Thursday, September 21, 2023

‹‹ኃይድሮ ዲፕሎማሲያችንን ከዓለም አቀፉ የውኃ ሕግ ጋር አስተሳስሮ የሚሠራ አካል የለንም››

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አቶ ጌታቸው መኮንን፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ዲፕሎማሲ ባለሙያ

አቶ ጌታቸው መኮንን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ዲፕሎማሲ ባለሙያ ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በታሪክ ትምህርት ዘርፍ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ መምህር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ በኅብረ ባህልና ኅብረ ትምህርት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ እንዲሁም ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ዲፕሎማሲ የትምህርት ዘርፍ ሁለተኛ ማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ግንኙነትና በዲፕሎማሲ ጉዳይ ላይ የጻፏቸውን ሥራዎች በሪፖርተርና በሌሎች የሚዲያ ውጤቶች ላይ አሳትመዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ወጣቶች ኔትወርክ›› በሚባል ድርጅት ውስጥ በኃላፊነት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ አቶ ጌታቸው ናይል ወንዝ በተፋሰስ አገሮች መካከል ስላለው አንድምታና ስለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከዘመኑ ተናኘ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እ.ኤ.አ. በ1929 እና በ1959 የተደረጉ የናይል ወንዝ ስምምነቶች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዴት ያዩታል?

አቶ ጌታቸው፡- የዓባይ ውኃን የመጠቀም መብት ቅኝ ገዢዎች ባዘጋጁትና ሲያገለግል በቆየው እ.ኤ.አ. በ1929 እና በ1959 የናይል ውኃ አጠቃቀም ስምምነት ተገድቦ ቆይቷል፡፡ በዚህም የተፋሰሱ አገሮች በመብታቸው እንኳንስ ሊጠቀሙ ቀርቶ ሐሳብ እንዳላቸው እንኳ መደመጥ ሳይችሉ ቆይተዋል፡፡ ሊደርስባቸው የሚችለውን ችግር ቀድመው የሚያውቁት ስለሆነ አይነኬ ሆኖ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡ አገራችን ለመስኖና ለኤሌክትሪክ ማመንጫነት የሚያገለግሉ በርካታ ወንዞች ያሏት ነች፡፡ በመሆኑም የምሥራቅ አፍሪካ ‹‹‹የውኃ ማማ›› በሚል ስያሜ ብትታወቅም፣ በተፈጥሯዊ የውኃ ሀብት የመጠቀም መብቷ ተገድቦ መቆየቱ ከሁላችንም የተሰወረ ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለዚህ አፍሪካ በቅኝ ገዢዎች ሥር በወደቀችበት ወቅት እንግሊዝ ግብፅን ስትቆጣጠር፣ ለእርሷ በተለይም ለጥጥ ምርት ምቹ የሆነችዋን ሱዳን በመጨመር ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዋ የሚሆን በቂ ጥጥ ለማምረት የመስኖ ሥራዋን በግብፅና በሱዳን ማስፋፋት ጀመረች፡፡ ታዲያ ይኼ ምርት እንዳይስተጓጎል ማናቸውም አገሮች ከእንግሊዝ ፈቃድ ሳያገኝ በዓባይ ወንዝ እንዳይጠቀም ሲከለክሉ ቆይተዋል፡፡ ስለዚህ እ.ኤ.አ. በ1929 የተፈረመው ስምምነት በዋነኝነት በእንግሊዝ መንግሥት ይሁንታና ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ ይኼ ለ30 ዓመታት ያህል የቆየው ስምምነት የላይኞቹን የተፋሰስ አገሮች መብት ነፍጎ፣ ለታችኞቹ የተፋሰስ አገሮች መብት የሰጠ ነበር፡፡ እንግሊዝ በስተጀርባ ብትሆንም ለዘመናት ቆይቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1959 የተደረገው ስምምነት ደግሞ በሱዳንና በግብፅ መካከል የተደረገ ስምምነት ሲሆን ናይል ወንዝ በየዓመቱ ይዞት ከሚጓዘው 85 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ፣ 55 ቢሊዮኑ ለግብፅ፣ 18 ቢሊዮኑ ደግሞ ለሱዳን፣ የቀረው ደግሞ የወንዙን ፍሰት ለማስቀጠል በሚል ስምምነት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ በመሆኑም በሁለቱ ስምምነቶች የተነሳ የተፋሰስ አገሮቹ የዓባይ ወንዝን በእኩል ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ አልነበራቸውም፡፡ የእነዚህ ስምምነቶች ዋነኛ ትኩረት የታችኛው የተፋሰስ አገሮች በተለይ ደግሞ የግብፅንና የሱዳንን መብት በሰፊ ሁኔታ ማስጠበቅ ነበር፡፡ እነዚህ ስምምነቶች በተለይም በላይኞቹ የተፋሰስ አገሮች ተቀባይነት አልነበራቸውም፡፡ እነዚህ ስምምነቶች ፍትሐዊ አይደሉም፡፡ የተፋሰሱ አገሮች ከኢትዮጵያ በስተቀር በቀኝ አገዛዝ ሥር በመሆናቸው የአገራቱን ጥቅም የሚያስጠብቁ ሊሆኑ እንደማይችሉ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ስምምነቶቹ በዋነኛነት የቅኝ ገዥ አገሮቹ ጥቅም የሚያስጠብቁ ስለነበር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. መሠረት ከተጣለበት ዕለት ጀምሮ ግብፅ ግድቡ ዕውን እንዳይሆን በሙሉ አቅሟ ተረባርባለች የሚሉ መረጃዎች አሉ፡፡ ይኼ የግብፅ ጥረት አሉታዊ ተፅዕኖ አለው ብለው ያምናሉ?

