Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉበርካታ የቤት ሥራዎች ያሉባት ኢትዮጵያና የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ

በርካታ የቤት ሥራዎች ያሉባት ኢትዮጵያና የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ

ቀን:

በአማኑኤል ነጋ

የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ የአፍሪካ አገሮች ወንድማማች መሪዎችን ማሰባሰብ ከጀመረች ከአምስት አሥርት በላይ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ያኔ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አገሪቱን በሚመሩበት ወቅት ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረት ግንባር ቀደም ሚና ከተጫወቱ መሪዎች አንዱ ነበሩ፡፡ በወቅቱ አኅጉሩ ከነበረበት የቅኝ ግዛት መልስ የፀብና ግጭት አጎበር ሳይላቀቅ አንዱን ከሌላው እየሸመገሉ፣ በጎራ ተከፋፍሎ መፋለም የያዘውን እያደራደሩ የነበሩ መሪዎች፣ ዛሬ እየጎለበተ ለመጣው አኅጉራዊ ኅብረት እርሾ የተጣለባት መዲና በመሆኗ አዲስ አበባም እስከዛሬ የዘለቀ የመቀመጫነት ክብርን ተጎናፅፋለች፡፡

በወዲያኛው ሳምንት መጨረሻ ላይ የአፍሪካ ኅብረት 24ኛ መደበኛ የመሪዎች ጉባዔ በኅብረቱ ሕንፃ ኔልሰን ማንዴላ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡ ከጉባዔው ጎን ለጎን የየአገሮቹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የየቀጣናው ድርጅቶች ውይይቶችም ተስተናግደዋል፡፡ የአዲስ አበባው የሰሞኑ ጉባዔ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በአገራቸው በተከሰተው የሽብር ጥቃት ምክንያት አቋርጠውት የሄዱበት ነው፡፡ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ መሪዎች ሽምግልናም እንደተለመደው ‹‹ለያዥ ለገናዥ›› እያስቸገረ አደራዳሪዎችን ሲያንገላታ ሰንብቷል፡፡

- Advertisement -

በዚያው ልክ መዲናችን አዲስ አበባ ፈርሳ በመገንባት በዘመናዊ ሕንፃዎች፣ በቀላል ባቡር መስመር ዝርጋታና ሰፋፊ ጎዳናዎች ሥራ ላይ ተጠምዳ ባለችበት ነው ጉባዔው የተካሄደው፡፡ ለመልሶ ማልማት የተዘጋጁ አሮጌ ሠፈሮች እንደ ጦርነት ቀጣና ፈራርሰው፣ ትልልቅ የንግድ ማዕከላትና ሆቴሎችም በርከት ብለው በሚገኙበት ወቅት አዲስ እንግዳ መቀበሏ የሚፈጥረው ስሜት መኖሩም አይካድም፡፡ በዚህ ሒደት ከወትሮው ለየትና ጠበቅ ያለ የፀጥታ አጠባበቅና የሕዝቡ የተለመደው እንግዳ ተቀባይነት ጎልቶ መታየቱንም መታዘብ ይቻላል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ወቅታዊ ጭንቀትና ጉባዔው

