ፈተናው ከዚህ ዓመት ጀምሮ ይሰጣል
በዲግሪ ደረጃ የሚመረቁ ሐኪሞችን ጨምሮ ሌሎችም የሕክምና ባለሙያዎች ከዘመኑ ቴክኖሎጂና ከአዳዲስ ዕውቀቶች ጋር መለማመዳቸውን፣ የተማሩትን ዕውቀትና ክህሎት አለመርሳታቸውን የሚያረጋግጥ ብሔራዊ የፈተና ቦርድ መቋቋሙን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር ጥር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ያካሄደውን 51ኛ ዓመታዊ ጉባኤ አስመልክተው ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፣ እያንዳንዱ ባለሙያ የሥራ ፈቃድ ከማደሱ በፊት ዕውቀቱን ሊያሻሽል የሚችል ትምህርት ማግኘት አለበት፡፡
ለቦርዱ ሥራ ተግባራዊነት መመርያ ተዘጋጅቶ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን፣ ፈተናው ዘንድሮ ከግልም ሆነ ከመንግሥት ኮሌጆች በሚመረቁ ተማሪዎች ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል፡፡
ፈተናው የሚጀመረው በአራት ዓይነት ሙያዎች ሲሆን፣ እነርሱም በሐኪሞች፣ በአዋላጅ ባለሙያዎች፣ በጤና መኰንኖችና በነርሶች ላይ ነው፡፡ ወደ ሌሎቹ የሕክምና ክፍሎች በ2008 ዓ.ም. እና በ2009 ዓ.ም እንደሚገባ ተገልጿል፡፡