Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትአያያዛችን ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን ይጎዳዋል

አያያዛችን ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን ይጎዳዋል

ቀን:

በመንግሥቴ አወቀ

2007 የምርጫ ዓመት ነው፡፡ ገና ምኑም ሳይያዝና ምንም ሳይታወቅ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የዕጩዎች የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ በይፋ የሚጀመርበት ወቅት (የካቲት 7 ቀን) ፊታችን ተደቅኗል፡፡

እንዲህ ስንል ‹‹ድንቁርና››ችን የሚደንቃቸው፣ የጋረደን ‹‹ጥቅም›› የሚገርማቸው ሰዎች ቂሎች ሲሉን፣ ከንፈራቸውን ሲመጡልን ይሰማናል፡፡ በተለይ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል የሚሠራበት ጊዜ አክትሟል፤ በሕጋዊ መንገድ መታገልና በምርጫ መሳተፍ ለገዢው ቡደን የሕጋዊነትና የዲፕሎማሲ ተቀባይነት መሣሪያ ከመሆን ሌላ ዋጋ የለውም፡፡ እንዲያውም የተቃውሞ ትግሉን የሚጎዳ ክህደት ነው የሚሉት ደግሞ በክህደት ሊከሱን ይችላሉ፡፡

- Advertisement -

ምርጫ ማካሄድ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ነፃና ሚዛናዊ ውድድር ተከናውኖ አያውቅም ማለትም የሕጋዊ መንገድንና የምርጫን ፋይዳ ቢስነት አያረጋግጥም፡፡ የሰላማዊና የሕጋዊ ትግል እንዲሁም የምርጫ ፋይዳ ባልታሰቡ አጋጣሚዎች መምጣት አለመምጣት ወይም ሥልጣን በማሸነፍና ባለማሸነፍ ብቻ የሚመዘን አይደለም፡፡

በተለይም በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ የምርጫ ፋይዳ ወደግብ ለመድረስ በሚረዱ እንጥብጣቢ ውጤቶችም የሚመዘን ነው፡፡ በዚህ ረገድ ለምሳሌ ከቡድን ቁጥጥር የተላቀቁ የምርጫ፣ የመንግሥትና የሚዲያ አውታሮች እንዲኖሩ መታገል እንጂ፣ እነዚህ ሳይሟሉ ምርጫ ውስጥ መግባት የለበትም፣ የሚገባ ካለም ማንነቱ ያጠራጥራል ማለት የፖለቲካ መሃይምነት ነው፡፡ የምርጫ ካርድ ብቻውን አድራጊ ፈጣሪነትን ለመሻር ባያስችልም የበኩሉን ድርሻ ያዋጣል፡፡ የ87 ልምድ ለ92፣ የ92 ልምድ ለ97 አዋጥቷል፡፡ 97ትም ለወደፊቱ ብዙ ትምህርት ሰጥቶ ነበር፡፡ የተጠቀመበትና የተማረበት መንግሥት ሆነ እንጂ፣ የ97 ልምድ የማይናቁ የማሻሻያና የግንባታ ድሎችን ከመንግሥት መዳፍ ፈልቅቆ ነበር፡፡

አሁንም ከተበረታ የማይናቁ ተግባራትን ማከናወን ይቻላል፡፡ የተዛቡ አስተሳሰቦችና ሽኩቻዎች በሕዝብና በፖለቲካ ቡድኖች ላይ የሚያደርሱትን መከፋፈል በበሰለ ጋዜጣና በበሰለ ሒስ ማምከንና በመንግሥት በኩል ያሉ ጥፋቶችን ማጋለጥ፣ በምርጫ ማሸነፍ ባይቻል የሕዝብ አንገብጋቢ ጥያቄዎችን አንጥሮ እያወጡ መልስ እንዲያገኙ ግፊት ማድረግ ሕዝብን መጥቀም ነው፡፡ የገዢዎችን አፈና እንደየአመጣጡና እንደየዕድገቱ እንዲጋለጥ ለማድረግ መቻልም በራሱ አንድ ውጤት ነው፡፡

