Sunday, December 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊደንብ ያልገደበው የጎዳና ላይ ንግድ

  ደንብ ያልገደበው የጎዳና ላይ ንግድ

  ቀን:

  በሺቢያምፅ ደምሰው

  የአገሪቱ ከ40 እስከ 50 በመቶ የሚሆን የንግድ ልውውጥ ይከናወንባታል በምትባለው አዲስ አበባ የጎዳና ንግድ በስፋት ይታያል፡፡ እነዚህም የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ‹‹ሕገወጥ ናችሁ፣ ሕጋዊ ሁኑ›› እየተባሉ ከግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እስከ መውረስ የሚደርስ ዕርምጃ ይወሰድባቸዋል፡፡ ሆኖም የሕግ አግባቡ የጎዳና ላይ ንግዱን አላስቆመውም፡፡ በየዕለቱ በፒያሳ፣ በአራት ኪሎ፣ በሽሮ ሜዳ፣ በመገናኛ፣ በሜክሲኮና በሌሎችም የመዲናዋ አቅጣጫዎች በርካታ የጎዳና ነጋዴዎች ይታያሉ፡፡ በመንግሥት በኩል ሕገወጥ የንግድ ልውውጥን ወደ ሥርዓት ለማምጣት እየተሠራ ቢሆንም በተለይ በከተማዋ ዋና ዋና አካባቢዎች በሠራተኛ መውጫና መግቢያ ሰዓት ላይ የጎዳና ንግድ ማየት የተለመደ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በሕገወጥ የንግድ ሥርዓት ውስጥ ናቸው ለሚባሉት የጎዳና ነጋዴዎች ዘላቂ መፍትሔ መስጠት አልተቻለም፡፡ በበርካታ የመዲናይቱ ክፍሎችም የጎዳና ነጋዴው ከየወረዳዎች የደንብ አስከባሪዎች ጋር ያለውን የአባራሪና የተባራሪ ሁነቶች መመልከት የዕለት ተዕለት ተግባር ነው፡፡ ነጋዴው ዕቃው እንዳይወረስበት ደንብ አስከባሪዎችን ሲያይ ይሮጣል፤ ደንብ አስከባሪውም ይከተላል፡፡ ይህ በከተማዋ ላይ የሚታይ የቀን ተቀን ውዝግብም ሆኗል፡፡

  ‹‹ከመርካቶ ነጋዴዎች ላይ በጅምላ በቅናሽ ዋጋ አልባሳትን እየገዛሁ በመነገድ ነው የምተዳደረው፡፡ በሥራው ከተሠማራሁ አምስት ዓመት ይሆነኛል፡፡ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ነኝ፡፡ የንግድ ሥራውን ስጀምር ሱቅ ተከራይቼ እሠራ ነበር፡፡ እያደር በአቅሜ ገዝቼ የማመጣቸው አልባሳት ገበያቸው እየቀዘቀዘ መሔድ ጀመረ፤ የተከራየሁትን ቤት ኪራይ ለመክፈል ሲያቅተኝ ቤቱን ለቅቄ የሕዝብ እንቅስቃሴ በሚበዛበት የመንገድ ጥግ ላይ እየዘረጋሁ መሸጥ ጀመርኩ፤ በዚህም የተሻለ ገቢ አግኝቼ ቤተሰቤንም ማስተዳደር ቻልኩ፤›› ይላል፡፡ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገና በአራት ኪሎ አካባቢ ያገኘነው የመንገድ ላይ የአልባሳት ነጋዴ፡፡  ነገር ግን ይህንን የመንገድ ላይ ንግድ ‹‹ሕገወጥ ነው፣ የንግድ ፈቃድም የለህም›› እያሉ የወረዳው ደንብ አስከባሪዎች በተደጋጋሚ የመውረስ ዕርምጃ እንደወሰዱበትም ይናገራል፡፡

