Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርለኢትዮጵያ የሚታሰቡ የመፍትሔ ሐሳቦች ሕዝባችንን ያማከሉ ይሁኑ

ለኢትዮጵያ የሚታሰቡ የመፍትሔ ሐሳቦች ሕዝባችንን ያማከሉ ይሁኑ

ቀን:

በብርቱካን ወለቃ

ይድረስ ለአቶ ኦባንግ ሜቶ

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ኤግዝኪዩቲቭ ዳይሬክተር

ዋሽንግተን ዲሲ

አሜሪካ

የተከበሩ ኦባንግ በአካል ባንተዋወቅም ኢትዮጵያ እያሉም ሆነ ኢትዮጵያን ትተው ወደስደት ከሄዱ በኋላ፣ እያደረጉ ባሉት የፖለቲካ እንቅስቃሴ በመጠኑም ቢሆን ማንነትዎን ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡

ይህችን ደብዳቤ  እንድጽፍ ያነሳሳኝ ዓብይ ነገር እርሰዎ ‹‹ይድረስ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ›› በሚል ርዕስ የጻፉትን ደብዳዳቤ  ከተመለከትኩ በኋላ ነው፡፡

እኔ የተገኘሁት ባለፈው የሰሎሞናዊ ሥርዓት ተብዬ አገዛዝና የሥርዓቱ  ተጠቃሚዎች ይህን ሕዝብ በቋንቋው፣ በባህሉና በታሪኩ በአጠቃላይ በማንነቱ ምክንያት እነሱ ‹‹እንንቀዋለን›› ከሚሉት የአገው የዘር ግንድ ከሆነው ‹‹ቅማንት›› ከሚባል ጎሳ ነው፡፡

ቅማንት የሚኖረው በአማራ ክልል በጎንደር ክፍለ አገር በተለያዩ ወረዳዎች ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ የሕዝቡ ብዛት ወደ አንድ ሚሊየን ይጠጋል ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህ ሕዝብ የራሱ ባህል፣ ቋንቋና ታሪካዊ አመጣጥ ያለው ቀደምት ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ነው፡፡ ነገር ግን ገዥዎች በተለያዩ ጊዜያት ባሳደሩበት ጫና አብዛኛው ሕዝብ ከመሬቱ ላለመነቀል ሲል ራሱን ‹‹አማራ ነኝ›› ብሎ እንዲጠራ ተገዷል፡፡

 ማንነቱን ጠብቆ ያለው ሕዝብ ደግሞ ዛሬም ቢሆን ከዘር አድልኦ ሳይላቀቅ ቀደምት አባቶቹ የደረሰባቸውን የዘር አድልኦ በባሰ ሁኔታ በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡ ከድሮ የጭቆናና የአድልኦ አገዛዝ ያልተላቀቁ የክልሉ ገዥዎች ዛሬም በዚህ ሕዝብ ላይ ከወላጆቻቸው የወረሱትን የጭቆና ቀንበር ጭነውበታል፡፡

በግሌ  ለብዙ ዓመታት አንድ ሕዝብ፣ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ባህል የሚል አቋም  አራማጅ ነበርኩ፡፡ ስለእኔ ይህን ያህል ካስተዋወቅኩ ወደ ዋናው ፍሬ ነገር ልግባ፡፡ ሰሞኑን ለአሜሪካን ፕረዚዳንት ኦባማ  የጻፉትን ደብዳቤ ካነበብኩ በኋላ፣ እርሰዎ በዋና ዳሬክተርነት የሚመሩትን የፖለቲካ ድርጅት (ንቅናቄ) የፖለቲካ ርዕይ፣ ተልዕኮ፣ ግብና ዓላማ በወፍ በረር (Bird’s Eye View) ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡

አሁን ያለንባት ኢትዮጵያ ያለፉት ሥርዓቶች መልካምና መልካም ያልሆኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ ብሎም የሕዝቦች ባህል፣ ልምድና ቋንቋ መስተጋብር ድምር ውጤት የተገኘች ናት፡፡ እኛ ደግሞ በተራችን ለቀጣዩ ትውልድ የምናስረክባት ኢትዮጵያ ከእኛ በፊት የተፈጸሙትንና በእኛ ዘመን የተከናወኑ መልካምና መጥፎ ድርጊቶች ድምር ለቀጣይ ትውልድ ያለፈውን ደምረን ወይም ቀንሰን በተራችን እናስተላልፋለን ማለት ነው፡፡

በዚህ ሒደት ውስጥ  የእኛ ትውልድ ሁለት ትላልቅ የቤት ሥራዎች እንዳሉበት እገነዘባለሁ፡፡ አንደኛውና ዋነኛው ባለፈው የአገዛዝ ዘመን የተበላሸውንና ወደዚህ ትውልድ የተጋባውን  የተዛባ የአገዛዝ ዘመን ስንክሳር፣ በሕዝቦች መካከል  ሥር የሰደደውን የእርስ በርስ መቃቃር ማለትም ባለፈው ሥርዓት ‹‹በደል፣ አድልኦና መገለል ደርሶብናል››  የሚሉ ሕዝቦች  ይኼኛው ትውልድ (ከበዳይ ወገን) ያልነበረበትን ዘመን ሒሳብ እንዲያወራርድ የሚያስብ አለ፡፡

በሌላ ጎን ደግሞ ባለፈው ሥርዓት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአንድም ሆነ በሌላ የሥርዓቱ ተጠቃሚ ‹‹ነበርን›› የሚሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ቡድኖች  ሕዝቦችን አንዱ ተገዥ ሌላኛው ገዥ አድርጎ የነበረው ሥርዓት በመወገዱ ጥቅማቸው የተጓደለ የሚመስላቸው የዚያ ሥርዓት አቀንቃኞችን  ከዚያ የባለፈ ዘመን አስተሳሰብ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ በተለያዩ የአስተሳሰብ ጎራዎች የተሠለፉ የአንድ አገር ሕዝቦችን አስተካክሎ መሀል ሜዳ ላይ እንዲገኛኙ ማድረግ  በእኛ  ትውልድ ላይ የተጫነ ከባድ  የቤት ሥራ  ይመስለኛል፡፡ ሁለተኛውና ሌላኛው ነጥብ  በዚህ ትውልድ በተራ ቁጥር አንድ የተጠቀሰው አስተሳሰብን ለመጨረሻ ጊዜ ቀብሮ በአዲስ አስተሳሰብ ለዚህና ለቀጣዩ ትውልድ ማስረፅና ከድህነት የተላቀቀችና የበለፀገች ኢትዮጵያን ማስረከብ አሁንም የዚህ ትውልድ ሥራ ይሆናል፡፡

እነኝህ ከላይ የጠቀስኳቸው መሠረታዊ ነገሮች እንዲሳኩ ጠንካራ የግል አቋሜና ዕምነቴ ቢሆኑም በተግባር ግን በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉ አዝማሚያዎች ለዚህ የሚያበቁ አካሄዶች አይመስሉኝም፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚገኙ ሕዝቦች፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና የማኅበረሰብ ሚዲያዎች በዚህ አቅጣጫ እየሠሩ እንዳልሆነ ለማንም የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ይልቅ በተቃራኒው ኢትዮጵያ በፍጥነት ፈራርሳ እንደ ጎረቤት መንግሥት አልባ አገሮች ለማድረግ ዘመቻ ላይ የተሰማራን ያህል ይሰማኛል፡፡ ለዚህ አስፈሪና መፃኢ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ በዋነኛነትና በብቸኝነት እየተከሰሰ ያለው እርሰዎ ለተወነ ጊዜም ቢሆን በከፍተኛ የአመራር ሰጪነት  ያገለገሉት በኢሕአዴግ የሚመራው ‹‹በጎሳ ላይ የተመሠረተ›› እየተባለ በአብዛኛው በዳያስፖራ ፖለቲከኞችና  በአገር ውስጥ በተቋቋሙ የፖለቲካ ድርጅቶች ውርጅብኝ የሚወርደበት የኢትዮጵያ  የፌዴራል ሥርዓት ነው፡፡

ይህን ስል በማንኛውም አገር እንደሚከሰተው የአመራርና የአስተዳደር እንከኖች ኢሕአዴግ የሚመራው የፌዴራል ሥርዓትም የራሱ የሆነ ችግር የለበትም የሚል ሐሳብ አላራምድም፡፡ ቁም ነገሩ ግን ይህ ሥርዓት በመርህ ደረጃም ቢሆን የሕዝቦችን እኩልነትና የማይገሰስ ልዕልና በሕገ መንግሥቱ አፅድቋል፡፡ እርስዎ የተገኙበት ሕዝብም ቢሆን የሥልጣን ደረጃው ይለያይ እንጂ ቢያንስ ራስን በራስ የማስተዳደሩ ጅምር መኖሩን በዓይናችን እየተመለከትን ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን ምንም ዓይነት ችግር የሌለበት አስተዳደር በጋምቤላም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት አባል ክልሎች ሰፍኗል ማለት እንዳልሆነ ግንዛቤ ይያዝልኝ፡፡ ምክንያቱም ዲሞክራሲ ሒደት ነውና በአንድ ጀንበር የሚገነባ አይደለም፡፡

አሁን በኢትዮጵያ እየተከሰተ ላላው የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የሰብዓዊ መብት መጓደል፣ የፍትሕና የዲሞክራሲ እጦት ሥርዓቱ ኃላፊነት የለበትም ባይባልም፣ ነገር ግን የዚህ ሁሉ ድርጊት ተጠያቂው የኢሕአዴግ መንግሥት ብቻ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት የሚያመላክቱ ብዙ ማሳያዎችን ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ አንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ በዳያስፖራው አማካይነት የተቋቋሙና በገንዘብ የሚደገፉ ድርጅቶች ዛሬም ቢሆን የሚያቀነቅኑት የኢትዮጵያ ሁሉም ሕዝቦች በእኩልነትና በመከባበር እንዲኖሩ አይደለም፡፡ ያ ያለፈ ሥርዓት አንድ ሕዝብ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ቋንቋ አባዜ የተለከፉ መሆናቸው የዚህን መንግሥት ድርጊት ለማኮሰስ ያላቸው የተቻኮለ አስተሳሰብ ጭምር የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡

የጋምቤላ ሕዝብም ሆነ ሌላው ኢትዮጵያዊ የሚፈልገውን ዓይነት ፍትሕ፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር በተለያዩ ምክንያቶች ተነፍጎ ሊሆን ይችላል፡፡ ተነፍጓል ብለን እንስማማ፡፡ ይሁን እንጂ እናንተ ከጎናቸው ሆናችሁ በፖለቲካው ረገድ ትብብር እያደረጋችሁላቸው ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች አባላት የጋምቤላ ሕዝብ ራሱን በራሱ ማስተዳደሩ፣ በእነሱ ላይ የተቃጣ ውርደት አድርገው የሚቆጥሩ ግለሰቦች ይህን ሁኔታ ወደነበረበት ቦታ ለመመለስ የራሳቸውን የፖለቲካ ድርጅት አቋቁመው በውጭም በአገር ቤትም ውር ውር ሲሉ በግልጽ ይታያሉ፡፡

ዛሬ የጋምቤላ፣ የቤንሻንጉል፣ የሶማሌ፣ የአፋርና ሌሎች ጭቁን ብሔሮች በራሳቸው የውስጥ አስተዳደር መተዳደራቸው፣ ቋንቋቸውን ማሰደጋቸውና ታሪካቸውን መንከባከባቸው በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣ አደጋ አድርገው የሚመለከቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ የሥርዓቱን ምንነት በውል ሳይረዱ በኢሕአዴግ የሽግግር መንግሥት ማግሥት ነፍጥ አንስተው ጫካ የገቡ ፋኖዎች መንግሥት የመሆን ዕድሉን ቢያገኙ ኖሮ፣ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በጅምር መልክም ቢሆን የተጎናፀፉትን መብት እነዚህ ፋኖዎች ሥልጣን በያዙ ማግሥት አሽቀንጥረው እንደሚጥሉት ከድርጊታቸው መገንዝብ ይቻላል፡፡ እነዚህ ያለፈው ሥርዓት ናፋቂዎች ያሰማሯቸው ፀረ ሰላም ኃይሎች ለተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ያላቸውን ንቀት በየደረሱበት በግልጽ እንደሚያንፀባርቁ እኛ ችግሩ የደረሰብን የቅማንት ሕዝቦች እናውቀዋለን፡፡

በግልጽ ሁሉም እንደሚገነዘበው ኢሕአዴግ በርግጥ በአሁኑ ጊዜ በጥቂት ግለሰቦች አጅ የወደቀ መሆኑና በቡድን የፖለቲካ አዙሪት እየተተራመሰ መሆኑን ማንም ተራ ኢትዮጵያዊ ያውቀዋል፡፡ ኢሕአዴግ በሕገ መንግሥቱና በፖለቲካ ፕሮግራሙ ካስቀመጣቸው በተቃራኒ እየነጎደ ለመሆኑ ብዙ ማሳያዎች ማንሳት ይቻላል፡፡ ድርጅቱ የግልና የቡድን ጥቅም በሚያራምዱ የድርጅት አባላት እጅ መውደቁን ለማወቅ ጠንቋይ መጠየቅ አያስፈልግም፡፡ ድርጅቱ በዚህ መንገድ ከቀጠለ ነገ ራሱን በራሱ እንደ ደርግ ጠልፎ እንደሚጥል ጥርጥር የለውም፡፡ ይሁን እንጂ ‹‹ከኢሕአዴግ  በተቃራኒ ተሠልፈናል›› የሚሉ የዳያስፖራና የአገር ውስጥ ፖለቲከኞችን አቋም በትክክል ለተገነዘበ ሁሉ የመንግሥትነት ዕድሉን ቢያገኙ፣ አገሪቱንና የአገሪቱን ሕዝቦች ወዴት አቅጣጫ እንደሚወስዷት መገመት ይቻላል፡፡ በእርግጥ የኢሕአዴግ ሥርዓት ይህ ዓይነት ጨለምተኛ አመለካከት ያነገቡና የኢሕአዴግን የፖለቲካ አባልነት ካርድ የተሸከሙ፣ ነገር ግን በተግባር ከአፍራሽ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በመሠለፍ እንቅስቃሴ እያደረጉ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡

በኢሕአዴግ ውስጥ የተሰገሰጉ የድርጅት አባላትም ሆኑ በግልጽ በተቃዋሚ ጎራ የተሠለፉ የሕዝቦችን የእኩልነት መብት መቀበል አይፈልጉም፡፡ ለአብነት የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በክልሉ የሚገኙ ሕዝቦችን ጨፍልቆ ለመግዛት ካለው  ድብቅ ፍላጎት የተነሳ፣ የብሔር ዕውቅናና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ያነሱ አንደ ቅማንት ያሉ ሕዝቦች በኃይል ጥያቄያቸው እንዲጨፈለቅ በመሥራት ላይ መሆኑ ግልጽ  ነው፡፡ በእነዚህ ሕዝቦች ላይ በዞንና በወረዳ አመራሮች የተደራጁ ጽንፈኛ ቡድኖች በቅማንት ሕዝብ ላይ ጦርነት አውጀዋል፡፡ በግልጽ የጦር መሣሪያ እያስታጠቁ ወደ ቅማንት ሕዝብ ለወረራ አሰማርተዋል፡፡

በመሆኑም እጅግ ብዙ የሆኑ አርሶ አደሮች ከቀያቸው እየተፈናቀሉ ይገኛሉ፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች በዘራቸው ምክንያት ከሚሠሩበት ቦታ እየተባረሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሲደረግ አንድም የፍትሕና የፖሊስ ተቋማት ድርጊቱን ለማስቆም አልተንቀሳቀሱም፡፡ ይሁን እንጂ የድርጅቱ ሕዝባዊ መስመር ሳይሸራረፍ እንዲተገበር በፅናት በሚታገሉ አንዳንድ ነባር ታጋዮች አማካይነት ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄው እልባት እንዲያገኝ በመታገል፣ ይህ ሥርዓት አልበኝነት ከመስመር ሳይወጣ ለመቆጣጠር ጥረት በማድረግ  ላይ ይገኛሉ፡፡

እርስዎ በስሞታ መልክ ለፕሬዚዳንት ኦባማ ‹‹አቤት›› ያሉላቸው በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ሁለት የፖለቲካ ድርጅቶች ሒደት ከፅንሰ ዕለታቸው አስካሁን ያላቸው አቋም ቢመረመር፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሕዝቦች ልዩነታቸውን ይዘው ተከባብረው እንዲቀጥሉ የማይፈልጉና አንድን ብሔር ከሌላኛው የሚያበላልጡ የድሮ ሥርዓት ናፋቂዎች ናቸው፡፡ ይህ ባይሆን ኑሮ በቅማንት ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ ቢያንስ ተቃውመው ይቆሙ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እነሱ ተገኝተንበታል የሚሉት ሕዝብ ከጋምቤላም ሆነ ከሌላ አካባቢ ሲፈናቀል ዓለምን በሙሉ ሲያደነቁሩ ይውላሉ፡፡ ይህን ስል ማንም ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ ምድር በነፃ ተንቀሳቅሶ የመኖርና የመሥራት መብቱን እየተቃወምኩ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡ በሌሎች ክልል በግፍ እንዲባረሩ የተደረጉ አማርኛ ተናጋሪ ሕዝቦች የደረሰባቸው ግፍ ሁላችንንም ያሳዝነናል፡፡