በምርጫ መሳተፍ የሚጠቅመው ኢሕአዴግን ነው ማለትም ግልብ ነው፡፡ አሁን ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች አለመታደል ሆነና አድሮ ጥጃ ሆነው እንዲህ ያለ ወግ ላይ አይደሉም እንጂ፣ በምርጫ አንሳተፍም ቢሉ ኢሕአዴግን አይጎዱትም፡፡ ካስፈለገ ከእነሱ የበለጠ ኢሕአዴግን ‹‹የሚነድፉ›› የውሸት ተቃዋሚዎች በአንድ ጀንበር ማዘጋጀትና ያሉት መናጆዎች ላይ መጨመር ይቻላል፡፡ ከኢሕአዴግ ‹‹ወዳጅነት›› ውጪ የሆኑ ተቃዋሚዎች በሕጋዊ መድረኩ ውስጥ መቆየታቸው ብቻውን (የረባ ነገር ባይሠራም እንኳን) ጥቅም ነው፡፡ በአጠቃላይ የሕጋዊ ትግልን እርባናና ፋይዳ ተከራክሮ ውድቅ ማድረግ አይቻልም፡፡

ከዚህ ይልቅ የእስከዛሬውን ሰላማዊ ትግል ፋይዳ ቢስ ያደረገው ትግሉን የሚመሩት ፓርቲዎችና የፖለቲካ ቡድኖች ፋይዳ ቢስ መሆን ነው፡፡ የኢሕአዴግ አገዛዝ ከቀዳሚዎቹ ጋር ሲነፃፀር ሐሳብን የመግለጽና የመደራጀት የተሻለ ዕድል የተገኘበት፣ ብዙ የፖለቲካ ቡድኖች የተፈጠሩበትና ምርጫም የሚያካሂዱበት መሆኑ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ፖለቲካና ፖለቲካዊ ቡድን ዛሬም አጋጣሚን የሚጠብቁ ጥቅመኞች የሚራኮቱበት አንድ መስክ ከመሆን አልዳነም፡፡ ደርግ በወደቀ ማግሥት ወደ ኢሕአዴግ የሰኔው ኮንፈረንስ ከሮጡት ብዙዎቹ ይኼው ጥቅመኝነት የወለዳቸው ነበሩ፡፡ ከዚያም በኋላ ከየብሔሩ ሰው በመብራት እየተፈለገ ንቅናቄ ሁን፣ በአካባቢህ እዚህ ቦታ ላይ ልሹምህ፣ አምባሳደር/ሚኒስትር ላድርግህ ሊባል አካባቢያዊ የፖለቲካ ንግድ ደራ፡፡

ዛሬም በሕዝብ ስም መንግሥታዊ ያልሆነ የዕርዳታ ድርጅት (NGO) አቋቁሜ ለመክበር ምን ፕሮጀክት ብነድፍ ያዋጣኛል ብሎ እንደሚያሰላ ጥቅመኛ፣ ፖለቲካና መቦዳደንም ይሠራበታል፡፡ ዴሞክራሲን፣ ነፃነትንና የብሔር መብትን ለዚህ ዓይነት ዓላማ መነገጃ አድርገው የሚጠቀሙ (ከዴሞክራትነት ጋር ግንኙነት የሌላቸው) ጥቅመኞች በርካታ ናቸው፡፡

ለፍቼ ያደራጀሁት/ያጠናከርኩት ፓርቲዬ እያሉ ድርጅትን እንደገዛ ንብረት መቁጠር፣ የፓርቲንም ሆነ ሌላ ታሳቢ ሥልጣንን የልፋት ድርሻ አድርጎ ማሰብ፣ በሁሉም ውስጥ በተቃዋሚውም በገዢውም ውስጥ ያለ ችግር ነው፡፡ ቀውጢና ፈታኝ ሰዓት ሲመጣ መካካድ፣ አንድ ላይ ያቦኳትን በሌላ ላይ ማላከክ፣ ወደ ሌላ መገልበጥ፣ ወደ ሌላ መሳብ፣ ሙልጭልጮሹ ተነግሮ አያልቅም፡፡ ኢሕአዴግም ጨው በማሳየትም ሆነ በማስፈራራት እየገዛ ለመከፋፈልና ለመበታተን የቀለለው ለዚሁ ነው፡፡

ለፖለቲካዊ መብቶች፣ ለፍትሕና ለእኩልነት እታገላለሁ የሚል ሁሉ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አይሆንም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲያውም ብልጭ ድርግምና ከምበል ቀና የሚሉ ጥረቶች ታይተዋል ከማለት በላይ መናገር ያስቸግራል፡፡ ዴሞክራሲንና ነፃነትን መውደድና መናፈቅም ብቻውን ዴሞክራት አያደርግም፡፡

ዴሞክራት ማለት ከተግባር ጋር በሚገናዘብ የዴሞክራሲና የእኩልነት አመለካከታዊ ለውጥ ውስጥ ራሱን አስገብቶ ፀረ ዴሞክራሲን የሚዋጋ እንጂ፣ መወጣጫውንና የግል ዝናውን በማመቻቸት ሥራ የሚዋጥ አይደለም፡፡ ዴሞክራት ማለት በፓርቲው ውስጥ የቅልበሳና የመላሸቅ ዕድልን ለማምከን፣ ለመከታተል ለማጋለጥና ለማስወገድ የሚያስችል የራሱ መጠበቂያ (ከመንግሥት አወቃቀርና አሠራር እስከ ሕዝብ ዓይንና ወሳኝነት) ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓት እስካልተደራጀ ድረስ፣ ነፃነቶች፣ የፍትሕና የእኩልነት መብቶች አስተማማኝ ተከባሪነት እንደማይኖራቸው አውቆ ለዘላቂነታቸው የሚታገልና እስኪሳካም የማይዘነጋ ነው፡፡ ዴሞክራት ተከራክሮ ማሳመንና ማመንን፣ በድምፅ የተበለጠበትን የፓርቲን ውሳኔ ማክበርን ዘላቂ ጥቅሜ ብሎ አርቆ የሚያይ፣ የፓርቲ በእርጅና መበላትና አለመበላት ዴሞክራሲያዊነትን ከማጣትና ካለማጣት ጋር ተያያዥ እንደሆነ የሚያውቅ፣ ስለዚህም ለድርጅቱ የውስጥ ዴሞክራሲ ሁልጊዜ ዘብ የሚቆም፣ ለአምልኩኝ ባይነት፣ ለሴረኝነትና ለአሻጥረኛነት ፀር የሆነ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የዴሞክራሲና የእኩልነት አስተሳሰብና አሠራር ያለበት፣ ሥልጣን በአንድ ግለሰብ ወይም አካል እንዳይዋጥ ቅንብር የሚበጅበት፣ ለዓላማ፣ ለአሠራርና ለውሳኔ መታመን የሚለመድበት በመሆኑ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር መለማመጃ ትንሽዬ ቤት ነው፡፡

በአገራችን ውስጥ እንኳን ትብብር ወይም ቅንጅት በፈጠሩ ፓርቲዎች፣ በእያንዳንዳቸው ውስጥም መሰነጣጠቅ ሲፈጠር ማየታችን እውነት ነው፡፡ ለምሳሌ የቅንጅት መሪዎች የዛሬ አሥር ዓመት ከእስር ተለቀው ሲወዛገቡ በታየ ጊዜ፣ ድሮም የዓላማ ውህደት ሳይኖር የተሰባሰቡት በሩጫ ነበር የሚል አስተሳሰብ ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡

በይፋ ዓላማ ረገድ ከተሄደ የዱሮውን ቅንጅት የፈጠሩት ብቻ ሳይሆኑ፣ ለዴሞክራሲ እንታገላለን የሚሉት ኅብረትን ጨምሮ ብዙዎቹ በአንድ ፓርቲ ለመጠቃለል የሚያስችል የጋራ መገናኛ ያልነበራቸው አይደሉም፡፡ የጋራ መገናኛ ነበራቸው፡፡ የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ አባላት ቁጥር የኢትዮጵያን ሕዝብ አጠቃላይ ቁጥር ያህል ነው፡፡ ያን ያህል ሚሊዮን አባላት ያሉት የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ የሶሻሊስቱንና የከበርቴውን ዝንባሌዎችን፣ የአሮጌና የአዲስ ትውልድ ቢሮክራቶችን፣ ምሁራንንና የግል ባለሀብቶችን፣ ወዘተ አሰባስቦ ያቀፈ መሆኑን፣ ከመቀራረባቸው ለመለያየት የሚቅበጠበጡት የኛዎቹ ፖለቲከኞች አያውቁትም ነበር ማለት ይቻላል፡፡

የአመራር ብቃትን የሚፈትኑና ከፍተኛ የሐሳብ ልዩነት ሊፈጥሩ የሚችሉ ከባድ ሁኔታዎችና ጉዳዮች የፖለቲካ ድርጅቶችን ማጋጠማቸው በቅንጅትና በኅብረት፣ ወይም ከዚያ በፊት በሕወሓት/ኢሕአዴግ (1993) የተጀመረ አይደለም፡፡ ወደፊትም ያጋጥማል፡፡

የፓርቲ አመራር አጥፊ ውሳኔና አካሄድ ሊያዝ የሚችልበት ጊዜ ሊኖር ይችላል፡፡ ልክ በዴሞክራሲያዊ መንግሥት ላይ ፀረ ዴሞክራት ሾልኮ ቢወጣ፣ ወይም የተመረጠ የመስተዳድር ቡድን ዴሞክራሲን የሚቃረን አካሄድ ቢያሳይ ሌላ መንግሥታዊ ሥርዓት ወደ መፍጠር መሄድ ሳያስፈልግ፣ በዚያው ሥርዓት ውስጥ ማስተካከል እንደሚኖር ሁሉ፣ ፓርቲም ዴሞክራሲያዊ ሕይወት እስካለው ድረስ አምባገነን ልሁን ባይና የሐሳብ ልዩነት በመጣ ቁጥር የግልበጣ ሴራ ማዘጋጀት፣ ወይም አንጃ ሠርቶ መነጠል ግድ መሆን ያለበት ነገር አይደለም፡፡ ባለው ዴሞክራሲያዊ አሠራር አመራር ይስተካከላል፣ አለመግባባት ይወገዳል፣ የሐሳብ ልዩነት እየተፈተገና እየተረታታ ይቀራረባል፡፡ ዴሞክራሲያዊ የውስጥ ሕይወትና የሐሳብ ነፃነት የሌለበት ፓርቲ የቱንም ያህል ትክክለኛ አቋም ቢይዝ ሄዶ ሄዶ ማርጀቱና መምከኑ አይቀርም፡፡ በአንድ ሰው ብስለት ላይ ተንጠልጥሎ ቢቆይ እንኳ ግለሰቡ አቅሙን ሲጨርስ ፓርቲውም አብሮ ያበቃለታል፡፡

ብዙ ሰው የደነገጠበት የቅንጅቶች ውዝግብ፣ ብዙ ሰው ከማለለበት ከውህደታቸውና ከ1997 ምርጫ ጋር ተያይዞ የመጣ የውስጣዊ ቀውሶቻቸው ቀጣይ ሒደት ነበር፡፡ የሆነውና አኳኋኑ ቢያሳዝንም፡፡ መሬት የለቀቀው የድርጅትና የግለሰቦች ተከፍቶ ድፍርስ እውነቱና ማን ምን እንደሆነ መታወቁ ለተሻለ ውጤት ይጠቅማል ተብሎ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ጭፍራ አሰባስቦ የመለየት ፍላጎትን ታዝባለች፡፡ በመርህ፣ በፖለቲካዊ እሳቤና በትግል ሥልት ፍሬ ነገር ላይ ያላተኮረ መካካድ ያለበት የአሉኝ አላሉኝ አተካሮ ሲካሄድ አይታለች፡፡ ሽማግሌ ተባልኩ፣ እነ እከሌ አይወዱኝም፣ ታምሜ አልጠየቁኝም፣ ስለዚህ በአንድ ፓርቲ አብሬ መሥራት ያስቸግረኛል ብሎ ማለት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሊከሰት የሚችል መሆኑንም ኢትዮጵያ ተረድታለች፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የድርጅቶች ደካማነት ጭምር ያገዘው ከፍተኛ ጥቃትና አፈና ደርሷል፡፡ ይህን ሁሉ ጥቃት፣ ድቆሳና አፈና አሸንፎ ለመውጣት ያለፉበትንና ያሉበትን ሁኔታ በቅጡ ገምግሞ በአሠራር፣ በአደረጃጀትና በትግል ሥልት መስተካከል ያለበትን መለየትና ከአቅመ ቢስ ትንንሽነት መውጫውን መንገድ አስቦ፣ ከዚህም በአሸናፊነት ወጥቶ ተዘጋጅቶ መጠበቅ ተቀዳሚ ተግባር ቢሆንም፣ ለየትኛውም ፓርቲ ይህ የተሳካ መንገድ አልሆነም፡፡

የድርጅቱ ትልቅነት የሚለካው የተገኘውን በማግበስበስ ሳይሆን፣ በፖለቲካና በትግል ሥልት ብስለትና በቁርጠኛ አታጋይነት ሚሊዮኖችን ከሁሉም የአገሪቱ ማዕዘን በዙሪያው አሳልፎ ለመንቀሳቀስ በመቻል ነው፡፡ ይህ በኢትዮጵያ አሁንም ገና በየትኛውም ፓርቲ ወይም ግንባር ያልተሞላ ክፍተት ነው፡፡

በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላት አሉኝ በሚለው ኢሕአዴግ ውስጥ ራሱ አባል መሆንና በግንባሩ አቋም ማመን እንደ ዱባና ቅል ለየቅል ሆኗል፡፡ በድርጅቱ ውስጥ የመከተብ ጉዳይ የእንጀራ ጉዳይ መሆኑ ዛሬ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

በዚህ ሁሉ ምክንያት የትኛውም ፓርቲ የድርጅት ውስጠ ዴሞክራሲን ፋይዳ ተገንዝቦ፣ ሁሉም ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ትግል ‹‹መዋደቅ›› አለበት፡፡ በለውጥ ውስጥ ለመኖር የሚፈልግ ፓርቲ መጀመሪያ የመረጃና የነባራዊ ግንዛቤዎች ድርቅ እንዳይኖርበት በሚያስችል ሁኔታ ውስጥ ራሱን ማስገባት ግድ ነው፡፡ ሐሳቦችና ጉዳዮች እየወጡ መነጋገሪያ እንዲሆኑ የሚያደርግ የውስጥ ጋዜጣና ውይይት አንዱ መሣሪያ ነው፡፡ ለእውነትና ለሕዝብ ቅርብ መሆን፣ ወቅታዊ ጉዳዮች ከፓርቲ ውጪ መወያያ እንዲሆኑና ጥናቶች እንዲካሄዱባቸው ማነሳሳትም ሌላው ኃላፊነት ነው፡፡ የተቃራኒ ፓርቲዎችን አቋም መመርመርና አባላቱ በክፍት አዕምሮ  እንዲገመግሙ ማድረግ የራስን አቋምና ጥንካሬ ለመፈተሽና ለማጥራት አስፈላጊ ነው፡፡

የተቀናቃኙን ድርጅት አቋም ከአባላቱ ሊደብቅ የሚሻ፣ የራሱ አቋም እንዳይተችና ጥፋቱ እንዳይጋለጥ የሚጥር ፓርቲ በመበስበስ መንገድ ውስጥ የሚጓዝ ነው፡፡ ባለፉት 40 ዓመታት ኢትዮጵያ የመበስበስ ምሳሌ የሆኑ በርካታ ቡድኖች ማሳያ አገር ሆና ቆይታለች፡፡

የድርጅት ውስጣዊ ዴሞክራሲ ሌላም ጥቅም አለው፡፡ የጋራ አመራር ባልፈዘዘበት ድርጅት ውስጥ የግለሰብ አድራጊ ፈጣሪነት መንገድ ይጠበዋል፡፡ የድርጅት አመራር ከላይ በተቀመጡ ጥቂት ሰዎች አስተዋይነት ላይ ብቻ እንዳይወሰን የውስጥ ዴሞክራሲያዊ መድረኮች በጣም ጠቃሚ ናቸው፡፡ መላ አባላቱ ከጊዜ ጊዜ ሐሳብ እንዲያዋጡ የውስጥ ጋዜጣ ዕድል ይሰጣል፡፡ ድርጅታዊ መብትና ግዴታም ይሆናል፡፡ ይህን የመሰለ የድርጅት ባህልም ይፈጥራል፡፡ የማያቋርጥ ሐሳብ የመስጠትና የመቀበል ሒደት ይኖራል፡፡ ተከራክሮ ማሳመን የቻለ ሐሳብ በግንዛቤና በሥልት ይመራል፡፡ ይህ አሠራር ድርጅትን ለመምራት ብቃት አለኝ የሚል ሁሉ ወንበር መያዝ ላይ እንዳይተናነቅ ይረዳል፡፡

በክርክር የተረታ ወገን ወይም ግለሰብ የአብላጫውን ውሳኔ የማክበር ኃላፊነት፣ የሐሳብ ተቀባይነት ለማግኘት ከሚደረግ የትኛውም ዓይነት ግለሰባዊ (ቡድናዊ) ትግል የላቀ ዋጋ ያለው፣ በቀጥታ የድርጅት ህልውናን የሚመለከት ነው፡፡ የፈለገውን ያህል ውሳኔው የተሳሳተ ቢሆን ‹‹ለበጎ ውጤት›› ተብሎ ውሳኔን መሻርም፣ ሕግንና ዴሞክራሲያዊ አሠራርን መጣስ እንዲሁም በድርጅት ላይ ጥቃት መፈጸም ይሆናል፡፡ በመንግሥት ደረጃም እንደዚያው ነው፡፡

አመራሩ ሊያፍነው በማይችል የውስጥ ጋዜጣና የስብሰባ ዕድል ሐሳቦች እንደልብ መንሸራሸርና መፋተግ ከቻሉ፣ መተንፈሻ ፍለጋ ከድርጅቱ ውጪ መሄድን ያስቀራል፡፡ ድርጅቱ አቋም ባስወሰደባቸው ጉዳዮች ላይ የግል አስተያየትንና አቋምን በመገናኛ ብዙኃን መስጠት መብት ነው፡፡ ድርጅቱ አቋም ከያዘ በኋላ ግን ያንን እየተቃረኑ የእኔ የግል አቋምና እምነት እንዲህ ነው እያሉ መለፈፍን ከመብት ለመቁጠር መሞከር ግን፣ ‹‹አንዱም ሳይያዝ›› እንዲሉ የውስጥ ልዩነቶችንና ባለልዩነቶችን እየተጠጉ ድርጅቱን ለመሰንጠቅ ለሚጥሩ መሰሪዎች ሰፊ መንገድ መስጠት ነው፡፡

ሸሪክና ድምፅ ለማግኘት ሲባል፣ ጥቅም ነክ ድርድሮችና ድለላዎች ሁሉ የሚካሄዱበት የፓርላማ ኮሪደር ሹክሹክታ በተለመደ ዴሞክራሲያዊ አሠራርነት በአገራችን ፓርቲዎች ውስጥ ማስገባትም ለአንጀኝነት ፈቃድ ከመስጠት አይደለም፡፡ (ለምሳሌ በቅንጅት ውህደት ጊዜ አቶ ልደቱ አያሌው ቁልፍ ናቸው ከተባሉ የኃላፊነት ቦታዎች እንዲርቅ የተደረገው በውስጥ ለውስጥ ምክክርም እንደነበር ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ መጽሐፍ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ መንገድ ይልቅ ለዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የሚጠቅመው እከሌ ለዚህ ቦታ ያንሳል? እከሌ የተሻለ ብቃት አለው? ብሎ ፊት ለፊት ክርክር ላይ በመመርኮዝ ነው)፡፡