  በየጎዳናው አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ጣፋጭ ብስኩቶች፣ ቸኮላት፣ ከረሜላና የመሳሰሉትን ከተፈቀደው የእሑድ ገበያ (ሰንደይ ማርኬት) ውጭ፣ ባልተፈቀዱ ስፍራዎችና የሥራ ቀናት ይታያሉ፡፡ ይህ ግን ሕገወጥ መሆኑን የሚመለከታቸው አካላት ይናገሩታል፡፡ የመንገድ ላይ የንግድ ልውውጥ በኅብረተሰቡም ሆነ በአገሪቱ የንግድ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የሚገልጹት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ረዳት ኮሚሽነር ኃይሌ አማረ ናቸው፡፡ እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ በመንገድ ላይ የሚከናወኑ የትኛውም ዓይነት የንግድ ልውውጦች በንግድ ፈቃድ ላይ ያልተመሠረቱና ሕገወጥ ናቸው፡፡ እነዚህ ሕገወጥ የሆኑት የመንገድ ላይ ንግዶች ደግሞ በአብዛኛው ጥራት የጎደላቸው እንዲሁም የአገልግሎት ዘመናቸው ያለፈባቸው በመሆኑ በኅብረተሰብ ጤና ላይ ችግር እንደሚያመጡ፣ በከተማው ውበት ላይ ተፅዕኖ እንዳላቸው፣ ለትራፊክ አደጋ የተጋለጡ መሆናቸው፣ በኅብረተሰብ እንቅስቃሴ ላይ ችግር ይፈጥራሉ፡፡ በዋነኝነት ደግሞ ሕጋዊና ፍትሐዊ ሆኖ የሚንቀሳቀሰውን ነጋዴ ፍትሐዊ ላልሆነ ውድድርና ለበርካታ ሕገወጥ ድርጊቶች መንስኤ ይሆናል፡፡

  ሕጋዊ ባልሆኑ ነጋዴዎች የሚቀርቡት ሸቀጦች ምንጫቸው በትክክል አይታወቅም፡፡ በጅንአድ የጉምሩክ ሸቀጦች ጉዳይ ኬዝ ቲም ኃላፊ የሆኑት አቶ ጥበቡ ዳባ፣ ከገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወደ አገሪቱ በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ ሸቀጦች፤ አገልግሎት መስጠት የሚችሉትን ተረክበው በሁለት ዓይነት መንገድ ለኅብረተሰቡ እንደሚያደርሱ ገልጸዋል፡፡

  የመጀመሪያው የተረከቧቸውን በዓይነታቸውና በብዛታቸው ከፍተኛ የሆኑት በየ15 ቀኑ ለጨረታ የሚቀርቡ ሲሆን፣ በጨረታው የሚሳተፉትም ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ ያላቸው ግለሰቦችና ተቋማት ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሚረከቡዋቸውን ሸቀጦች በአገሪቱ ባላቸው ስምንት የችርቻሮ መሸጫ ጣቢያዎች በዓይነትም በብዛትም በመወሰን ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል የሚገዛበት ሥርዓት አለ፡፡ አቶ ጥበቡ እንደሚሉት፣ ይህ በአገሪቱ ውስጥ እየተበራከተ ለመጣው ሕገወጥ የመንገድ ላይ ንግድ መንስኤ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በመንገድ ላይ የሚታዩት ሸቀጦች በዓይነታቸውም በጥራታቸውም ድርጅቱ በማከፋፈያ ጣቢያዎቹ ከሚሸጠው ሸቀጦች ጋር ልዩነት አላቸው፡፡ አንዳንድ ተመሳሳይ የሆኑት ሸቀጦችም በማከፋፈያ ጣበያው ከሚሸጡበት ዋጋ በታች በጐዳና ላይ ይሸጣሉ፡፡ ይህም የሸቀጦቹ ምንጭ ጅንአድ እንዳልሆነ ያረጋግጣል፡፡  

  ከዚሁ የሕገወጥ ነጋዴዎች የሸቀጦች ምንጭ ጋር በተያያዘ ረዳት ኮሚሽነር ኃይሌ፣ በከተሞች ውስጥ እየተስፋፋ ላለው የጎዳና ላይ ንግድ ምንጮችን በትክክል ማስቀመጥ እንደማይቻል ተናግረው፣ ነገር ግን በአገሪቱ የተለያዩ አቅጣጫዎች ከቁጥጥር ውጪ ሆነው የሚገቡ የኮንትሮባንድ ሸቀጦች ዋነኛ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ በአገሪቱ ያሉት አንዳንድ ትላልቅ የአልባሳትና ሸቀጣሸቀጥ አከፋፋይ ተቋማት እንዲሁም ቸርቻሪዎች ከመደብሮቻቸው አልነሳ ያላቸውንና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ሸቀጦች በጐዳና ንግድ ላይ ለተሠማሩ ሕገወጥ ነጋዴዎች ሊያከፋፍሉ፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘም አንዳንድ ሕጋዊ የሆኑ ነጋዴዎች ፈርቅ (ከዋጋው በላይ ትርፍ) በመያዝ ለጐዳና ንግድ ግለሰቦችን ሊያሰማሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

