Sunday, April 21, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ምርጫው ከሸፍጥና ከአሉባልታ ይፅዳ!

ምርጫ 2007 እየተቃረበ ነው፡፡ በድምፁ ወሳኙን ዳኝነት የሚሰጠው ሕዝብ ለመምረጥ የሚያስችለውን ምዝገባ በማከናወን ላይ ነው፡፡ ወደ ምርጫ የሚገቡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችስ ምን እያደረጉ ነው? ራሳቸውን ለቅስቀሳ እያዘጋጁ ነው? ወይስ የተለመደው ሽኩቻ ውስጥ ናቸው? መራጩን ሕዝብ ከጐናቸው አሠልፈው ለሰላማዊው የፖለቲካ ትግል ፉክክር ሙሉ ጊዜያቸውን እያዋሉ ነው? ወይስ በውስጥና በውጭ ቅራኔዎች ተወጥረዋል? ምርጫ ዋዜማ ላይ ሆነው ያሉበትን ሁኔታ ካልገመገሙ ችግር አለ፡፡ ከሸፍጥና ከአሉባልታ ካልፀዱ ችግር አለ፡፡

በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ሥልጣን የሚያዘው በምርጫ ብቻ ነው፡፡ የፖለቲካ ትግሉ በውጣ ውረድና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሚካሄድ ቢሆን እንኳ፣ ወሳኙን መራጭ ሕዝብ ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ ካልተደረገ ልፋቱ ሁሉ ከንቱ ይሆናል፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ምርጫውን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲያደርጉት ይጠበቃሉ፡፡ ሁሉም ወገኖች የሚፈለግባቸውን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማከናወን ሲያቅታቸው የሕዝብን አደራ እንደበሉ ይቆጠራሉ፡፡ ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት እንደሆነ በተጨባጭ ሊረጋገጥ የሚችለው፣ እንደሚባለው ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ከሸፍጥና ከአሉባልታ ሲፀዳ ነው፡፡

እንደ ማንኛውም ታዳጊ አገር በኢትዮጵያም የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ሒደት አንድ ዕርምጃ ወደፊት እንዲራመድ ሲፈለግ፣ ሕዝቡን ማዕከል ማድረግ አለበት፡፡ ሕዝብ በንቃት የሚሳተፍበትና መብቱን የሚያስከብርበት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የግድ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የምርጫውና የፖለቲካው ሒደት ተዓማኒነት ሊኖረው ይገባል፡፡ የሕዝቡ ተሳትፎ ሊኖር የግድ ነው ሲባልም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለውና የሕዝብን ይሁንታ ያገኘ ምርጫ እንዲካሄድ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ ሕዝቡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ ተጠብቀው ያለምንም መሸማቀቅ የፈለገውን ፓርቲ እንዲመርጥ መንገዱ መመቻቸት አለበት፡፡

በቅርቡ በሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የተከሰተው ችግር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ እልባት አገኘ ቢባልም፣ በዴሞክራሲው ሒደት ላይ የሚፈጥረው ሳንካ ሊጤን ይገባዋል፡፡ የቦርዱ ውሳኔ አንድን ፓርቲ ሁለት ቦታ ከፍሎታል፡፡ ይህ በምርጫ ዋዜማ ለፓርቲው አባላት ወደ ሌላ ፓርቲ መሰደድን ሲያስከትል፣ የሚፈጥረው ሥነ ልቦናዊ ጉዳትና ግራ መጋባት ለዴሞክራሲው ግንባታ ፈተና መሆኑ አይቀርም፡፡ በሌላ በኩል የውስጥ ችግሮችን በሠለጠነና በዴሞክራሲያዊ አግባብ መፍታት የሚሳነው ፓርቲ አባላቱን፣ ደጋፊዎቹንና መራጩን ሕዝብ ጭምር ጥያቄ እንዲያነሱ ስለሚያደርግ ይህንንም ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ለምርጫ ሽርጉድ በሚባልበት ወቅት እንቅስቃሴን የሚገቱ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ መራጩን ሕዝብ ያሳዝናሉ፡፡ ለሸፍጥና ለአሉባልታ በር ይከፍታሉ፡፡

