Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርእኛንም ግድቡንም የማይመጥን ማስታወቂያ

እኛንም ግድቡንም የማይመጥን ማስታወቂያ

ቀን:

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባበሰቢያ እንዲሆን በ8100 የስልክ ቁጥር ‹A› ብለን አስተዋጽዖ በማድረግ ዕድላችንን እንድንሞክር በመገናኛ ብዙኃን እየቀሰቀሳችሁንና እያስቀሰቀሳችሁን ያላችሁ ወገኖች፤ ቢያንስ፣ ባታከብሩን እንኳ፤ ለምን እንድናከብራችሁ አትሆኑም? ከምንም በላይ ሕዝብ የተከበረ ነው፡፡ እንኳን በመገናኛ ብዙኃን፤ ለጥቂት ስብስብም ቢሆን የማይሆን አቀራረብ ስላየሁ ነው ስሜታዊ ሆኜ አስተያየቴን እየሰጠሁ ያለሁት፡፡

እስካሁን በዕድል ሙከራ የ8100 ቅስቀሳችሁ በኮሜዲያኑ ከተሠራው በላይ የሚወደድ ማስታወቂያ አልገጠመንም፡፡ ይህ የእኛን የአዋቂዎቹን ብቻ ሳይሆን የሕፃናትን ቀልብ ሁሉ የገዛ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- አንድ ዓመት ከአምስት ወራት የሆናት አፍ ያልፈታች ሕፃን ልጄ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአፏ የወጣው ቃል ‹A› ነው፡፡ ይህች ልጄ በኮሜዲያኑ የተሠራው ማስታወቂያ ገና ሲጀምር  ‹A›፣ ‹A›፣ ‹A›፣… እያለች ሮጣ ወደ ቴሌቪዥኑ ትጠጋና ‹A›፣ ‹A›፣… እንዳለች ቆይታ ነው ትመለስ የነበረው፡፡ ከእሷ ከፍ የምትለው የዘጠኝ ዓመቷ ልጄ ደግሞ በየጊዜው በ8100 ‹A› ብለን መልዕክት እንድንልክ ታደርገን ነበር፡፡ አሁን ግን ከስፖርተኞች ጋር ተሠርቶ እየተላለፈ የሚገኘው ማስታወቂያ መነገር ከጀመረ ወዲህ ትንሿ፣ ቃሉም እየጠፋባት ሲሆን ትልቋ ደግሞ ‹ኤጭ፤ ጀመሩ ደግሞ› እያለች ትገኛለች፡፡ ይህን ምሳሌ ከእኔ ቤት ያሳየሁት የሌሎችንም እንደሚወክል ስለምገምት ነው፡፡  

ከአሁን በፊትም ከነሜሮን ጌትነትና ነቢዩ ባዬ ጋር የተሠራውን ማስታወቂያ በርካታ ሰዎች እንዳልወደዱት በራሴ ባደረግሁት ቅኝት ያረጋገጥሁ ሲሆን፣ የዚህንም ማስታወቂያ ስሜት ከቤተሰብ ጀምሮ አብረውኝ ከሚሠሩት ጋርና በየሄድኩበት እስካገኘኋቸው ድረስ አረጋግጫለሁ፡፡ ለእንዲህ ዓይነት አቀራረብ ለቃላቱ ይቅርታ ይደረግልኝና፤ ከማሾፍና ከማላገጥ አልፎ መሞላፈጥ የሚመጥነው ይመስለኛል፡፡

- Advertisement -

ማስታወቂው እየተሠራበት ባለው ዓላማ በጎነት ላይ ብዙዎቻችን የምንግባባ ሲሆን፣ ለዓላማው ማሳኪያ የምንጠቀምባቸው መንገዶች ግን በቆሻሻ ትሪ እንደሚቀርብ ምግብ ይቆጠራል፡፡ አንድ ሰው ምግብ የሚመገበው ረሃቡን ለማስታገስ ወይም አምሮቱን ለመወጣት ነው፡፡ ለዚህ ሲባል የሚመገበውን ምግብ ንጹህ ባልሆነ ትሪ ስንሰጠው ‹አተርፍ ባይ አጉዳይ› ሆኖ ለበሽታ እንዲዳረግ እናደርገዋለን፡፡ ልክ እንደ ምግቡ እንደዚህ ዓይነቶቹ የወረደ አቀራረብ ያላቸው ማስታወቂያዎች ልባችን ፈቅዶ ለመሳተፍ ከመፈለግ አልፎ በተደጋጋሚ የምንሞክረውን መልዕክት የመላክ ተግባር እየጎረበጠን እንድናደርገው እያደረጉን ነውና መከባበሩ ቢኖር!

