Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የንግድ ሥራን በዕውቀት ለማስመራት የቆመው ማኅበር

በ1940ዎቹ በአብዛኛው በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩት ዓረቦች በተለይም የመኖች መሆናቸው ይወሳል፡፡ ቅድመ አብዮት በነበሩት ዓመታት ውስጥ ችርቻሮ የሚፈጸምባቸው ቦታዎች ‹‹ዓረብ ቤት›› (ሱቅ) በመባል ይታወቁ የነበሩት፣ ነጋዴዎቹ ዓረቦች ስለነበሩ ነው፡፡ በኋላ ላይ ኢትዮጵያውያኑ በብዛት ንግድ ውስጥ ቢገቡም የንግድ ሥርዓቱን እምብዛም የማያውቁ ይገኙ በነበረበት አጋጣሚ ነው፣ በ1942 ዓ.ም. በያኔ አጠራሩ ‹‹የንግድ ሥራ ወጣቶች ማኅበር›› የአሁኑ የንግድ ሥራ ትምህርት ምሩቃን ማኅበር የተቋቋመው፡፡ በአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ትምህርት ቤት (የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግድ ሥራ ኮሌጅ) የ1941 ዓ.ም. 12 ምሩቃን የተመሠረተው ማኅበር፣ በቀዳሚነት ባቋቋመው የንግድ ሥራ የማታ ትምህርት የመርካቶ ነጋዴዎችንና ስለ ንግድ ሥራ ትምህርት ፍላጎቱ ያላቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞች ተከታታይ ትምህርት በየዓመቱ በመስጠት አስመርቋል፡፡ ከሦስት ዓመታት በኋላ 70 ዓመት በሚሞላው ማኅበር ወቅታዊ የሥራ እንቅስቃሴ ዙሪያ የንግድ ሥራ ኮሌጁ የቀድሞ ተማሪና የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ሆነው እያገለገሉ የሚገኙትን ወ/ሮ ፋንታዬ ሸዋዬን ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡– ማኅበሩ መቼና እንዴት እንደተቋቋመ ቢያስረዱን?

ወ/ሮ ፋንታዬ፡- ማኅበሩ የተቋቋመው በ1942 ዓ.ም. ነው፡፡ ያቋቋሙትም በ1941 ዓ.ም. የተመረቁ 12 አባቶች ናቸው፡፡ ሊያቋቁሙት የቻሉበትም ከአዲስ አበባና ከየክልሉ መጥተው ለሁለት ዓመት የተማሩት በአዳሪነት ስለሆነ ከተመረቁ በኋላ እንዳይበታተኑ በማሰብ ሁልጊዜ ሊያገናኛቸው የሚችል አንድ ማኅበር እናቋቁም ከሚል ሐሳብ በመነሳት ነው፡፡ ይህንንም ሐሳባቸውን በወቅቱ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ለነበሩት ለዶ/ር ዊልያም ናጊብ አማከሯቸው፡፡ ዳይሬክተሩም ማኅበር ካቋቋማችሁ ሰፋ ባለ መልኩ ፕሮፌሽናል የምሩቃን ማኅበር አድርጉት፡፡ ወደፊትም ትምህርት ቤቱ እየሰፋ ስለሚሄድ የቀሩት ምሩቃን በወጡ ቁጥር ሊቀላቀሏችሁ ይችላሉ የሚል ሐሳብ ይመክሯቸዋል፡፡ ዶ/ር ዊልያም በዚሁ ሐሳብ ዙሪያ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ተነጋገሩበትና ከሚኒስቴሩም ዕውቅና ተችሮት ‹‹የንግድ ሥራ ወጣቶች ማኅበር›› በሚል ስያሜ ተቋቋመ፡፡ ቢሮውንም በትምህርት ቤቱ ውስጥ ከፈተ፡፡ ማኅበሩ በዚህ ስያሜ ሊጠራ የቻለው መሥራቾቹ በወቅቱ ወጣቶች ስለነበሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡– የንግድ ሥራ ወጣቶች ማኅበር ዓላማው ምን ነበር? ዓላማውን ለማሳካት ምን ዓይነት አካሄድ ያራምድ ነበር?

