‹‹ፅኑ የሆነ የምግብ እጥረት የገጠማቸው 2.5 ሚሊዮን ዜጎች መሆናቸውን መንግሥት ማመን ባይፈልግም፣ እኛ ግን ጫና ማሳደራችንን መቀጠል አለብን፡፡››
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ ቫለሪ አሞስ፣ የደቡብ ሱዳንን አሳሳቢ ረሃብ አስመልክተው ከሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የተወሰደ፡፡ ኃላፊዋ ሰሞኑን ለሦስት ቀናት ስላደረጉት የደቡብ ሱዳን ቆይታ ሲናገሩ፣ በደቡብ ሱዳን ላይ የጦር መሣሪያ ማዕቀበ ካልተጣለ ረሃቡ ከእርስ በርስ ጦርነቱ ጋር ተደባልቆ ሰብዓዊ ቀውስ ይፈጥራል ብለዋል፡፡ የጦር መሣሪያ ከሌለ ተቀናቃኝ ወገኖች መዋጋት አይችሉም ብለው፣ የደቡብ ሱዳን ሕዝብም ግጭት ከሌለ ያለምንም ችግር የምግብ ዕርዳታ እንደሚያገኝ አስታውቀዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡም የእርስ በርስ ግጭቱን ለማስቆምና ሕዝቡ ዕርዳታ እንዲያገኝ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቀዋል፡፡ መንግሥትም የረሃቡን አስከፊነት ተገንዝቦ ለሰብዓዊ ርብርቡ እንዲተጋ ጥሪ አቅርበው፣ ተቀናቃኙ ወገንም ከግጭቱ ይልቅ ለነፍስ አድን እንቅስቃሴው አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡ በምሥሉ ላይ የሚታዩት ቫለሪ አሞስ ናቸው፡፡