Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

አውቶቡስ ተራ በአዲሱ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚቀመጡ ነዳያን

ትኩስ ፅሁፎች

አውቶቡስ ተራ በአዲሱ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚቀመጡ ነዳያን አመሻሽ ላይ የሚመጣላቸውን ውኃ በጉጉት መጠባበቅ የዕለት ተዕለት ሥራቸው ነው:: ሁለት ሰዎች ውኃ በባልዲ ይዘው ወደነሱ እየሄዱ ሳለ፣ ሁሉም ነዳያን ያላቸውን ዕቃ እያወጡ የመጣውን ውኃ ኮዳ ያለው በኮዳው የሌለው ደግሞ በኩባያው እየተቀበሉ ሲጠጡ በፎቶው ላይ ይታያል :: ፎቶ በመስፍን ሰለሞን

********

ዓለም ባጠቃላይ የተዋናይ መድረክ

የተዋናይ መድረክ ዓለም በደፈና፤

 

ወንዱም ሆነ ሴቱ ተጫዋች በተራ።

መውጫቸው መግቢያቸው የተወሰነ ነው፤

አንድ ሰው በዕድሜው ብዙ ዓይነት ተራ አለው፤

ተራዎቹ ደግሞ ሰባቱ ዕድሜዎች፤ በፊት ሕፃን ሆኖ፤

በሞግዚቱ አንቀልባ የሚያለቅስ አስታውኮ።

ቀጥሎም አልቃሻ ተማሪ የሆነው፤ ኮረጆ ያዘለው

የማለዳ ገጹ እንዲያ የሚያበራው፤ ፍላጎት የሌለው

ልግመኛ ቀንዳውጣ ወደ ትምህርት ቤት የሚንፏቀቀው።

ግሎ እንደምድጃ ፍሞ እያቃሰተ፤ በሚያሳዝን ቅኔ

ለጮኛው ቅንድቦች የተገጠመላት አንድ ግሩም ዝማሬ፤

በውትድርና ዘብራቃ መኃላ ዘፍቆት ጢመ ነብሮ፤

ለክብሩ የሚቀና፤ ችኩል ላምባጓሮ፤

ሁሌም የሚያሳድድ የዝናን አረፋ

የመድፍ አፍም ቢሆን ከቶ የማይፈራ።

ከዚያም ዳኛ ሆኖ፤ ሙክት ዶሮ ሥጋ ቦርጩን የሞላው፤

ኮስተርተር ያሉ ዓይኖች፤ ጢምም እንደዚያው፤

ቋሚ ሕጎች ሆኑ ዘመናይ ደምቦችም ከቶ የማይገደው፡

እንደዚህ ተጫውቶ፤ ወደ ስድስተኛው ዕድሜ የሚያሸጋግረው

ወደ ከሲታና ሞላጫው ቦላሌ የተንቦለቦለ፤

ባፍንጫው መነጥር፤ ከረጢት በጎኑ የተንጠለጠለ፤

የልጅነት ሱሪው ይቅር ይቀመጥ፤ ዓለም ሰፍቶበታል

ዳሌውም ጠውልጓል፤ ደማቁ ልሳኑም ቀጭጯል አብቅቷል፤

የጭቅላ ድምጽ ሆኗል፤ ያናፋል ያፏጫል። በመጨረሻውም፤

እንደ ማሳረጊያ ለዚህ ድንቅ ታሪክም፤

ዳግመኛ ጭቅላነት መናኛ ዝንጋታ፤

ጥርስ አልባ፤ ዓይን አልባ፤ ጣዕም አልባ፤ ሁሉ አልባ።

ከዊልያም ሼክስፒር፤ ነፃ ትርጉም በዳዊት ዘኪሮስ

********

‹‹ምድር ቤቱን ስጠው አላችሁኝ ሰጠሁት››

እነሆ ሁለት ቂሳ ባጭሩ አብዱልቃዱር ጅላሊ ከባግዳድ ነው የመጡት ይባላል፡፡ እሮብ በስማቸው የሚከበርላቸው፡፡