  ሕገወጥ የጎዳና ላይ ንግድንና ሌሎች ችግሮችንም ለማቃለልና ለማስወገድ እስከ ወረዳ ድረስ የደንብ አስከባሪ ጽሕፈት ቤቶች ተቋቁመው ደንብ የማስከበር አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ኮሎኔል ብርሃኑ መርካ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ ዘጠኝ ደንብ ማስከበር አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በወረዳው ልክ እንደ ሌሎች የከተማዋ ክፍል ሁሉ በርካታ በጎዳና ላይ የንግድ ልውውጥ የሚያከናውኑ አሉ፡፡ ኮሎኔል ብርሃኑ እንደሚሉት፣ በጎዳና ንግድ ላይ የተሰማሩትንና ምንም ዓይነት የንግድ ፈቃድ የሌላቸውን ሕገወጥ ነጋዴዎች ኅብረተሰቡ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ የማይችሉ የንግድ ሸቀጦችን ግንፍሌ አካባቢ እንዲሸጡ ቢመቻችላቸውም የመንገድ ላይ ነጋዴዎቹ ‹‹ቦታው ለንግድ ምቹ አይደለም›› በማለት በተሰጣቸው ቦታ ከመጠቀም ይልቅ የሕዝብ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው መንገዶችና አደባባዮች ላይ የንግድ ዕቃዎቻቸውን ይዘው ለሽያጭ ያቀርባሉ፡፡ ባልተፈቀዱ ቦታዎች ላይ ሲነግዱ የሚገኙትንም በወረዳው ደንብ አስከባሪዎች አማካይነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ይሰጣቸዋል፡፡ ሆኖም ብዙዎቹ ሕጉን እያወቁ መተግበር አይፈልጉም፡፡ በተደጋጋሚ ከሕገወጥ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ተነግሯቸው ለሕግና ሥርዓት ‹‹አንገዛም፣ ሕግን አናከብርም›› በሚሉት ላይ የንብረት መውረስ ዕርምጃ እንደሚወስድም ተናግረዋል፡፡ እንደ ኮሎኔሉ፣ እስካሁን ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት አልተቻለም፡፡

  በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ ሁለት የደንብ ሥርፀትና መረጃ አያያዝ ባለሙያ የሆኑት አቶ እንዳልካቸው አያሌው እንደገለጹትም ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓይነትና በብዛት የጎዳና ላይ ንግዶች እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ ሕገወጥ የንግድ ልውውጡን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት ዘላቂ መፍትሔ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማምጣት ባይቻልም እየተከናወኑ ባሉ ሥራዎች አግባብነት የሌላቸው የንግድ ሥርዓቶች ወደ ሕጋዊ መንገድ እየገቡ እንደሚሔዱ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

  በደንብ ማስከበር ሥርዓቱ የሚወረሱትን ሸቀጦች አስመልክቶ ረዳት ኮሚሽነር ኃይሌ፣ ውርሱ በእያንዳንዱ ወረዳዎች ከተሰበሰበ በኋላ አገልግሎት መስጠት የሚችሉት፣ ዘርፉን በሚመለከት በተዋቀሩት የጨረታ ኮሚቴዎች አማካይነት ተሸጦ ገንዘቡ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ገቢ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

  በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት በደንብ ማስከበር ሥራ የተሰማሩት ወ/ሮ በየነች ገዳሙ እንደሚሉት፣ በተደጋጋሚ መንገድ ላይ ሲነግዱ የተያዙትን ዕቃቸውን ሲወርሱ የሚያየው ብዙኃኑ ኅብረተሰብ ክፍል ደንብ አስከባሪዎችን በዳይ ሻጮቹን ደግሞ እንደተበዳይ አድርገው ይናገራሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ነጋዴዎች ደንብ አስከባሪዎችን አይተው ሊያመልጡ ሲሞክሩ አባረው ሲይዙም ‹‹ምን አድርጉ ትሏቸዋላችሁ፣ ሠርተው አይብሉ ነው የምትሉት፣ በአገራቸው ካልሠሩ የት ሠርተው እንዲኖሩ ትፈልጋላችሁ›› እያሉ ይናገራሉ፡፡ ‹‹አንዳንዶች የምንወርሳቸውን ሸቀጦች ወደ ራሳችን ኪስ እንደሚገባ አድርገው አላስፈላጊ ንግግርም ይናገሩናል፡፡ ይህ ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦችን የአመለካከት ግድፈት ነው፡፡›› አንዳንዴም ‹‹ተጭበረበርኩ፣ የተቀደደ፣ ጊዜው ያለፈ፣ የተበላሸ ዕቃ ተሸጠልኝ መንቀሳቀስ አልቻልንም፣ የእግረኛ መንገድ ተዘጋብን›› እና ሌሎች በርካታ አቤቱታዎችን ወደ ደንብ አስከባሪዎች የሚያመጡ ግለሰቦች መኖራቸውንም በማለት ደንብ አስከባሪዋ ይገልጻሉ፡፡

