ኢንጂነር ብርሃኑ አባተ፣ የኢትዮጵያ የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማኅበር የቦርድ ሊቀመንበር
የኢትዮጵያ የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማኅበር በአሜሪካ በካሊፎርኒያ ግዛት በኢንጂነር ብርሃኑ አባተና በኢንጂነር ሥዩም ገበየሁ አነሳሽነት የተቋቋመው በ1994 ዓ.ም. ነው፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ወደ አዲስ አበባ የተዛወረው ደግሞ በ2001 ዓ.ም. ሲሆን በትምህርት፣ በጤናና በሥልጠና የመንግሥትንና የኅብረተሰብን የልማት ጥረት በማገዝ ላይ ይገኛል፡፡ ዓላማው በትምህርት ቤቶችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች ውስጥ ያለውን የመጻሕፍትና የትምህርት መሣሪያዎች እጥረት ማቃለል፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ የማንበብ ልምድና ባህልን በማዳበር አጠቃላይ ግንዛቤን ማሳደግ፣ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት እስከ ወረዳ ማዳረስ ሲሆን፣ በልማት ከበለፀጉት አገሮች ለትምህርት ልማትና ለጤና የሚጠቅሙ ቴክኖሎጂዎችን፣ ልምዶችን፣ ምርጥ ተሞክሮዎችንና የማቴሪያል ዕርዳታዎችን በማስመጣት፣ በማስረጽና ከአገሪቷ ተጨባጭ ፍላጎት ጋር አዛምዶ ተግባራዊ በማድረግ የአገሪቱን የልማት ጥረት ማገዝ ነው፡፡ ኢንጂነር ብርሃነ አባተ የማኅበሩ የቦርድ ሊቀመንበር ሲሆኑ፣ ኮሎኔል ካሳሁን ጌታቸው ደግሞ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ከሪፖርተር ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩን ለመመሥረት ያነሳሳችሁ ምንድን ነው?
ኢንጂነር ብርሃኑ፡- በደርግ ጊዜ ቢያቋርጡብንም ባብዛኛው ስንሠራ የነበረው በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ነው፡፡ በርታ የሚባል የኮንስትራክሽን ድርጅት አቋቁመን ነበር፡፡ በደርግ ጊዜ አገር ለቀን ከወጣን በኋላ ከጓደኛዬ ኢንጂነር ሥዩም ገበየሁ ጋር ኢትዮጵያን እንዴት ማሳደግ እንደምንችል ስንወያይ ቅድሚያ የሰጠነው ለትምህርቱ ነበር፡፡ በወቅቱ በኢትዮጵያ በጣት የሚቆጠሩ ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ቢኖሩም አገሪቱ ትምህርት ለማስፋፋት እየሠራች ነበር፡፡ እኛም የበኩላችንን ለማገዝ ኮምፒዩተሮችና የመማሪያ መጻሕፍት ብናቀርብ አገሪቱን እንጠቅማለን ብለን ተነሳን፡፡ ከዚያም የኢትዮጵያ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማኅበርን በካሊፎርኒያ መሠረትን፡፡ አንዳንድ ድርጅቶች የመማሪያ መጻሕፍት በነፃ እንደሚሰጡን ቃል ገቡልን፡፡ 100 ዶላር የሚያወጣ መጽሐፍ በነፃ አግኝተን 5 ዶላር ከፍለን ወደ ኢትዮጵያ ብናጓጓዝና ብናሰራጭ ያዋጣል በሚል ነው የጀመርነው፡፡ ባለፉት 14 ዓመታት እንዳሰብነውም ባይሆን ሠርተናል፡፡ መነቃቃትን ፈጥረናል፡፡ ብዙ መማሪያ መጻሕፍትን አምጥተናል፡፡ በአሜሪካ ተማሪዎች ትምህርት ሲጨርሱ መጻሕፍታቸውን ኮንቴነር ይጨምሩታል፡፡ ይህንን መጻሕፍት ኢንተርናሽናል ቡክ ባንክ፣ ቡክ ፎር አፍሪካ የሚባሉ የተለያዩ ድርጅቶች አንስተው ለታዳጊ አገሮች ይሰጡታል፡፡ ብዙ የአፍሪካ አገሮች በዚህ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግን አልነበረችም፡፡ በመሆኑም ጠይቀን እንደምንፈልገው ዓይነት መጻሕፍት በነፃ እንደሚሰጡን፣ ማጓጓዣው ግን የኛ ወጭ እንደሆነ ነገሩን፡፡ አገሪቷ በምትፈልገውና እኛ በመረጥነው መሠረት መጻሕፍት አዘጋጅተው ያቀርቡልናል፡፡ እስከ ጅቡቲ ልከን ከዛም አገር ውስጥ ገብቶ ለሚፈልጉ አካላት እናከፋፍላለን፡፡ አገር ውስጥ ያሉት ሲወስዱ ካጓጓዝንበት 5 በመቶ የማይሞላ ገንዘብ እናስከፍላለን፡፡ በዚህ መልኩ የትግራይ ልማት ማኅበር 20 ኮንቴነር፣ ትምህርት ሚኒስቴር 20 ኮንቴነር አዘውን አምጥተናል፡፡ አንድ ኮንቴነር እስከ 20 ሺሕ መጽሐፍ ይይዛል፡፡
ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲዎች አያዙም?
ኢንጂነር ብርሃኑ፡- የሚገርመኝ ይህ ነው፡ አያዙም፡፡ በጀት እንጠብቃለን ይላሉ፡፡ አሁንም ቢሆን የተሟላ መጻሕፍት አላቸው ብለን አናምንም፡፡ በከፍተኛ ውጭ ምንዛሪ የሚገዙ መማሪያ መጻሕፍትን ለትራንስፖርት ከሚወጣው በጣም ጥቂቱን ከፍሎ መውሰድ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ብዙ የግል ትምህርት ቤቶችና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚፈልጉት አይነትና መጠን አስመጥተንላቸው ወስደዋል፡፡ ከመዋለ ሕፃናት ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲዎች ድረስ ዘመኑ የደረሰባቸውን የመማሪያና የማጣቀሻ መጻሕፍት በነፃ ሰብስበንና የትራንስፖርት ሸፍነን ነው የምናመጣው፡፡ ኮምፒዩተሮች ግን ከፍለን ሲሆን ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት የሠሩና በጥሩ ደረጃ ያሉ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ከመጽሐፍ አቅርቦቱ ጋር ተያይዞ የማኅበሩን የትምህርት ድጋፍ ፕሮግራም ቢያብራሩልን?
ኢንጂነር ብርሃኑ፡- የትምህርት ፕሮግራሙ ዓላማ ትምህርት ቤቶች፣ በየደረጃው የተቋቋሙ የንባብ ቤቶች፣ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት የሚያስፈልጓቸው፣ ተፈላጊ መማሪያ፣ ማስተማሪያ ማጣቀሻ መጻሕፍት፣ የላቦራቶሪ መሣሪያዎችና ኮምፒዩተሮች እንዲሁም ሌሎች ለትምህርት አገልግሎት ብቃትና ጥራት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እንዲሟላላቸው ማድረግ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ የትምህርት ቤቶችና ክፍተኛ የትምህርት ተቋሞች በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ አቻ ተቋሞች ጋር የእህትማማችነት ፕሮግራም እንዲመሠረት ጥረት አድርገናል፡፡ ዓላማችንን ተግባራዊ ለማድረግ በትምህርት ድጋፍ ፕሮግራሙ ሥር በመሠረታዊ የትምህርት ግብዓቶች ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶችም ተቀርጸው ሥራ ላይ ውለዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በጤናው ዘርፍ የምታደርጉት ድጋፍ ምን ይመስላል?