ወ/ሮ ፋንታዬ፡- በዛን ዘመን በአገራችን የንግድ ሥራ ትምህርት ብዙም አይታወቅም፡፡  ንግድ ሲባል እንደችርቻሮ ብቻ ነበር የሚታየው፡፡ ይህንን የችርቻሮ ሥራ ደግሞ ብዙም የአገር ልጆች ስለማይሠሩት ከየመን በመጡ ዓረቦች ብቻ ነበር ይካሄድ የነበረው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ኢትዮጵያውያን እያደር በሥራው መሳተፍ ጀመሩ፡፡ ይህም ሆኖ ግን የንግዱን ሥርዓት አያውቁትም ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የማኅበሩ መሥራቾች የንግድ ሥራ ትምህርት በኢትዮጵያውያን ዘንድ አይታወቅም፡፡ ስለሆነም በጣም ጠቃሚ ትምህርት መሆኑን ለኅብረተሰቡ ማሳወቅ አለብን ከሚል ተነስተው ነው የማኅበሩን ዓላማ የነደፉት፡፡ በዚህም የተነሳ መሥራቾቹ መርካቶ እየሄዱ ለኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች የመዝገብና የሒሳብ አያያዝ፣ ታክስ እንዴት እንደሚቀመጥ፣ ኪሳራና ትርፍ ምን እንደሆነ ወዘተ የሚያስረዳ ትምህርት በነፃ ይሰጡ ነበር፡፡ ትልልቅ ሱቅ ያላቸውና ነቃ ያሉ ነጋዴዎች ‹‹እኛ እኮ አሁን ትምህርት ቢኖር ኖሮ እንማር ነበር፡፡ ቀን እንዳንማር ንግዳችንን ያስተጓጉላል›› የሚል ሐሳብ መሰንዘር ጀመሩ፡፡ መሥራቾችና  አባላቱም ነጋዴዎችን ማታ ማታ እንድናስተምር ክፍል ይፈቀድልን ሲሉ ትምህርት ቤቱን ጠየቁት፡፡ ትምህርት ቤቱም ጥያቄያቸውን ተቀብሎ ፈቀደላቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ትምህርቱ እየሰፋ ከመጣ የመምህራን ችግር አላጋጠመም?

ወ/ሮ ፋንታዬ፡- በአስተማሪነት የተመደቡት ፈቃደኛ የሆኑ የማኅበሩ አባላትና የትምህርት ቤቱ መምህራን ናቸው፡፡ አባላቱ ከክፍያ ነፃ በሆነ መንገድ ነው ሲያስተምሩ የነበሩት፡፡ ለመምህራኑ  ግን መጠነኛ የሆነ ክፍያ ይሰጣቸው ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ውስጥ የንግድ ሥራ የማታ ትምህርት ማስተማር የጀመሩት የማኅበሩ አባላት ናቸው፡፡ የማታው ትምህርት ብዙ ፈላጊ እያገኘና እየታወቀ መጣ፡፡ በዚህም የተነሳ ሥርዓተ ትምህርቱ ሰፋ ብሎ ቢካሄድ ብዙ ሰው ይጠቀማል በሚል የተነሳ የማታውን ትምህርት ትምህርት ቤቱ ወሰደው፡፡ ይህም የሆነው ከማኅበሩ መሥራቾችና አባላት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት ከተደረገበትና ከስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ዓይነቱ አካሄድ ምሩቃኑ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ በተጨባጭ ቢገለጽ ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ፋንታዬ፡- ምሩቃኑ የማታ ትምህርቱን የጀመሩት በ1950ዎቹ የነበረውን የንግድ ሥራ ባለሙያ ዕጥረት በማጤን ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በሥራ ላይ የነበሩ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎቻችን በጽሕፈት ሥራ ሙያ፣ በቢሮ አስተዳደር፣ በሒሳብ መዝገብ አያያዝ ወዘተ አሠልጥነውና አስመርቀው በወቅቱ የነበረውን የባለሙያዎች ክፍተት እንዲቀረፍ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የማታው ትምህርት በትምህርት ቤቱ ሥር ከሆነ በኋላ በማኅበሩ አባላት መካከል ክፍተት አልፈጠረም?

