ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በአገሪቱ በሚገኙ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ላይ ቅኝት ሊያደርግ ነው፡፡ ኤጀንሲው በመላ አገሪቱ ባሉት 25 ቅርንጫፎች አማካይነት ከሚቀጥለው ወር በኋላ ቅኝቱን እንደሚያካሂድ ታውቋል፡፡
ቅኝቱ ትኩረት የሚያደርገው በአገሮቹ ምን ያህል ኢንዱስትሪዎች በሥራ ላይ ናቸው? የሚያመርቱት ምርት ምን ያህል ነው? የቀጠሩዋቸው ሠራተኞች ብዛት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ያላቸው ድርሻ ምን ያህል ነው? በሚሉት ጉዳዮች ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነትና መረጃ ሥርጭት ዳይሬክተር አቶ ሳፌ ገመዲ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቅኝቱ ኢንዱስትሪዎቹ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ማወቅ ያስችላል፡፡
ኤጀንሲው ይህንን ሥራ በዋናነት ለማከናወን በርካታ ባለሙያዎችን እየቀጠረ መሆኑ ታውቋል፡፡
አቶ ሳፌ እንዳሉት፣ እነዚህ ተቀጣሪዎች ከየካቲት 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ወር ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ በቀጥታ የቅኝት ሥራው ይጀመራል፡፡
ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በየጊዜው ከሚያካሂዳቸው ጥናቶች መካከል የሰብል ትንበያ፣ የግብርና ቆጠራ፣ የተፈጥሮና የዱር እንስሳት ጥናት፣ የአርብቶ አደርና የገጠር ሶሺዮ ኢኮኖሚ ጥናት ይገኙበታል፡፡
እነዚህ ዘርፈ ብዙ ጥናቶች መንግሥት የሚመራበትን ፖሊሲ በማውጣት ሒደት ወሳኝ ድርሻ እንዳላቸው ተመልክቷል፡፡
ኤጀንሲው ከዚህ ጥናቱ ባሻገር ከሦስት ዓመት በኋላ በ2010 ዓ.ም. አራተኛውን የሕዝብና የቤቶች ቆጠራ ለማካሄድ መወሰኑ ታውቋል፡፡
ይህንን ቆጠራ ለማካሄድ የዝግጅት ሥራዎችን እያካሄደ መሆኑን፣ ኤጀንሲው በዘመናዊ የመረጃ አሰባሰብና አደረጃጀት ዘዴዎች እየዘረጋ መሆኑን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