የጥቁሩ አኅጉር ሕዝቦች ድህነት፣ ጦርነትና ስደት ብዙም አዲሳቸው አይደለም፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙዎቹ ደሃ አገሮች መሻሻልና ለውጥ ቢያሳዩም የአፍሪካ ገጽታ ይኼው ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሃይማኖት አክራሪነትና ጽንፈኝነት የወለደው ሽብርተኝነት ዋነኛው ሥጋት ሆኗል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶ/ር ንኮዛሳና ድላሚኒ ዙማ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ያደረጉት ንግግርም የሽብርተኝነትን ወቅታዊ ሥጋትነት ይበልጥ አመላክቷል፡፡ ‹‹አፍሪካ የደረሰችበትን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ይበልጥ ለማስቀጠል የበለፀገችና በሁሉም መስክ የተሳሰረች አኅጉር ለመፍጠር የኅብረቱ አባል አገሮች መረባረብ አለባቸው፡፡ በቀጣይ ለሚተገበረውና የአፍሪካ ራዕይን ለሚያረጋግጠው የ2063 የልማት አጀንዳ ልዩ ትኩረትም መሰጠት አለባቸው፤›› ብለው፣ ለዚህ ደግሞ በአኅጉሪቱ ሰላምና ፀጥታ የማረጋገጡን ሥራ ክፉኛ እየተፈታተነ ያለውን ሽብርተኝነት በጋራና በፅናት መፋለም ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተለይ ቦኮ ሐራም የተሰኘው የሽብር ቡድን እንቅስቃሴ ለአኅጉሩ ሥጋት እየሆነ በመምጣቱ በተለይ በቻድ፣ በኒጀር፣ በካሜሩንና በሌሎች ጎረቤት አገሮች እያደረሰ ያለው ዕልቂት፣ የንፁኃን ሴቶችና ልጃገረዶች እንግልትና ስቃይ፣ የሕፃናትና የአረጋዊያን ሰለባነት ማንንም የሚያስቆጭ ሆኗል ነው ያሉት፡፡

በጉባዔው ላይ የነበረውን ሥነ ሥርዓት በተከታተልኩበት ወቅት ያነጋገርኳቸው የውጭ ግንኙነት ባለሙያዎች አፍሪካ ከመካከለኛው ምሥራቅ ቀጥሎ ለሽብርተኝነት የተጋለጠች መሆኗን አረጋግጠውልኛል፡፡ ለዚህም በአንድ በኩል እንደ ቦኮ ሐራምና አልሸባብ ያሉት ጽንፈኛ ቡድኖች አልቃይዳና አይኤስ የመሳሰሉት አሸባሪዎች ያላቸው ዓላማ ተጋሪነት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች የተጠናከረ የፀረ ሽብር ሕግ የሌላቸው፣ የፀጥታና የደኅንነት መዋቅራቸውም የተዳከመ በመሆኑ ለፈተና ተጋልጠዋል፡፡ በተለይ ሽብርተኝነት ከሙስና፣ ከመልካም አስተዳደር እጦትና ከዴሞክራሲ መዳከም ጋር ያለው ጥብቅ ቁርኝትን ፈትሾ፣ ድህነትና ተስፋ ቆራጭነትን በመፋለም ረገድ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የገለጹልኝ ነበሩ፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ያላትን በጎ ልምድ በአርዓያነት የጠቀሱልኝም አሉ፡፡

በአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ላይ የተሳተፉ የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንድ ባልደረባ እንደተናገሩት፣ ‹‹ኢትዮጵያ ካላት የሕዝቡ እንግዳ ተቀባይነትና ሰላማዊነት በላይ ለድህነትና ለፀጥታ ሥራ የምትሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡ በተለይ አልሸባብና ጽንፈኛ የሶማሊያ አሸባሪ ቡድኖች አገሪቱን በጠላትነት ፈርጀው ተከታታይ ዛቻና መግለጫ ቢያወጡም፣ ጥበቃዋን በማጠናከሯ የከፋ ጥቃት ሳይደርስባት ቀርቷል፡፡ ከዚህ አልፋ ኢትዮጵያ የሰላምና የፀጥታ አስከባሪ ኃይሉን በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ለማሰማራት የምትፈጽመው ተግባር ልዩ ዋጋ የሚሰጠው ነው፤›› ብለዋል፡፡

አፍሪካና አፍሪካዊያንን የሚያስጨንቀው ቀዳሚው ጉዳይ ሽብርተኝነት መሆኑን 24ኛው ጉባዔ በግልጽ አሳይቷል፡፡ ሌላው ቀርቶ ጉባዔው እየተካሄደ እያለ በግብፅ ሲናይ በረሃ 27 ሰዎች በሽብር ጥቃት መሞታቸው፣ የሊቢያ መፈራረስ አይቀሬነት በግልጽ እየታየ መምጣቱ፣ እየደቀቀ ያለው አልሸባብ እንኳን አለሁ እያለ ቦምብ ማፈንዳቱን አለማቆሙ፣ በኮ ሐራም ከአገር አልፎ አካባቢውን ወደማመስ ማደጉ አብነት ናቸው፡፡ በእርግጥ በሶማሊያ፣ በማዕከላዊ አፍሪካ፣ በቡርኪና ፋሶና በማሊ የተመዘገቡ የሰላም መሻሻሎችን መዘንጋት ያዳግታል፡፡

ሌላኛው የአፍሪካ መሪዎች ሥጋት የኢቦላ በሽታ ሆኗል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባን ኪ ሙን በንግግራቸው እንዳሰመሩበት ባለፈው ዓመት በኢቦላ ወረርሽኝ የተጠቁት ጊኒ፣ ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮንና ማሊን መጎብኘታቸውን በመግለጽ አደገኛውን ወረርሽኝ ለመከላከል ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ያሳዩት ርብርብ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው መሆኑን አውስተዋል፡፡

ኢቦላ የአፍሪካ ያለፈው ዓመት ሥጋት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በአሥር ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡ በተለይ የምዕራብ አፍሪካ ማኅበረሰብ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በመረበሽ የአየር መንገዶችን በረራ አስቀይሯል (አሰርዟል)፡፡ አኅጉሩን ብቻ ሳይሆን ምዕራብ ምሥራቅ ሳይል ዓለም ለዕርዳታ እንዲነሳና ‹‹የተለመደውን የዘወትር ተጎጂ አፍሪካን ሊታደግ›› እንዲነሳ አድርጎታል፡፡ የዘንድሮውን የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ የውድድር ቦታ እስከመቀየር ያደረሰው ኢቦላ ነው፡፡ በሽታው አሁንም ተጠራርጎ ያልተወገደ ቢሆንምና በተለያዩ ወገኖች ርብርብ ጋብ ያለ ቢመስልም፣ አሁንም ኅብረቱ የሥጋት ምንጭ ሲል ኢቦላንና ሌሎች የጤና ቀውሶችን ከማንሳት እንዲቆጠብ አላደረገውም፡፡

የአፍሪካ ኅብረት የረጅም ጊዜ ተስፋና ጉባዔው

ጉባዔው ከመክፈቻው አንስቶ በትኩረት የተመለከተው አፍሪካን ወደ ብልፅግና የሚወስደውን የ2063 (እ.ኤ.አ) የጋራ ራዕይና የልማት አቅጣጫ የተመለከተው ጉዳይ ነው፡፡ ዶ/ር ዙማ በተለይ በቀዳሚው ንግግራቸው ሲገልጹ፣ አኅጉሪቷ የሕዝቦቿን ሰላም፣ ልማትና ብልፅግና ቀጣይነት ለማረጋገጥ እየተጋች መሆኗን በበጎ ጠቅሰዋል፡፡ በዋናነት ግን የ2063 የልማት አጀንዳ ለማስፈጸም ከወዲሁ አገሮችን በባቡር፣ በአቪዬሽንና በመንገድ መሠረተ ልማት የማስተሳሰሩ ጥረት መጠናከር ይኖርበታል፡፡ የኢንዱስትሪ ቀጣናዎችና ተመጋባቢነትን ጉዳይ ትኩረት በመስጠት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብና ተፈላላጊ ኢኮኖሚ የመገንባቱ ጉዳይም ሊዘነጋ አይገባውም ነው ያሉት፡፡ በተለይ አገሮቹ የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ነፃ የአቪዬሽን ቀጣና የመመሥረት ውሳኔ ተግባራዊነት እንዲታይም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

