Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የማሞ ካቻ ቤተሰቦች ወደ ሆቴል ቢዝነስ መግባት ጀመሩ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አምስት ተጨማሪ ብራንድ ሆቴሎች ይጠበቃሉ

ላለፉት ሰባ አምስት ዓመታት በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ውስጥ በማለፍ ስማቸውን ተክለው ያለፉት የአቶ ማሞ ይንበርበሩ (ማሞ ካቻ) ቤተሰቦች፣ ወደ ሆቴል ንግድ ሥራ በመግባት ሁለት ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ሆቴሎችን ለመገንባት ዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ታወቀ፡፡

በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ይገነባሉ ተብለው ለሚጠበቁት ሆቴሎች የአዋጭነት ጥናትና ዝርዝር የዲዛይን ሥራዎችን እንዲያካሂድ ኮሊር ኢንተርናሽናል የተባለውን ታዋቂ የእንግሊዝ ኩባንያ መቅጠራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የማሞ ካቻ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ይንበርበሩ ማሞ (ዓብይ) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሁለቱም ሆቴሎች ይገነባሉ ተብሎ የሚጠበቀው በውርስ ከአባታቸው በተላለፉ ሁለት ቦታዎች ላይ ነው፡፡

የመጀመሪያው ሆቴል የሚገነባው ማሞ ካቻ እየተባለ የሚጠራውና ከአቶ ማሞ ይንበርበሩ ስያሜውን ያገኘው አካባቢ ላይ በሚገኝ 2,300 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ መሆኑን አቶ ዓብይ አስታውቀዋል፡፡ ከአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት ወረድ ብሎ ገነት ሆቴል አካባቢ ባለው በዚህ ቦታ ላይ ከ4.5 እስከ አምስት ኮከብ ደረጃ ያለው ሆቴል ለመገንባት መታሰቡን ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ በየካ ክፍለ ከተማ በሚገኘው አካባቢ ቡቲክ ሆቴል በሚባለው ደረጃ ከ4.5 እስከ አምስት ኮከብ ደረጃ የሚኖረው ሆቴል ለመገንባት እንደታቀደ አስታውቀዋል፡፡

የሁለቱን ሆቴሎች ግንባታ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱን የገለጹት አቶ ዓብይ፣ ለሆቴሎች ግንባታ የሚወጣውን ወጪ ግምት ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ይኼውም የአዋጭነት ጥናቱም ሆነ የዲዛይን ዝርዝር ጥናቶች ገና ያልተጠናቀቁ በመሆናቸው እንደሆነ በመጥቀስ ሲሆን፣ የሆቴሎቹ ግንባታ የሚጠይቀውን ገንዘብ ለማውጣት ግን ቤተሰባቸው ዝግጁ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ውጪ በአሜሪካ ግዙፍ የቢዝነስ ይዞታዎች ያሏቸው የማሞ ካቻ ቤተሰቦች፣ በኢዮብ (ጆ) ማሞ የግል ባለቤትነት የሚተዳደሩ 300 ያህል የነዳጅ ማደያዎች ሲኖሩ፣ በተለይ ካፒታል ፔትሮሊም ግሩፕ የተባለው ኩባንያቸው በዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኙ ማደያዎች ውስጥ 42 በመቶ ድርሻ መያዙን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር በሪል ስቴት ዘርፍና በታክሲ አገልግሎቶችም የማሞ ካቻ ቤተሰቦች ትልቅ ድርሻ እንደያዙ ይታወቃል፡፡

ለማሞ ካቻ ቤተሰብ ወደ ሆቴል ቢዝነስ መምጣት ምክንያት የሆነው አጋጣሚ የተፈጠረው፣ ከአራት ወራት በፊት በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም መሆኑንና በዚህ ወቅትም ኮሊር ኢንተርናሽናል ከተባለው ኩባንያ ጋር በተፈጠረ ግንኙነት መሆኑን አቶ ዓብይ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ዘንድሮም አምስተኛው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም ለሁለተኛ ጊዜ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰኑና ከዘጠኝ ወራት በኋላ እንደሚጀምር በይፋ ተገልጿል፡፡ ከዚህ ቀደም በተካሄደው ፎረም ላይ ስድስት ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ሆቴሎች እንዲገነቡ ስምምነት ሲደረግ፣ ከስምምነቱ ጀርባ የነበረው አገር በቀሉ ካሊብራ ሆስፒታሊቲ ኮንሰልታንሲ ኩባንያ መሆኑ ይታወሳል፡፡ የኩባንያው ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነዋይ ብርሃኑ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በመጪዎቹ ዘጠኝ ወራት ውስጥ ሦስት ተጨማሪ ብራንድ ሆቴሎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲገነቡ ስምምነት ላይ እንደሚደረስ ተናግረዋል፡፡

ይህ በመሆኑም ተጨማሪ አምስት ብራንድ ሆቴሎች ይመጣሉ ተብሎ እንዲጠበቅ አድርጓል፡፡ የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ባለአምስት ኮከብ ማሪዮት ሆቴል በቅርቡ በይፋ ይከፈታል በመባሉም፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚኖሩትን የብራንድ ሆቴሎች ቁጥር አሁን ያሉትን ሦስት ሆቴሎች ጨምሮ ከአሥራ አምስት በላይ ያደርሰዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አቶ ነዋይ ሦስቱ ሆቴሎች እነማን እንደሆኑና ዓለም አቀፍ ብራንዶቹም እነማን መሆናቸውን እንዲገልጹ ቢጠየቁም፣ የሚያማክሯቸው ኩባንያዎች መፍቀድ ስለሚገባቸው የሆቴሎቹንም ሆነ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ማንነት ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

በመጪው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ከ520 ያላነሱ ተሳታፊዎች እንደሚጠበቁ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ ይህንን ፎረም በየዓመቱ በአፍሪካ አገሮች እያዘጋጀ አምስተኛው ላይ ያደረሰው ተቀማጭነቱ እንግሊዝ የሆነው ቤንች ኤቨንትስ የተባለው ኩባንያ ነው፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች