Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ሕዝቡ የሥልጣን ባለቤት ከሆነ ሁሉም ነገር ቀላል ይሆናል››

ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፣ የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት

ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ቀደም ሲል የነበሩበት አንድነት ፓርቲ ከመድረክ ጋር በጋራ ለመሥራት ሲንቀሳቀስ ይህን በመቃወም ፓርቲውን ለቀው በመውጣት ፓርቲውን ከሌሎች ግለሰቦች ጋር መሥርተዋል፡፡ በቅርቡ የተላለፈውን የምርጫ ቦርድ ውሳኔን ተከትሎ በምርጫ ቦርድ ዕውቅና የተነፈገው የእነ አቶ በላይ ፈቃዱ ቡድን በርካታ አባላት ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀላቸው እየተዘገበ ይገኛል፡፡ በዚህና በሌሎች የፓርቲው እንቅስቃሴ፣ ፓርቲው ስላዘጋጀው አዲስ ማኒፌስቶ፣ ሰማያዊ በአባልነት ስለሚገኝበትና በቅርቡ ስለተቋቋመው የዘጠኝ ፓርቲዎች ትብብርና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በመተለከተ ኢንጂነር ይልቃልን  ነአምን አሸናፊ አነጋግሯዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የፊታችን ግንቦት ከሚካሄደው ምርጫ ጋር ተያይዞ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ያየነው ነገር አለ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲም ይቅርታ ይጠይቅ የተባለበት ጊዜ ነበረ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በምርጫው ለመሳተፍ ያደረጋቸው እንቅስቃሴዎች፣ ዕቅዶችና ስትራቴጂዎች ምን ይመስላሉ?

ኢ/ር ይልቃል፡- መስከረም ላይ የዚህን ዓመት ዕቅድ ስናፀድቅና ያለፈውን ዓመት ሪፖርትና አፈጻጸም ስናቀርብ፣ ከመስከረም ጀምሮ ይህ ዓመት የምርጫ ዓመት በመሆኑ ልዩ ዕቅድ በሚል ተይዞ ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ለሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ቀርቦ፣ ሁለት ሦስት ስብሰባዎች ከተደረጉ በኋላ ፀድቆ በዚያ መሠረት እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ በዚያ እንቅስቃሴያችን እንደ ዋና አጀንዳ ተብሎ የታያዘው ሁለት ሦስተኛ ወይም በፍፁም የአብላጫ ድምፅ ማሸነፍ ነው፡፡ ለዚያ የሚሆኑ አሠራሮችና ዕቅዶችን ማውጣት የሚል ነው፡፡ ለዚህም ዳር ዳር ባሉና ባልደረስንባቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች ካልሆነ በስተቀር፣ በሁሉም ክልሎች ውስጥ ዕጩዎችን ለማቅረብ አቅደን እየሠራን ነው፡፡ በአጠቃላይ ከ400 በላይ ዕጩዎች ማቅረብና በ380 ፍፁም አብላጫ ድምፅ ማሸነፍ ዋናው ዓላማችን ነው፡፡ ለዚያ አፈጻጸም የሚሆኑ አሠራሮችና አደረጃጀቶች በዝርዝር ቀርበዋል፡፡ በጥናትና በስትራቴጂያችን መሠረት የሰነድ ዝግጅቶች ፕሮግራም እንደምታውቀው በጣም ጥቅል ነገር ነው፡፡ ግን በዚህ ፕሮግራማችን መሠረት ዝርዝር የአፈጻጸም ሰነዶችና የፖሊሲ ማብራሪያዎች ወይም ማኒፌስቶ እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡ እሱ ወደ ጫፍ ደርሷል፡፡ ከዚህ በኋላ የኅትመትና የአርትኦት ሥራ ነው የሚቀረው፡፡ እሱ በሚገባ ተኪዶበታል፡፡ የምርጫ ዕጩዎችን የማስመዝገብ ነገርም አሁን በተራዘመው ጊዜ ይኖራል፡፡ በጊዜ እጥረት የነበረንን ነገሮች ለማስተካከል ካልሆነ በስተቀር ከሞላ ጎደል ዕቅዳችንን አሳክተናል፡፡ በዚህ ውስጥ ደግሞ እንደምታውቀው ከ1997 ዓ.ም. የምርጫ የውድድር ሜዳውና አጠቃላይ የፖለቲካ ምኅዳሩ በእጅጉ እየተሸማቀቀና እየተጨማደደ ነው የመጣው፡፡ ያንን ለማስፋት ሰማያዊን ጨምሮ ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ‹‹ነፃነት ለፍትሐዊ ምርጫ›› የሚል ዕቅድ ነድፈን በዚህ በፖለቲካ ምኅዳሩ ያለውን ነገር ለማስፋት፣ በእነዚህ በሁለት ስትራቴጂዎች ተመጋጋቢነት በዚህ ምርጫ አሸናፊ ለመሆን ሕዝብን በማነቃቃት፣ አደረጃጀትን በማጠናከር፣ የድርጅታችንን ገጽታ በመገንባት፣ የሕዝቡን ተስፋ ከፍ በማድረግና የተነጠቁ ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻችንን ከአገዛዙ በማስመለስ፣ የምርጫ ሜዳውን በማስከፈትና በመጫወትም ሁለቱን ተመጋጋቢ አድርገን በመሥራት ጥሩ ውጤት ለማምጣት ነው በአጠቃላይ እየሠራን ያለነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ጋር በተገናኘ ፍፁም አብላጫ ድምፅ የማግኘት ዕቅድ ይዛችሁ እየተንቀሳቀሳችሁ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ምን ያህል አባላት አስመዘገባችሁ?

ኢ/ር ይልቃል፡- ባለኝ መረጃ ከ400 በላይ እንዳለን አውቃለሁ፡፡ የምናሸንፈው በ380 ነው፡፡ ባለን ጊዜ ውስጥ ከዚያ ባለፈ ግን እስከ 500 ልንሄድ እንችላለን፡፡ ምን ያህል ጠንካራ ናቸው? ተወዳድረንስ እናሸንፋለን ወይ? የሚለውን አሁን ደግሞ በአንድነትና በመኢአድ ውስጥ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ብዙዎቹ በአቶ በላይ በኩል የነበሩትና ዕውቅና ከተነፈጉት ሰዎች ሙሉ በሙሉ፣ አንዳንዶች በፖለቲካ መሳተፍ ከማይፈልጉና ባለው ሁኔታ ተስፋ ከቆረጡ ውጪ መዋቅሩ ወደኛ ገብቷል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ወጣ ገባ የምናደርጋቸው ነገሮች የሚገኘውን ተስፋና ፍጥነቱንም ስለሚጨምሩ 500 ድረስ ልንደርስ እንችላለን የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ግን ከ400 በላይ እንደሄደ መረጃው አለኝ፡፡                                                                                                                                                     

ሪፖርተር፡- አሁን የነገሩኝ አጠቃላይ የምርጫውን እንቅስቃሴ ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በዋነኛነት የተዘጋጀበትን ከርዕዮተ ዓለም እንቅስቃሴ ውጪ ያለውን ይንገሩኝ፡፡ ኢሕአዴግም ሌሎች ፓርቲዎችም የራሳቸው የሆነ አለን የሚሉት ርዕዮተ ዓለም ለማስፈጸም ነው የሚፈልጉት፡፡ ነገር ግን በቀላል ቋንቋ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሚገባው ቋንቋ ከርዕዮተ ዓለምና ሌሎች እንደ ሊበራል ዴሞክራሲ፣ ወዘተ ከሚለው ውጪ በዚህ ምርጫ ላይ ብትመረጡ ያለው አማራጭ ወይም በፖሊሲ ደረጃ ለሕዝቡ ሊቀርብ የሚችለው ምንድን ነው?