ቀጥተኛም ሆነ የሽፍንፍን አፈና የሌለበት አሠራርን እያጠናከረ የሚሄድ ፓርቲ ልዩነትንና ቅሬታን እያራገቡ ድርጅትን ለመሰነጣጠቅ ለሚፈልጉ ጥቅመኞችና ሰርጎ ገቦች በቀላሉ አይበገርም፡፡ ተንኮሎች እንደተዳፈኑ እንዳይቀሩ፣ ገና በእንጭጩ እንዲጋለጡና እንዲቀንሱ በማድረግ ደኅንነቱን ለመጠበቅ የተሻለ አቅም ይኖረዋል፡፡

የአንድ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ የውስጥ ሕይወት ደብዝዞ እንዳይጠፋ የሚጠብቀው የመላ አባላቱ ንቁነት ነው፡፡ ንቁነት ማለት ምንድነው? እንዴትስ ነው?

አባላት ‹‹ሕዝብ ማለት መንግሥት ነው፣ መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው›› እንደሚባለው ‹‹አመራር ማለት ድርጅት፣ ድርጅት ማለት አመራሩ ነው፣ እንደኛ ሆናችሁ ሁሉን ሸፍኑ›› ከሚል ኃላፊነትን የመሸሽ አባዜ የተላቀቁ ንቁ አባላት መሆን አለባቸው፡፡

አባላት መስዋዕትነት የተራው ደጋፊና አባል፣ በስደት ማምለጥ የአመራር አባላት ወግ አድርገው የሚያስቡ ብልጣ ብልጦች መጫወቻ የማይሆኑና አባል የሆኑበት ድርጅታቸው በቆራጦች የሚመራ ስለመሆኑ ትኩረት ሰጥተው በትጋት የሚሳተፉ መሆን አለባቸው፡፡

አባላት የድርጅታቸውን መተዳደሪያ ደንብ የሰርክ ግንዛቤና መሣሪያ አድርገው ከራሳቸው ጋር ያዋሀዱ መሆን አለባቸው፡፡ አባላት በድርጅትና በግለሰብ አምላኪነት ዓይናቸው የማይከለል፣ ጠያቂ አዕምሮ ያላቸውና የድርጅታቸውን አካሄድ ሥራችን ብለው የሚከታተሉ መሆን አለባቸው፡፡

አባላት ጥፋትና ስህተት ሲሠራ አሳልፈው፣ ነገር ከተበላሸ በኋላ ተመፃዳቂና በሆዴ ይዤው እንዳልቀር የሚል ተቺነት የማይጫናቸው፣ በዝምታም ይሁን በንቃት ድጋፋቸውን ሰጥተው አብረው ከወሰኑ በኋላ ለውሳኔውና ለሚከተለው ውጤቱ የጋራ ኃላፊነትን ከመውሰድ ፋንታ፣ የሐሳቡ አመንጪና ዋና ተከራካሪ የነበረውን ግለሰብ ኃላፊና ተጠያቂ (የስብሰባን ውጤት የግለሰብ ሥራ) የማድረግ ‹‹ዘመናዊ›› ሾላካነትን የሚዋጉ መሆን አለባቸው፡፡

