም፤›› ያሉት ተሿሚው ሙጋቤ፣ ከጉባዔው ተሳታፊዎች ከፍተኛ ጭብጨባ የታከለበት ድጋፍ ተችሯቸዋል፡፡

በሁለቱ ቀን የአኅጉሪቱ መሪዎች ጉባዔ ወቅት ከዋና አጀንዳዎች ጎን ለጎን የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከተለያዩ አገሮች መሪዎችና ተቋማት ተወካዮች ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ተወያይተውም ነበር፡፡ በተለይ ከዋና ስብሰባ አንድ ቀን ቀደም ብለው ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አጭር ውይይት ማድረጋቸውን የመንግሥት ምንጮች የገለጹ ቢሆንም፣ በስፋት ተገናኝተው ለብዙ ጊዜ ሲጠበቅ በነበረው በዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ስላለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ መወያየት አለመቻላቸውን ተዘግቧል፡፡ በግብፅ ከ30 በላይ የፀጥታ ኃይሎች በመገደላቸው ምክንያት ፕሬዚዳንት አልሲሲ ስብሰባውን አቋርጠው ወደ አገራቸው መመለሳቸው ሌላው ክስተት ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -