Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምረሃብ ያንዣበበባቸው 2.5 ሚሊዮን ደቡብ ሱዳናውያን

ረሃብ ያንዣበበባቸው 2.5 ሚሊዮን ደቡብ ሱዳናውያን

ቀን:

ደቡብ ሱዳን ከዋናዋ ሱዳን በሕዝብ ውሳኔ ነፃ ወጥታ ራሷን ማስተዳደር በጀመረች ማግሥት የገጠማት የርስ በርስ ጦርነት፣ ዜጎቿን ለከፋ ረሃብ አጋልጧል፡፡ በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና በቀድሞ ምክትላቸው ሪክ ማቻር መካከል በተፈጠረ አለመግባባት፣ ከሥልጣን የተባረሩት ሪክ ማቻር በደቡብ ሱዳን ለተከሰተው ዳግም ጦርነት ፕሬዚዳንቱን ሲኮንኑ፣ ሳልቫ ኪር ደግሞ ሪክ ማቻር ለመንግሥታቸው ታማኝ አለመሆናቸውን ሲገልጹ ከርመዋል፡፡

ከተለያየ ብሔር የመጡት ሁለቱ መሪዎች የፈጠሩት የሥልጣን ይገባኛል ውዝግብ፣ አገሬውን ብሎም ጦር ኃይሉን በብሔር የከፈለ ሲሆን አገሪቷንም ቅጥ ላጣ ጦርነት ዳርጓታል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2013 ጀምሮ በአገሪቱ የታጣውን ሰላም ለማስፈን ኢትዮጵያን ጨምሮ የኢጋድ አባል አገሮች ጥረት ቢያደርጉም ተጨባጭ ለውጥ አልመጣም፡፡

በፕሬዚዳንቱ ወታደሮችና በሪክ ማቻር ተከታዮች መካከል ያለውን ግጭት ለማቆስም የተኩስ አቁም ስምምነት በተደጋጋሚ ቢደረስም ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም፡፡

ደቡብ ሱዳናውያን ከሱዳን ጋር የነበራቸውን ሁለት አሥርት ያስቆጠረ ጦርነት አብቅተው ነፃነትን ቢቀዳጁም፣ ነፃነትን ማጣጣም ግን አልቻሉም፡፡ ዛሬም ደቡብ ሱዳን በሥልጣን ሽሚያ ትታመሳለች፣ ዜጎቿ ይሰደዳሉ፣ ይገደላሉ፡፡ አገሬው በብሔር ተከፋፍሎ ለከፋ ድህነት፣ ሰላም ማጣትና ረሃብ ተጋልጧል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሰሞኑን እንዳስታወቀው፣ በደቡብ ሱዳን ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለረሃብ አደጋ ተጋልጠዋል፡፡ ሕዝቡን ለከፋ የረሃብ አደጋ ያጋለጠው ደግሞ በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ምክትላቸው በነበሩት ሪክ ማቻር ወታደሮች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ሰባት ጊዜ ተሞክሮ ተግባራዊ መሆን ባለመቻሉ ነው፡፡ በመሆኑም ደቡብ ሱዳናውያን የጦርነት ጥቃት ሰለባ ከመሆናቸው ባለፈም ለረሃብ ተጋልጠዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለረሀብ አደጋ የተጋለጡ ደቡብ ሱዳናውያንን ለመታደግ 1.8 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል በማለት የጠየቀ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች 529 ሚሊዮን ዶላር ለመለገስ ቃል ገብተዋል፡፡

በኬንያ ናይሮቢ በተዘጋጀ ኮንፈረንስ ላይ የተገኙት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ አስተባባሪ ቫለሪ አሞስ፣ በደቡብ ሱዳን በነበራቸው የሦስት ቀናት ቆይታ አገሪቱ እየወደመች መሆኑንና ዜጎችም ለስቃይ መጋለጣቸውን ማየታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በአገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት እ.ኤ.አ. ከ2013 ወዲህ 50 ሺሕ ሰዎች እንደሞቱ ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ የገመተ ሲሆን፣ የተከሰተው የረሃብ አደጋ ደግሞ የከፋ ጉዳት ያደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ፣ አገሪቱ ካላት 12 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ግማሽ ያህሉ በዕርዳታ የሚተዳደር ነው፡፡ 100 ሺሕ የሚጠጉ ሰላማዊ ዜጎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ካምፖች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እንገደላለን በሚል ሥጋትም ከካምፑ መውጣት አይፈልጉም፡፡ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ደግሞ ከአገሪቷ ተሰደዋል፡፡ ‹‹በአገሪቱ የተከሰተው ግጭት ደቡብ ሱዳንን ለከፋ ችግር አጋልጧታል፡፡ በአገሪቱ ሰላም በቶሎ ካልሰፈነ ችግሩ የቀጣናው ይሆናል፤›› ሲሉ ሚስ አሞስ ተናግረዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕርዳታ በጠየቀበት ወቅት እንዳስታወቀው፣ በደቡብ ሱዳን ግጭቱና ጦርነቱ የሚጎላው በደረቃማው ወቅት ነው፡፡ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች በደረቃማ ወቅት እንደልባቸው መንቀሳቀስ ስለሚችሉ፣ ደረቃማው ወቅት ለወታደሮች መልካም አጋጣሚ ለንፁኃን ዜጎች ደግሞ ሰቆቃ ነው፡፡