በአጠቃላይ ለእውነት፣ ለመረጃ፣ ለዕውቀትና ለለውጥ ሁልጊዜ ቅርብ ለመሆን የሚጣጣሩ አባላት ናቸው፣ አባላት የሚባሉት፡፡ ድርጅታቸውን ከመበስበስ አደጋ የሚያድኑት ብሎም ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ድልና ግንብታ ትልቅ ኃይል መሆን የሚችሉት እንዲህ ዓይነት ዴሞክራቶች ናቸው፡፡ ያሉበትን የፖለቲካ ድርጅት ፖለቲካዊ ባህሪይ አቃንተውም ሆነ ተስፋ ከሌለው ቡድን እየተላቀቁ፣ እርስ በርስ በመቀራረብ ቁርጥራጭ ሩጫዎችንና ሥልቶችን በማሳፈር የየፓርቲዎቹና የኢትዮጵያ ሕዝቦች የትግል መሰባሰቢያ መሆን የሚችሉት እንዲህ ያሉ ዴሞክራቶች ናቸው፡፡

ቀደም ሲል እንዳልነው የምንገኘው ሦስት ወራት ብቻ በቀሩት የምርጫ ዓመት ውስጥ ነው፡፡ በምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች ምዝገባ የሚካሄድበት ከተኅሳስ 16 እስከ ጥር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ የተያዘው የ40 ቀን የምዝገባ ጊዜ ምኑም ሳይያዝ የተቃጠለው ባለፈው ሳምንት ነው፡፡ ‹‹ለመጨረሻ ጊዜ›› የተራዘመውም ለአንድ ሳምንት ብቻ ነው፡፡

የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ይጀምራል የተባለው የዕጩዎች የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ (በጠቅላላው የዘጠና አራት ቀናት ያህል ነው) በተመሳሳይ ሥሌት በአንድ ሳምንት ተራዝሟል፡፡ የአንድነትና የመኢአድ ፓርቲዎች ለየብቻቸው ለሁለት መሰንጠቅ የምርጫ ቦርድን ‹‹ውሳኔ›› ያገኘው ገና ጥር 21 ቀን 2007 ነበር፡፡

በዚህ ሁሉ መካከል የምንሰማው ስለአንድነት ፓርቲ የእነ አቶ በላይ ፍቃዱና የእነ የአቶ ትዕግሥቱ አወሉ ቡድኖች፣ ስለመኢአድ ደግሞ የእነ አቶ ማሙሸት አማረና የእነ አቶ አበባው መሐሪ ቡድኖች ነው፡፡ የአባላት ድምፅና አቋም አይሰማም፡፡ ስለአባላት የሚሰማ አንድ ነገር ቢኖር ‹‹ከእነዚህ ፓርቲዎች በስተጀርባ ሕዝብ አለ›› ሲባል ነው፡፡ መቼም የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት አባላት ከእያንዳንዱ ፓርቲ ‹‹ቡድኖች›› ድምር በላይ የላቀ ቁጥር አላቸው፡፡ እነዚህን ‹‹ከፓርቲው በስተጀርባ›› ያሉ ሕዝቦች ወደፊት አስቀድሞ፣ ድምፃቸውን ማስተጋባት እንዲችሉ የሚያደርግ አሠራር ኢትዮጵያ የላትም ወይ? የተሰጠውስ ውሳኔ ሰላማዊና ሕጋዊውን የፖለቲካ ትግል ንቀው የጠመንጃ መንገዱን አብልጠውና መርጠው ትግል የገቡትን ወገኖች ‹‹አይበልናንዶ?›› አያሰኝም ወይ?

ዋናው ጉዳይ ግን፣ ሰላማዊ ትግሉ አያዋጣም ያሉት እውነትም ለጊዜው ‹‹አላልንም ወይ?››፣ ‹‹ብለን አልነበረም ወይ?›› ማለት መቻላቸው ይህንን ማለት የሚያስችል ‹‹ማስረጃ›› ወይም ‹‹የምስክር ወረቀት›› ማግኘታቸው አይደለም፡፡ ከዚህ የበለጠ የሚያሳዝነውና የሚያስፈራራው በኢትዮጵያ በባለብዙ ፓርቲዎች ሰላማዊና ሕጋዊ የፖለቲካ ትግል ላይ የደረሰው የማይጠገን አደጋ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...