Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊፍትሕ ሚኒስቴር በብሔራዊ ስታዲየም ጨረታ ላይ ስፖርት ኮሚሽን ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠየቀ

ፍትሕ ሚኒስቴር በብሔራዊ ስታዲየም ጨረታ ላይ ስፖርት ኮሚሽን ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠየቀ

ቀን:

ፍትሕ ሚኒስቴር አወዛጋቢ በሆነው የብሔራዊ ስታዲየም ዲዛይንና አማካሪ ድርጅት የተመረጠበት መንገድና ውል ከመፈረሙ በፊት ለፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ ያልተላከበትን ምክንያት እንዲያብራራለት ስፖርት ኮሚሽንን ጠየቀ፡፡

ስፖርት ኮሚሽን በአዲስ አበባ ለሚያስገነባው ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ብሔራዊ ስታዲየም የዲዛይንና የአማካሪ ድርጅት ጨረታ የካቲት 14 ቀን 2004 ዓ.ም. አውጥቶ የነበረ ሲሆን፣ በጨረታው ከተወዳደሩ የአገር ውስጥ ድርጅቶች መካከል ከአንድ እስከ ሦስት የወጡትን ዲዛይኖች ሸልሞ ነበር፡፡

በወጣው ጨረታ መሠረት አንደኛ የወጣው የዲዛይን ባለቤት በቀጥታ የግንባታ ፕሮጀክቱ አማካሪ ሆኖ እንደሚቀጠር ይገልጻል፡፡ ይሁን እንጂ ስፖርት ኮሚሽን አንደኛ የወጣውን ጄዳው አማካሪ አርክቴክቶችና መሐንዲሶች የተባለውን ድርጅት በቀጥታ በአማካሪነት ከመቅጠር ይልቅ፣ ከአንድ እስከ ሦስት የወጡት ድርጅቶች የግንባታ ፕሮጀክቱን በተቆጣጣሪነት ለማማከር በድጋሚ እንዲጫረቱ ማድረጉን ለመረዳት ተችሏል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዚህ ቅር የተሰኘውና አንደኛ የወጣው ጄዳው አርክቴክቶችና መሐንዲሶች ቅሬታውን ለፌዴራል የግዥና የንብረት አወጋገድ ቅሬታ ሰሚ ቦርድ አቅርቦ ቢወስንለትም፣ ውሳኔው ተግባራዊ ሊሆን ባለመቻሉ ጉዳዩን ለፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በ2006 ዓ.ም. የመጀመሪያ ወራቶች አቅርቦ የካቲት 20 ቀን 2006 ዓ.ም. በስፖርት ኮሚሽን ላይ ተወስኖበታል፡፡

ይሁን እንጂ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቅር የተሰኘው ስፖርት ኮሚሽን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በግንቦት ወር 2006 ዓ.ም. ይግባኝ አቅርቦ፣ የፌዴራል መጀመሪያው ደረጃ ፍርድ ቤት የቀረበውን ክስ የመመልከት ሥልጣን የለውም በማለት ያነሳው መከራከሪያ ተቀባይነት ማግኘቱን የፍርድ ቤቱ የውሳኔ ሰነድ ያመለክታል፡፡ ጄዳው አርክቴክቶችና መሃንዲሶች ውሳኔውን በመቃወም ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቢሄድም፣ ፍርድ ቤቱ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ውሳኔ ማፅናቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህ ተስፋ ያልቆረጠው አንደኛ የወጣው ድርጅት ታህሳስ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ጉዳዩን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርቧል፡፡

ሰበር ሰሚ ችሎቱ አቤቱታውን ተቀብሎ ጉዳዩ በቀጠሮ ላይ እንደሚገኝ ባለፈው እሑድ እትማችን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ በዋናው ፍሬ ነገር ላይ ለመወሰን ሳይሆን የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀደም ብሎ ጉዳዩን የተመለከተው በሕጉ መሠረት ሥልጣን ሳይኖረው ነው በሚለው ላይ ለመወሰን መሆኑን የፍርድ ቤቶቹ ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡

ጄዳው አርክቴክቶችና መሐንዲሶች አቤቱታውን ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት ከመውሰዱ ቀናቶች በፊት ማለትም ታኅሳስ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍትሕ ሚኒስቴር ለስፖርት ኮሚሽን በጻፈው ደብዳቤ የዲዛይንና አማካሪ ድርጅት መረጣ የተከናወነበት መንገድ እንዲብራራለት ጠይቋል፡፡

በሚኒስቴሩ የፍትሐ ብሔር ፍትሕ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ አያሌው የተጻፈውና ለፍትሕ ሚኒስትሩ ግልባጭ የተደረገው ደብዳቤ፣ በዲዛይንና አማካሪ ድርጅት መረጣ እስካሁን ድረስ ስላለው የጉዳዩ አካሄድ መግለጫ እንዲቀርብ ይጠይቃል፡፡

‹‹መሥሪያ ቤታችሁ በአዲስ አበባ ለማስገንባት ላቀደው ብሔራዊ ስታዲየም ዲዛይን የሚሠሩ፣ ከዲዛይኑ ሥራ በኋላ የግንባታውን ሥራ የሚቆጣጠርና የውል አስተዳደር ሥራውን የሚያከናውን አማካሪ ድርጅት ለመቅጠር ሲንቀሳቀስ መቆየቱንና አሸናፊ ሆኖ ቀርቦ ከነበረው ጄዳው አርክቴክቶችና መሐንዲሶች ከተባለው ድርጅት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ውሉን ሁለተኛ ለወጣው ድርጅት ለመስጠት ስታደርጉ የነበረውን ጥረት በመቃወም ወደ ፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በመውሰድ እንደተወሰነባችሁ ይታወሳል፤›› በማለት ደብዳቤው ይገልጻል፡፡

ስፖርት ኮሚሽን ጉዳዩን በይግባኝ ወደ ፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት በመውሰድ ውሳኔውን ያሻረ ስለመሆኑ እንደሚያውቅ የሚገልጸው የሚኒስቴሩ ደብዳቤ፣ ኮሚሽኑ ሁለተኛ ከወጣው ድርጅት ጋር ውል ከመፈራረሙ በፊት ውሉ ለፍትሕ ሚኒስቴር ተልኮ መመርመር እንዳለበት ተጠይቆ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

‹‹የጨረታ ሒደቱ የሕዝብንና የመንግሥትን ጥቅም በማይነካ አኳኋን ሒደቱ መመራት እንዳለበት ማረጋገጥ እንዲቻል አስቀድማችሁ እንድታሳውቁን የገለጽንላችሁ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ተቋማችሁ ይህንን ሳያደርግ በጨረታው ሁለተኛ ከወጣው ድርጅት ጋር ሒደቱን መቀጠሉን ለማወቅ ችለናል፤›› ይላል ደብዳቤው፡፡

ሁለተኛ ከወጣው ድርጅት ጋር የቀጠለውን ሒደት በመቃወም አንደኛ የወጣው ድርጅት ለፍትሕ ሚኒስቴር ቅሬታ ያቀረበ በመሆኑ፣ የሒደቱን አጠቃላይ ሁኔታ መመርመር እንዳስፈለገ ደብዳቤው ያስረዳል፡፡

በመሆኑም የስታዲየም ግንባታ ሥራው አጠቃላይ ገጽታ፣ የጨረታው አጠቃላይ ሒደት፣ በጨረታው አሸናፊ ስለነበሩ ድርጅቶች አጠቃላይ መግለጫና አሸናፊ የሆኑባቸው ምክንያቶች፣ እንዲሁም በአሸናፊዎቹ መካከል ስላለው ልዩነት ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

በተጨማሪም ከጨረታው አሸናፊ ጋር ስለተፈጠረው አለመግባባት፣ ቅሬታውን የተስተናገደበት መንገድ፣ በተለያዩ ተቋማት የግዥና የንብረት ማስወገድ ቅሬታ ሰሚ ቦርድን ጨምሮ የተሰጡ ውሳኔዎችና አስተያየቶችን ከመተግበር አንፃር የተደረገው ጥረትና በአጠቃላይ ሁለተኛ የወጣው ድርጅት የተመረጠበት ሒደት፣ ከድርጅቱ ጋር ኮሚሽኑ የፈረመው ውልና በመጨረሻም ስለውሉ ለፍትሕ ሚኒስቴር ኮሚሽኑ ቀደም ብሎ እንዲያሳውቅ በተጠየቀው መሠረት ያላሳወቀበትን ምክንያትና ተያያዥ ጉዳዮች እስከ ታኅሳስ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ በጽሑፍ እንዲያሳውቁ ደብዳቤው ያሳስባል፡፡

በደብዳቤው መሠረት ስፖርት ኮሚሽን የሰጠውን ምላሽ ለማወቅ ሪፖርተር ኮሚሽነር አብዲሳ ያደታን ለማግኘት በግል ስልካቸው ላይም ሆነ በጽሕፈት ቤታቸው በመገኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

ደብዳቤውንና የተሰጠውን ምላሽ በተመለከተ የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት የሥራ ሒደት ዳይሬክተር አቶ ናስር ለገሠ፣ እንዲሁም የስፖርት ፋሲሊቲ ዳይሬክተሩ አቶ ጥበቡ ጐርፉን ቢጠይቅም፣ ስለደብዳቤው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

ደብዳቤውን የጻፉትና ጉዳዩን እየተከታተሉ የሚገኙት የፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሐ ብሔር ፍትሕ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ሙሉጌታ አያሌውን ሪፖርተር አነጋግሮ፣ ስፖርት ኮሚሽን ለሚኒስቴሩ ጥያቄ የሰጠው ምላሽ አለመኖሩን አረጋግጧል፡፡

ኮሚሽኑ ለደብዳቤው ምላሽ ባይሰጥም ፍትሕ ሚኒስቴር ከ500 ሺሕ ብር በላይ የሆኑ የመንግሥት ግዢዎች ከመፈጸማቸው በፊት የማወቅና የመመርመር ሕጋዊ ሥልጣን ስላለው፣ ሕጋዊ አግባብን ተከትሎ የኮሚሽኑ የጨረታ ሒደትን በመመርመር የሕዝብና የመንግሥት ጥቅምን ያስከብራል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ አንደኛ የወጣው ድርጅት ጉዳዩ በሰበር ሰሚ ችሎት እንዲታይለት ጠይቆ በችሎቱ በመያዙና ይህ ሒደት እስኪጠናቀቅ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ዳይሬክተሩ አቶ ሙሉጌታ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ስፖርት ኮሚሽን ውዝግቡ ባልተፈታው የጨረታ ሒደት ሁለተኛ ከወጣው ኤምኤች ኢንጂነሪንግ የተሠራውን የስታዲየም ዲዛይን በመምረጥ የግንባታ ቁጥጥርና የአማካሪነትን ሥራ እንዲሠራ በጥቅምት ወር 2007 ዓ.ም. ተዋውሏል፡፡

በተፈረመው ውል መሠረትም ኤምኤች ኢንጂነሪንግ ላቀረበው የስታዲየም ዲዛይን 24 ሚሊዮን ብር የሚከፈለው መሆኑንና ግንባታው ተጀምሮ ይጠናቀቃል ተብሎ በተገመተው ሁለት ዓመታት ጊዜ ለሚያደርገው ቁጥጥር በወር 640 ሺሕ ብር እንደሚከፈለው ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ በመሆኑም ኤምኤች ኢንጂነሪንግ በዚህ ሥራ በአጠቃላይ 39.3 ሚሊዮን ብር ያገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...