እዚህ ላይ በ23ኛው የኅብረቱ ጉባዔ ማላቦ ላይ የተደረሰውን አኅጉራዊ የኢኮኖሚ ስምምነት ለማስፈጸም የሚረዳ ፍኖተ ካርታ መቀረፁን በጠንካራ ጅምር የሚያነሱም አሉ፡፡ በተለይ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት ያላትና የሕዝብ ቁጥሯም ከአንድ ቢሊዮን በላይ የደረሰው አፍሪካ ወደላቀ የኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ ሽግግር ለመምጣት፣ የግብርናውን ዘርፍ አሟጦ መጠቀም እንዳለባት መታመኑ ይጠቀሳል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2025 አፍሪካ በግብርናው መስክ ራዕይዋን ለማሳካት ሰባት ግቦችን መከተል እንደሚገባት የተደረሰው ስምምነት ይጠቀሳል፡፡ አገሮች ከአጠቃላይ በጀታቸው አሥር በመቶውን ለግብርና ከመዋል አንስቶ፣ ዓመታዊ የግብርና ዕድገቱን ስድስት በመቶ ማድረስ፣ ባለ 11 ነጥብ የገበያ መሠረተ ልማትን ማሳደግ፣ ቀጣናዊ የንግድ ውህደትን ማጠናከር፣ የእሴት ሰንሰለትን ማጎልበት፣ የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደርን ማዘመንና የግብርና ዕውቀትን ማሳደግ የሚሉት በጉልህ ይጠቀሳሉ፡፡

ጉባዔው የአፍሪካ መንግሥታት ለግል ባለሀብቶች ሚና፣ ለኢንዱስትራላይዜሽንና ለተፎካካሪ ቴክኖሎጂ ተኮር ግስጋሴ ሊሰጡት የሚገባውን ትኩረትም ዳስሷል፡፡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በስፋት መሳብና የተፈጥሮ ሀብቶችን ያማከለ ምርታማነትን ማጎልበትም ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ በአፍሪካ ኅብረትና በቻይና መንግሥት ደረጃ ከሁለት ዓመት በፊት ኅብረቱ 50ኛ ዓመቱን ሲያከብር የተያዙ ጉዳዮችን ጭምር ፈትሿል፡፡ በውይይቱ ማብቂያ ላይ አዲሱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤም ያረጋገጡት፣ ጉባዔ በ2063 የአኅጉራዊ ጉዳዮች አተገባበሮች ላይ አፅንኦት ሰጥቶ መምከሩንና በየደረጃው የተቀናጀ ትግበራን መፍጠር እንደሚገባ መስማማቱን ነው፡፡

በኅብረቱ የ2063 ራዕይና ዕቅዱ ዙሪያ ያነጋገርኳቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ነበሩ፡፡ ‹‹በእርግጥ በኢኮኖማዊና በማኅበራዊ ተግባራት፣ በመሠረተ ልማትና በንግድ ልውውጥ መምከርና አቅም የፈቀደውን ያህል መንቀሳቀስ በጎ ጅምር ነው፤›› ሲሉ ይጀምራሉ፡፡ ከሁሉም በላይ የአፍሪካ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ውህደትና የተሳሰረ ጉዞ መገንባት ያለበት ግን በመተማመን፣ በረተጋጋ የድንበር እንቅስቃሴና በማይናወጥ ሰላምና ድኅንነት ላይ ተመሥርቶ መሆን እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡ በተለይ አሁንም ብዙዎቹ አገሮች የውስጥ መልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ሥርዓታቸውን ሳያጎለብቱ፣ የጎሳ ፖለቲካና የግል ፍላጎት ከተጫጫነው ፖለቲካዊ መገዳደርና መፎካከር ሳይላቀቁ፣ አኅጉራዊ ራዕዩን ለመቀላቀልም ሆነ ጠንካራ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ጥምረት ለመገንባት እንደሚቸገሩም አስረድተዋል፡፡

የፖለቲካ ተንታኙ አኅጉሩ በድህነት ላይ የሚያደርገው ጥረትም ሆነ የዲሞክራሲና ሰላም ጉዞውን ለመደገፍ ሌላው ዓለም የሚጫወተው ሚናም መፈተሽ እንዳለበት አልሸሸጉም፡፡ በተለይ ከቅኝ ግዛት በኋላ ቅኝ ግዛት በሚመስል አካሄድ የአፍሪካ መሪዎችን መሾምና መሻር የሚያምራቸው፣ የሕዝቡ ነፃ ፍላጎትና እምነት የሚጎዱ፣ እንዲሁም በአገሮች የውስጥ ጉዳይ የሚገቡ መንግሥታት ፖሊሲዎችን ተችተዋል፡፡