በውጭ አገር በሚኖሩ ፅንፈኛ ግለሰቦች በሚሰበሰብ ገንዘብ በሕዝብ ላይ የሚተኮስ የጦር መሣሪያ መግዣ እየዋለ ያለውን ገንዘብ እርስዎ ጠበቃ የቆሙላቸው ድርጅቶች ጭምር እንዲዋጣ አስተባብረዋል፡፡ ከአሜሪካና ከአውሮፓ በሚላክ ገንዝብ አማካይነት በሕገ መንግሥቱ  መሠረት የውስጥ የራስ አስተዳደር የጠየቀ ሕዝብን ‹‹ለምን?›› በሚል ጦርነት አሳውጀውበታል፡፡ ለድርጊታቸው የሚጠቀሙት ሽፋን ደግሞ ኢትዮጵያ ተበታተነች፣ ተቆራራሰች፣ ይኼኛው ቦታ ወደዚህኛው ክልል ተከልሏል ወይም ሊከለል ነው  የሚል ተራ አሉባታ በመንዛት ነው፡፡

ይህን ስል ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ትክክለኛ የብዙኃን ሥርዓት እንዳይሰፍን እያደረገ ያለው አፍራሽ ተልዕኮ እንዳለ ቢሆንም፣ በመጀመርያ የእነዚህ ድርጅቶች በየወቅቱ እንደ አክርማ መሰነጣጠቃቸው በኢሕአዴግ አፍራሽ ተልዕኮ ብቻ የመጣ ሳይሆን፣ የድርጅቱ አባላት በተጣባቸው  የሥልጣን ጥም ጭምር መሆኑን ሁላችንም ልንገንዘብ ይገባል፡፡ እነሱ በመጀመርያ አንድ ቢሆኑ ኑሮ ኢሕአዴግ በውስጣቸው ሊገባበት የሚችልበት ቀዳዳ አያገኝም ነበር፡፡

በግልጽ እርሰዎ በደብዳቤዎ እንዳመለከቱት በቀጣይ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል መተንበይ ባይቻልም፣ ከዚያ በባሰ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በተቃዋሚ ድርጅቶችና በዳያስፖራ የሕዝብ መገኛኛ የሚደሰኮረው እኩይ ንግግር ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ትልቅ ሥጋት መሆኑን መረሳት የለበትም፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባን ሌላኛው ነጥብ የኢትዮጵያን ችግር የሚፈቱት የአሜሪካ ወይም የአውሮፓ መሪዎች ሳይሆኑ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ናቸውና የመፍትሔ ሐሳባችሁ የኢትዮጵያን ሕዝብ ያማከለ መሆን አለበት፡፡ ካልሆነ ግን ለህልውናችን ስንል አሠላለፋችን በተዛባ መንገድ ላይ ይሆንና እርስ በራሳችን የጉግ ማንጉግ ጦርነት ውስጥ እንዳንዘፈቅ እፈራለሁ፡፡ እናንተ በዴሞክራሲያዊነታቸው የምታሞግሷቸውና ገንዘብ የምታዋጡላቸው ድርጅቶች፣ በተለያዩ ሕዝቦች ላይ እየደረሰ ያለውን በደል በስውር እየመሩ መሆናቸውን ብትገንዘቡ መልካም ነው፡፡

የፖለቲካ መመርያችሁ (Motto) ‹‹ከጎሳ (ከዘር) ይልቅ ሰብዓዊነት ይቅደም›› ይላል፡፡ ግን በዘራቸው ምክንያት ከምድረ ገጽ እንዲጠፉና የዘር ማጥፋት የሚካሄድባቸው ጎሳዎች  በምን መልክ እንዲከላከሉ ትመክሯችዋላችሁ? አንድ ጎሳ ራሱን ለመከላከል የሚያደርገው  ድርጊት ዘረኝነት ይባላል? በቦታና በወንዝ አንድነት ስም ግፍ እየደረሰባቸው ላሉት ሕዝቦች ምን ትላላችሁ? ምናልባት በቅማንት ሕዝብ ላይ በአሁኑ ጊዜ እየደረሰ ያለበትን ግፍ ለማሳያ ያህል ከፈለጋችሁ የተደራጀ ሪፖርት እናቀርብላችኋለን፡፡ ምናልባት ይህም ዘረኝነት ይሆን? ለፍትሕ ከቆማችሁ በቅማንት ሕዝብ ላይ በዳያስፖራ በሚመራው የፖለቲካ አደራጅነትና በውስጥ ተላላኪዎች እየደረሰበት ያለውን ግፍ ለዓለም አሰሙልን፡፡ ሕዝባዊነት ማለት ይህ ነው፡፡ ድል ለኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...