ኢ/ር ይልቃል፡- አንደኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች የተሻለ የትምህርት ጥራት እንዲኖራቸውና በትምህርት ጥራቱ በአገራቸውም ሆነ በየትኛውም ዓለም ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በትምህርት ጥራት ላይ ሰፊ ሥራ እንደሚሠራ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የኑሮ ልዩነት ወይም የገቢ ልዩነት የሚባለው ነው፡፡ ጥቂቶቹ በጣም በልፅገዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ወደ 34 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች ይኖራል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ሥራ ፈጠራና ደሃውን ከግምት ውስጥ ያስገባና እነዚህን ዜጎች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዋስትና እንዲኖራቸው በፍጥነት ድህነትን በመቀነስ ላይ አተኩረን እንሠራለን፡፡ የኢትዮጵያ ገበሬ የመሬቱ ባለቤት እንዲሆን እናደርጋለን፡፡ ያ ማለት ገበሬው መሬቱን በፍጥነት ሸጦ ወደ ድህነት ይግባ አይደለም፡፡ የመሬት ባለቤት ሲሆን በደንብ ያለማዋል፡፡ ከባንክ አስይዞ ይበደርበታል፡፡ እዚያ ላይ ያለውን የሀብት ፈጠራ ችሎታ ያዳብራል፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግር ያመጣል፡፡ የፖለቲካ ዋስትና ይኖረዋል፡፡ መሬቴን ማንም ይቀማኛል ስለማይል ነፃነቱ ይረጋገጣል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ገበሬ የሚያርሰው መሬት የራሱ እንዲሆን እናደርጋለን፡፡ በአጠቃላይ ደግሞ ከልዩነት ይልቅ በአንድነታችን ላይ አተኩረን፣ ልዩነታችንን ውበት አድርገን፣ በኢትዮጵያዊነት ኮርተን፣ የአገራችንን የነበረንን ታሪክ አበልፅገን፣ ያሉብንን ጉድፎች አሻሽለን ወደፊት የምንኖርበት እንጂ፣ ከዚህ በፊት የነበሩን ቁርሾዎችና ቁስሎች ለመለያየትና ለመጣላት መሠረት ሳይሆን፣ እነዚያን እንደ ደረቅ ታሪክነት ተምረን እንዳይደገሙ አድርገን ወደፊት ኢትዮጽያዊነትን እየገነባን እንሄዳለን የሚሉ ናቸው፡፡ ቀለል ባለ ሁኔታ ስላልከኝ እነዚህ አንኳር አንኳር ነጥቦች ናቸው፡፡ የሥራ ፈጠራ ዋናው ሥራችን ይሆናል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ፓርቲ የራሱ የሆነ ፕሮግራም ይኖረዋል፡፡ ማኒፌስቶም እየተዘጋጀ እንደሆነና ኅትመትና አርትኦት ነው የቀረው ብለውኛል፡፡ አሁን የዘረዘሯቸው ነገሮች በዝርዝር ፕሮግራሞቹ ወይም ማኒፌስቶዎች ውስጥ ተካተው እንደዚህ በቀለለ ቋንቋ ሕዝብ ሊደርሱ ተዘጋጅተዋል?

ኢ/ር ይልቃል፡- እውነት ነው ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ መጀመርያ አጠቃላይ የማኒፌስቶው ይዘት አሁን ያለው ሥርዓት ድክመቶችና አሠራሮች ምን ይመስላሉ? የሚከተለው ፖሊሲ ምንድን ነው? የሚል አለ፡፡ ለዚህ ደግሞ የእኛ አማራጭ ምን ይመስላል? በዝርዝር ድክመት ናቸው ካልናቸውና በዚህ ፖሊሲ መለወጥ አለባቸው የሚለው የኛን አማራጭ የሚያሳይ ሁለት መልክ ያለው ማኒፌስቶ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ያልኩህን ነገሮች ሁሉ ቋንቋው ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍልና በሁሉም  ንቃተ ህሊና ደረጃ ያለን ሰው ሊያግባባና መራጭ ሊረዳው በሚችለው መልኩ ተዘጋጅቷል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማኒፌስቶው መቼ ይፋ ይሆናል?

ኢ/ር ይልቃል፡- የምርጫ ቅስቀሳ በሚጀመርበት ጊዜ ይፋ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ የምርጫ ቅስቀሳው የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው ይጀመራል የተባለው፡፡ ግን በ15 እና እዚያ አካባቢ ይደረጋል፡፡ የአሠራር ጉዳይ የመቀላጠፍ ነገር ካልሆነ መሠረታዊ ሐሳቡና ሥራው ያለቀ ስለሆነ፣ ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ይፋ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት ሰማያዊ ፓርቲ ምን ያህል አባላት አሉት?

ኢ/ር ይልቃል፡- አሁን ላይ ያለውን ማወቅ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም እንደነገርኩህ አንድነት ፓርቲ ለትዕግሥቱ አወሉ ከመሰጠቱ በኋላ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ከሞላ ጎደል የአንድነት አባላት የሰማያዊ አባላት ሆነዋል፡፡ ይኼ በፍጥነት የነበረውን የአባላት ቁጥር፣ የሕዝቡን ሥነ ልቦና፣ አጠቃላይ በፖለቲካው የነበረውን ተስፋ ሁሉ የለወጠና ፈጣንና ብዙዎቻችን ያልጠበቅነውና ባላሰብነው ሁኔታ የተፈጠረ ነገር ነው፡፡ በዚህ ደረጃ በጣም ሄዷል፡፡ የእኛ አባላት ግን በፊት የነበሩ 50 ሺሕ እና ከዚያ በላይ እንደነበሩ ከሁለትና ከሦስት ወራት በፊት በነበረው መረጃ መሠረት አውቃለሁ፡፡ አሁን የአንድነት አባላት በሙሉ መጥተዋል፡፡ እነዚያ ሲመጡ ደግሞ በሕዝቡ ውስጥ የሚፈጥረው ተስፋና መልካም ምኞት አለ፡፡ በዚያ ውስጥ የተገናኘም ነገር አለና ቁጥሩን በትክክል ለመናገር አሁን ያስቸግረኛል፡፡ ግን ብዙ ተስፋ እንዳለ ማየት ችያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ከገዥው ፓርቲም ከተቃዋሚውም፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጋር ያለው መሠረታዊ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ምንድነው?

ኢ/ር ይልቃል፡- ዋናው መሠረታዊ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት የኢሕአዴግ የቁጥጥርና መንግሥት ሁሉን ቻይ አድርጎ የመጠቀም ሲሆን፣ በሰማያዊ አመለካከት ደግሞ ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት አድርጎ በሕዝብ ውስጥ ያለን ችሎታና ብቃት የማፋፋት፣ የማበልፀግና የማሳደግ ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች ባላቸው የሕይወት ጥሪ ሁሉ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ ማመቻቸት ነው እንጂ፣ መንግሥት የሁሉ ነገር አዋቂ፣ የሁሉ ነገር ሠሪና የሁሉ ነገር መሪ ሳይሆን አመቻች ነው፡፡ እነዚያን ችሎታዎችን በሥልጠና፣ በፖሊሲ፣ በብድር፣ በአቅም ግንባታና በልዩ የዜግነት ክብር እንዲሰማቸው በማድረግ ለማኅበራዊ አገልግሎት የሚከበር ሥራ በማድረግ ዜግነትን በመቅረፅ እነዚያን ሁኔታዎች መፍጠር እንጂ፣ ራሱ አልሚ፣ አበዳሪና ራሱ ችግር ፈቺ እንዲሆን አንፈልግም፡፡ የኢትዮጵያን እምቅ የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ልጅ ችሎታን ማፋፋትና ማበልፀግ፣ ዕድል መፍጠርና ያንን ዕድላቸውን የማመቻቸት የፖሊሲ አቅጣጫ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ እነሱ ግን የቁጥጥርና ከላይ ወደ ታች በሚወርድ በትንሽ ሰዎች ታቅዶ ሌላው ሕዝብ እንዲፈጽም የማድረግ ነገር ነው ያለው፡፡ ይኼን አንኳር ልዩነታችን ብዬ መናገር እችላለሁ፡፡ በተለይ እነሱ የሚያተኩሩት በልዩነት ላይ ነው፡፡ እኛ የምናተኩረው በብዝኃነትና በአንድነት ላይ ነው፡፡ እነሱ የሚከተሉት ፌዴራል ቋንቋን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ እኛ ከቋንቋ ባለፈ ቋንቋን ጨምሮ ባህልን፣ የሕዝብ አሰፋፈርን፣ የአስተዳደር ምቹነትን፣ መልከዓ ምድርን፣ የሕዝቡን ሥነ ልቦናና እምቅ ሀብት ከምግት ውስጥ ያስገባና የዜጎችን አኗኗር እንዲሁም አስተዳደሩ ወደ ታች እንዲወርድ የሚያደርግ ነገር እናደርጋለን፡፡ በመሬት ፖሊሲያቸው ላይ በመንግሥት ተይዞ ሁሉ ነገር በመንግሥት ቁጥጥርና በፓርቲ እንዲሆን አድርጓል፡፡ እኛ ደግሞ መሬት በከተማም ሆነ በገጠር የሚያርሱ ሰዎችና የከተማ ሰዎች ቤት የሠሩበትና ንብረት የያዙበት የራሳቸው፣ ነገር ግን ለልማት ያልዋሉ በመንግሥትም በሕዝብ የሚያዙ እንደሚኖሩ፣ የሕዝብ የምንላቸው እንደ ዕድር ቦታዎችና መዝናኛዎች ያሉ የሕዝብ ሲሆኑ፣ ልማት ላይ ያልዋሉ ደግሞ በመንግሥት እጅ ተይዘው ለግል ለወደፊት የሚሰጡበትና የሚተላለፉበትን ለልማት የሚወሉበትን መንገድ የሚሉ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጋር ያላችሁን ልዩነት ገልጸውልኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተቃውሞ ጎራ በተደጋጋሚ የሚነሳ አለ፡፡ እርስ በርስ በመፎካከራቸው ኢሕአዴግ በርካታ ድምፆች እንዲያገኝ ዕድሉን እየከፈተለት ነው የሚባል፡፡ ከዚህ አንፃር  መኢአድ፣ አንድነትና ሌሎችም ፓርቲዎችን ጨምሮ ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋርስ ሰማያዊ ፓርቲ ያለው አንድነትና ልዩነት ምንድን ነው?

ኢ/ር ይልቃል፡- በተቻለ መጠን የፖለቲካ ፓርቲ ስትለው በሕዝቡ ውስጥ ከፍ ብሎ የሚታይ የድጋፍ ደረጃውም በገንዘብም፣ በሰው ኃይልም፣ በሚዲያውም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ተፅዕኖ የማድረግና ለሥልጣን ቅርብ መሆኑን ማየት ይኖርብናል እንጂ፣ አንድ ሰው ሁለት ሰውም ሆነው ፓርቲዎች ይኖራሉ፡፡ እነዚያ ፓርቲዎች በውድድር ውስጥ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለአብዛኛው ሰው ውክልና ቢኖራቸው ተስፋ እስካልሆኑ ድረስ ያንን ዝርዝር ማየት አይቻልም፡፡ ግን ጎላ ጎላ ያሉትን ከሞላ ጎደል ብናይ አሁን ያሉት ኢሕአዴግ፣ መድረክ፣ ሰማያዊና አንድነትም ወደ አንድ መጥተዋልና እነዚህ ሦስት ኃይሎች ናቸው አሁን ለእኔ የሚታዩኝ፡፡ መኢአድም እንደምታውቀው ሁለት ሆኖ በዚያ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው፡፡

      ዝርዝሩን ከኛ አገር ባህልና ተቃዋሚዎችን የመተቸት ገና እዚያ ደረጃ ላይ አልደረስንም፡፡ ያ ደግሞ በዕውቀትና በእውነት ላይ ተመሥርተህ በሐሳብ ልዩነት ላይ የምንከራከርበት ሳይሆን፣ አንድ ትልቅ አገዛዝ ቡድን ይዞ ሌሎች የሚፍጨረጨሩበት ጊዜ ስለሆነ በፓርቲዎች መካከል ያለውን ፉክክርና መናናቅ ሕዝቡ አይፈልገውም፡፡ ወደዚያ ዝርዝር ባታስገባኝ ደስ ይለኛል፡፡ በአጠቃላይ ግን ኢሕአዴግ ፖለሲ ጋር ተቀራራቢ ኖሯቸው ነገር ግን አካሄዱ ማታለል ማጭበርበር አለበት፡፡ ውስጥ ባለው አደረጃጀት የተወሰኑ ማዕከላዊነትን በያዘ ሁኔታ ሥልጣኑን የተቆጣጠሩ የተወሰኑ ናቸው እንጂ፣ እውነተኛ የፌዴራል ሥርዓትም እውነተኛ የብሔር ብሔረሰቦች መብትም አልተከበረም ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡ የእነመድረክ ዓይነቱ ስብስብ ማለት ነው፡፡ ከዚያ ለየት ባለ የኢትዮጵያን ቀደምት ታሪኮችና ጉድፎች አስተካክሎ፣ መልካም ተሞክሮዎችን ይዞ አንድነታችን ላይ ያተኮረ ልዩነታችንን ውበት አድርገን እንሥራ፣ በዝርዝር የፖሊሲ ጉዳዮች በዚህ በዚህ እንለያያለን የሚሉ ሰማያዊንና የመሰሉ አንድ ጎራ አለ፡፡ በአጠቃላይ አሁን በሦስት ጎራ ውስጥ ሆኖ ፖለቲካው የሚሄድ ይመስለኛል፡፡ ከመድረክ ጋር ያለን ልዩነት በፌዴራል አወቃቀር ሆነ በመሬት ፖሊሲም ቢሆን የእነሱ ወደ ሶሻል ዴሞክራሲ የሚጠጋ ዓይነት አለው፡፡ እኛ ግን ‹‹ሴንተር ራይት›› ሆኖ መንግሥት አሁን ባለንበት ሁኔታ ውስጥ ከሁሉም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሊወጣ አይችልም እንላለን፡፡ ነገር ግን የመንግሥት ሚና አምራች ሆኖ ባለሀብቱን እየፈጠረ በሒደት አነስተኛ መንግሥት የሚሆንበት ነው፡፡ አሁን ግን ባለንበት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትሕ በሌለበትና ጠንካራ ተቋማት በሌሉበት ሁኔታ፣ ሁሉንም ነገር ለግል ባለሀብት ብትሰጠው ደሃውን ለቀማኛ ሰጥተኸው ታርፋለህ፡፡ ስለዚህ የመንግሥት ሚና የመካከለኛ ክፍል ነዋሪ እየተፈጠረና እነዚያ በማይገቡበት የኢኮኖሚ ዘርፎች እየገባ፣ ቀስ በቀስ ወደ ሊበራል ኢኮኖሚ የምንሄድበትን ፖሊሲ ‹‹ሴንተር ራይት›› ብለን ስናስብ እነሱ ግን ሶሻል ዲሞክራሲ ዓይነት ነው ያላቸው፡፡  መድረክ አካባቢ ያሉት ይኼ ይመስለኛል፡፡ ጎላ ብሎ የሚታየው ይኼ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርብ ወደ ተፈጠረው ጉዳይ እንምጣና በምርጫ ቦርድ በመኢአድና በአንድነት ላይ የተወሰነ ውሳኔ ነበር፡፡ በውሳኔው መሠረት አንድነት ለአቶ ትዕግሥቱ አወሉ መኢአድ ደግሞ ለአቶ አበባው መሐሪ ተሰጥቷል፡፡ ይህንን ተከትሎ በርካታ የአንድነት አባላት በመዋቅር ደረጃ ሰማያዊን ተቀላቅለዋል እየተባለ ነው፡፡ ግን አንድነት ወደዚህ ከመምጣቱ በፊት በአስተሳሰብና በትግል ዓላማ አንድ ዓይነት ነገርም ቢኖር፣ ይኼ ጉዳይ ባይመጣ ኖሮ ተፎካካሪ  ነበራችሁ፡፡ በዋነኛነት የአንድነትና የሰማያዊ ፓርቲዎች ልዩነት ምን ይመስል ነበር?

