Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየወሎ ተርሸሪ ሆስፒታል ግንባታ በዚህ ዓመት መጨረሻ ይጀመራል ተባለ

የወሎ ተርሸሪ ሆስፒታል ግንባታ በዚህ ዓመት መጨረሻ ይጀመራል ተባለ

ቀን:

ግንባታው ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ይፈልጋል

በደሴ ከተማ ልዩ ስሙ ጢጣ በተባለው አካባቢ ከ1.5 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ሊሠራ ለታቀደው የወሎ ተርሸሪ ኬርና ማስተማሪያ ሆስፒታል ግንባታ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ይጀመራል ተባለ፡፡ በዚህም የሚያስፈልጉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተገባደዱ ሲሆን፣ ከተከናወኑት የዝግጅት ሥራዎቸ መካከል የደሴ ከተማ አስተዳደር 47 ሔክታር መሬት መስጠቱና የካርታ ርክክብ መፈጸሙም ይገኝበታል፡፡

የወሎ ተርሸሪ ኬርና የማስተማሪያ ሆስፒታል ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር አቶ እሸቱ አየለ እንደሚሉት፣ የሕንፃው ዲዛይን ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችል ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡   

ለወሎና አካባቢው ብቻ ሳይሆን በብሔራዊና በምሥራቅ አፍሪካ ደረጃ ከፍተኛ የሕክምና ማዕከል ለሚሆነውና ዘመናዊና የላቀ ደረጃ ላለው ለዚሁ ሆስፒታል እውን መሆን የመልክአ ምድር ቅኝት የቶፖግራፊ ሰርቬይ ሥራ ተጠናቅቆ የአፈር ምርመራ ሥራ ለማካሄድም በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

ለሆስፒታሉ ግንባታ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማሰባሰብ እንዲቻል ሰኔ 26 ቀን 2003 ዓ.ም. በይፋ ታውጆ ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን፣ በዚህ መሠረት 40 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የቶምቦላ ሎተሪና 36 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የተለያዩ የብር ኖት ኩፖኖች ታትመው በመላው አገሪቱ በመሸጥ ላይ ይገኛሉ፡፡

በእስካሁን ሒደትም ከቶምቦላ፣ ሎተሪና ከብር ኩፖን ሽያጭ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ተችሏል፡፡ ኢትዮጵያውያን በብዛት በሚኖሩባቸው የዓለም አገሮች የሚሸጥ ግምቱ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ የሚያስገኝ 70 ሺሕ የብር ኩፖን ቲኬቶች ታትመው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በተቋቋመው ኮሚቴ አማካይነት ለማሠራጨት እየተሠራም ነው፡፡

በመሸጥ ላይ ለሚገኙ የቶምቦላ ሎተሪና ከወራት በኋላ ለሚጀመረው ስልክ መልዕክት (ኤስኤምኤስ) አገልግሎት ተሳታፊ ዕድለኛ ባለ ዕጣዎች የሚሆኑ ሽልማቶች በስፖንሰር ለማሰባሰብ በተደረገው ጥረት ከበላይ አብ ሞተርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የተገኘውን ዘመናዊ የቤት አውቶሞቢል ጨምሮ ከ800,000 ብር በላይ የሚያወጡ የኤሌክትሮኒክስና የመገልገያ ቁሳቁሶች ለማሰባሰብ ተችሏል፡፡

ሳምሰንግ ኩባንያ፣ ጣና ኮሚዩኒኬሽን፣ አምባሰል ንግድ ሥራዎች፣ ኢትሆፍ፣ ዋሪት የሺጥላ፣ ሐሮን ኮምፒዩተር፣ ስናፕ ኮምፒዩተር፣ አልታ ኮምፒዩተር፣ ጋራድ ኩባንያ፣ ትሩ ናይስ፣ ኦሜዳድና በላይ አብ ሞተርስ የተባሉ ድርጅቶች ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ይገኝበታል ተብሎ ለታሰበው መለስተኛና አገር አቀፍ ቴሌቶን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ ፕሮጀክቱን አገራዊ ለማድረግ በተደረገው እንቅስቃሴ የሆስፒታል ፕሮጀክቱ ምክር ቤት አገር አቀፍ እንዲሆን ከሁሉም ክልሎችና ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ ግለሰቦች እንዲካተቱበትም ተደርጓል፡፡

ብሔራዊ ሎተሪና ኢትዮ ቴሌኮም ቶምቦላ ሎተሪ አትሞ በመሸጥና በስልክ መልዕክት አገልግሎት ለማካሄድ ይጠይቁት የነበረው በተከታታይ 15 በመቶ እና 40 በመቶ ክፍያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ነፃ እንዲያደርጉ በሰጠው መመርያ መሠረት፣ ተቋሞቹ የተባለውን ክፍያ ነፃ በማድረግ ከፕሮጀክቱ ዓላማ ጐን ቆመዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተመረጡባቸው ክልሎችና አካባቢዎች በመሄድ የቶምቦላ ሎተሪና ኩፖኖችን የማሠራጨት ሥራ ያከናወኑ ሲሆን፣ የሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮችም የቶምቦላ ሎተሪውንና የብር ኩፖኖቹን የሚሸጥና ድጋፍ የሚሰጥ ኮሚቴ አዋቅረው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ታዋቂ ግለሰቦች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና የሙያ ማኅበራት ልዩ ልዩ የጥበብ ዝግጅቶችን ለማዘጋጀት እየሠሩ ሲሆን፣ ሚዲያዎችም የበኩላቸውን ድጋፍ በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡

ዶ/ር በላይ አበጋዝ ወሎ ተርሸሪ ኬርና የማስተማሪያ ሆስፒታል ፕሮጀክት የሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ፣ የደሴ ሪፈራል ሆስፒታልን አፍርሶ በዘመናዊ መልክ ለመሥራት በቅድሚያ ታቅዶ እንደነበር ገልጸው፣ ይህ ዓይነቱን ሆስፒታል በዘመናዊ መልክ ለማሠራት ከማቀድ ይልቅ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ የአገሪቱን ስም ሊያስጠራ፣ የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን ለማድረግ የሚያስችልና ሁሉንም ሕክምና የሚሰጥ የማስተማሪያ ሆስፒታል መገንባት በሚል ሐሳብ የተጀመረ ፕሮጀክት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የቦርድ ሰብሳቢ፣ የሆስፒታሉ ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ሲዘጋጅ መንግሥት እንደሚረከበው፣ ነገር ግን የፌዴራል ወይስ የክልል መንግሥት ይረከበው የሚለው ወደፊት እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