ለአያሌ ዓመታት ሲያገለግሉዋቸው የኖሩትን ሁለት ተከታዮቻቸውን የሚያሰናብቱበት ጊዜ ደረሰ፡፡ የትኛውን ወዴት እንደሚልኩትና እዚያስ ምን እየሰራህ ትተዳደራለህ እንደሚሉት ለማወቅ በሌላ አባባልም የሁለቱን ዋጋ ወይም ክብደት ለመመዘን እንዲህ አደረጉ፡፡ ለሁለቱም አንድ ዶሮ ሰጡዋቸውና “ለየብቻችሁ ሂዱና ዶሮዋን እኔ በሌለሁበት ስፍራ አርዳችሁ አምጡልኝ አሉዋቸው፡፡ ተቀብለው ቢላ ቢላቸውን ይዘው ሄዱ፡፡

አንደኛው ሄዶ ዶሮዋን አርዶ መጣ፡፡ ሁለተኛው ግን ቆይቶ ዶሮዋን ሳያርዳት ይዟት ተመለሰ፡፡ ‹‹ምነው አላረድካት›› ቢሉት ‹‹እርስዎ የሌሉበት ቦታ አጣሁ›› አላቸው፡፡ (ሌላውን ለአንባቢ እንተዋለን፡፡)

አንድ ነክናካ (ነፍናፋ) ሼህ ፎቅ ቤታቸው ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡ ደርጉ መጣና የቤታቸውን ፎቁን ተወረሱና የቀበሌ ባለሥልጣን ገባበት፡፡ ለሳቸው ምድር ቤቱን ተውላቸው፡፡

እሳቸውም ቤቴን አስመልሱልኝ፤ ልወረስ አይገባኝም እያሉ ቀበሌ ጽህፈት ቤት እየተመላለሱ ሊቀ መንበሩን አሰለቹት፡፡ ማመልከቻ ይጻፉ ሲላቸው ‹‹እኔ ምኑን አውቄ እጽፈዋለሁ? አንተው ፃፍ ፃፍ አርግና እንደሚሆን አርገህ አስመልስልኝ፡፡

እሱም አላስመለሰላቸውም እሳቸውም መመላለሳቸውንም አልተው፡፡ በመጨረሻም ‹‹ወይም ፎቁን እርስዎ ይውሰዱትና ምድር ቤቱን ለሱ ይስጡት›› አላቸው፡፡ ‹‹እንዲያ ካላችሁኝ መልካም!›› ብለውት ሄዱ፡፡

በነጋታው ጧት ፎቃቸው ውስጥ ይኖር የነበረው ባለሥልጣን ሞቶ ተገኘ፡፡ ሊቀ መንበሩ መጥቶ ‹‹ምን ተደረገ እነ ሼህ?›› ቢላቸው ‹‹ምድር ቤቱን ስጠው አላችሁኝ፤ ምድር ቤቱን ሰጠሁት›› አሉት፡፡ 

  • ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ‹‹አንድ ሺ ከአንድ ሌሊቶች›› (1987)

****************

እንደገና መስማቱ….

በለምለም መስክ ላይ ብዙ ልጆች ይጫወታሉ፡፡ ከመካከላቸው አንዱ ተለይቶ ይሮጣል፡፡ እማሆይ በመቋሚያቸው እየተደገፉ ሲያዘግሙ ከሩቅ ታይተውታል፡፡ የሚወዳቸው አያቱ ናቸው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን መመለሳቸው ነበር፡፡ ተንደርድሮ አንገታቸው ላይ ይጠመጠምና ይስማቸዋል፡፡ እርሳቸውም አበባ መሳይ ጉንጮቹን አገላብጠው ከሳሙ በኋላ ዳቦ ያመጡበትን ቅርጫት እንዲይዝላቸው ሰጥተውት ጉዞው ወደ ቤት ይቀጥላል፡፡