ተመልካች ወይም አድማጭ ማን እንደሆነ ማሰብ ቢገባም ይህ ቅድመ-ሁኔታ አለመታሰቡ ትንሽ ታዳሚን ከግምት በታች ማየት ይመስለኛል፡፡ ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕፃን አይደለምና እባካችሁ እንዲህ ዓይነቶቹ ማሳታወቂዎች ከመተላለፋቸው አስቀድሞ ከመገናኛ ብዙኃንም ሆነ ማስታወቂያ ባለሙያዎች ጋር ቢገመገሙ፤ ምክያንቱም በዓላማው ብቻ በመዘናጋት በስሜት እየተላለፈ ስለሚመስለኝ!

(እስክንድር መርሐጽድቅ፣ ከአዲስ አበባ)

**************

 

የመፈክሮቹን ያህል ለሥራም ትኩረት ይሰጥ

ትንንሾቹም ሆኑ ትልልቅ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሚያገርም መልኩ የመፈክር ጋጋታ ያስተጋባሉ፡፡ አንዳንዴ መንግሥትን የሚያስተቹ ሲብስም የሚያንስቁ ጉራማይሌ መፈክሮች አደባባዮችን ሲያዥጎደጉዱ መታዘብ ይቻላል፡፡ በየቀበሌው፣ የፓርቲ ልደትን፣ የነጻነት በዓልን፣ የሴቶች መብት መከበርን፣ የደን ቀንን፣ የጡት ማጥባት ቀንን ወዘተ. ለመዘከር የሚለጣጠፉ የመንግሥት መሥርያ ቤቶች ማስታወቂያዎች የመፈክራቸውን ያህል ሥራ ተሰርቶባቸው እንዴት ባማሩ ነበር ያስብላሉ፡፡

በአንዳንድ ቀበሌዎች ውስጥ የሚታየው ደግሞ ከግርምትም በላይ ነው፡፡ በየቀበሌው ተሰሙ የወረዳ ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ባልደረቦች ሥራቸው መፈክር በማስጻፍና በማስለጠፍ ብቻ የታጠረ እስኪመስል ድረስ ውለውና አድረው በዚህ ተግባር ላይ ሲባዝኑ ይታያሉ፡፡ መረጃ አደራጅተው ለጠያቂው አካል፣ ለባለመብቱ ሁሉ መስጠት ሲገባቸው ራሳቸው መረጃ ለማግኘት ሲዋትቱ፣ አንዳንዴም እነሱም፣ የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች፣ ቢሮዎች፣ ጽሕፈት ቤቶችና ሌሎችም በአስተዳደሩ እርከን ውስጥ ያሉ መሥሪያ ቤቶች ሊሰጧቸው ያልቻሏቸውን መረጃዎች እንደመሰላቸው ሲያወጡ ይስተዋላሉ፡፡

የመፈክር አባዜው ከቀበሌና ከክፍለ ከተሞች አልፎ በፌደራል መሥሪያ ቤቶችም ሲስተጋባ ይታያል፡፡ አንዳንዴማ የሚከበረው በዓልና የሚለጠፈው መፈክር አራምባና ቆቦ እየሆኑ ለማየት እንኳ እንዴት ያሰለቻሉ መሰላችሉ፡፡ መንግሥት የማስፈጸም አቅሜ ደካማ ነው፣ በዚህ ምክንያትም በርካታ ዕቅዶች ሳይሳኩ ቀርተውብኛል እያለ በቁንጮ ባለሥልጣናቱ በኩል እሮሮ እያሰማ፣ በዚህ በኩል ‹‹የተቀጣጠለውን የልማት ችቦ በማፋፋም ውጤታማና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን እናደርጋለን›› ወዘተ. ያሉ ማስታወቂያዎችና ፕሮፓጋንዳዎች ዳር እስከዳር ይስተጋባሉ፡፡ የአገሪቱን ልማትም ዕድገትም ማንም አይጠላውም፡፡ ማደግ መመንደግ ለሁላችንም የለውጥ ፋና ነው፡፡ ግን በፉከራ ሲሆን አላየንም፡፡ ከዚህ ይልቅ በብርቱ እየሠራ ሥራውንም በብቃት የሚፈጽሙ፣ ለአገርና ለወገን አለኝታ መሆናቸው በሕዝብ የሚመሰከርላቸው ኃላፊዎች በዝተው ብናይ ነበር ከፉከራው በላይ የምንደሰት፡፡ የተገላቢጦሽ ሆኖ በስንት ውትወታና ልቅሶ ጉዳይ የሚያዩ፣ አቤቱታ የሚሰሙ፣ ቅሬታችንን ከአንገት በላይ የሚመለከቱ ኃላፊዎችና የመንግሥት ሹማምንት ባሉበት አገር፣ ከሚሠራው በላይ መፎከር ትችትና ትዝብትን ሲያልፍም መናቅን ያመጣልና መንግሥትና አገር መሪው ፓርቲም ሌላው ቢቀር ስለክብራቸው ሲሉ እንኳ አንዳንድ መፈክሮቻቸውን ቢመለከቷቸው እላለሁ፡፡

(አምባቸው ታዬ፤ ከአዲስ አበባ)

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...