ኢንጂነር ብርሃኑ፡- በሰሜን አሜሪካና በካናዳ ከተቋቋሙ የኢትዮጵያውያን የጤና ባለሙያዎች የዳያስፖራ ማኅበር ጋር በመተባበር ሠርተናል፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር አባላቱን ማለትም የሕክምና ዶክተሮችንና ስፔሻሊስቶችን ወደ ኢትዮጵያ በማስመጣትና ነፃ አገልግሎት በመስጠት ረገድ የአየር ትራንስፖርት ማጓጓዣ ወጪ እንዲሸፈን፣ ጉዳዩን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ አቅርቦ ከሚፈለገው ጠቅላላ ወጪ 50 ከመቶ ቅናሽ በማስፈቀድና ቀሪው 50 ከመቶ ከራሱ ካዝና ማለትም ከ294 ሺሕ ብር በላይ ወጪ በመሸፈን ፕሮጀክቱ እንዲሳካ ድጋፍ ሰጥቷል፡፡ በጤናው ዘርፍ በተለይ ፋሲሊቲ በማሟላት ላይ በቀጣይ እንሠራለን ብለን አስበናል፡፡ እንዳየነው ክፍተቶች አሉ፡፡ ሁሌ የሚሰማው እንዲህ አደረግን የሚለው እንጂ ጉድለቱ አይደለም፡፡ ችግር አለ፣ ክፍተት አለ ብሎ ቢነገር ክፍተቱን ለመሙላት እንሠራለን፡፡ ሁሌ ጥሩ ነው ከተባለ ግን ችግሩ እንዳለ ይቀጥላል፡፡ በዚህ ጊዜ ችግሩን የሚሸከመው ሕዝቡ ነው፡፡ በየጤና መስጫው ዳሰሳ ስናደርግ ከመድኃኒት፣ ጓንት ጀምሮ ችግር ያለበት አጋጥሞናል፡፡ መንግሥት በጀት ለመመደብ ይከብደዋል፡፡ እኛ ተባብረን መሥራት አለብን፡፡ ተባብረን የምንሠራውና ለውጥ የምናመጣው ደግሞ መንግሥት ችግሮቹን ግልጽ አድርጎ ሲያሳውቀን ነው፡፡ እዚህ ላይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ እኛ ለምሳሌ ትምህርት ቤቶች ላይ የምናደርገው ድጋፍ በጣም ጥቂት ቢሆንም ግን ይጠቅማል፡፡ የመጻሕፍት ድጋፍ ፕሮጀክታችን አንዱ ዓላማው በትምህርት ቤቶቻችን የሚታየውን አሳሳቢ የመጻሕፍት እጥረት ለመቅረፍና በተለይም በትምህርት ቤቶች ውስጥ የቤተ መጻሕፍት አገልግሎትን በመጻሕፍትና በቁሳቁስ በማጠናከር የመማር ማስተማሩን ተግባር ለማገዝ ነው፡፡
ዓላማውን ለማሳካት የውጭ ዕርዳታ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ማኅበሩ በአሜሪካ፣ በካናዳና በእንግሊዝ አገር ከሚገኙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ በእነዚህ አገሮች ከሚኖሩ አገር ወዳድና ተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያን ማኅበራትና ግለሰቦች ጋር ግንኙነት በመፍጠር በተደረገው ዕርዳታ የማሰባሰብ ጥረት 1,755,000 ልዩ ልዩ መጻሕፍት ማግኘት ተችሏል፡፡ ዕርዳታውን አጓጉዞ ወደ አገር ለማስመጣት በየጊዜው የሚደረገው ወጪ ምንም የገቢ ምንጭ በሌለው ማኅበር ላይ ከባድ ጫና ስለሚያስከትል የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች ማቴሪያሉን በነፃ እያገኙ ለትራንስፖርት የተደረገውን ወጪ ግን በሚወስዱት ዕርዳታ መጠን እየታሰበ አነስተኛ ክፍያ እንዲከፍሉ ማኅበሩ ፖሊሲ በማውጣቱ በዚህ መልክ እየተሠራ ይገኛል፡፡
ሪፖርተር- የፕሮጀክቱን ተጠቃሚዎች እንዴት ነው የምትለዩት?