ኢ/ር ይልቃል፡- ቅድም እንደተናገርኩት በዝርዝር የፖሊሲ ጉዳዮችና በልዩነቶች ላይ ባልገባም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነት ከፖሊሲና ከፕሮግራም ባሻገር የመሪዎቹ የመሰጠት ደረጃና ትግሉን እንዴት ይረዱታል የሚለው አንድ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ በእኛ አካባቢ የሚደረጉ መብታችንን ለማስጠበቅ ሠልፍ እንጠራለን፡፡ ማሳወቅ እንጂ ማስፈቀድ የለብንም እንላለን፡፡ እነዚህን ነገሮች ለማድረግ የሚያስከፍለውን ዋጋ እንከፍላለን፡፡ በአንዳንዶቹ እነዚህ ነገሮች እንደ ጀብደኝነት፣ ብልኃት እንደ መጉደልና እንደ ስሜታዊነት ተደርጎ የሚታይበት ሁኔታ ነበር፡፡ ከዚያ ግን በዋናነት እኔን ጨምሮ ከአንድነት ስንወጣ የነበረን ነገር አንድነት ወደ መድረክ ሲገባ ወደ ግራ ርዕዮተ ዓለም ማዘንበልና በቅንጅት ጊዜ የነበሩትን መሠረታዊ ሐሳቦችና እምነቶች የመሸርሸር አዝማሚያ ነበራቸው፡፡ አንድነትን ደግሞ እኛ ስንመሠርት የነበረን ሐሳብ አንድነት የቅንጅት ወራሽ ነው የሚል መንፈስ ነበረው፡፡ እዚያ ላይ መጠነኛ ልዩነት ነበር፡፡ በአጠቃላይ ግን ይኼ በፖለቲካ አመለካከት ትልቅ ልዩነት ነው፡፡ ዲሞክራቶች የወጡት ከሪፐብሊካን ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ እኛ የያዝናቸው ሐሳቦችና እምነቶች፣ ለኢትዮጵያ ያለን ዕይታ በዚህ መንገድ ነበር፡፡ በታክቲክ ደረጃ ሕዝቡን ቶሎ ለማግኘት የሚደረገው ነገር መሠረታዊ እምነቶችንና ሐሳቦችን ስለሚያሳጣ ብለንን በነበረን አቋም የቀረን ሰዎች እንደዚያ ሆነናል፡፡ ከዝርዝር የፖሊሲ ሰነድ ይልቅ ብዙ አባልና ኃይል ማሰባሰቡ ብዙ ጥቅም አለው በሚል ያንን ድጋፍ አድርጎ ነበር ወደ መድረክ የሚደረገው ሒደት፡፡ ለውጡንም ያፋጥነዋል፡፡ እነዚያም እኛም ስንቀላቀል ትልቅ ነገር እናመጣለን ከሚል መንፈስ ነበር፡፡ እንደምታየው እሱ ከዳር አልደረሰም፡፡ አንድነትም ከመድረክ ወጣ፡፡ መድረክና አንድነትም የነበራቸው ግንኙነት በተሳካ ሁኔታ አልሄደም፡፡ እንዲያውም በፉክክርና በፍትጊያ የተሞላ ነበር፡፡ በመቻቻልና በትዕግሥት እንጂ የተዋጣና የተሳለጠ አንድነታቸው እየበዛ አልሄደም፡፡ ስለዚህ በእኔ እምነት እኛ የያዝነው ሐሳብ ትክክል ነበር፡፡ ብዙዎቹ እዚያ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ስህተት እንደነበረ፣ ያ ነገር ብዙ ርቀት እንዳልሄደና በምኞት፣ በተስፋ፣ በወረቀትና በቀናነት ያየነው እንጂ፣ በአፈጻጸም የአመለካከት ርቀት ያላቸውን የፖለቲካ ኃይሎች አንድ ላይ አሰባስቦ በተግባር መሄድ ከባድ እንደሆነም ተገንዝበዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በቀደም መግለጫ ሲሰጡ ምርጫ ቦርድና ኢሕአዴግ ይኼን ውሳኔ መወሰናቸው ለበጐ ነው ብለው ነበር፡፡ ምክንያቱም ሁለታችንን አዋሀዱን በማለት ተናግረው ነበር፡፡ እርስዎ ደግሞ ከአንድነት ነው መጀመርያ የወጡት፡፡ አንድነት ወደ መድረክ ያደረገውን ጉዞ በመቃወም ከአንድነት ወጥተው ይኼን ፓርቲ አቋቁመዋል፡፡ አሁን ኢሕአዴግ ወይም ምርጫ ቦርድ ይኼንን ያደረገው ለበጐ ነው መዋሀዱን አፋጠነልን ሲሉ፣ መጀመርያ ከነበረው የአንድነት የቅንጅት ወራሽነት መንፈስ ጋር በተገናኘ ነው? በተፈጠሩት ፖለቲካዊ ውጣ ውረዶች ብዙ ውህደቶች ከሽፈው ቆይተው ነበርና እስኪ አብራሩልኝ?

ኢ/ር ይልቃል፡- አሁን እዳልከኝ ሁለቱም ይሆናል፡፡ ሁለቱም ተመጋጋቢ ነው፡፡  በምርጫ ቦርድና በኢሕአዴግ በመኢአድና በአንድነት ላይ የተደረገው በሰማያዊ ፓርቲ ሄደውበታል፡፡ ያኔ ሲያደርጉ እንደሚመስለኝ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቋማትን እያጣጣሉ ስለሆነ እኛ ጨከን ብለን እላያችን ላይ እየወጡ ስለሆነ ቆንጠጥ ማድረግ አለብን የሚል፣ አጠቃላይ አቋም በኢሕአዴግ ተወስዷል፡፡ በምርጫ ቦርድም የተፈጸመ ይመስለኛል፡፡ ለዚያ ነው በአንድ ጊዜ መኢአድም አንድነትም ዘመቻ ተደረገባቸው፡፡ በዚያን ሰሞን በመድረክ ላይም ማስጠንቀቂያ ተጽፏል፡፡ አንድ መግለጫ አውጥቶ ትክክል አይደለም እንዴት እንደዚህ ታደርጋላችሁ ተብሎ የታዛቢዎች ምርጫ ይደገም ወይም የምርጫ አስፈጻሚዎች ምርጫ ይደገም ብሎ፣ በሱ ላይም ሆነ በሰማያዊ ላይ ነገር ፈልጐና ይኼን ጻፍ ተብሎ በዚያ ደረጃ አቋም ተወስዶ ነው፡፡ ያ ነገር በሁላችንም በአጠቃላይ ተቃዋሚዎች የተከፋፈሉ፣ አቅመ ቢስና እርስ በርሳቸው የማይግባቡ ተብሎ ተራ ፕሮፓጋንዳ ነዝቶ ሕዝቡ ሳይወድም ቢሆን ከኢሕአዴግ ጋር እንዲቆይ የማድረግ ፖሊሲ ነበር፡፡ ይኼኛው ያንንም ፖሊሲ ያከሽፋል፡፡ ወዲያው የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ ተቃዋሚዎች በአገዛዙ ከሚደርስባቸው ጫና ባሻገር፣ በአስቸጋሪም ሁኔታ ቢሆን ተመልሰው አብረው ለመሥራት ይችላሉ የሚለው በጊዜያዊነት የተሰነዘረብንን ማጥቃትና ፕሮፓጋንዳ ያከሽፋል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ በጥቃቅን ልዩነቶች፣ በአፈጻጸም ምኞትና ከፕሮግራም ባለፈ በነበረን ነገር ረዥም ጊዜ ተለያይተናል፡፡ እንዳልኩት አንድነትና መድረክ አብረው ነበራ፡፡ አሁን ግን ተለይተው የራሳቸውን ሥራ ጀምረዋል፡፡ ያ ማለት አንድነት ከሰማያዊ ልጆች ጋር ብዙም የሚያለያየው ነገር አይኖርም ማለት ነው፡፡ ያንን ነገር ግን በሒደት እናድርገው ቢባል ማን ሊቀመንበር ይሁን? ስሙ ሰማያዊ ይሁን ወይስ አንድነት? ከዚያ ስንት ሰው ከዚህ ስንት ሰው ከዚያ ይምጣ? የትኛው ጠንካራ ነው? እየተባለ በእኛ በኢትዮጵያውያን ባህል ትናንሽ ልዩነቶች ጊዜ ይፈልጉ ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን የአንድነትን ስም ለሌላ ሲሰጡ እኛም በፍቅር የምንፈልጋቸው ስለሆኑ፣ እነሱም በፍቅር የሚፈልጉን በመሆናቸው አጥሩን በፍጥነት ፈረሰልን፡፡ ሕዝቡ የሚወደው ነገር በፍጥነት ተፈጸመ፡፡ ሁለቱም ይመጋገባል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ግለሰብ የሰማያዊ ፓርቲ አባል መሆን ሲፈልግ የሚያልፍባቸው ደረጃዎች አሉ፡፡ እነዚህ ደረጃዎች ከአንድነት ለሚመጡ ግለሰቦች እንደማይሠሩ በቀደም ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም እንደመጡ ሙሉ በሙሉ አባል ይሆናሉ፡፡ አንድ ሰው ግን የሰማያዊ ፓርቲን ለመቀላቀል ሲመጣ የሚያልፍባቸው ደረጃዎች ምን ይመስላሉ?