ወ/ሮ ፋንታዬ፡- ትንሽ ክፍተት ተፈጥሯል፡፡ የትስ እንስባስባለን? ለምን ራሳችንን አንችልም? የሚል ጥያቄ በወቅቱ በነበሩት አባላት ዘንድ ተፈጠረ፡፡ በዚህም የተነሳ ከግል ኪሳቸው እያወጡ ትንሽ ገንዘብ ካጠረቃቀሙ በኋላ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት አካባቢ የማኅበሩ ክበብ አሁን ያለበትን 4,800 ካሬ ሜትር የሆነ ቦታ በ1954 ዓ.ም. ገዙ ገንዘቡን ከየትም ከየትም አጠረቃቅመውና ከራሳቸውም ኪስ ጨምረው በአሁን ጊዜ ያለውን የማኅበሩን አዳራሽ ሠሩ፡፡ የአዳራሹን ግንባታ በጀመሩበት ወቅት ግን የገንዘብ ድጋፍ ፍለጋ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘንድ ቀረቡ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም በጉዳዩ በጣም ተደስተው፣ አባላቱንም አበረታተው ለአዳራሹ ግንባታ የሚውል በግላቸው ወደ 35 ሺሕ ብር ለግሰዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን ለአዳራሹ ግንባታ የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል ይባላል፡፡ በዚህ ዙሪያ ቢያብራሩልን?

ወ/ሮ ፋንታዬ፡- ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን የትምህርት ቤቱ ምሩቅ ነው፡፡ በትምህርት ቤቱ የድራማ ክበብ ውስጥ ሆኖ ‹‹የእሾህ አክሊል›› በሚል ስያሜ የደረሰው ድርሰት ለትምህርት ቤቱ ተማሪዎች፣ እንዲሁም በብሔራዊ (ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) ቴአትር ለሕዝብ አቅርቦ ከፍተኛ ዝናን አትርፏል፡፡ በብሔራዊ ቴአትር በታየበት ወቅት የተገኘውን ገቢ በሙሉ ለአዳራሹ መሥሪያ እንዲውል አበርክቷል፡፡

    የአዳራሹ ግንባታ ተጠናቅቆ የተመረቀው በ1964 ዓ.ም. ሲሆን መርቀው የከፈቱትም አፄ ኃይለ ሥላሴ ናቸው፡፡ በሥነ ሥርዓቱም ላይ ባደረጉት ንግግር ‹‹ይህ ቤት በጽኑ ፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው›› በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህንንም አነጋገር እስከዛሬ ድረስ እንደ መመሪያችን አድርገን  እየተጠቀምንበት ነው፡፡ በቀድሞው ሥርዓት አዳራሹ ለመሠረተ ትምህርት አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ አሁንም ቢሆን የወረዳው አስተዳደር ስብሳባ ሲያደርግና አንዳንድ ዝግጅት ሲኖረው በነፃ ይገለገልበታል፡፡ ማኅበሩን ይህን ሊፈቅድ የቻለው የኅብረተሰቡ አንጡራ ሀብት ነው ከሚል በጎ አስተሳሰብ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ በገዛው በተለይ የሠራው አዳራሹን ብቻ ነው? ወይስ ሌሎች መገልገያዎች አሉት?

ወ/ሮ ፋንታዬ፡- አዳራሹ ሁለገብ ነው፡፡ የካፍቴሪያና ልዩ ልዩ የቤት ውስጥ ወጪዎች ያሉት ሲሆን ለስብሰባም ያገለግላል፡፡ ሦስት ቴኒስ ሜዳዎችና በተሟላ የመገልገያ መሣሪያ የተደራጀ ጅምናዚየም፣ ቢሮና የኢንተርኔት አገልግሎት አሉት፡፡ በስተጀርባውም ባለ አንድ ፎቅ ቤትም አለው፡፡ በቅርቡም የመረብና የቅርጫት ኳስ ሜዳዎችን ለማሠራት እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ያሉት አባላት በዕድሜ እየገፉና እየደከሙ ሲሄዱ የሚተኳቸውን ወጣቶች ለማሰባሰብ ምን የታሰበ ነገር አለ?