ኢንጂነር ብርሃኑ፡- የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች ሕጋዊ ዕውቅና ያላቸው ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሥር የተደራጁና በከተማ የሚገኙ ቤተ መጻሕፍትና የወጣት ማኅበራት በትምህርትና ሥልጠና ዙርያ የሚንቀሳቀሱ አገር በቀል ድርጅቶችና የልማት ማኅበራት ናቸው፡፡ ከየአገራችን የትምህርት ማኔጅመንትና አስተዳደር በአዲሱ ፖሊሲ ምክንያት ወደ ክልል እንዲወርድ ሲደረግ በክልል የትምህርት ቢሮዎች ላይ የተሰጠውን አዲስ ኃላፊነት ለማቃለል ማኅበራችን ኢንተርናሽናል ቡክ ባንክ ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅት በዕርዳታ ያገኛቸው 7.4 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያላቸው 20 ባለ 40 ኮንቴይነር መጻሕፍት ለትምህርት ሚኒስቴር ለመስጠት ስምምነት በመደረሱ ከጠቅላላው 248,031 የሚሆኑ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ መጻሕፍት ለ11 የክልል ትምህርት ቢሮዎች ሲከፋፈሉ የቀሩት 99,411 መጻሕፍት በወቅቱ ለነበሩት ስድስት ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲዎች ተከፋፍለዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በ1989 ዓ.ም. ስለጀመራችሁት የኮምፒዩተር አቅርቦት ፕሮጀክት ቢያብራሩልን?
ኮሌኔል ካሳሁን፡- የትምህርት ድጋፍ ፕሮግራም ካቀፋቸው ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የኮምፒዩተር አቅርቦት ፕሮጀክት ነው፡፡ ዓላማውም ትምህርት በዘመናዊ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እየታገዘ በጥራት እንዲሰጥ፣ ተማሪዎቻችን ከዝቅተኛ ክፍሎች ጀምሮ ስለኮምፒዩተር መሠረታዊ ዕውቀት ይዘው እንዲያድጉ፣ የትምህርት አመራርና አስተዳደር እንዲሁም ከፍተኛ ጊዜና ሀብት የሚጠይቀው የተማሪዎች የፈተና አዘገጃጀት፣ እርማትና ሪኮርድ አያያዝ ከወረቀት ሥራ ተላቆ ደረጃ በደረጃ ኮምፒዩተራይዝድ እንዲሆን፣ የመማር ማስተማሩ ተግባር ዘመናዊ ማድረግ ነው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ ባወጣው መመሪያ መሠረት የትምህርት ቤቶች የኮምፒዩተር ፍላጎት እየጨመረ ቢመጣም የኮምፒዩተሮች የገበያ ዋጋ ከትምህርት ቤቶች አቅም በላይ በመሆኑ የፕሮጀክቱን ጠቃሚነትና አስፈላጊነት ያጎላዋል፡፡ ዘመናዊ ትምህርት ያለ ኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ቀልጣፋም ሆነ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል በመረዳት ‹‹Computer Aid International›› ከተሰኘ ኢንተርናሽናል በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር እስካሁን 29 ኮንቴይነር ወይም 8,278 ኮምፒዩተሮችን በዕርዳታ በማስመጣት ከ800 በላይ ለሚሆኑ ትምህርት ቤቶች የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች ሰጥተናል፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ ጎን ለጎን ከትምህርት ቤት ውጭ የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ትሰጣላችሁ፡፡ የትኞቹን ክልሎች ተጠቃሚ አድርጋችኋል?