ኢ/ር ይልቃል፡- መብቱ ለእከሌ የሚባል ልዩነት የለውም፡፡ በመሠረቱ የሰማያዊ አባል ለመሆን ከ18 ዓመት በላይ መሆን፣ የአዕምሮ በሽተኛ አለመሆን፣ በሕግ መብቱ ያልተገደበ መሆንና አንድ ጊዜ የሁለት ፓርቲ አባል መሆን አይቻልም፡፡ የሚሉትን ካከበረ ማንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሰማያዊን ሐሳቦችና ፕሮግራም እስካመነ ድረስ አባል የመሆን መብት አለው፡፡ ያንን ሲያደርግ ግን በዕጩ አባልነት የሚቆይበት የስድስት ሳምንታት ጊዜ አለ፡፡ የዕጩዎች ጊዜ ስለፓርቲው ፕሮግራምና ዓላማ እንዲያውቅ ምናልባትም በእኛ አገር ትግል ውስጥ ሰርጎ ገብነትና አፍራሽነት ስላለ ያንን ነገር በሒደት የምንከታተልበት፣ እንዲሁም ስለፓርቲው እንዲያውቅ ሥልጠና የሚሰጥበት  ነው፡፡ ስድስት ሳምንት ሲሞላው ሁለት አመራሮች ይፈርሙለትና ሙሉ አባል ይሆናል፡፡ ሌላው ደግሞ አባሉን ወደ ሙሉ አባልነት ማምጣት ለፓርቲው ጠቃሚ ነው ተብሎ ሲታመን፣ ሥራ አስፈጻሚው ወስኖ ሙሉ አባል ሊያደርገው ይችላል ይላል ደንባችን፡፡ እንደምታውቀው የአንድነት አባላት በቆራጥነት በትግሉ የቆዩና በዚህ ደረጃ የሚጠረጠሩ የተለየ ሥልጠና የማያስፈልጋቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ለእነዚህ ሰዎች የስድስት ሳምንታት ጊዜ ሳያስፈልጋቸው በሥራ አስፈጻሚው ውሳኔ መሠረት እንዲሆኑ  ወስነናል፡፡ ሁለቱም አሠራሮች ያሉ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህን በሚመለከት ደንባችሁ ላይ የተጻፈ አለ?

ኢ/ር ይልቃል፡- በደንብ የተጻፈ አለ፡፡ የአባላት አመላመል ዘዴ ስድስት ሳምንታት በዕጩነት የሚኬድበት አንዱ ዘዴ ነው፡፡ ከዚያ ደግሞ ሥራ አስፈጻሚው ያ ሰው ስድስት ሳምንት ሳያስፈልገው ለሙሉ አባል በቂ ነው ብሎ ካመነ በሥራ አስፈጻሚው ውሳኔ ይሆናል ተብሎ በግልጽ የተጻፉ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ከአንድነት መጥተው ፓርቲውን የተቀላቀሉ ሰዎች አሉ፡፡ እንዳሉት በትግል ላይ የቆዩ ስለሆኑ የስድስት ሳምንት ሒደት ማለፍ አልተጠበቀባቸውም፡፡ ባለፈው መግለጫ ላይ ጠቅሰውት ነበር፡፡ ባላቸው ችሎታና ዕውቀት ፓርቲውን ያገለግላሉ ብለዋል፡፡ አሁን የዕጩዎች ምዝገባ ባለፈው ረቡዕ ያልቅ የነበረው በአንድ ሳምንት ተራዝሟል፡፡ እስካሁን ከአንድነት ከመጡት ምን ያህሉ ሰማያዊ ፓርቲን ለመወከል ተመዝግበዋል?

ኢ/ር ይልቃል፡- እውነቱን ለመናገር መረጃው የለኝም፡፡ ዛሬ ስትጠይቀኝ  [ጥር 28 ቀን 2007 ዓ.ም.] አጭር ጊዜ ስለሆነ፡፡ ግን በክፍለ አገር ባሉ መዋቅሮቻችን ሁሉ ብዙ ሰዎች ተወዳድረዋል፡፡ ቁጥሩ ይኼ ነው ብዬ ባልነግርህም 23 የአዲስ አበባ ምክር ቤት መቀመጫዎች አሉ፡፡ በዚያ ውስጥ እኛ ያቀረብናቸው ዕጩዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ነገሮች ምዝገባውንም አዘግይተውት ነበር፡፡ እነዚህን ነገሮች ለማየት ብለን፡፡ በዚያ ውስጥ እኛ ካቀረብናቸው ዕጩዎች የተሻለ ሰማያዊን ሊወክሉና ጥሩ ውጤት ሊያመጡልን የሚችሉ እነሱ አቅደዋቸው የነበሩ ሰዎች ካሉ፣ ያለምንም ጥርጥር የእገሌ የእገሌ ሳንላቸው አሁን አንድ ፓርቲ ሆነናልና የሰማያዊ በዛ የአንድነት በዛ የምንልበት አይደለም፡፡ ፓርቲያችን አንድ ነው፡፡ ዋናው ነገር የሚወክለው ሰው የሰማያዊን ዓላማ ይዞ በሕዝብ ፊት መልካም ስምና ዝና ያለው፣ የትምህርት ዝግጅት ያለውና መልካም ባህሪ ያለው ከሆነ እዚያ ያሉትን ሁሉ የምናሳትፍበት ዕድል አለ፡፡ ያ ደግሞ በቀናትና በጥሩ የሚታይ ነው፡፡ ማነው የበለጠ ውጤታማ የሚሆን በማለት በብዙ ቦታዎች እንዲወዳደሩ ክፍተቱ አለ፡፡ እየሠራንበትም ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ከሬዲዮ ፋና ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ነበር፡፡ ሪከርድ አልተደረገም በሚል ምክንያት ባለመቅረቡ መረጃውን በማኅበራዊ ድረ ገጽና በሌላ መንገድ ተገኝቷል፡፡ ከሬዲዮ ፋና ጋር የተፈጠረው ምንድነው?