የዕርዳታ ሠራተኞች የዕርዳታ ሥራ ለማከናወንም አይችሉም፡፡ በታጣቂዎች ይታገታሉ፣ ይዘረፋሉ፡፡ መንገዶች በድንገት ስለሚዘጉም የዕርዳታ ምግብ የጫኑ መኪኖች ሳይከፍሉ ማለፍ አይችሉም፡፡ ይህ የሚያሳየው አገሪቷን የሚቆጣጠረው አካል ሁኔታዎች ከእጁ እንደወጡ ነው፡፡

በደቡብ ሱዳን ሰላም ጠፍቷል፡፡ ሕዝቡ እየታረዘና እየተሰደደም ይገኛል፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ. በ2011 ለደቡብ ሱዳን ነፃ መውጣት ትልቁን ሚና እንደተጫወተች የሚነገርላት አሜሪካ የፈየደችው መላ የለም፡፡ በአገሪቱ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ እንዲጣል የቀረበውን ሐሳብም እስካሁን ከዳር አላደረሰችውም፡፡ በነዳጅ ሀብቷ የምትታወቀው ደቡብ ሱዳን ነፃ የመውጣቷን ያህል መሪዎቹ ለዜጎቿ አልጠቀሙም፡፡ ሥልጣንና ብሔርተኝነት እየፈተኗቸው ይገኛሉ፡፡

አሜሪካ ደቡብ ሱዳንን ከካርቱም ነፃ ለማውጣት የነበራትን ጉልህ ሚና ያህል በአገሪቱ ሰላም ለማስፈን ገፍታ አለመሥራቷን የፖለቲካ ተንታኞች ይነቅፋሉ፡፡ በተለይ በጦር መሣሪያ ማዕቀብ ላይ ከፍተኛ ባለሥልጣናቷ ያነሱት ‹‹ማዕቀብ አይጣል፣ ይጣል›› ውዝግብ ለሰላም ወዳድና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ያስገረመ ነበር፡፡

በደቡብ ሱዳን የተጋረጠውን የረሃብ አደጋ ለመታደግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 1.8 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ቢልም፣ አሜሪካ ለመለገስ ቃል የገባችው 273 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ በአሜሪካ የስደተኛ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አኒ ሪቻርድ አንደሚሉት፣ ሰዎች አላስፈላጊ በሆነና መሪዎች ማስፈን ባልቻሉት ሰላም ምክንያት መጎዳታቸውንና መሞታቸውን ይቀጥላሉ፡፡

ደቡብ ሱዳናውያን በቃላት ሊገለጹ በማይችሉ መከራ ውስጥ እንደሚገኙ ሰሞኑን ለሦስት ቀናት በደቡብ ሱዳን ጉብኝት ያደረጉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው፣ ደቡብ ሱዳናውያን በስቃይ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከፍተኛ ዕርዳታም ያስፈልጋቸዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ተቃዋሚያቸው የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር የፊታችን ዓርብ ቀጣይ የሰላም ድርድር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የሰላም ድርድሩ ተሳክቶ በረሃብ አደጋ ውስጥ የሚገኙ 2.5 ሚሊዮን ደቡብ ሱዳናውያንን ለመታደግ ዕድል ይገኝ ይሆን የሚለው ዛሬም አጠራጣሪ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከዚህ በፊት የተደረጉ ሰባት ድርድሮችና ስምምነቶች ተግባራዊ ሆነው አለመታየታቸው ነው፡፡

ለደቡብ ሱዳናውያን መሰቃየት፣ መሰደድ፣ መራብ፣ መታረዝና መሞት ፕሬዚዳንቱም ሆኑ የቀድሞ ምክትላቸው ይወቀሳሉ፡፡ በአገሪቱ ላለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትም ሁለቱም ወገኖች ተጠያቂ እንደሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ ባለሥልጣን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም በደቡብ ሱዳን ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ ለመቀነስም ሆነ ለማስቆም ወይም ፍትሕ ለማስፈን ከባድ ፈተና ነው፡፡ ምክንያቱም 70 በመቶ ያህሉ የፖሊስ አባላት ያልተማሩ ናቸው፡፡ በአገሪቱ ያሉት ዳኞችም ከ200 አይበልጡም፡፡

የሂዩማን ራይትስ ዎች ረዳት ዋና ጸሐፊ ኢቫን ሲሞኖቪች እንደሚሉት፣ በአሁኑ ጊዜ በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማስፈን የሚያዋጣው በሁለቱ ተቀናቃኞች መካከል መተማመን የሚፈጠርበትን መንገድ ማጎልበት ነው፡፡ እስረኞችን የመጠየቅ፣ በትብብር የጠፉ ሰዎችን የማፈላለግ እንዲሁም በሁለቱም ወገኖች ከግጭት ጋር በተያያዘ የታሰሩ ዜጎችን መፍታትን ከሁለቱም ወገኖች የሚጠበቅ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...