ኮሎኔል ካሳሁን፡- የቤተ መጻሕፍት አገልግሎቱን ከትምህርት ቤት ውጭ ለሚገኘው የኅብረተሰብ ክፍል ማለትም ጎልማሶች፣ ወጣቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ አዛውንት፣ እናቶች፣ ሕፃናት፣ ተደራሽ ለማድረግ ነው፡፡ ማኅበሩ ይህን ዓላማ ለማሳካት በመጀመሪያው ምዕራፍ በክልል ዋና ከተሞች ላይ ያተኮረ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ፕሮጀክት በማቋቋምና ፕሮጀክቱን ለማገዝ ፈቃደኛ የሆኑ ለጋሽ ድርጅቶችን በማፈላለግ እንቅስቃሴ የጀመረ ሲሆን ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ በተደረገው ጥረት ቡክ ኤይድ ኢንተርናሽናል ከተባለ ድርጅት ጋር በገባው የትብብር ስምምነት መሠረት አበረታች ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ የኅብረተሰቡን የንባብ ባህልና የወጣቱን አጠቃላይ ዕውቀትና ግንዛቤ ለማዳበር የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት የሚሰጠው ጥቅም በመረዳት ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር በጉለሌ፣ በልደታ፣ በቂርቆስና አራዳ ክፍላተ ከተሞች ከሚገኙ የቀበሌ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት መካከል በመምረጥ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ከተለያዩ የክፍለ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤቶች ጋር በመተባበር ለጊዜው ለስምንት የቀበሌ ቤተ መጻሕፍት በየዓመቱ የመጻሕፍት ድጋፍ የሚሰጥ ሲሆን በአዲስ አበባ ከሚገኙ ፌደራል ሆስፒታሎች መካከል ለአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ለዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታልና በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሥር ለሚገኘው የታራሚዎች ሆስፒታል የሜዲካል መጻሕፍት ድጋፍ ተዳርጓል፡፡ በአዲስ አበባና ጅማ ለሚገኙ ማረሚያ ቤቶች በየዓመቱ የመጻሕፍት ዕርዳታ የሚሰጥ ሲሆን ዘመናዊ ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ለገጠሩ ኅብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ በሐዋሳ፣ ባህር ዳር፣ መቀሌና ጅማ ከተሞች ውስጥ እያንዳንዳቸው 10,000 መጻሕፍትና 23 ኮምፒዩተር ያላቸው ዘመናዊ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት በማቋቋም አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል፡፡ ቤተ መጻሕፍቱም በሙሉ አቅማቸው መንቀሳቀስ ሲጀምሩ በየዓመቱ ለ1,400,000 አንባቢያን አገልግሎት እንደሚሰጡ ይገመታል፡፡
አሁን ያለው የማንበብ ባህል የሚቀየረው ሕፃናት ላይ ሲሠራ በመሆኑም ቤተ መጻሕፍቱ 2000 መጻሕፍት የያዙ የሕጻናት ኮርነሮች አላቸው፡፡ ከ70, 000 በላይ ኢቡክስ (e-books) በኔትወርክ አማካይነት ግልጋሎት ይሰጣሉ፡፡ ፕሮጀክቱ ለቤተ መጻሕፍት ሙያተኞችም ሥልጠናን ያካትታል፡፡ ኸኽኽት ሐሕ
ሪፖርተር፡- የመንግሥትና የኅብረተሰብ ተሳትፎ እንዴት ታዩታላችሁ?
ኢንጂነር ብርሃኑ፡- የማኅበሩን ዓላማ ለመተግበር ማኅበሩ በአገር ውስጥና ውጭ ከሚገኙት የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ቢሆንም ከዕርዳታው ጋር የተያያዙ በለጋሽ ድርጅቶች ሊሸፈኑ የማይችሉ በርካታ ተግባራት አሉት፡፡ የአገር ውስጥ በዋናነትም የመንግሥት ተሳትፎና ድጋፍ ካልታገዘ በስተቀር የሚፈለገውን ያህል ውጤት ማስመዝገብ አዳጋች ይሆናል፡፡ ማኅበሩ አሁን ባለበት ሁኔታ የተለያዩ ቁሳዊ ዕርዳታዎችን የማፈላለግና የማሰባሰብ አቅም ያለው ቢሆንም ከዚህ የዘለለ ወጪ የሚጠይቁ ተግባራት ለማከናወን የዳበረ አቅም የለውም፡፡ ለምሳሌ ያህል ዕርዳታዎች የሚገኙት ከኢትዮጵያ ውጭ እንደመሆኑ መጠን አጓጉዞ ወደ አገር ለማስመጣት ለመርከብ፣ ለኢንሹራንስና ከዚህ ጋር ለተያያዙ የወደብ አገልግሎቶች ወጪ እንደሚጠይቅ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ወጪው በውጭ ምንዛሪ መከፈል ስላለበት የማኅበሩ ተግባር በጣም ከባድና ውስብስብ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ የዕርዳታ አቅርቦት ችግር ሳይኖር ዕርዳታውን አስመጥቶ ለመጠቀም ባለው የፋይናንስ አቅም ውሱንነት ምክንያት ማኅበሩ በየዓመቱ በርካታ ዕርዳታዎችን አጥቷል፡፡ ወደፊትም ዕርዳታ ከማፈላለግ ውጭ ያሉት ከፋይናንስ ጋር የተያያዙ ተግባራት ባለቤት ካላገኙ በስተቀር ዕርዳታ የማፈላለጉ ጥረት የተፈለገውን ያህል ሊሆን አይችልም፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ በዕርዳታ የሚመጡት መጻሕፍት በዋናነት የሚፈለጉት በትምህርት ቤቶችና ተቋሞች በመሆኑ በሴክተሩ በየደረጃው የሚገኙት ባለ ድርሻ አካላትና በትምህርት ልማት ዙሪያ የተሰለፉት ብሔር አቀፍ የልማት ማኅበራት ፕሮጀክቶቹን እንደራሳቸው በመውሰድና በሚፈልጉት መንገድ በማስተካከልና በማዳበር ከማኅበሩ ጋር ተቀናጅተው በዕቅድ መሥራት የሚችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር አገራችን ሰፊ የዓለም አቀፍ ዕርዳታ ተጠቃሚ በመሆን የመንግሥትም ወጪ በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ እንደሚቻል ማኅበሩ ያምናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እንደ እኛ የመሰለ በጎ አድራጎት ድርጅት ዓላማውን ለማሳካት ሊያተኩርባቸው ከሚገቡ ተግባራት መካከል አንዱ ከመንግሥትና ከኅብረተሰቡ ጋር ያለው ግንኙነት የጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ብሎም ለዓላማው ተፈጻሚነት በርካታ አባላትና ደጋፊዎች በዙርያው ማሰለፍ በመሆኑ ማኅበራችን በዚህ ረገድ ያደረገው ጥረትና የተገኘው ውጤት እንደተጠበቀው ስላልሆነ ሁኔታውን በመዳሰስ አማራጭ ስትራቴጂን መቀየስ አስበናል፡፡
ሪፖርተር፡- የምናስበውን ያህል መሥራት አልቻልንም ብላችኋል፡፡ ምንድነው ችግሩ?
ኢንጂነር ብርሃኑ፡- በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከሚማሩበት የትምህርት መጻሕፍት ውጭ ብዙ ተጨማሪ ማጣቀሻ መጻሕፍት የላቸውም፡፡ ይህ የልጆቹን ዕውቀት ይገድባል፡፡ እኛ የምንችለውን ያህል ለማድረግ እንድንችል ከመንግሥት ጋር በቅርበት መነጋገር መቻል አለብን፡፡ መንግሥት በጀት ይዞ መጽሐፍ በሚፈለገው ደረጃ ለማሟላት ይቸግረዋል፡፡ እኛ አማራጭ ይዘን መጥተናል፡፡ መሥራት እንችላለን፡፡ ተማሪዎች ተጨማሪ መጽሐፍ እንደሚያስፈልጋቸው መታወቅ አለበት፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲህ ያሉ መጻሕፍት ያስፈልጉናል ብለው መጠየቅ አለባቸው፡፡ እኛ በብዙ ዶላር የሚገዛውን መጻሕፍት የምናመጣው በነፃ ነው፡፡ ተቋማትም በርካሽ ዋጋ ነው የሚወስዱት፡፡ በየመጋዘናችን አንድ መጽሐፍ ከ1 ብር እስከ 50 ብር ዋጋ ያላቸው ዘመናዊ መጻሕፍት አሉን፡፡ ካወጣነው የትራንስፖርት ዋጋ አምስት በመቶ ያህል ብቻ በመክፈል ማንኛውም የትምህርት ተቋማት መውሰድ ይችላሉ፡፡ ግን ምን ታደርጉልናላችሁ ተብለን መጠየቅ ሲገባን እኛ እየሄድን ነው ውሰዱ የምንለው፡፡ በጉምሩክ በኩል መጽሐፍ አይቀረጥም ቢባልም በአንድ ኮንቴይነር ከ50 ሺሕ እስከ 60 ሺሕ ብር ያስከፍሉናል፡፡ እኛ የምናመጣው በነፃ ለምነን ለዩኒቨርሲቲዎችና ትምህርት ቤቶች ነው፡፡ ግን ‘ዩኒቨርሲቲውን የራሱ በጀት አለው፡፡ እናንተ ምንድናችሁ?’ ይሉናል፡፡ መሥራት አለብን ብዬ የማምነው በጎ ፈቃደኝነት ላይ ነው፡፡ በአገራችን እያንዳንዳችን ያለንን መልካም አጋጣሚ መጠቀም፣ አገራችንን መርዳት አለብን፡፡ መንግሥት ሁሉን ማሟላት አይችልም፡፡ እርስ በርሳችን መደጋገፍና ወደ ውስጥ ማየት መቻል አለብን፡፡ ማኅበራችን አብዛኛውን መጽሐፍ በዕርዳታ ከውጭ ቢያመጣም ለአገልግሎት መስጫ የሚሆን ቤት ሰዎች በፈቃደኝነት ሰጥተውን ነው የምንሠራው፡፡ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ከሕንፃው አንድ ቢሮ በነፃ ሰጥቶን እየሠራንበት ነው፡፡ ዳር ሆነን ከማየት ከውስጥ ገብተን በበጎ ፈቃደኝነት ተባብረን መሥራት ከቻልን ገጠር ድረስ ገብተን በመማር ማስተማሩ ላይ እንሳተፋለን፡፡ ሚዲያውም በትምህርት ላይ በስፋት መሥራት አለበት፡፡ ስለሚሠሩ ማኅበራት መረጃ መስጠት አለባቸው፡፡ በየሜዳው ያለውን ወጣት ላይብረሪ ለማስገባት መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በመንግሥት ደረጃ ቀረጥ የሚከፍልና የማይከፍል መለየት አለበት፡፡ ጉምሩክ አካባቢ ለግል ትምህርት ቤት የምትሰጡ ከሆነ ይከፈላል ይሉናል፡፡ የትምህርት ጥራት የግል የመንግሥት ሳይል አብሮ በመሥራት የሚመጣ ነው፡፡ የማኅበራችን ዓላማም ለአገሪቱ የትምህርት ግብዓትን ማቅረብ ነው፡፡ ለሁሉም ተቋማትም እናገለግላለን፡፡ ከኛ ተሰብስባ የምትሄደው 40,000 ብር ሳይሆን መታየት ያለባት መጻሕፍቱ ተማሪው ላይ ምን ለውጥ ያመጣሉ የሚለው መሆን አለበት፡፡ ተቋማት ከማኅበሩ ተጠቃሚ እንዳይሆኑም የመረጃ ክፍተት አለ፡፡