ኢ/ር ይልቃል፡- በቆየ ፖሊሲ ምክንያት ነው፡፡ በእኛ እምነት ኢሕአዴግ የሕዝብ ተቀባይነት አጥቷል፡፡ ያለበትም ችግር ብዙ ነው፡፡ የሠራቸውን ሥራዎች ይዞ ወደ ሕዝብ በመቅረብ የሕዝቡን ፍላጎት ማሟላትና መመረጥ እንደማይችል አውቋል፡፡ የያዘው ፖለሲ ምንድን ነው? ተቃዋሚዎች አይረቡም የተከፋፈሉ ናቸው ብሎ ሕዝብን ተስፋ አስቆርጦ፣ እየመረረውም ቢሆን ሕዝቡ በኢሕአዴግ ጉያ ውስጥ እንዲቆይ ማድረግ ነው፡፡ በዚያ ፖሊሲ መሠረት በአንድነትና በመኢአድ ላይ የተሠራው ይታወቃል፡፡ በሬዲዮ ፋና አቀነባባሪነት ቪዲዮዎች ተቀርፀው ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አሳልፎ በመስጠት፣ በእነዚህ ፓርቲዎች ላይ ተከታታይ ውርጅብኝ እየተሠራ ተቃዋሚዎች አይረቡም የሚል መልዕክት ሲተላለፍ ቆይቷል፡፡ እነዚያን እንግዲህ አሸንፈናል፡፡ አሁን የቀረው ሰማያዊ ነው በሚል ሬዲዮ ፋና ወደ እኛ መጣ ማለት ነው፡፡ ወደ እኛ ደወሉ፡፡ ስቱዲዮ ነው ቀረፃው የሚደረገው፡፡ ቪዲዮ ካሜራ ጭምር አለ፡፡ የፋና ስቱዲዮ በጣም ትልቅ የሚዲያ ተቋም ነው፡፡ ከሕንፃው ጀምሮ ባለሙያዎችም መሣሪያዎችም የረቀቁ ናቸው፡፡ በዚያ መሠረት እነዚህን የሰማያዊ ጎረምሶች ልካቸውን አሳይልኝና ተቃዋሚን አጥፉ ተብሎ ተልዕኮ ነው የሚመስለው ነገሩ፡፡ ስለዚህ የቪዲዮ እናንሳህ ሲሉኝ ያኔ ሐዘን ላይ ነበርኩ፡፡ ታላቅ ወንድሜ አርፎ አለባበሴም፣ ፂሜም አድጎ ስለነበር ቪዲዮ እንደማልፈቅድላቸው፣ ነገር ግን በድምፅ ብቻ እንድቀረፅ እንደመጣሁ ስነግራቸው ያዘጋጁትን የቪዲዮ መቅረጫ ይዘው ወጡ፡፡ ከዚያ በኋላ እኔም ሪከርድ መያዝ አለብኝ ብዬ የራሴን በሞባይል ሪከርድ አደረኩ፡፡ በኋላ እንደምሰማው የተቀረፁት ነገሮች ሲታዩ ባለሥልጣናት ሥራ የሚሠሩ ስላልሆኑ ያ ቀረፃ ሲደረግ በኢርፎን ስቱዲዮ የሚያዳምጥ አለ፡፡ እኛ የምንነጋገረው ውስጥ ማይክ አለ፣ ማንም ግን የለም፡፡ ድምፃችንን እየሰማን ነው እስከ መጨረሻው የተቀረፀው፡፡ ስወጣ የሸኘኝ እንዲያውም ቴክኒሽያኑ ነበር፡፡ የዛሬው ቀረፃ ጥሩ ነበር፡፡ የባለፈው የአንድነት ስሜት በዝቶባቸው ነበር ብሎኝ ነበር፡፡ ተራ ጭቅጭቆችም ነበሩ፡፡ የእናተን ግን በጥሩ ሁኔታ አይቸዋለሁ ብሎ ነው የወጣሁት፡፡ ሁለት ሰዓት ተቀርፆ እሑድ ሊተላለፍ ቅዳሜ አቶ ብሩክ ደውሎ ተበላሽቶብኛል መተላለፍ አይችልም አለኝ፡፡ እኔ የቀረፅኩት አለ ልስጥህ አልኩት፡፡ በሚክሰር ካልሆነ አይቻልም አያገለግልም አለኝ፡፡ ይኼንን የበለጠ ያጠናከረልኝ እንደዚሁ ተመሳሳይ ሁኔታ ይዘው ከኢቢሲ የመጡ አንድ ሰዓት ተኩል ያህል ከሕዝብ ግንኙነት ኃላፊያችን አቶ ዮናታን ተስፋዬ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ እሱም እኔን እንደጠየቁን አሳሳች ናችሁ፣ አመፀኞች ናችሁ፣ አብዮት ቀስቃሽ ናችሁ፣ ዘጠኝ ፓርቲ በጋራ የሆናችሁት ሕዝብ ለማነቃነቅና ምርጫውን ለማተራመስ እንጂ ለሌላ አይደለም የሚሉ ተመሳሳይ ጥያቄዎች ቀርበውበታል፡፡ የታሰበውን ነገር አላመጣም፡፡ ያም ኢንተርቪው አልተላለፈም፡፡ ያሰቡት ነገር ሰማያዊ እውነተኛ ለሕዝብ አማራጭ ፓርቲ ሆኖ ሊታይባቸው ስለሆነ፣ በዚያ ምክንያት ቀሩ ማለት ነው፡፡ ከእኔ ጋር የነበረውን ለተለያየ ሚዲያ አውለነዋል፡፡ ከዮናታን ጋር የነበረውን እነሱን ስለማናምን ባክአፕ አስቀርተናል፡፡ ይህም ይለቀቃል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አቶ ብሩክ ባለፈው እሑድ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን ባቀረቡበት ወቅት የፕሮግራሙ መግቢያው ላይም አሁንም እርስዎን እየጠበቁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዝርዝር ባይገለጽም በቴክኒክ ችግር ምክንያት ሪከርድ የተደረገው ባለመገኘቱ መጥተው መወያየት ከፈለጉ በሩ ክፍት ነው ብለዋል፡፡ ደግመው የመሄድ ዕቅድ አለዎት?

ኢ/ር ይልቃል፡- ከጠሩኝ አዎ፡፡

ሪፖርተር፡- ደውለን ቴክስት አድርገን አይመልሱም ብለዋል ሬዲዮ ላይ፡፡ እርስዎ እንደሚሉኝ ከሆነ ነጥቦቹን እንደገና በትክክል ማስረዳት የሚችሉ ከሆነ ሄደው ይወያያሉ?

ኢ/ር ይልቃል፡- አሁንም እሄዳለሁ፡፡ ነገር ግን ለባክአፕ እኔም ድምፅ መቅረጫ እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ፡፡ መጀመርያም የሄድኩት ለዚያ ነው፡፡ እኔ አስተላልፍልኝ ብየው እንቢ አለ እንጂ አልሄድም አላልኩም እስካሁን ድረስ፡፡ እኔም በእጄ የያዝኩት አለኝ፡፡ አንተም የቀረፅከው ፋና የረቀቀ መቅረጫ ያለው እየሰማንና እያየን የሆነ ነገር እንዴት ሊጠፋ ይችላል? ያንተ ከጠፋ ደግሞ ኢቢሲ እንዴት አስቀረው? ከዚህ በፊት በፓርቲዎች የተሠራ ሥራን ፋና ቀርፆ በፊልም አድርጎ ለቲቪ እንደሰጠ ዓይተናል፡፡ እኔንም በቴሌቪዥን ሊቀርፁኝ አዘጋጅተው ነበር፡፡ ባለመስማማቴ ነው እንጂ፡፡ ይኼን ሁሉ መራቀቅ እንደ ፖለቲከኛ ሳየው ያ እንዳልጠቀመው ሲያውቅና እንደገና ሳንሱር አድርጎ ለመቀጣጠል ነው፡፡ እኔ ኮፒውን ይዤበታለሁ፡፡ አበላሽቶ ቆርጦ ቀጥሎ ቢሠራ የኔ ስላለ ያለው አማራጭ ሁሉንም ማጥፋት ነበር፡፡ ያ ከሆነ ደግሞ ተቆራርጦ ሲቀርብ ምን እንደሚመስል ሕዝቡም እንዲያውቅ ከጠራኝ ደስተኛ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ የሚመሩት የዘጠኝ ፓርቲዎች ትብብር አለ፡፡ ትብብሩ እስካሁን  ከምርጫ ቦርድ ጋር እስጥ አገባ ውስጥ አለ፡፡ ዕውቅና የለውም ሕጋዊ አይደለም በሚል፡፡ እሱ እንዳለ ሆኖ ትብብሩ አሁን ምን እየሠራ ነው? የኅዳር ወር ፕሮግራሙን ይፋ ስታደርጉ ተገኝቼ ነበር፡፡ አብዮት አደባባይ ሠልፍ ተጠርቶ የተፈጠረው ቀውስ ይታወሳል፡፡ የታኅሳስም ዕቅድ ተይዞ ነበር፡፡ አሁን ጥር እያለቀ ነው፡፡ ዕቅዶቹ ምን ያህል ተሳክተዋል?