 ልጁ ወዲያው ጥያቄውን ያቀርባል፡፡ ‹‹እማዬ እስኪ ንገሪኝ አባ ክርስቶዶሉ ዛሬ ምን አስተማሩ?›› የደብሩ አለቃ ስም መምህር ገብረ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህኛውን ስም ያወጣላቸው ተማሪ ነው፡፡ የሚናገሩት የምሁራን ቋንቋ ከሰፊው ሕዝብ ሕይወት ጋር ግንኙነት የሌለው መሆኑን ለማጥላላት በማሰብ፡፡ ‹‹አልያዝኩትም እንጂ ብዙ ጥሩ ጥሩ ነገር ተናግረዋል›› አሉ እማሆይ ጥያቄውን ሲመልሱ፡፡

ልጁ እንደገና ‹‹አዬ የእማ ነገር ተጨባጭ የምትይዥው የምታስቀሪው ነገር የማታገኚ ከሆነ ለምን በየጊዜው ትመላለሻለሽ?›› አለ ጠንከር ባለ ድምፅ፡፡ እማሆይ ቆም ብለው እጃቸውን በመዘርጋት ‹‹ነገሩ እሱን የያዝከውን ቅርጫት የሚመስል ነው፡፡ ለውሃ መቅጃ አይሆንም፡፡ ከላይ ሲጨምሩበት ከታች ይፈሳል፡፡ ነገር ግን ውሃው በየጊዜው ባለፈበት መጠን ቅርጫቱ ይጸዳል፤ አቧራው ስለሚወገድ፡፡ የሰውነትም ነገር እንደዚሁ ነው፡፡ ጥሩ ነገር ሰምቶ ወዲያውኑ ቢረሳም ለቅፅበት ያህል ወደ ንጹሕ ቦታ ይሻገራል፡፡ ስለዚህ እንደገና መስማቱ መድገሙ ይበጃል፡፡

  • እጓለ ገብረ ዮሐንስ (ዶ/ር) ‹‹ብፁዓን ንጹሐን ልብ›› (2005)

* * *

ኖርዌይ ልመናን እንደ ወንጀል የመቅጣት ዕቅዷን ሰረዘች

የነዳጅ ሀብት ያላትና ከዓለም የበለፀጉ አገሮች አንዷ የሆነችው ኖርዌይ ልመና እንደ ወንጀል የሚያስቀጣ እንዲሆን የማድረግ ዕቅዷን መልሳ ውድቅ ማድረጓ ተዘገበ፡፡

የአገሪቱ ቀኝ ዘመም መንግሥት ለማኞችንና ለእነሱ የዕርዳታ እጃቸውን የሚሰነዝሩ ሰዎችንም በገንዘብና እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ እስራት የመቅጣት ውጥኑን የተወው ተቃዋሚው ሴንተር ፓርቲ ለዕቅዱ ድጋፍ አልሰጥም በማለቱ ነው፡፡

ውድቅ የተደረገው ሕግ ለማኞችን በመኪናው የጫነ፣ መጠለያ ወይም ሌላም ዓይነት ዕርዳታ በመስጠት የተባበረ እንዲከሰስ የሚያደርግ ነበር፡፡

ሕጉ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የተሰማሩትን እንዲሁም ወንጀለኞችን ዒላማ ያደረገ ነበር ቢባልም መንግሥት በጐ አድራጐትን ሕገወጥ ለማድረግ እየሞከረ ነው በሚል ትልቅ ተቃውሞ አስነስቶ ነበር፡፡

የተቃዋሚው ፓርቲ ፓርላሜንታዊ መሪ ማሪት አርባ ስታድ ‹‹ሰዎች ለማኞችን ስለረዱ መቀጣት አለባቸው ማለት ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው፡፡ ለሰዎች ልብስ፣ ምግብና መጠለያ መስጠት በጭራሽ ወንጀል ሊሆን አይችልም፤›› ብለዋል፡፡

 

 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች