Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ኢትዮጵያና ጂቡቲ ለበለጠ ኢኮኖሚያዊ ምናልባትም ፖለቲካዊ ውህደት ሊሠሩ የሚገባበት ጊዜ ነው›› ...

‹‹ኢትዮጵያና ጂቡቲ ለበለጠ ኢኮኖሚያዊ ምናልባትም ፖለቲካዊ ውህደት ሊሠሩ የሚገባበት ጊዜ ነው›› ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

ቀን:

በጂቡቲ የሦስት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው እሑድ በአገሪቱ ፓርላማ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያና ጂቡቲ ለበለጠ ኢኮኖሚያዊ ምናልባትም ፖለቲካዊ ውህደት ሊሠሩ የሚገባበት ጊዜ አሁን መሆኑን ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ለሦስት ቀናት በጂቡቲ ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት በርካታ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ከማድረግ ባለፈ፣ የጉብኝታቸው ዋና ዓላማ እንደሆነ የገለጹትን ንግግር በጂቡቲ ፓርላማ አማካይነት ለሕዝብ እንዲደርስ አድርገዋል፡፡

‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ከጂቡቲ ሕዝብና መንግሥት ጋር ላለን ወንድማዊ ግንኙነት ትልቅ ቦታ እንሰጣለን፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የዚህ ምክንያቱ ሁለቱ አገሮች ጎረቤት ስለሆኑ ነው የሚል ሐሳብ ካለ ለሁለቱ አገሮች ግንኙነት ቦታ አለመስጠት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ወይም የሁለቱ አገሮች ልዩ የሆነ ግንኙነት የመነጨው የማይተካ ሚና ባለው የጂቡቲ ወደብ እንደሆነ የሚገልጹ ካሉ ወደቡን በተመለከተ ትክክል ቢሆንም ተሳስተዋል፤›› ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹የጂቡቲ ወደብ ለኢትዮጵያ መውጫ በር መሆኑ እንዲሁም ለጂቡቲ የገቢ ማግኛ ምንጭ መሆኑ ትክክል ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ሁለቱ አገሮች በተለያዩ መሠረተ ልማቶች እንዲገናኙ ያደረገው ይኸው ወደብ ነው፡፡ ነገር ግን የሁለቱ አገሮች ወዳጃዊ ግንኙነት ምንጭ ነው ከተባለ ሙሉውን ገጽታ ያላገናዘበ ስህተት ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹እንደነዚህ ያሉ መሠረታዊ ልማታዊ ቁርኝቶች ምርጥ የተባለ ወንድማዊ ግንኙነት የማይፈጥሩ መሆናቸውን ከተረዳን ቆይተናል፡፡ በጣም ወርቃማ የሆነ እሴታችን አንድ እና በደም የተገናኘው ሕዝባችን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በደም የተገናኘው የሁለቱ አገር ሕዝብ ራዕይ አንድ ዓይነት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ የሁለቱ አገሮች የፖለቲካ መሪዎችም ለሁለቱ አገሮች ሕዝቦች የጋራ ህልምና ፍላጎት ሙሉ ይሁንታቸውን መስጠታቸው የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹እኛ ሁለታችን ያለን ነገር ቢኖር ለታላቅ አንድነትና ቅንጅት የጋራ ሐሳብ  እንዲሁም በደም የተሳሰረ ሕዝብ መያዛችን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኼንን ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት 70 መቀመጫዎች ባሉትና የእሳቸውን ንግግር ለመስማት የጂቡቲ ባለሥልጣናትና በጂቡቲ የሚገኙ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በታደሙበት ፓርላማ፣ ደመቅ ያለ የይሁንታ ጭብጨባ አግኝተው ነበር፡፡

‹‹ዛሬ እዚህ የመጣሁትና ፊታችሁ የቆምኩበት ከፍተኛ አጀንዳ የሆነውንና የሕዝባችንን  ትብብርና የቅንጅት ፍላጎት በበለጠ ለማጠከር ዕርምጃ መውሰድ እንድንጀምር ጥሪ ለማቅረብ ነው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ‹‹የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች የበለጠ እንዲተባበሩ መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ውህደት ከተፈጠረ ፖለቲካዊ ውህደትን ሊያመጣ እንደሚችልም አክለዋል፡፡

በተጨማሪም፣ ‹‹ለዚህ ዓይነቱ ግንኙነት የፖለቲካ ተመራማሪዎችና ተንታኞች ምን ዓይነት ስም እንደሚሰጡት አላውቅም፡፡ እኛ ግን ወደዚያ ቀስ በቀስ ነገር ግን በእርግጠኝነት እየተጓዝን ነው፤›› ብለዋል፡፡ እንደ እሳቸው አባባል ይህ የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች የጋራ ራዕይና ጉጉት ዕውን ሆኖ ልጆቻቸው ጭምር ኖረው ሊያጣጥሙት የሚገባ ብሩህ የወደፊት ቀን ነው፡፡

‹‹ይህ እንዲሆን የሚኬደው መንገድ ቀላል ነው፡፡ ልጆቻችንን ወደሚመቻቸው የጂቡቲ ወይም የኢትዮጵያ ትምህርት ቤት እንልካለን፡፡ ባለሥልጣኖቻችን አንዱ ከሌላው ልምድ እንዲወስድ ስናደርግ፣ አንዱ የሌላውን ሀብት ለሁለቱ አገር ሕዝቦች የመጨረሻ ጥቅም ሲባል ይጠቀም፡፡ ኢንዱስትሪዎቻችን አንዱ የሌላውን አገር ፍላጎት ያሟሉ፤›› በማለት መንገዱ ከሚታሰበው በላይ ቀላል ይሆናል የሚል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

      በመጨረሻም ለአጭር ጊዜ ጥቅም ሲባል መንግሥታት የረዥም ጊዜ የሕዝቦችን የጋራ ራዕይና ጥቅምን እንዳያበላሹ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በጁቡቲ ላይ የሚቃጣ ጥቃት በእጥፍ የሚያማት አገር ናት፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም ለዓለም ይሰማ ብለዋል፡፡ ‹‹ይህ ለእኛ ዋጋ የምንከፍልበት የተጻፈ ዕጣ ፈንታችን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ይህንን ንግግር ከማድረጋቸው ቀደም ባለው ቀን ከጂቡቲ ፕሬዚዳንት ጋር ዘጠኝ ያህል የኢኮኖሚ ትብብሮችን ተፈራርመዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ትራንስፖርት፣ ንግድ፣ ቴሌኮምና ጉምሩክ ይገኙበታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጂቡቲ ፓርላማ ንግግር ባደረጉበት ወቅት የነበሩት በኢትዮጵያ የጂቡቲ አምባሳደር መሐመድ ኢድሪስ ፋራህ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አቋም የጂቡቲ መንግሥትም አቋም መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ የፖለቲካ ውህደት የሕዝቦች ፍላጎትና ጥያቄ እንጂ የፖለቲለኞች ምርጫ አይደለም የሚሉት አምሳባደሩ፣ ‹‹የሕዝባችን ፍላጎት እስከሆነ ድረስ ልንተገብረው ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ ይህንን መሰሉን ግንኙነት ለመፍጠር የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና አቻቸው ፕሬዚዳንት እስማኤል ኡመር ጌሌህ ተስማምተው የጀመሩት መሆኑንም ያስታውሳሉ፡፡

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያውያን በጂቡቲ እንደ ዜጋ እንደሚቆጠሩ ሁሉ፣ ጂቡቲያውያንም በኢትዮጵያ እንደዚሁ ይታያሉ፡፡ ነገር ግን በአፈጻጸም ላይ ችግር ወይም የመረጃ እጥረት መኖሩን ተናግረዋል፡፡ በጂቡቲ ኢንቨስት የሚያደርግ ኢትዮጵያዊ ባለሀብት አለመኖር በማስረጃነት የጠቀሱት አንድ ክፍተት ነበር፡፡ ሆኖም ግን በዚህ ጉበኝት ወቅት ኩሪፍቱ ሪዞርት በጂቡቲ በሰባት ሚሊዮን ዶላር ሪዞርት እየገነባ መሆኑ ታውቋል፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...