Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሰይጣን ምን ሠርቶ ይብላ?

ሰላም! ሰላም! የ“ዳሽ” ሙላ ኑሮ እንዴት ይዟችኋል? ነገራችን ሁሉ ባዶ ቦታ ሙላ እየሆነ ተቸገርን አይደል? በበኩሌ ኑሮ ተከርቸም ሆነብን የሚሉኝ ሰዎች ዙሪያዬን ከበው አላስቀምጥ ብለውኛል። “ዳሽ” ሙሉ ሲባሉ ቅንድብ ነቅለንም ቢሆን የምንመርጥበት ምርጫ ይዘጋጅ ይላሉ። እስኪ አሁን ማንን ለማሳጣት ነው ካልጠፋ ሰው እኔን መርጠው እንዲህ ያለ ጥያቄ የሚጠይቁኝ? አይገርማችሁም? ሰው ነገረኛ ነው አለ የደረሰበት። ይገርማችኋል በቀደም እለት ዕዳ በዕዳ ላይ ተዋልዶ ኮንዶሚኒየም ቤቷን ለመሸጥ የተገደደች ደንበኛ አግኝቼ ነበር። ቤቷን ላሸጥ ደፋ ቀና ስል ተግባብተን፣ “እኔምልህ አንበርብር!” ብላ ጨዋታ ጀመረችኝ። መቼም እንደ ስሜ ከማሻሻጥ እስከ ብሶት ጆሮና ቀልብ ሰጥቶ ልቦናን መበርበር ሥራዬ ስለሆነ ‘እህ’ እያልኩ እሰማት ጀመር።

“አሁን እኔ ምርጫ ካርድ ወሰድኩ አልወሰድኩ ለውጡ ምንድነው? ቤቴ ይመለስልኛል? ኑሮዬ በአንድ ጀንበር ከአቀበት ወደ ቁልቁለት እንደተሽቆለቆለው በአንድ ድምፅ ቦታው ይመለሳል? ንገረኝ እስኪ?” ስትለኝ የኑሮዬ አልበቃ ብሎ ጥያቄው “ዳሽ” ሙላ ሆኖ ቁጭ። ቤቱን በፍጥነት በጥሩ ዋጋ ማሻሻጥ ከብዶኝ ሳለ ጭራሽ ደግሞ የምረጡ አትምረጡ አማካሪ መሆን ሲደረብብኝ ዝም ብላችሁ ማሰብ ነው። ታዲያ ምን አልካት አትሉኝም? ምን እላታለሁ? በሕይወት ውጣ ውረድ የምንከፍለውን ዋጋ በመንግሥት ምርጫ አጣጣለሁ ብሎ ማሰብ ምን ነውር ምን ኃጥያት አለው ብዬ ላስብላችሁ ኖሯል? ትቀልዳላችሁ ልበል!  “መምረጥማ የውዴታ ግዴታ ነው እንዳታወላውይ፤” አልኳት። የባሻዬን ልጅ ያልኳትን ስነግረው፣ “በምርጫው ባታምኝ በድምፅሽ ማመን አለብሽ ብለህ አልጨመርክላትም?” አለኝ። በየሄድኩበት የምሰማው እሮሮ አልበቃ ብሎ ጭራሽ እሱ ይሻለኛል ስል ይጨምርልኛል። እሳቱን ለማጥፋት ውኃ ሁነኝ ስትሉት ጭድ በጉያው ይዞ የሚያባብስ ሆነ እንዴ የዘመኑ ሰው? ‘ኧረ ምን ይሻለኛል?’ አለ ጥላሁን ገሠሠ!

መቼስ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል ። ባዶ ቦታ ከመሙላት ወደ ምርጫ ተሸጋግረናል። ‘ያውም በባቡር ሐዲዳችን አሳብረን’ እንዳትሉኝና እንዳልስቅ። አይ እናንተ! ገና ሳንሳፈርበት ባቡራችንን ልታሳሙኝ ነው? አላደርገውም! (ፈጥሮብን ማማት ‘ሆቢያችን’) ወላ በኤሌክትሪክ ባቡራችን አሳብረን ሆነ በዘመን ባቡር፣ የእጅ አሻራም አስቀመጥን የእግር፣ ኮሮጆ ውስጥ ድምፃችንን የምናሰማበት ቀን እየተቃረበ ነው። (በቁመትና በሰውነት የክፍል አለቃ ሆናችሁ እኩዮቻችሁን ስታስጨንቁ ያደጋችሁ በዴሞክራሲ ስም አሁን ንስሐ መግባት ያለባችሁ ይመስለኛል) እናም ሰሞኑን ከወዳጆቼ ጋር በዚህ ጉዳይ ስንጫወት መቼም አፌ አያርፍም “ብናውቅበት እኮ የመራጮች ድምፅ የሚሰበሰብት ቀን ትልቅ ዓመት በዓላችን መሆን አለበት፤” አልኩ። “ምን ዋጋ አለው? ጎድን ጥብስ የሌለበት፣ ፍሪዳ የማይጣልበት፣ ዶሮ የማይታረድበት ዓመት በዓል፤” አይለኝ መሰላችሁ ከወዳጆቼ አንዱ። ‘ዓመት በዓል ያለዝልዝል ጥብስ በዓል አይባልም?’ ልለው አስቤ ሐሳቤን ወደ ውስጥ ሳብኩት። ስንቱን ወደ ውስጥ ስበን ይሆንልን ይሆን?

ደግሞስ አብጃለሁ እንዴ በዚህ ጊዜ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ሆነ በገዢው ፓርቲ የምታማው? ቀድሞም አዳልጦኝ እንጂ ወገኔ ከወገን ሥጋ ይልቅ የበሬና የበግ ሥጋ እንደሚያፈቅር አውቃለሁ። የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሚጠሩት ለፌሽታ ‘ፓርቲ’ ሲጠራ ልቡ እንደሚያብጥ አውቃለሁ። እውነት እውነቱንማ ስንነጋገር ቅር እንዳይላችሁ! ምን ግለኝነት፣ ሙስና፣ የሥነ ምግባር ዝቅጠት እንደተጠናወተን ብንክድ የፌሽታ የፌሽታው ጊዜ ተውሶ ለባሽ ተንጋግቶ ተጓዥ መሆናችን እንክዳለን? እንዲያው ብቻ አንዳንዴ ሳስበው የጋራ ኑሯችንን ለማስተካከል ወዲህ በል ከሚለን የስበት ኃይል ለአንዲት ቀን ጥጋብ የሚጎትተን የሆድ ‘ግራቪቲ’ ታላቅ ይመስለኛል። እውነቴን እኮ ነው። እናንተ ደግሞ አሥር ጊዜ ማስማል ትወዳላችሁ። “አሁን ማን ይሙት ስንቶቻችን ነን የነቃ ተሳትፎ ያደረግንበትን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ቁጭ ብለን ስንጨፈጭፍ የምንውለው? ደርሶ ብቻ መንገዱ ሁላ ለምን አልጋ ባልጋ አልሆነም ብለን መደንፋት? ጉድ እኮ ነው!” የሚሉኝ ባሻዬ ናቸው። እግዜር አሁንም ዕድሜና ጤናውን ጨምሮ ጨማምሮ ይስጣቸውና ብዙ ከመኖር መጀመሪያ የገዛ ራስን አቋቋም መገምገም ይቀናቸዋል። እኛስ ጉንፋን ብቻ እርስ በርስ ከሚተላለፍብን ይኼ ይኼም ቢተላለፍብን? እ?

እናም በአውላላው ጥር በሠርግና በአፍሪካ ዋንጫ ግብግብ ‘ቢዚ’ ሆነናል። የሚፈለገው ‘ቢዚ’ መሆን እስከሆነ ድረስ እንኳን ስፖርትና ‘ዓለምሽ ዛሬ ነው ዛሬ’ ተገኝቶ እንዲሁም በተገኘው ሁሉ መስመጥና መመሰጥ ሥራችን ነው። ታዲያ ወዲያ ወዲህ ተፍ ተፍ ስል ውዬ ለወጪ ቁጠባ ምሳዬን ቤቴ ገብቼ ከውዷ ማንጠግቦሽ ጋር ከበላሁ፣ ባሻዬ ዘንድ ደግሞ አቦል ቡና ፉት ልል ጎራ እላለሁ። ጎራ እንዳልኩ ባሻዬ በማይሰለች ጨዋታቸው ሲጠምዱኝ ፀሐይዋም ሥራ ለማስፈታት እንደምታዩዋት ችክ ትልና ለ20 ደቂቃ ብዬ የተቀመጥኩት ሰውዬ አንድ ሁለት ሰዓት ወሬ እሰንቃለሁ። (እህ ወሬ ባይኖርልን አገልግል መሰነቅ ብቻ ያኖረን ነበር እንዴ? ያውስ በዚህ ኑሮ? ኧረ ተውኝ) ወሬ ፍሬ ባይኖረውም ቅሉ ገለባው እኮ እንደ ነዳጅ እየተቀጣጠለ እያኖረን ነው። ካላመናችሁ ፌስቡክ ጎርጉሩና ድረሱበት። እናንተ ደግሞ አንዳንዴ የምትጠረጥሩትን አታውቁም በእምዬ ሞት፡፡ 