ወ/ሮ ፋንታዬ፡- ማኅበሩ እስካሁን ድረስ ከንግድ ሥራ ትምህርት ኮሌጅ ጋር የጠበቀ ቁርኝት አለው፡፡ ስለዚህ ኮሌጁ ወጣቶች ከማኅበሩ ጋር እንዲተዋወቁና እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡ ከሚደረጉትም ጥረቶች መካከል ተማሪዎች ሲመረቁ እጅግ ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ልዩ ልዩ ሽልማት በመስጠት፣ ታዋቂ ሰዎች በአዳራሹ ንግግር ሲያደርጉ መጥተው ልምድ እንዲቀስሙ በማድረግ ወጣቶችን እያሰብን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የማኅበሩ ስም የንግድ ሥራ ወጣቶች ማኅበር ከሚለው ወደ ‹‹ንግድ ሥራ ትምህርት ምሩቃን ማኅበር›› ተቀይሯል፡፡ መቀየሩ ለምን አስፈለገ?

ወ/ሮ ፋንታዬ፡- ድሮ የንግድ ሥራ ምሩቃን የምንለው ከኮሜርስ የወጡትን ብቻ ነበር፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ብቸኛ የሙያ ትምህርት ቤት ስለነበረ ነው፡፡ አሁን ግን ትምህርቱ በየዩኒቨርሲቲው ተስፋፍቷል፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ቢዝነስ ነክ በሆነ ሙያ ወይም በማኔጅመንት የተማሩና አንድ ዓይነት ባክግራውንድ (ዳራ) ያላቸው በጋራ የሚወያዩበት መድረክ ተፈጥሮ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ሁሉ መግባት አለባቸው በሚል የተነሳ የቀድሞ ቀርቶ ወደ ‹‹ንግድ ሥራ ትምህርት ምሩቃን ማኅበር›› ሊቀየር ቻለ፡፡

ሪፖርተር፡- የማኅበሩ የወደፊት ዕቅድ ምንድነው?

ወ/ሮ ፋንታዬ፡- ማኅበሩ እስካሁን የሚንቀሳቀሰው በአባላት መዋጮ ነው፡፡ ሌላ ገቢ ማስገኛ እምብዛም የለውም፡፡ ጊዜው በጣም ውድ ነው፡፡ በአባላት መዋጮ ብቻ የትም አይደርስም፡፡ በዚህም የተነሳ ማኅበሩ ትንሽ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝበት ዘዴና ፕሮፌሽናሊዝምን ይዞ የሚጔዝበት መንገድ ይፈልጉለት ከሚል ቀና ሐሳብ በመነሳት ተጨማሪ ገቢ ለማስገኘት የሚያስችል ዕቅድ ተዘጋጅቷል፡፡ ለዕቅዱም ዕውን መሆን አምስት አባላትን ያቀፈ አማካሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ በዕቅዱ ላይ ተገቢውን ጥናት ካደረገና ጠቋሚ አቅጣጫን ከቀየሰ በኋላ ለማኅበሩ ቦርድ አቅርቧል፡፡ ለዕቅዱም ዲዛይንና ስትራቴጂክ ፕላን  ተዘጋጅቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ዕቅዱ ምን ምን ሥራን ነው ያካተተው?

ወ/ሮ ፋንታዬ፡- ደረጃውን የጠበቀ የስብሰባ ማዕከል ግንባታ፣ የሥልጠና አገልግሎት መክፈትና በአጠቃላይ ገቢውን ማሳመር ነው፡፡ ሥልጠናው በዓመት አራት ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን የሚሰጠውም ለቢዝነስ ጀማሪዎች፣ ወይም ቢዝነስ ጀምረው ወደ ሚቀጥለው ደረጃ ለመሄድ ለተደራጁ ሰዎች ወይም ከትምህርት ቤት ገና የወጡ ወጣቶች በቢዝነስ ዓለም ውስጥ እንዴት አድርገው ሊሳተፉና የትኛውን ኤቲክስ ተከትለው ምን መድረስ እንዳለባቸው ልምድ ካላቸው አባሎቻችን ትምህርት እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ከዚህም ሌላ አዳራሹ ለስብሰባ፣ ለዓውደ ጥናት፣ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላላቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች በኪራይ መልክ አገልግሎት ሊሰጥ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- የማኅበሩ መሥራቾች አሁን በሕይወት አሉ?

ወ/ሮ ፋንታዬ፡- ከመሥራቾቹ መካከል እስካሁን በሕይወት ያሉት አንድ አረጋዊ ብቻ ናቸው፡፡ 93 ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ ከቤታቸው ጠዋት ወጥተው እዚሁ ሲጫወቱ ውለው ለዓይን ያዝ ሲል ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከታክስ በፊት 27.5 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2014 ሂሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 27.5...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...