ገዥው ፓርቲ በተደጋጋሚ ለሕዝብ ቃል እየገባ ነው፡፡ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃና ተዓማኒነት ያለው እንደሚሆን ቃል ገብቷል፡፡ ይህ ለሕዝብ የተገባ ቃል እዚህ ግቡ በማይባሉ ምክንያቶች ቢጣስ ስለሚያሳፍር ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አባላቱም ሆኑ ደጋፊዎቹ ከፀረ ዴሞክራሲ ተግባራት እንዲታቀቡ ማድረግ አለበት፡፡ ለሕዝብ የገባው የአደራ ቃል እንዳይታጠፍ ፅኑ ፍላጎት ካለው የመወዳደሪያ ሜዳው ከእንከን የፀዳ እንዲሆን መሥራት አለበት፡፡ ሥልጣን ላይ ለመቆየት የረጅም ጊዜ ዕቅድ ቢኖረው እንኳ፣ ሥልጣኑ የሚገኘው በሕዝብ ድምፅ ብቻ እንደሆነ ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡ ምርጫ ሕገ መንግሥታዊ መብት በመሆኑ ሁሉም ዜጋ የፈለገውን በነፃነት መርጦ ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ብርሃን እንዲታይባት ኃላፊነቱን መወጣት ግድ ይለዋል፡፡ ‹‹መልካም ስም ከመልካም ሽቶ ይበልጣል›› እንደሚባለው ከሥልጣን በላይ የአገር ህልውና ይቅድም፡፡ ሕዝብ ይከበር፡፡ የሸፍጥና የአሉባልታ በር ይዘጋ፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫ ሲቃረብ ድምፃቸው ከምንጊዜውም በላይ ጎልቶ ይደመጣል፡፡ ይኼ ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን ከአንድ ምርጫ ወደ ሌላ ምርጫ ሽግግር ከተደረገ ከአምስት ዓመታት በኋላ ከ60 በላይ ፓርቲዎች ቀፎው እንደተነቀነቀ ንብ ከየመሸጉበት ወጥተው ግርግር መፍጠራቸው ዴሞክራሲያዊ ሒደትን አያሳይም፡፡ እውነተኛ ዴሞክራሲ በአንድ አገር ላይ የሚያብበው ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት ሲንቀሳቀሱ ብቻ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚያራምዱት አቋም የሕዝብን ቀልብ ለመሳብ ተግተው መሥራት አለባቸው፡፡ የራሳቸውን የቤት ሥራ ሳይሠሩ በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ድክመቶች ላይ ብቻ በማተኮር ለመንቀሳቀስ ሲሞክሩ ሕዝቡ የእናንተስ አማራጭ የታለ ይላል፡፡ ሰብዓዊ መብት ታከብራላችሁ? ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽ መብት ትቆማላችሁ? የፕሬስ ነፃነት ታረጋግጣላችሁ? የመደራጀት መብት ታስከብራላችሁ? የኃይል ማመንጫ ግድቦችን፣ መንገዶችን፣ የባቡር መስመሮችን፣ ዘመናዊ የግብርናና የኢንዱስትሪ ልማቶችን ታስፋፋላችሁ? ትምህርት ቤቶችን፣ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ ሆስፒታሎችን፣ ወዘተ ትገነባላችሁ? የአገሪቱን ሉዓላዊነት ታስከብራላችሁ? የጠራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አላችሁ? የመሳሰሉ  በርካታ ጥያቄዎች ከሕዝብ ይቀርባሉ፡፡ ሕዝብ ሊከበር ይገባዋል፡፡ ሸፍጥና አሉባልታ ለዴሞክራሲ አይጠቅምም፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር ያላችሁን ችግር እንዴት ነው የምትፈቱት? ገዥው ፓርቲስ ተቃዋሚዎችን ለምንድነው ግማሽ መንገድ ሄደህ ለማነጋገር የማትፈልገው? ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገራዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ለምን ከገዥው ፓርቲ አቋማችሁ የተለየ ይሆናል? ገዥው ፓርቲስ ለምን የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተሳትፎ እንዲገደብ ታደርጋለህ? ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ስትሉ በሰጥቶ መቀበል መርህ ለምን ገዥውን ፓርቲ ለማወያየት አትፈልጉም? ገዥው ፓርቲስ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ፋይዳ ቢስ እያደረግክ ለምን ታጣጥላለህ? ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገር ውስጥ እንቅስቃሴያችሁ ችግር ሲገጥማችሁ ሕጋዊውን መንገድ ተከትላችሁ ለምን መብታችሁን ለማስከበር እስከ መጨረሻው አትታገሉም? ገዥው ፓርቲስ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ውስጥ የሚገኙትን ፓርቲዎች ለምን እንዲገፉ ታደርጋለህ? ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወሳኙን የሕዝብ ድጋፍ ቸል ብላችሁ ለምን ዳያስፖራው ላይ ብቻ ትለጠፋላችሁ? ለምን እርስ በርስ ትበላላችሁ? ገዥው ፓርቲስ ለምን የሕዝብ ድጋፍ እንዳያገኙ ታደናቅፋለህ? በርካታ የሕዝብ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች መመለስ አለባቸው፡፡ ሕዝብ ይከበር፡፡ ሕዝብን የማያከብር የፖለቲካ ትግል ውጤት አይኖረውም፡፡ አሉባልታና ሸፍጥ የዴሞክራሲ ፀሮች ናቸው፡፡

ምርጫ 2007 ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሊሆን የሚችለው ከሸፍጥና ከአሉባልታ ሲፀዳ ብቻ ነው፡፡ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሊኖር የሚችለው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሕዝቡን አክብረው ሲንቀሳቀሱ ብቻ ነው፡፡ ለዘመናት ውስጣቸው የተቋጠረውን ቂምና ጥላቻ ይዘው ወደ ምርጫ የሚገቡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ እያንዳንዱን ችግር ለምርጫው እንከንነት ስለሚጠቀሙበት ሕዝቡን ያሳዝኑታል፡፡ በሕዝብ ድምፅ እተማመናለሁ የሚል ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ግን ሕዝብን ብቻ ነው የሚያከብረው፡፡ ሕዝብን እናከብራለን የምትሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳችሁን ለዚህ አዘጋጁ፡፡ ምርጫው ከሸፍጥና ከአሉባልታ ይፅዳ!       

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...

የአገሪቱ ባንኮች የመጭበርበር ተጋላጭነት እየጨመረ መሆኑን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ

በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ2 ቢሊዮን ብር መጭበርበሩን ገልጿል ቀሲስ በላይ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

እንደገና ያገረሸው ግጭት መፍትሔ ይፈለግለት!

ሰሞኑን በራያና አካባቢው እንደገና ያገረሸው ግጭት አስቸኳይ መፍትሔ ካልተሰጠው፣ አድማሱ ሰፍቶ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚደርስ አያጠራጥርም፡፡ በራያ በኩል የተጀመረው ትንኮሳ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተዛምቶ ተጨማሪ...

ስልታዊ መፍትሔን የሚሻው የኪነ ጥበቡ ዘርፍ

የኪነ ጥበቡ ዘርፍ በተለይም ፊልምና ሙዚቃ በውስብስብ ችግሮች ውስጥ እያለፈ ይገኛል፡፡ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ሲስተም በአግባቡ አልተበጁለትም፡፡ ስለሆነም ይህ ችግር ከመሠረቱ እየተፈታና እየተቀረፈ ካልሄደ ከዓመት...

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...