ምን ነበር የምንጫወተው? አዎ! ባሻዬ ደጋግመን ቡና ስናንቃርር ደጋግመው፣ “ሰሚ ጆሮ ጠፋ አስተዋዩ መነመነ፤” ይሉኛል። “ባሻዬ ምነው ይኼን ያህል? ምን ሆኑ?” ስላቸው፣ “ተወኝ ልጄ! በጉልበት ካልሆነ እኮ ሐሳብ ለሐሳብ ተለዋውጠን፣ በቀናነት የሚረባንን ተነጋግረን መቀባበል በቃ አልሆነልንም፤” ብለውኝ ይተክዛሉ። መልሰው ምርቃት ስለሚወድ አንድ ብላቴና ታሪክ ወግ ያመጣሉ። “ይኼውልህ ልጁ እንደ ያዕቆብ ባርኮት ምርቃት አብዝቶ የሚጠማ ነው። ታዲያ እናትና አባቱን ሲያከብርና ሲታዘዝ እንዲህ እንዳይመስልህ። አባትም ይኼን እያዩ በወጣ በገባ ቁጥር ‘ስፋ፣ ልማ፣ እደግ፣ ተመንደግ’ ሲሉት አደገ። ጎልምሶ የሚኖረው ኑሮ ግን የእርግማን ሆነበት። ታዲያ አባቱ ዘንድ ሄዶ ‘አባዬ ያ ሁሉ ምርቃት ያ ሁሉ በረከት የት ሄዶ ነው እንዲህ አመድ አፋሽ የሆንኩት?’ ብሎ ቢጠይቅ አባት ‘አይ ልጄ የምርቃት በረከቱ እኮ ያለው ከአሜኑ ነው። ከልቤ ስመርቅህ ከልብህ አሜን አላልክ ይሆናላ’ አሉት እልሃለሁ። እኛም መስማቱን በጆሮ ሰምተን በልቦና አሳድረን፣ መተማመኑን ንቀን ይኼው በየአቅጣጫው በጉልበት ካልሆነ በሐሳብ አንዳንችን ከሌላችን አንኗኗር ብለናል፤” ብለው የልባቸውን ተነፈሱልኝ። ልብ አወቅ ቢታጣ የልብን መተንፈስ ሌላው ቢቀር ሕገ መንግሥታዊ መብትም አይደል?

“ከምርቃቱ ሳይሆን ከአሜኑ ነው፤” ብለው ባሻዬ ያጫወቱኝን ጨዋታ ደጋግሜ እያብላላሁ ወደ ሥራዬ ተጣደፍኩ። በግሩም ሁኔታ ተሠርቶ የተጠናቀቀ ዘመናዊ ባለአራት ፎቅ ሕንፃ መኖሪያ ቤት እጄ ላይ ነበር። እንዴት ያደለው ይሆን ይኼን ቤት የሚገዛ እያልኩ ላይ ታች ስል በአንፃሩ ደግሞ እንዴት ያልታደለ ሰው ነው ይኼን የመሰለ ቤት ሠርቶ ሠርቶ የሚሸጠው እያልኩ አውጠነጥናለሁ። ኋላ ስሰማላችሁ ለካ ቤቱ የሚሸጠው በፍቺ ምክንያት ኑሯል። “እርስ በርስ ባል ከሚስት፣ እህት ከወንድም፣ ወዳጅ ከወዳጅ ስንለያይ ስንፋታ የሚሰምረውን ያህል ምናለበት ያሉብን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችም ሲፈቱ ቅፅበት ባይፈጅባቸው?” ብዬ የባሻዬን ልጅ ባዋየው፣ “ሰይጣን ምን ሠርቶ ይብላ?” አይለኝ መሰላችሁ። “እኔ ከተማረ ሰው ሳይንሳዊ ምላሽ አገኛለሁ ብዬ ስጠይቅህ ‘ሰይጣን ምን ሠርቶ ይብላ’ ትለኛለህ?” ስለው ደግሞ፣ “አላወቅክም እንዴ ሳይንስ ራሱ በእኩይና በሰናይ መንፈስ ማመን እንደጀመረ!” ብሎኝ ሄደ። የአባባሉ እርግጠኝነት ሳይንቲስቶችን አንገታቸው ላይ ቆሞ ጠበል ያስረጫቸው ነበር የሚመስለው። እንዲያው ምን ይሻለዋል? እያልኩ መንገድ መንገዱን ሳይ ስልኬ ጠራ። ሳነሳው ማንጠግቦሽ “እየጠበቅኩህ ነው፡፡ እኔ ሠርግ ቤት አርፍዶ መሄድ አልወድም፤” ብላኝ ጆሮዬ ላይ ዘጋችብኝ። በዚህ በፍቺ ነገር ስጨነቅ በዚያ የጋብቻ ጥሪ እንደተላከልኝ ዘንግቼው ኖሯል። በፍቺና በጋብቻ ሐሳብ ስዋልል ደግሞ የሥራ ስልኬ ጠራ። የተምታታበት የበዛው ለካ ያላንድ አይደለም ጎበዝ!

በሉ እስኪ ደግሞ እንሰነባበት። ያልኳችሁ ሕንፃ በአንድ ደንበኛ እይታ ብቻ ከተፋቺዎች እጅ ይወጣል ብዬ አልጠበቅኩም። ያለማንገራገር ገዢው ደንበኛዬ ቤቱን እንደሚያስቀረው ከመግለጹ፣ የኮሚሽኔን ግማሽ ቼክ ፈርሞ ሰጠኝ። ማንጠግቦሽ በ ‘ሚስድ ኮል’ ልታሳብደኝ ደርሳለች። ለነገር ሲሆን ደግሞ እዚህ አገር ‘ኔትወርኩ ፍሪ’ ነው። እንግሊዝኛ ካበዛሁባችሁ ‘ሶሪ!’ ቤት ስደርስ ማንጠግቦሽን አላውቃትም። “እንዲህ ሙሽራ መስለሽማ ካንቺ ጋር አልሄድም ዝነጣሽን ቀንሽ፤” ማለት። “አዘናነጤ የመልሶ ማልማቱ አካል ከመሰለህ እንግዲህ ቻለው፤” ብላ እሷም በነገር መሸንቆጥ። እንዲህ በመዘግየቴ ምክንያት ተኳርፈን ‘ቡፌ’ ስናነሳ ቪዲዮ እንዳንነሳ እያለሳለስኳት ወደተጠራንበት ባለአምስት ኮከብ ሆቴል አዳራሽ አመራን። ‘እህል ጡር ከነሳ ዛሬ አለቀልን’ እያለ ታዳሚው ሲዝናና ሲጫወት ተመሸ። ‘ዘመድ ነን ያላችሁ?’ ሲባል ግን ሸሸት ሸሸት እያለ ጥጉን የሚይዘው ሰው በዛ። እኔና ማንጠግቦሽም ጥግ ከያዙት ተጠግተን፣ “ምን ጉድ ነው?” ስንባባል ማንጠግቦሽ “ስማ!” ትለኛለች። “ምን ልስማ?” ብዬ ጆሮዬን ጣድ ሳደርግ አንዱ፣ “አሁን ይኼን ያህል ወጪ የወጣበትን ሠርግ ምን ትለዋለህ?” ሲል ይጠይቃል። “ልማታዊ ሠርግ ነዋ!” ሲል ሌላው ይመልሳል። “ይኼን ሁሉ ገንዘብ አውጥቶ መደገስ ግን ‘ፌር’ ነው? መንግሥት ያለበት አገር ይመስላል ግን?” ትላለች ወዲያ ደግሞ። (ይታያችሁማ!) ጥርሱን በጥርስ እንጨት እየጎረጎረ የተቆዘረ ሆዱን የሚያሻሽ ሌላ ታዳሚ ደግሞ፣ “እነሱ ምን ያድርጉ ብለሽ ነው? ስንቶች መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት አቅቷቸው በቁም ሲሞቱ እያየ የኑሮ ልዩነቱ ይኼን ያህል ሲሰፋ የሚያስበላንማ መንግሥት ነው። ሰውማ ምን ያድርግ?” ይላል። “በሸንጎ ሲረታ ሚስቱን ገብቶ መታ’ ማለትስ አሁን ነው፤” የምትለኝ ደግሞ የእኔዋ ማንጠግቦሽ ናት። ወይ ልማታዊ ቡፌ! አጥግቦ ቆዝሮ ሊያስጨፍር ሲገባው ጥግ ጥግ አስይዞ በነገር ያጠዛጥዝ? በዚህ ወሬ መሀል ጋባዥን ማማት አሰልቺ ቢሆንብን እኔና ማንጠግቦሽ ከሠርጉ አዳራሽ ሹልክ ብለን ወጥተን የበላነውን ለማወራረድ አንድ ግሮሰሪ ተሰየምን፡፡ ከአምስት ኮከብ ሆቴል ወደ ግሮሰሪ አይገርምም? ሪነገራችን ላይ ሰዎቹ በአንድ ሌሊት ከእንትን ወደ እንትን ተቀየሩ እንደተባለው እኮ ነው፡፡ ‹‹ሁለት ባላ ትከል፣ አንደኛው ሲሰበር በአንደኛው ተንጠልጠል›› ወይም ‹‹አንቺ ምናለብሽ ሁለት አባት አለሽ፣ አንዱ ቢሞትብሽ በአንዱ ትምያለሸ›› ነው የተባለው? ወይ የሰይጣን ነገር? መልካም ሰንበት!              

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት