ሦስተኛው ‹‹ሆፕ ዊዝ አርት ኤንድ ሚውዚክ›› የሥነ ጥበብ ፕሮጀክት እሑድ የካቲት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. በአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ተካሂዷል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ በተራድኦ ድርጅት የሚረዱ ሕፃናት በሥዕልና ሙዚቃ ተሳትፈዋል፡፡
በዕለቱ በእስራኤላዊቷ ድምፃዊት ሞኒካ ማናክርና ፐርከሽኒስት ኤላድ ኔማን መሪነት የሙዚቃ ወርክሾፕ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የእስራኤል ኤምባሲ ከኤሆፕ ኢትዮጵያ የዕርዳታ ድርጅት፣ ነፃ አርት ቪሌጅ፣ ስለእናት ማኅበር፣ ሐደሳህ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ኦፍ እስራኤል፣ አርቲስቲስ ፎር ቻሪቲ ኦርጋናይዜሽንና ፕሮፌሰር ዳኒ ኢግልሀድ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው መርሐ ግብር ላለፉት ሁለት ዓመታትም ተካሂዶ ነበር፡፡
ፕሮጀክቱ የነፃ አርት ቪሌጅ አባላትን ጨምሮ በጎ ፈቃደኛ አርቲስቶች፣ በጐ አድራጐት ድርጅቶች በየዓመቱ ያሳትፋል፡፡ በተለይም ወላጆቻቸውን በኤችአይቪ ያጡ ሕፃናት በጥበብ ሥራዎች እንዲሳተፉ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በጐ አድራጊዎች በሕክምና ከሚሰጡት ድጋፍ በተጨማሪ ጥበብን በሕፃናቱ ሕይወት ለማካተት ያለመ መሆኑን አዘጋጆቹ ለሪፖርተር በላኩት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ በሕፃናቱ የተሠሩት ሥዕሎች ለጥቂት ቀናት ለሕዝብ ዕይታ ክፍት ይሆናሉ፡፡