Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ሙዚቃችን ሁሌም ከጥቁሮች ታሪክ ጋር ያስተሳስረናል፤›› ስዊት ሃኒ ኢን ዘ ሮክ

‹‹ሙዚቃችን ሁሌም ከጥቁሮች ታሪክ ጋር ያስተሳስረናል፤›› ስዊት ሃኒ ኢን ዘ ሮክ

ቀን:

‹‹ለዓለም ሁሉ ሰላም ይሁን… ሰላምም ከኔ ይጀምር፤›› የሚለውን የዘፈን ሐረግ ታዳሚዎቹ ከድምፃውያኑ እየተቀበሉ በእንግሊዘኛ ይዘፍናሉ፡፡ ባለፈው ሳምንት በማማስ ኪችን የተገኙ ታዳሚዎች ከሰላም በተጨማሪ ልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ  ዜማዎችን ከድምፃውያኑ እኩል ሲዘፍኑ ነበር፡፡ ድምጻውያኑ  ‹‹ስዊት ሃኒ ኢን ዘ ሮክ›› የሚባል የጥቁር ሴት አሜሪካውያን አካፔላ ባንድ አባላት ናቸው፡፡ በየዓመቱ በያዝነው ወር የሚከበረውን የጥቁር ታሪክ ወር ምክንያት በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ሳምንታት አስቆጥረዋል፡፡

እንስቶቹ የወጣት ሴቶች ስብስብ ከሆነው ‹‹የኛ›› ጋር በባህር ዳር ከተማም ኮንሰርት አቅርበዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ በአሜሪካ ኤምባሲና በማማስ ኪችን ሥራዎቻቸውን አሳይተዋል፡፡ በመካነ እየሱስ የጃዝ ትምህርት ቤት ተገኝተው  ለተማሪዎች ልምዳቸውንም አካፍለዋል፡፡ በማማስ ኪችን ነጻነት፣ ለውጥ፣ ፍቅርና መሰል ጉዳዮችን የሚያነሱ ሙዚቃዎች አስደምጠዋል፡፡ ስለ ጥቁርነት፣ ሴትነት እንዲሁም ዘረኝነትን የመቃወም ጭብጥ ያላቸው ዘፈኖች ሞቅ ባለ ሁኔታ በታዳሚው ይታጀቡ ነበር፡፡

ድምፃውያኑ ያለ ሙዚቃ ማሣሪያዎች ሲያቀነቅኑ ከአባላቱ አንዷ በምልክት ቋንቋ ተርጉማለች፡፡ ‹‹አፍሪካውያን የቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችንን ታሪክ እንወቅ›› ና ‹‹ሕፃናት ማንኛውንም ነገር መፍጠር የሚችሉበት ዓለም እንፍጠር›› የሚል መልዕክት ያላቸውን ዜማዎች ያቀረቡት በስሜት ተሞልተው ልዩ ልዩ ድምፅ እያወጡ መሬቱን በእግራቸው እየመቱ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙዚቃቸውን በማቅረባቸው እንደተደሰቱ ገልጸው ‹‹በድጋሚ መምጣት እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡

የ‹‹ስዊት ሃኒ ኢን ዘ ሮክ›› አባላት ወደ አሜሪካ ከመመለሳቸው በፊት ሪፖርተር አነጋግሯቸው ነበር፡፡ አባላቱ አይሻ ካህሊል፣ ልዊስ ሮቢንሰን፣ ኬረል ሜላቮድ፣ ናታኒሁ ቦሌድ ካስል፣ ሼርሊ ቺልድረስ (የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ) በኅብረት እንደተናገሩት፣ በቅኝ ያልተገዛችና የሰው ዘር መነሻ ወደሆነችው ኢትዮጵያ መጥቶ መዝፈን ህልማቸውን ነበር፡፡ ከዘመናት አስቀድሞ የሰው ልጅ በኖረበት ምድር ተገኝቶ መዝፈን ከባንዱ የሙዚቃ መልዕክት ምርጫ አንፃርም ተገቢ ነው ትላለች ኬረል፡፡ ናታኒሁ እንደምትለው፣ የባንዱ አባላት ጥቁር አሜሪካውያን እንደመሆናቸው አፍሪካ መገኘታቸው ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሲሆን፣ ቅኝ ባለመገዛት በዓለም ታሪክ ከፍተኛ ቦታ ያላትና የነጻነት ተምሳሌት ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑ ደግሞ ነገሩን ያጎላዋል፡፡

ጥሪ የተደረገላቸው ከአሜሪካ ኤምባሲ ሲሆን፣ ከኬረል በስተቀር ሁሉም ኢትዮጵያ ሲመጡ የመጀመሪያቸው ነው፡፡ ናታኒሁ እንደምትለው፣ በሴቶች ጉዳይ ከሚያቀነቅኑት የ‹‹የኛ›› አባላት ጋር ያቀረቡት የጥምረት ሥራ ሁለቱም ባንዶች የተነሱለትን ተመሳሳይ ዓላማ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ‹‹ሴትነት፣ የሴቶች ስብስብ የሆነው ስዊት ሃኒ ለዓመታት የዘፈነለት ጉዳይ ነው፤ ‹‹የኛ››ም መሰል መልዕክት ያዘሉ ሙዚቃዎች አሏቸው፤ የተጣመርነው በሴትነት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ስለ ሰው ልጅ ነጻነት በመስበክ ጭምርም ነው፤›› ስትል አክላለች፡፡

የኢትዮጵያ ሙዚቃና እነሱ የሚጫወቱት ሙዚቃ ተመሳሳይ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ በተለይ የሙዚቃው ምትና የወንጌል ሙዚቃዎቹ ተቀራራቢ ናቸው ትላለች፡፡ ከበሮ አጨዋወቱና የሙዚቃ መሣሪያው (ከበሮ) የጥቁሮች መሆኑ የበለጠ እንደሚያስተሳስረው እምነቷ ነው፡፡ ሼርሊ እንደገለጸችው፣ ፍትሐዊነትና እኩልነት የሰፈነበት ዓለም እንዲፈጠር የሚያሳስብ ሙዚቃ በመጫወት የሚታወቀው ባንድ፣ መስማት የተሳናቸው እንደማንኛውም ሰው በሙዚቃ እንዲደሰቱ ያደርጋል፡፡

የምልክት ቋንቋ ማካተት የባንዱ መልዕክቶች ያለ ልዩነት ለሁሉም ሰው መዘጋጀታቸውን የሚያሳዩበት መንገድ እንደሆነ ትገልጻለች፡፡ መስማት የተሳናቸው በሙዚቃ መሳተፍ እንደሚችሉ በመግለጽ፣ ትኩረት የተነፈጋቸውን በሙዚቃ ማካተት ከዓላማችን አንዱ ነው ትላለች፡፡ ልዊስ እንደምትናገረው፣ ስዊት ሃኒ በደረሱበት ሁሉ መልዕክታቸውን ከማስተላለፍ ጎን ለጎን በየአገሩ ያለውን ነበባራዊ ሁኔታ በመመልከት ለሙዚቃቸው ግብዓት ያገኛሉ፤ ለባህል ልውውጡም ከፍተኛ ቦታ ይሰጣሉ፡፡

ባንዱ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ሴት አባላት ነበሩት፡፡ አባላት በዕድሜና በልዩ ልዩ ምክንያት ሲወጡ በሌላ ይተካሉ፡፡ እንደ ልዊስ ገለጻ፣ አዳዲስ ሰው ቡድኑን ሲቀላቀል ልዩ ነገር ይዞ ይመጣል፡፡ የስዊት ሃኒን የማይቀየር ዓለማ የሚያራምዱ መሆናቸው ቢያመሳስላቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ ያሳያሉ፡፡

አብዛኞቹ አባላት በሐሳቡ ይስማማሉ፡፡ በየጊዜው የየአባላቱ የሕይወት ተሞክሮ ይዘታቸው የተለያዩ ዘፈኖች እንዲያዘጋጁ ያደርጋቸዋል፡፡ ማንኛውም ሰው ሙዚቃቸውን ሲሰማ ከመዝናናት በተጨማሪ እንዲማርና ኃይል እንዲያገኝ እንደሚፈልጉ ይገልጻሉ፡፡ እያንዳንዱ ሰው ለዓለም የሚያበረክተው ነገር እንዳለ የሚያሳስቡ ሙዚቃዎቻቸው በማንኛውም ዕድሜ ያለል እንደሚያነሳሱ ያምናሉ፡፡ በሙዚቃ ሰው ለሚያነሳው ጥያቄ መልስ መስጠት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ሰው በሕይወቱ የሚመልሰው ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ የማኅበረሰቡን እሴቶች በማጉላት በዓለም አንዳች ለውጥ እንደሚመጣ ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ቀደም በጥቁር ታሪክ ወር በተለያዩ አገሮች ተዘዋውረዋል፡፡ ባንዱ ስለ ጥቁሮች ማንነት የሚያወሱ በርካታ ዘፈኖች ስላሉት በሌሎች ወራት የሚያስደምጧቸው ሙዚቃዎች በዚህ ወር ደግሞ የበለጠ ትርጉም እንደሚሰጡ ይገልጻሉ፡፡ በጥቁር ታሪክ ወር ከነበሯቸው መድረኮች የእ.ኤ.አ. 2009ን ያስታውሳሉ፡፡ ስዊት ሃኒ ወደ ኋይት ሐውስ የተጋበዙበት ነበር፡፡ ኬረል ከቀድሞ ስዊት ሃኒ ጋር ስታዜም ከባራክ ኦባማ እናት ጋር ተዋውቃለች፡፡ የሚሼል ኦባማ እናት ከመሞታቸው በፊት ከሚሼል ጋር የታደሙት የመጨረሻ ኮንሰርት የስዊት ሃኒ ነበር፡፡ የኦባማ ልጆችም የስዊት ሀኒን ሙዚቃዎች እያደመጡ ነው ያደጉት፡፡ ከባንዱ ጋር ቁርኝት ላለው የኦባማ ቤተሰብ  ሥራዎቻቸውን ማቅረባቸው  ያስታውሱታል፡፡

ናታኒሁ ‹‹ሙዚቃዎቻችን ሁሌም ከጥቁሮች ታሪክ ጋር ያስተሳስረናል፤›› በማንኛውም ወር ዝግጅት ቢኖረን የጥቁሮችን ታሪክ የሚያወሱ ሙዚቃዎችን እናካትታለን ትላለች፡፡ ተመሳሳይ ሐሳብ ያላት ሼርሊ እንደምትለው፣ የአሜሪካ ታሪክ የጥቁሮች ታሪክ ነው፡፡ ለአንድ ወር ቢከበርም በዓሉ ዘወትር የሚኖሩበት ታሪክ ነፀብራቅ እንደሆነ ታስረዳለች፡፡ ‹‹ጥቁሮች ከቅኝ ግዛት ውጪ ታሪክ እንደሌላቸው ይታሰባል፤ ምንጊዜም ባሪያዎች እንደሆንን እንዲሰማን ይደርጋል፤ እውነታው ግን ከዚህ ፈጽሞ የራቀ ነው፤›› ትላለች፡፡ እውነታውን ለማሳየት ከሚታገሉ መካከል የስዊት ሃኒ ሙዚቃዎች ከፍተኛ ሚና እንዳላችው ታምናለች፡፡

አሠርታትን ባስቆጠረ የሙዚቃ ሕይወታቸው በየዘርፉ ያነሷቸው ጽንሰ ሐሳቦች በመጠኑ ለውጥ እንዳመጡ ያምናሉ፡፡ ብዙዎች የሕይወታቸውን ግማሽ የስዊት ሃኒን መዚቃዎች እንዳዳመጡ ማወቅና ለመልዕክታቸው ትልቅ  ቦት ሲሰጡት ማየት በሐሴት እንደሚሞላት ልዊስ ትናገራለች፡፡ ኢትዮጵያ ስለነበራቸው ቆይታ መልካምነት በመግለጽ ድጋሚ መጥተው በተለይ ስለ አገሪቱ ሙዚቃና ውዝዋዜ የበለጠ ማጥናት እንደሚሹ ይናገራሉ፡፡

ስዊት ሃኒ ብሉዝ፣ ጃዝ ፣ አር ኤንድ  ቢ፣ የአፍሪካና የወንጌል ሙዚቃዎችን ይጫወታሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1973 የተቋቋመው ባንዱ 23 ድምጻውያን በተለያየ ዓመት ተጫውተውበታል፡፡ ባንዱ ሲመሠረት አሁንም ድረስ ያሉት ኬረልና ልዊስን ጨምሮ ዶ/ር በርኒስ ጆሀንሰን ሬባንና ሌሎች በመጀመሪያ የዘፈኑት ዘፈን ‹‹ስዊት ሃኒ ኢን ዘ ሮክ›› መጠሪያቸው ሆኖ ዘልቋል፡፡

ከመፅሐፍ ቅዱስ መዝሙረ ዳዊት የተወሰደውን ስያሜያቸውን ሲያብራሩ፣ ‹‹ስዊት ሃኒ ትኩረቱ እጅግ የበለፀገ ምድር ላይ ነው፤ የምድሩ አለት ሲሰበር ማር ይፈሳል፡፡ ለኛ አለቱ እንደ ጥቁር ሴቶች ነው፡፡ ውጫቸው ጠንካራ ሆኖ ውስጣቸው እንደ ማር ጣፋጭ ነው፤›› ይላሉ፡፡ በርካታ አገሮችን እየተዘዋወሩ የዘፈኑት አባላቱ በግላቸው የዘፈኑትና ከሌሎች ጋር የተጣመሩበትን ጨምሮ ከ13 በላይ አልበሞች አሳትመዋል፡፡

ሁለት ጊዜ የግራሚ ተሸላሚ ሲሆኑ፣ በርካታ ጊዜ ታጭተዋል፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁንየርን ጨምሮ በበርካታ ታዋቂ ታጋዮች መታሰቢያ ዝግጅቶች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ የቡድኑን መሥራች ዶ/ር በርኒስን ጨምሮ ሌሎች አባለትም በፀረ አፓርታይድ ትግል ታስረው ነበር፡፡ በተለያየ ወቅት አንገብጋቢ የሚባሉ ርዕስ ጉዳዮችን አንስተው የዘፈኑት የስዊት ሃኒ አባላት ዛሬም በመሰል ሥራዎቻቸው እንደሚገፉ ይናገራሉ፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...