  በሌላ በኩል ደግሞ የመንገድ ላይ ንግድ የሚያከናውኑት ንግድ ፈቃድ አልባ ነጋዴዎች ሕጋዊ ሆነው በሚነግዱት የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸው አልቀረም፡፡ አቶ ስንታየሁ አስታወሰኝ፣ ሽሮ ሜዳ የሚባል አካባቢ በአልባሳትና መጫሚያዎች ንግድ ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ አውጥተው ቤት ተከራይተው መሥራት ከጀመሩ ዓመታትን እንዳስቆጠሩ ይናገራሉ፡፡ እንደ ነጋዴው አነጋገር፣ ሕገወጥ የሆኑት የመንገድ ላይ ነጋዴዎች በተለይም በዋጋ ላይ የሚፈጥሩት ቅናሽ በንግድ ሥራቸው ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ገልጸው፤ ጥቂት የማይባል ኅብረተሰብም ጥራትና የአገልግሎት ዘመንን ከማየት ይልቅ የዋጋ መቀነስን በማተኮር ጐዳና ላይ በተሰማሩ ነጋዴዎች እንደሚሳብ፣ ከዚህ በተጨማሪም የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ለመንግሥት ግብር ስለማይከፍሉ፣ የቤት ኪራይና ሌሎች ወጪዎችን ስለማያወጡ ተመሳሳይ የሆኑ ሸቀጦችን ‹‹እኛ ከምንሸጥበት ዋጋ በታች እየሸጡ በንግድ ሥርዓቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠሩብን ይገኛሉ›› ብለዋል፡፡

  በተመሳሳይ መልኩ አንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎችም የጎዳና ነጋዴዎች ላይ የተለያዩ ቅሬታዎችን ያቀርባሉ፡፡ አቶ ግዛቸው አበራ ከጎዳና ነጋዴዎች ላይ ተጠቃሚ ነበሩ፡፡ ‹‹አልባሳትን፣ መጫሚያዎችን እንዲሁም ቅባቶችን ለዋጋ ቅናሽ ብዬ ለእኔም ለቤተሰቦቼም ከመንገድ ላይ ነጋዴዎች እገዛ ነበር፡፡ ነገር ግን በተለይ የምንገዛቸው አልባሳት ሲታጠቡ ቀለማቸው የሚለቅ፣ ቶሎ እየተቀደዱም እንቸገር ነበር፡፡ አሁን ምንም ዓይነት ሸቀጥ ከጎዳና ነጋዴዎች ላይ አልገዛም፤›› ይላሉ፡፡

  ረዳት ኮሚሽነር ኃይሌ፣ ሕገወጥ የመንገድ ላይ የንግድ ልውውጥን በመከላከሉ ረገድ ኅብረተሰቡ ትልቅ ድርሻ እንዳለውም ይገልጻሉ፡፡ መንገድ ላይ የሚነገዱ ሸቀጦች በአብዛኛው የተለያዩ ችግሮች ያለባቸውና በኅብረተሰቡም በአገርም አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው አሳስበው፣ ኅብረተሰቡም ለደኅንነቱ እንዲሁም ለአገሩ ዕድገት በማሰብ የትኛውንም ዓይነት ሸቀጦች ከሕጋዊ የንግድ መደብሮች እንዲገዛ ይህንንም ማድረግ ከተቻለ ሕገወጥ የጎዳና ንግድን መከላከል እንደሚቻል አሳስበዋል፡፡

  በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የንግድ ቁጥጥርና ክትትል ንኡስ የሥራ ሒደት መሪዋ ወይዘሪት አስካለ ተክሌ፣ የጎዳና ላይ ሕገወጥ የንግድ ልውውጥን ለመከላከል ረቂቅ የፖሊሲ ሰነድ መዘጋጀቱን፣ የፖሊሲ ሰነዱ ፀድቆ ወደ ትግበራ ሲገባ በሕገወጥ የንግድ ሥርዓቱ ላይ የተሠማሩትንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ወደ ሕጋዊ ሥርዓት ገብተው የሚሠሩበትን መንገድ እንዳካተተ ገልጸዋል፡፡  

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...