እዚህ ላይ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት (ICC) በሚል በአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ተቋቁሞ በአፍሪካዊያን ላይ ብቻ አተኩሮ የሚንቀሳቀሰውን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እንቅስቃሴ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ እዚህ ላይ ‹‹Justice Denied›› በሚል ርዕሰ ዴቪድ ሆይሌ የተባሉ ፕሮፌሰር በቅርቡ ባስመረቁት መጽሐፍ የጉዳዩን ዝርዝር ገመናም ጠቅሰዋል፡፡

በጥቅሉ ግን የአኅጉሩ መንግሥታትና ሕዝቦች ከየትኛውም የውስጥና የውጭ ተፅዕኖ ነፃ ሆነው የሕዝባቸውን ተጠቃሚነት ማስቀደም ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰላም፣ የአገር ደኅንነትና የሕዝቦች መረጋጋትም ሆነ ዴሞክራሲያዊ ባህል ወሳኝ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከምሁሩ አስተያየት ጋር የተቀራረበ አስተያየት የሰነዘሩት የኮሚሽኑ የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት ኮሚሽነር ኢስማኤል ቺርጎ፣ ኅብረቱ በናይጄሪያ ሽብርተኝነት እያደረሰ ያለውን ጥፋት ይገነዘባል ብለዋል፡፡ ሚሊዮኖችን ከቀያቸው በማፈናቀል፣ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩትን ለሞት የዳረገውን ቦኮ ሐራም ለመፋለምም 7,500 ያህል አኅጉራዊ ሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ አገሪቱ ለመላክ ተዘጋጅቷል፡፡ አልሸባብ በሶማሊያ የሚያደርሰውን ጥቃት ሙሉ በሙሉ ለመግታትና የደቡብ ሱዳንን የውስጥ ቀውስ ለማስቆምም ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህና ሌሎች የሰላምና የመረጋጋት እንዲሁም የሕዝቦች ደኅንነት ጋር እያስተያዩ 2063 ኢኮኖሚያዊ ግብን ለማሳካት መረባረብ ወሳኝ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የመሪነት ሚና አኅጉራዊ አንድምታ

በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የአፍሪካውያን መሰባሰብ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ እንዳንዶች ‹‹ለውስጥ ቀጋ፣ ለውጭ አልጋ›› ከሚሉት የንጉሣዊ ፊውዳላዊ አገዛዝ አንስቶ እንደ አገር የነበረን ሚና ከአኅጉሩም በላይ የጎላ ነው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀዳሚ የአፍሪካ ተወካይነት አንስቶ በዝተው የሚነገሩ ዲፕሎማሲያዊና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች በኢትዮጵያ መሪነት ተካሂደዋል፡፡

የደርግ ወታደራዊ መንግሥት በተከተለው ግራ ዘመምና አምባገነናዊ ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት፣ ድርቅና ረሃብ በፈጠሩ ፅልመት የአገራችን የአፍሪካ ጭራነት ጎልቶ ታይቷል፡፡ ከጎረቤት አገሮችም ሆነ ከአኅጉሩ መንግሥታትና ሕዝቦች ጋር የረባ ወዳጅነትና መልካም ጉርብትና ነበረን ሊባልም አይችልም፡፡

ካለፉት ሃያ ዓመታት አኳያ በተለይ ከአሥር ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ግንባር ቀደምነት ሚናዋን ይበልጥ አጠናክራለች ብሎ መግለጽ ድፍረት አይመስለኝም፡፡ አንደኛው የአኅጉሩ መቀመጫ አዲስ አበባ ሆና እንድትቀጥል የተደረገው ብርቱ ጥረት ነው፡፡ በመቀጠልም በሁሉም የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የመሠረተ ልማት መስኮች ፈጣን ለውጥ በማስመዝገብ አርዓያ ለመሆን ያደረገችው ጥረት ነው፡፡ ለዚህ አብነት ሊሆን የሚችለው አኅጉሩ ባለፉት አሥር ዓመታት ከአምስት እስከ ስድስት በመቶ በአማካይ ሲያድግ፣ ኢትዮጵያ 10.5 በመቶ በማደግ መቀጠሏ ነው፡፡ አገራችን በአኅጉሩ የተቀሰቀሱ የውስጥ ቀውሶችን ለመታደግ ከአምስት በማያንሱ አገሮች ሰላም አስከባሪ ሠራዊቷን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተልዕኮ ሥር አሠልፋ መላኳም የቀዳሚነት መገለጫ ነው፡፡

