Thursday, September 21, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቻይና ኩባንያዎች አገር በቀል ኮንትራክተሮችን ከመንገድ ጨረታ ውጪ አደረጉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ባወጣቸው ሦስት የመንገድ ፕሮጀክት ጨረታዎች አገር በቀል ኮንትራክተሮች በቻይና ኩባንያዎች ተሸነፉ፡፡

አገር በቀል ኩባንያዎቹ ፕሮጀክቶቹን አሸንፈው ለመረከብ ከፍተኛ ጉጉት እንደነበራቸው የሚናገሩት ምንጮች፣ ባልተጠበቀ ሁኔታ የቻይና ኩባንያዎች ዝቅተኛ የመጫረቻ ገንዘብ በማቅረባቸው ከጨዋታ ውጪ ሊሆኑ እንደቻሉ ገልጸዋል፡፡

ለጨረታ የቀረቡት መንገዶች በአማራ ክልል ከላሊበላ ሰቆጣ፣ በደቡብ ክልል በሁለት የተከፈለው ከኮንታ ልዩ ወረዳ (ጭዳ ከተማ) እስከ ዳውሮ ዞን (ተርጫ ከተማ) ድረስ የሚዘረጉት ሦስት መንገዶች ናቸው፡፡

እነዚህን ፕሮጀክቶች ለማግኘት ከተወዳደሩት ከአገር በቀል ኮንትራክተሮች መካከል የንኮማድ ኮንስትራክሽን፣ ሱር ኮንስትራክሽን፣ ዲኤምሲ ኮንስትራክሽንና ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ይገኙበታል፡፡

አሸናፊ የሆኑት የቻይና ኩባንያዎች ደግሞ ሲሲሲሲና ቻይና ሬልዌይ ናቸው፡፡ ምንጮች እንደገለጹት፣ የመንገድ ግንባታ የሚካሄድባቸው ቦታዎች አመቺና ቀላል ከሚባሉት መሀል ቢሆኑም፣ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ከፍተኛ የመጫረቻ ገንዘብ ማቅረባቸው ታውቋል፡፡

በአንፃሩ የቻይና ኩባንያዎች ከተወዳዳሪዎቻቸው ሲነፃፀር እጅግ ዝቅተኛ ገንዘብ በማቅረባቸው፣ አገር በቀል ኮንትራክተሮች በጨረታው መሸነፋቸው ተገልጿል፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ አገር በቀል ኩባንያዎች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ሲወዳደሩ 7.5 በመቶ ከፍ ያለ ዋጋ ቢያቀርቡ እንኳ ቅድሚያ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡

‹‹ይህ ማለት የአገር ውስጥ ኩባንያዎች አንድ መቶ ሚሊዮን ብር ቢያቀርቡና የውጭ ኩባንያዎች ደግሞ 92.5 ሚሊዮን ብር ቢያቀርቡ፣ የመንግሥት ፖሊሲ አገር በቀሎቹን የሚደግፍ በመሆኑ አገር በቀሎቹ ሥራው ይሰጣቸዋል፤›› ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የባለሥልጣኑ ባለሙያ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ከቻይና ኩባንያዎች ጋር በጨረታው የዋጋ አቀራረብ ምን ያህል እንደተራራቁ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ጨረታ ከጨዋታ ውጪ የሆኑት የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ባገኙት አጋጣሚ ቅሬታቸውን እየገለጹ ቢሆንም፣ ያለው ሕግ ግን ሊያስተናግዳቸው እንደማይችል እየተገለጸ ነው፡፡

የጨረታውን ውጤት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ሥራ አመራር ቦርድ ካፀደቀው፣ ባለሥልጣኑ ከአሸናፊ የቻይና ኩባንያዎች ጋር በቅርቡ ስምምነት ይፈራረማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡     

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች