የግንቦት ሰባት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የነበሩትና የመን ለኢትዮጵያ አሳልፋ የሰጠቻቸውን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ለመጐብኘት ለኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ ያቀረቡት የእንግሊዝ የፓርላማ ልዑካን፣ ጥያቄያቸው ውድቅ መደረጉ ተሰማ፡፡
አቶ አንዳርጋቸው በእንግሊዝ ይኖሩበት በነበረው አካባቢ የምርጫ ክልል ውስጥ ነዋሪ በሆኑት ሚስተር ጀርሜይ ኮርቢይን የሚመራው የእንግሊዝ ፓርላማ ልዑክ፣ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ከበደን ባለፈው ሳምንት አግኝተው ካነጋገሯቸው በኋላ፣ ጉብኝቱ እንደማይፈቀድላቸው ማወቃቸውን የውጭ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡
ልዑኩ በዚህ ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ለመወያየት አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት እንዳልተፈቀደላቸው ሚስተር ኮርቢይን ለሚዲያዎቹ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የአቶ አንዳርጋቸው ጠበቃ ሚስተር ክሊቭ ስታፎርድ ስሚዝ አቶ አንዳርጋቸውን መጠየቅ እንደሚችሉና እሳቸውን በሚመለከት የፈለጉትን ጥያቄ ማንሳት ወይም ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር መነጋገር እንደሚችሉ ፈቅዶ እንደነበር አክለዋል፡፡ ልዑኩ ባለፈው ወር አቶ አንዳርጋቸውን ለመጠየቅ ለኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ ማቅረቡ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው የግንቦት ሰባት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በአሸባሪነት ክስ ተመሥርቶባቸው በሌሉበት ከስድስት ዓመታት በፊት በሞት እንዲቀጡ እንደተወሰነባቸው አይዘነጋም፡፡ አቶ አንዳርጋቸው በሰኔ ወር 2006 ዓ.ም. አጋማሽ ከዱባይ ወደ ኤርትራ በመጓዝ ላይ እያሉ፣ የተሳፈሩበት አውሮፕላን የመን ዋና ከተማ ሰነዓ አውሮፕላን ማረፊያ ሲያርፍ፣ በየመን በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውለው ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠታቸው ይታወሳል፡፡