ኢትዮጵያ እንደቀደመው አኅጉራዊ ታሪኳ ሁሉ አፍሪካዊ ወንድም ሕዝቦችን በመሸምገል በኩልም እየታየች ነው፡፡ የደቡብ ሱዳንና የሱዳንን ሕዝቦች ውሳኔ መሠረት ያደረገ ስምምነትን በተሳካ ሁኔታ ሸምግላለች፡፡ የተሳካና ያለቀለት ነው ባይባልም የደቡብ ሱዳንን የውስጥ ቀውስ ለመታደግ እያደረገች ያለው ጥረትም የሚደነቅ ነው፡፡ ኢጋድና ኔፓድን በመሳሰሉ ተቋማት ያላት ሚና፣ በተፈጥሮ ሀብት የጋራ ተጠቃሚነት የምክክር መድረኮች (ለምሳሌ NBI) እየተገኙ ያሉ ስምምነቶች ሁሉ፣ አኅጉሩ ወደ 2063 ራዕይ ስኬት የሚያደርገውን ጉዞ በተገቢው ሥፍራ ላይ ሆና መቀላቀሏን ያሳያሉ፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣዩ የአፍሪካ ጉዳይ ላይም ሆነ በራሷ ስኬታማ ዕርምጃ ውስጥ ተጠናክራ ለመቀጠል ግን በርከት ያሉ የቤት ሥራዎች እንዳሉባት ብዙዎች ምክር አላቸው፡፡ አንደኛው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን ሊያደናቅፉ የሚችሉ አስተሳሰቦችና ተግባራትን ነቅሶ በማስወገድ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር ነው፡፡ አገሪቱ ከሙስና፣ ከብልሹ አሠራርና ከመልካም አስተዳደር እጦት ርቃ የሁሉም ሕዝቦች ፍትሐዊ መጠቀሚያ መሆኗን የማረጋገጥ ተግባርም ወሳኝ ነው፡፡

አገሪቱ የምትገኝበት አካባቢ ለአክራሪነትም ሆነ ለሽብርተኝነት የተጋለጠ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የራሷ ወደብ የሌላት ‹‹ሰፊና ትልቅ አገር›› መሆኗም የሚፈልገው ሥራ አለ፡፡ እዚህ ላይ የአፍሪካ ኅብረት ‹‹የአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት›› ንድፍና የባህር በር ደኅንነት (The African Peace and Security Architecture and Maritime Issue) በሚል የቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍን መመልከት ያስፈልጋል፡፡ እንደ አገር ያለንን የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም፣ የዜጎችን ሕገወጥ ስደት በማስቆም፣ የውጭ ባለሀብቶችን በመሳብ፣ የአገር ውስጥ የግሉን ሴክተርና የኢንዱስትሪ ተፎካካሪነት በማጠናከር ሚናን ማጉላት ያስፈልጋል የሚሉ ትንታኔዎች በዝተዋል፡፡

አዲስ አበባ በለውጥ፣ በፈጣን ዕድገትና በአዲስ የባቡር ዘመን ላይ ሆና የተካሄደው 24ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና መጪው ጊዜ መመዘን ያለበትና ከላይ በተካተቱት ጉዳዮች ጭምር ነው፡፡ በእርግጥም ኢትዮጵያ ደግሞ በበለጠ የቤት ሥራዎችን ታቅፋ ነው ይህንን ጉባዔ በስኬት ያስተናገደችው፡፡

  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...