በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር የሚገኘው ሁዳ ሪል ስቴት በመሀል ፒያሳ መንታ ሕንፃዎች ለመገንባት የያዘውን የዲዛይን ዕቅድ በመሰረዝ፣ አነስተኛ ሕንፃዎችን ለመገንባት ማቀዱ ተሰማ፡፡
ኩባንያው በአራዳ ክፍለ ከተማ፣ ማዘጋጃ ቤት ፊት ለፊት የሚገኘውን 34,500 ካሬ ሜትር ቦታ ላለፉት 18 ዓመታት አጥሮ መያዙ ይታወቃል፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ከ25 እስከ 30 ፎቅ ከፍታ ያላቸውን መንታ ሕንፃዎችን ጨምሮ ሌሎች ባለአራትና ባለስድስት ፎቅ ሕንፃዎች ለመገንባት ዕቅድ ነበረው፡፡
ነገር ግን ከዓመታት ቆይታ በኋላ ሁዳ ሪል ስቴት የመጀመሪያውን ዕቅድ በመሰረዝ፣ ባለአራትና ባለስድስት ፎቅ ከፍታ ያላቸውን ሕንፃዎች ለመገንባት ዲዛይን እያሠራ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ሁዳ ሪል ስቴት የዲዛይን ለውጡን ለምን ማድረግ እንደፈለገ ባይታወቅም፣ ለአራዳ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት የፕላን ስምምነት ጥያቄ ማቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ክፍለ ከተማው በሚሰጠው የፕላን ስምምነት መሠረት ሁዳ ሪል ስቴት ዝርዝር ዲዛይን በማሠራት፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግንባታ ፈቃድ ባለሥልጣን አቅርቦ ማስፀደቅ ይኖርበታል፡፡
የአዲስ አበባ የግንባታ ፈቃድ ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይሉ ወልደ ሥላሴ ለሪፖርተር እንደገጹት፣ ሁዳ ሪል ስቴት ዲዛይን ሠርቶ ለባለሥልጣኑ አላቀረበም፡፡ ኩባንያው ዲዛይኑን ሲያቀርብ ግን በሕጉ መሠረት እንደሚስተናገድ አስረድተዋል፡፡
‹‹ባለሥልጣኑ ለግንባታው ያልፀደቀ ዲዛይን ተግባራዊ እንዳይሆን የማድረግ ኃላፊነት ያለበት ሲሆን፣ ግንባታ ያልተካሄደበትን መሬት ግን የመንጠቅ ኃላፊነት የከተማው መሬት ባንክና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ነው፤›› በማለት አቶ ኃይሉ አስረድተዋል፡፡
ምንጮች እንደገለጹት፣ አዲሱ ዲዛይን ተሠርቶ ከተጠናቀቀና የግንባታ ፈቃድ ባለሥልጣን ዲዛይኑን ካፀደቀው ግንባታው ይጀመራል፡፡ ምንጮች ጨምረው እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ኅብረት ክልል ውስጥ ንብረትነቱ የሚድሮክ የሆነውን ባለአምስት ኮከብ ሆቴል በመገንባት ላይ የሚገኘው ሚድሮክ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ወደ አዲሱ የግንባታ ሳይት ይንቀሳቀሳል፡፡ ነገር ግን ባለፉት 18 ዓመታት አምስት የአዲስ አበባ ከንቲባዎች ቢፈራረቁም፣ ካለበት መንቀሳቀስ ያልቻለው የሚድሮክ ፕሮጀክት ተግባራዊ ይደረጋል የሚል እምነት እንደሌላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለሥልጣናት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በከተማው ውስጥ የግንባታ ጊዜ ያለፈባቸው 140 ቦታዎች ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት አቅርቦ ነበር፡፡ የከንቲባው ጽሕፈት ቤት በተለይ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ለሚወስደው ዕርምጃ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በውሳኔ አሰጣጡ ተሳታፊ እንዲሆን ጠይቋል፡፡
ለውሳኔ ከቀረቡ 11 የሚድሮክ ቦታዎች ውስጥ ሁለቱ እንዲነጠቁ፣ የተቀሩት በልዩ ሁኔታ የግንባታ ጊዜ እንዲጨመርላቸው ተወስኗል፡፡ የግንባታ ጊዜ እንዲጨመርላቸው ከተወሰኑ ቦታዎች ውስጥ ይህ የፒያሳ ፕሮጀክት ይገኝበታል፡፡ ነገር ግን ከተወሰኑ አነስተኛ እንቅስቃሴዎች ውጪ ታጥሮ በተቀመጠው ቦታ ላይ ለውጥ የሚያመጣ ግንባታ ሲካሄድ አልታየም፡፡