Sunday, June 16, 2024

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 21 ይከበር!

በ1987 ዓ.ም. በፀደቀው የኤፌዲሪ ሕገ መንግሥት በክፍል አንድ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ሥር የተቀመጠው አንቀጽ 21፣ በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎችን መብት በተመለከተ የሚከተለውን አስፍሯል፡፡

  1. በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች የመያዝ መብት አላቸው፡፡
  2. ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሃይማኖት አማካሪዎቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸውና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘትና እንዲጎበኙዋቸውም ዕድል የማግኘት መብት አላቸው፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 21 ላይ የሠፈረው ይህ መብት እንዲከበር ከማንም በላይ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ነው፡፡ ይህ ሕገ መንግሥታዊ መብት ሳይከበር ሲቀር በርካታ ታሳሪዎችና ቤተሰቦቻቸው ብዙ ጊዜ አቤቱታ ሲያቀርቡ ተደምጠዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አቤቱታም በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሳይቀር ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶታል፡፡ ከሰሞኑም የፍትሕ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ለአንድ ወር ያህል በቤተሰብም ሆነ በወዳጅ ዘመዶቹ እንዳይጠየቅ መከልከሉን፣ ወላጅ እናቱ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የአቤቱታ ደብዳቤ አስገብተዋል፡፡ በግልባጭም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላትና ለውጭ ኤምባሲዎች አስታውቀዋል፡፡ መንግሥት ይህንን አቤቱታ መርምሮ መፍትሔ መስጠት አለበት፡፡

በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች በሕግ ጥላ ሥር የሚገኙ እስረኞች እንደሚጎበኙት ሁሉ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሳይቀሩ መብታቸው ሊከበር ይገባዋል፡፡ ከዚህ በፊት በቤተሰብም ሆነ በወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዳይጎበኙ የተከለከሉ ወገኖች በተለያዩ አቤቱታዎች ችግሮች እንዳጋጠሙዋቸው በፍርድ ቤቶችም ሆነ በተለያዩ መንገዶች አሳውቀዋል፡፡ በሕግ ጥላ ሥር ያለ ማንኛውም ዜጋ ሕገ መንግሥታዊ መብት ተከብሮለት እያለ፣ ይህ ጉዳይ የሚመለከተው የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ለምን ክልከላውን እንደፈጸመ መንግሥት ማጣራት አለበት፡፡ ተገቢውን ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድም ይኖርበታል፡፡ በሕግ ጥበቃ ሥር ያሉ ዜጎች በደል ደርሶብናል ሲሉ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን መወጣት አለበት ማለት ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 21 ላይ የሠፈረው በፍርድ የታሰሩ ሰዎችን ሰብዓዊ አያያዝ በተመለከተ ጥያቄ ሲቀርብ፣ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ምላሽ የመስጠት ኃላፊነት ሲኖርበት፣ ይህንን አካል በቀጥታ የሚመራው የመንግሥት አስፈጻሚ ደግሞ የበለጠ ኃላፊነት አለበት፡፡ በሕግ ጥላ ሥር ሆኖ በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት የማይስተናገድ እስረኛም ሆነ ቤተሰቦቹ አቤቱታ ሲያቀርቡ ዝም ማለት አይገባም፡፡ ቤተሰቦች እስረኛቸውን መጠየቅ ተከለከልን ሲሉ፣ ሰብዓዊ መብት ሲጣስ ዝም አንልም የሚሉ ዜጎች እስረኞች ምግብና መድኃኒት ተከልክለዋል ብለው አቤቱታ ሲያቀርቡ ዝም አይባልም፡፡ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ ሕጋዊ ዕርምጃ መወሰድ አለበት፡፡

ለብዙ ጊዜያት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎች ለምን ወደ ዳር ይገፋሉ? በተለይ ደግሞ በሕግ ጥበቃ ሥር የዋለ ዜጋ ሰብዓዊ ክብሩ ተጠብቆ መያዝ አለበት ተብሎ የሕጎች ሁሉ የበላይ በሆነው ሕገ መንግሥት ሠፍሮ እያለ፣ እንዲህ ዓይነቱን የሕግ ጥሰት የሚፈጽም ካለ በአስቸኳይ ተጣርቶ ሕጋዊ ዕርምጃ ይወሰድ፡፡ ከወላጆች ጀምሮ የትዳር አጋሮች፣ የቤተሰብ አባላት፣ ዘመዶችና ወዳጆች እስረኛ ወገናቸውን መጠየቅ እንደሚችሉ ሕገ መንግሥቱ በግልጽ ደንግጎ እያለ ይህንን መብት መከልከል አይቻልም፡፡ ይህ ሕገ መንግሥትን የሚጋፋ ተግባር ሊጣራ ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም የሕግ የበላይነትን የሚጋፋ ተግባር ነውና፡፡ ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ በተጨማሪም የኢትዮጵያዊያንን መልካም ባህልና እሴቶች ይጋፋል፡፡

ኢትዮጵያውያን የታመመን በማስታመም፣ የታሰረን በመጠየቅ፣ የተራበና የታረዘን በማብላትና በማልበስ፣ ከዚህ ዓለም በሞት የሚለይን በወግ በማዕረግ ቀብሩን በማስፈጸም ነው የሚታወቁት፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አኩሪና የአብሮነት መገለጫ ያሉት ይህ ኩሩ ሕዝብ እስረኛ ጠያቂ ተከለከለ፣ በዚህም ምክንያት ዘመዶቹ እያለቀሱ ናቸው ሲባል አይመቸውም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሳዛኝ ተግባር ተፈጽሟል ሲባል ‘መንግሥት በአገሩ የለም ወይ?’ ብሎ ይጠይቃል፡፡

አሁንም ደግመን ደጋግመን የምንጠይቀው ሕግ ይከበር ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ይኑር ነው፡፡ ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል ተጠያቂነት ይኑርባቸው፡፡ እኩልም ይሁኑ ነው የምንለው፡፡ የሕግ የበላይነትን የሚገዳደሩ ተግባራት አገሪቱን ለኢዴሞክራሲያዊና ለአምባገነናዊ አስተሳሰቦች ይዳርጉዋታል፡፡ አገሪቱ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ዘንድ ከበሬታ የምታገኘው ከአስከፊው ድህነት ውስጥ ለመውጣት በምታደርገው ጥረት ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ዋስትና የተሰጣቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለምንም መሸራረፍ ተግባራዊ ሲሆኑ ነው፡፡ የዴሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና የመልካም አስተዳደር እጦት ሕዝቡን ሊያማርሩት አይገባም፡፡

በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች በሙሉ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 21 መሠረት ሰብዓዊ ክብራቸው መጠበቁ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በሕግ ጥላ ሥር ሆነው ሕጉ የሚፈቅድላቸው በሙሉ ሊሟላላቸው ይገባል፡፡ በቤተሰቦቻቸውም ሆነ በወዳጅ ዘመድ መጠየቅ አለባቸው፡፡ መንግሥትም ሕገ መንግሥቱን የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ ተገቢውን ማጣራት አድርጎም በጥፋተኞች ላይ ተገቢውን ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ አለበት!

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 21 በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብትን በተመለከተ የወጣው ድንጋጌ ይከበር! መንግሥትም ሕገ መንግሥቱን ያስከብር!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...