ኢ/ር ይልቃል፡- በዋነኛነት የያዝነው ሕዝቡ ለፍትሕና ለነፃነት የምርጫ መብቱ ተጠብቆ በሕገ መንግሥቱ የሥልጣን ትስስር እንዲኖር፣ በኢሕአዴግ በኩል ያሉት አፈናዎችና ማነቆዎች ይስተካከሉ የሚል ነው መሠረታዊ ሐሳቡ፡፡ በዚያ ሒደት ውስጥ ግን የማነቆውን ትክክለኛነት የሚያሳዩ ነገሮች በእኛ ላይ በተደጋጋሚ የሚደርሱብን በደሎችና ስቃዮች አሉ፡፡ አሁንም ቢሆን የካቲት 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በ15 የኢትዮጵያ ዋና ዋና ከተሞች ይህንኑ በተመለከተ ሰላማዊ ሠልፍ ጠርተናል፡፡ ለዚያ የሚያስፈልገውን የሥራ እንቅስቃሴ መግለጫ እንሰጣለን፡፡ አሁን በተገኘው የሰው ኃይል በየአካባቢውም ለማድረግ የበለጠ መነቃቃትና ኃይል ከሕዝቡ ስላገኘን በ15 ከተሞች በተመሳሳይ ቦታና ሰዓት ሠልፍ ለማድረግ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ኮሚቴዎች ተዋቅረዋል፡፡ መሀል ላይ ግን በረድ ያልንበት ጊዜ ነበር፡፡ ዕጩዎች በማስመዝገብ ሒደት የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር በጣም ሰፊ ነው፡፡ የተራራቀ ነው፡፡ ግንኙነታችንም ደካማ ነው፡፡ ሰው መሰጨራትና መሠራት ነበረበት፡፡ አሁን እዚህ የነበሩት የሰማያዊ አባላት በክፍለ አገር ሥራ ላይ ነበሩ፡፡ ሁሉም ፓርቲዎች ያንን እየሠሩ ስለነበር አስቸኳይና አጣዳፊ ውሳኔ ነበር በዚያ ላይ ለማተኮር፡፡ ላለፉት 20 ቀናት ያህል ወደዚህኛው ወቅታዊ ሥራ በመግባታችን ወደ ሥራው መመለሳችንን የሚያሳይና የሚያነቃቃ መግለጫ ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዘጠኙ ፓርቲዎች አንዱ መኢአድ ነው፡፡ መኢአድ ደግሞ በምርጫ ቦርድ የተወሰነበት ውሳኔ አለ፡፡ የአቶ ማሙሸት ቡድን ሕጋዊ አይደለም ተብሎ የአቶ አበባው መሐሪ ቡድን ገብቷል፡፡ ትብብር ውስጥ ያለው መኢአድ የትኛው ነው?

ኢ/ር ይልቃል፡- ትብብር ውስጥ ያለው መኢአድ መጀመርያ ማኅተሙንና ሰርተፊኬቱን ይዞ የነበረው ነው፡፡ እኛ ከተቋሙ ጋር ነበር ግንኙነት እናደርግ የነበረው ከግለሰቦቹ ጋር አልነበረም፡፡ የመኢአድን ቢሮ የያዘውና ማኅተሙን የተቆጣጠረው አመራር በምርጫ ቦርድ በተለያየ ጊዜ የሚጠራው የአቶ አበባው ቡድን ነው፡፡ ሕጋዊ ሆኖ ይንቀሳቀስና ከአንድነትም ጋር ለመዋሀድ እንቅስቃሴ ባደረገበት ጊዜ አመራር ይዞ፣ ምርጫ ቦርድም እየጠራው፣ በተለያዩ ስብሰባዎች እየተሳተፈ፣ ማኅተም አድርጎ ጉባዔ እየጠራ የነበረ ቡድን ነው፡፡ ፓርቲውም ሕጋዊ ስለሆነ በአመራር ጉዳይ ላይ ነው ጥያቄዎች የሚመጡት እንጂ፣ ከዚያ ያለፈ መዋቅራዊ ግንኙነት ስለሌለ በአመራር ምርጫችሁ ላይ ይህን አድርጉ የሚል ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ እንደተባለው ሥራውን በፍጥነት ለመሥራትና ያላቸውን ኃይል ለማሰባሰብ ውስንነት ፈጥሮብናል፡፡ አንዱ በሌላው ሲተካ ሕዝቡም በእነሱ ላይ ያለው እምነት እየተሸረሸረ ሲሄድ ችግር ፈጥሯል፡፡ ያሉትን ችግሮች ፈትቶ ሕጋዊ ከሆነው አካል ጋር ለመሥራት ዝግጁ ነን፡፡ ትንሽ ችግር ፈጥሮብናል ቢሆንም የተቻለውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በፊትም የነበረው የአቶ አበባው ነው፡፡ አሁንም ያለው የአቶ አበባው ነው፡፡ ዕውቅና ያለው መኢአድ ይህ ነው ማለት ነው?

ኢ/ር ይልቃል፡- አዎ፡፡ ነገር ግን ምርጫ ቦርድ ከወሰነ በኋላ ምንም ዓይነት ግንኙነት  አላደረግንም፡፡ እነሱም ጊዜ ኖሯቸው ተጠናክረው አመራሮቻቸውን አላኩም፡፡ እርስ በርሳቸውም የሚወነጃጀሉበት ነገር አለ፡፡ በሚዲያ የተፈጠረ ፕሮፓጋንዳ አለ፡፡ ያንን ለማጥራት እነሱ የውስጥ ሥራዎችና ችግሮች አሉባቸው፡፡ ይወጣሉ ብለን ግን እናምናለን፡፡ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ይጠቅማልና እውነተኛ አመራር ሆኖ ድርጅቱን አጠናክሮ እስከመጣ፣ በጋራ በሚያግባቡን ነገሮች ላይ ለመሥራት አሁንም ክፍት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ትብብሩ ‹‹ነፃነት ለፍትሐዊ ምርጫ›› የሚል መርህ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ያሉት የትብብሩ ፓርቲ አባላት በሙሉ በምርጫው ተዘጋ የሚሉትን በር ለማስከፈት የተለያዩ ጥረቶች እያደረጉ ነበር ተብሏል፡፡ በዚህ መሀል መኢአድ በርካታ የአመራር ውጣ ውረዶች ነበሩበት፡፡ መኢአድ እንደ ትብብሩ አባልነቱ የአመራር ለውጡ በትብብሩ ላይ ምን ዓይነት እንቅፋት ፈጥሯል?

ኢ/ር ይልቃል፡- መከራ የምለው ኃይልን ለማሰባሰብ በደጋፊዎች በኩል ያለው ብዥታ ነው፡፡ በውጭ አገርም በአገር ቤትም ደጋፊዎች አሉ፡፡ ያንን ኃይል ለመጠቀም ችግር ነበረው፡፡ ለምሳሌ ባለፈው የኅዳር 27 እና 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ሠልፍ ወደ 100 የሚጠጉ አባላት ሲታሠሩ ብዙዎቹ የሰማያዊ አባላት ናቸው፡፡ ያ ማለት አምስት ስድስት የሚሆኑ የመኢአድ አባላት ናቸው የታሠሩት፡፡ መኢአድ ባለው የአመራር ክፍተት ምክንያት ሙሉ አቅሙን ለዚህ ሥራ አላዋለም፡፡ ምናልባት ለዚያ ሥራ የሚወጣው 200 ወይም 250 ሰው መድረስ ነበረበት፡፡ ብዙ ሰው ይታሰር ማለቴ ሳይሆን በሥራው ላይ የሚሳተፈው ሰው ሲበዛ ያንን ለማስቆም ብዙ የመኢአድ አባላትም እዚያ ውስጥ መገኘት ነበረባቸው፡፡ ያ ብዙ እክል ፈጥሮብናል፡፡ ያለ ጥርጥር የአቅም ውስንነት አምጥቷል፡፡ ሙሉ አቅሙን እንዳይጠቀም ከማድረግ አልፎ፡፡

ሪፖርተር፡- ገዥው ፓርቲ ከምርጫ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ነገሮችን ያሳያል፡፡ ለምሳሌ ባቡር ያስመርቃል፡፡ ይኼንን ነው ብትመርጡኝ የማደርገው ሊል ይችላል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በሕዝቡ ለመመረጥ በአማራጭነት ይኼንን አቀርባለሁ ብሎ ለሕዝቡ የሚያሳያቸው መሬት የወረዱ ነገሮች አሉ? መሬት ከወረደ ልማት ጋር የተገናኙ ምን ሥራዎችን ይዞ ነው ሰማያዊ ሕዝብን የሚቀሰቅሰው?

ኢ/ር ይልቃል፡- የመጀመርያው ነገር ኢሕአዴግ የምርጫ ቅስቀሳ ስላልደረሰ ሊሰርቅ ስለሚችል፣ ዝርዝር ጉዳዩን አሁን ላይ ከነገርኩህ የምርጫ ቅስቀሳ አልተጀመረም፡፡ ምክንያቱም ብዙዎች ከምርጫ 97 በኋላ የምንሰማቸው ነገሮች በሙሉ የቅንጅት ፖሊሲዎች ባቡርን ጨምሮ የነበሩ ናቸው፡፡ ለምርጫ ቅስቀሳ ስላላቀረብን ጉዳዩን አሁን ለማውራት ከሥልጣኑ አንፃር ልክ ላይሆን ይችላል፡፡ ለምን ቢባል ኢሕአዴግ ይሉኝታ የሚባል ነገር አያውቅም፡፡ ባያደርገውም ያለጥርጥር ያወራዋል፡፡ ስለዚህ ብትታገሰኝ ደስ ይለኛል፡፡ ያለ ጥርጥር ወጣቶች ሥራ የሚያገኙባቸው ዝርዝር ፖሊሲዎች አሉ፡፡ የአገሪቱ ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚከፋፈልበትን፣ ሥልጣን ወደታች ወርዶ ለሕዝብ ተጠያቂ የሚሆንበትን አመራር መጥቀስ ይቻላል፡፡ አሁን እስከ አንገታችን ያጨማለቀን ሙስና ነው፡፡ ከቀበሌ ጀምሮ ወደ ኢሕአዴግ አንድ ሰው ሲሄድ ተጠቃሚነት እንጂ ማኅበራዊ አገልግሎትና ሕዝብን የመጥቀም አዝማሚያ ጭራሹኑ ጠፍቷል፡፡ በዚያ ሥርዓት ውስጥ ሹማምንት የሕዝብ ጠቃሚ ሳይሆኑ፣ በሕዝብ ላብና ሀብት ተጠቃሚ የሆኑበት ሥርዓት ነው የተፈጠረው፡፡ ይህ ከተገለበጠ ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት ፍትሐዊ በሆነ ሁኔታ ሁሉም በየደረጃው የሚጠቀምበት፣ ሕዝብ ደግሞ ጠያቂ ሆኖ ዓይንና ጆሮ ሆኖ የሚሠራበት ይህንን የሚያጋልጡ ነፃ ሚዲያዎች የሚስፋፉበትን፣ ሰዎች ሁሉ ባሉበት የሥራ ሁኔታ ሁሉ በጥረታቸው፣ በትጋታቸውና በብቃታቸው ሀብት የሚፈጥሩበት ሥርዓት መፈጠር አለበት፡፡ አንድ ሰው በአቋራጭ ሚሊየነር ሆኖ ሌላው ደግሞ በትምህርት ብቃቱ፣ በሥራውና በችሎታው እየተኮረኮመና እየኳተነ የሚኖርባት አገር ነች ያላችው፡፡ ስለዚህ ችሎታ፣ ብቃትና የተከበረ ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎች በእውነቱ የሚያድጉባት ኢትዮጵያ እንድትሆንና በአፈ ጮሌነትና በዘዴ የሚከናወኑ አሠራሮች የሚጠፉበት ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ ይኼ ደግሞ ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት ከሆነ ቀላል ነው፡፡ አሁን ሁሉን የተቆጣጠረ ገዥ ቡድን አለ፡፡ ሰጪና ከልካይ ነው፡፡ ስለዚህ ወደሱ ለመጠጋት እየተሸረቡ መግባት ግዴታ ስለሆነ ነው እንጂ፣ ነፃነትን ካወጅን ማንም በማንም ላይ ጉልበት የለውም፡፡ ተመራጩም ቢሆን የሕዝብ ተጠያቂ ነው፡፡ ሀብታችን ነው ብለው ዜጎች ሁሉ በአካባቢያቸው መጠየቅ ይጀምራሉ፡፡ ያንን ካደረግን ብዙ ሊሻሻሉ የሚችሉ ነገሮች አሉ፡፡ ነፃ ሚዲያ ኖሮ መንግሥት የሚተችበት አሠራር ከተፈጠረ በስርቆት በየአገሩ የሚሸሸውን ገንዘብ፣ ብቃትና ችሎታ ያላቸው ሰዎች አቅማቸው ተወስኖ የሚኖሩበት ማብቃት አለበት፡፡ ያ ማለት ኢትዮጵያ ደሃ አገር ናት፡፡ ሥር የሰደደ ድህነት ስላለ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ የተቋማት ግንባታና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ከአገዛዝ በኋላ ሕዝብ የሚጠብቀው ብዙ ነው፡፡ ያንን ለማድረግ ውስንነቶች እንዳሉ ሆነው፣ ለኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ሥርዓት በመመሥረት ብዙ የምናልፋቸውና የምንቀርፋቸው ችግሮች እንዳሉ እንተማመናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከአንድነት የቀድሞ አመራሮች ከአቶ በላይና ከአቶ ተክሌ ጋር ግንኙነት አድርገው እንደነበር ባለፈው መግለጫ ላይ ገልጸው ነበር፡፡ በዝርዝር ሲያስረዱ ቴክኒካሊ እንጂ ከሞላ ጎደል አጠቃላይ መዋቅሩ ወደዚህ መጥቷል ብለው ነበር፡፡ ከአንድነት የቀድሞ አመራር ጋር የነበራችሁ ውይይትና አሁንስ ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?

ኢ/ር ይልቃል፡- በፊትም የቀረበ ነው፡፡ በላይም የቅርብ ጓደኛዬ ነው፡፡ አጠቃላይ በምርጫው ሒደት እርስ በርስ ሳንወዳደር የምናልፍበት፣ በዘጠኙ ትብብር ውስጥም አንድ ላይ የምንሠራበት ሁኔታና ወደ ውህደት ከሄድን አንድ ላይ እንሥራ እየተባባልን በተለያየ ጊዜ እንነጋገር ነበር፡፡ አሁን ይኼ ችግር በባሰ ሁኔታ ሲመጣ ችግሩ ሊያመጣቸው የሚችላትውን አማራጮች የአንድነት አመራሮች በተደጋጋሚ ያዩ ነበር፡፡ ሌላ ፓርቲ ለማቋቋም የፖለቲካ ምኅዳሩ ለመድበለ ፓርቲ ስለማይሠራ ጥለን ወደየቤታችን መሄድ፣ ሌሎች ፓርቲዎች ዘንድ መግባት፣ ሌሎች ፓርቲዎች ዘንድ ከገባን ተበታትነን ነው ወይም ሳተበተን፣ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚጠቅም ታሪካዊ ውሳኔ ወስነን የተሠራ ኃይል ደግፈን ነው በሚል በቤታቸው ሲወያዩ ነበር፡፡ በኋላ ቁጭ ማለት መፍትሔ እንደሌለው ይታወቃል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ሌላ በአመለካከት የሚቀርብ ፓርቲ ማግኘትም እንደሚታወቀው ነው፡፡ ከእኛ ጋር የተጀመሩ ነገሮችም ጥሩ ጓደኛሞችም ስለነበርን በዚያ ሒደት ወደዚህ ማጋደሉ ከጊዜ ወደጊዜ እየበዛ መጣ፡፡ አሁን ይኼ ብቻ አይበቃም፡፡ ደንባችን የሚፈቅድልን አሠራር አለ፡፡ የምክር ቤት አባላት በተጓደሉ ጊዜ ጠቅላላ ጉባዔ ሳንጠራ ከአባላት መካከል የማስገባት መብት አለ ፡፡ ስለዚህ ባሉን ክፍት ቦታዎች አንድነት ውስጥ ያለውን ችሎታ ሁሉ ለአመራር የማምጣት ነገር በአጣዳፊና በቅርብ የምንሠራው ነገር ነው፡፡ ያንን እነሱ እንደ ድርድር ጠይቀው ሳይሆን ድርጅታችንን ለማጠናከርና አሳታፊም ለመሆን፣ በራስ መተማመን ለማምጣትና የሰው ኃይልም ስለሚያስፈልገን እነዚያን ነገሮች በቀናነት እናደርጋቸዋለን፡፡ በችኮላ ለታክቲክ እነሱ ቅር እንዳይላቸው ለማድረግ አይደለም፡፡ እኛ ራሳችን እንዲኖሩ እንፈልጋለን፡፡ እዚህ ሥራ አለ፡፡ የእነሱ ኃላፊነትና ችሎታ ያስፈልጋል፣ ይመጣሉ፡፡ በምክር ቤታችንም በሥራ አስፈጻሚም በቀናነት ስለሆነ ይህንን ለማስፈጸም በጉጉት ነው ያለነው፡፡

 

 

 

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...