አቶ ጌታቸው፡- ከመጀመሪያው ግብፅ የነበራትን የታሪክ ሁኔታ ስንመለከት፣ ዓባይን ለመቆጣጠር በኢትዮጵያ ላይ በተለያዩ ጊዜና ወቅት የተለያዩ ወረራዎችን ቃጥታለች፡፡ ይኼ የሆነበት ምክንያት ምንድነው? ብለን ብንጠይቅ ኢትዮጵያ ምናልባት ግድቡን ብትገነባ ከዓባይ የምታገኘው ውኃ ሊቀንስ ይችላል የሚል ሥጋት ስለነበረባት ነው፡፡ ዋነኛ ፍላጎቷ ዓባይን መቆጣጠር ነበር፡፡ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከተው ደግሞ በተለያየ መንገድ የምትከተለው አቋም ከፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም መርህ ጋር የሚስማማ አይደለም፡፡ ግብፆች ለናስር እንደሚጨነቁት ሁሉ፣ ኢትዮጵያም ከዓባይ ጥቅም ማግኘት መቻል አለባት፡፡ ይኼንን ጉዳይ አበክሮ ካለመገንዘብ አሁንም ግብፆች የተለያየ ነገር ሊፈጥሩ ይችላሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ ከሚፈጥሩት ችግር መካከል አንዱ ኢትዮጵያን ማዳከም ነው፡፡ ኢትዮጵያ በታላቁ ግድብ ላይ ያላትን አቋም ሚና ካላቸው የውጭ ኃይሎች ጋር በጋራ ሆኖ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማዳከም ሊሞክሩ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ማዳከም የሚለው በምን ይገለጻል?

አቶ ጌታቸው፡- የውጭ ፖሊሲው እንደሚለው ኢትዮጵያ በመጀመሪያ የውስጥ ሰላሟን ማስጠበቅና ልማቷን ማፋጠን አለባት፡፡ ኢትዮጵያ የውስጥ ሰላሟን እንዳታስጠብቅ ግብፅ በተለያየ ምክንያቶችና ሁኔታዎች ጫና ለመፍጠር መሞከሯ የማዳከም መገለጫ ነው፡፡ ለምሳሌ ከኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ጋር በመሆን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዕውን የማይሆንበትን መንገድ ማመቻቸት አንደኛው ተፅዕኖ ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለተኛው በተለይ ከሃይማኖት ጋር ተያይዞ ግብፅ በተለያየ መንገድ እዚህም እዚያም ችግር ልትፈጥር ትችላለች፡፡ ስለዚህ እነዚህን ችግሮች ለመፍጠር ግብፅ የምትነሳሳበት ዋና ዓላማዋ ምንድነው? በድርድር፣ በውይይትና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ለምን አታምንም? በጠንካራ አፍሪካዊነትና ወንድማማችነት መንፈስ ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ ካለመጓዝ እሳቤ የመነጨ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ካላት የቆየ የበላይነት አስተሳሰብና ህልም ጋር ተያይዞ ሊነሳ ይችላል፡፡ ሌላኛው ተፅዕኖ ደግሞ ኢትዮጵያ ከተለያዩ አበዳሪ አካላት የፋይናንስ ድጋፍ እንዳታገኝ ተፅዕኖ ልትፈጥር ትችላለች፡፡ ይኼም ሆኗል፡፡ ምናልባትም ነገ ከነገ ወዲያም ቀና የሆነ አስተሳሰብ ያላቸው ዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት ላይ ልዩ ተፅዕኖ ልታሳድር ትችላለች ተብሎ ይታሰባል፡፡

ሪፖርተር፡- ሦስቱ የተፋሰስ አገሮች ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሊያደርስ ይችላል የተባለውን አሉታዊ ተፅዕኖ እያስጠኑ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይኼ ጥናት ይፋ በሚሆንበት ወቅት የተለየ አቋም ያመጣል ብለው ያስባሉ?

አቶ ጌታቸው፡- አዎ፡፡ በተለይ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለኢትዮጵያ የሚያስገኘው ጥቅም ምንድነው? ለታችኞቹስ ተፋሰስ አገሮች የሚያስገኘው ጥቅም ምንድነው? ለላይኞቹ ተፋሰስ አገሮችስ የሚያስገኘው ጥቅም ምንድነው? ብሎ በሦስት ከፋፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ ከመነሻው ዛሬ የናይል ተፋሰስ አገሮች የጋራ ስምምነት ማዕቀፍ በመባል የሚታወቀውን ለፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል ተግባራዊነት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ይኼ እ.ኤ.አ. በ2010 የተፋሰስ አገሮቹ የተፈራረሙት የትብብር ማዕቀፍ በአብዛኛው የሚያተኩረው ውኃውን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የመጠቀም መብት ላይ ነው፡፡ ያረጀውንና ያፈጀውን ስምምነት የተካ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ የመሆኑን ጉዳይ ሁሉም ሰው ማወቅ መቻል አለበት፡፡ በመጀመሪያ ከግድቡ የምናገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል በአገሪቱ እየተስፋፋ ላለው ኢንቨስትመንት በቂ ምላሽ የሚሰጥ ነው፡፡ በአገሪቱ የኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመፍጠር እየተሠራ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ዋነኛውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ የኃይል አቅርቦት ጥያቄን ይመልሳል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከግድቡ ከሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት አገሮች በመሸጥ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት፣ የአገሪቱን ፍላጎት ከማሳካት አኳያ በቀላሉ የማይገመት አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ በአንድ በኩል የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር መፍጠሪያ መንገድ በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው ይኼ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ ሁሉንም የጎረቤት አገሮች የኃይል አቅርቦት የሚያሟላ በመሆኑ አገራዊ ኩራት ነው ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ በቅርቡ ኢትዮጵያ ለጂቡቲና ለሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል እየሸጠች የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ጀምራለች፡፡ ከዚህ አንፃር የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት አንፃርም ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ድህነትን ለመቅረፍ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ ግድቡ ከውጭ ጉዳይ ደኅንነት ፖሊሲያችን ጋር በመናበብ ለቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ትስስር መጎልበት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ  አይደለም፡፡ ፖሊሲያችን በጋራ በመልማትና በጋራ በማደግ ሕዝባችንን መጥቀም ላይ ያተኩራል፡፡ የጎረቤት አገሮችንም ዕድገትና ብልፅግና ይፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ጎረቤቶቿ እኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ያለባቸው በተግባር ነው፡፡

ግድቡ በአንድ በኩል ለሱዳንና ለግብፅ ያለውን የኃይል አቅርቦት ችግር በማቃለል ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ በመሆኑም የቀጣናውን ኢኮኖሚ ከማስተሳሰር ባሻገር ሰላምን ከማስፈን አኳያም ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡ የቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ትስስር በተለይ አንፃራዊ ጠቀሜታ በሚለው የኢኮኖሚው ጽንሰ ሐሳብ መሠረት ልዩ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ ሱዳን በመስኖ የሚለማ ሰፊና ምቹ የእርሻ መሬት አላት፡፡ ግብፅ ደግሞ የምግብ እህል በተለይ ስንዴ በማስገባት በዓለም ከመጀመሪያዎቹ ተርታ የምትሠለፍ አገር ነች፡፡ ከሱዳን ጋር ካላት መልክዓ ምድራዊ ቀረቤታ የሱዳንን ምርት በመጠነኛ ዋጋ በማስገባት ተጠቃሚ ትሆናለች፡፡ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ አካባቢ የምትሠራው የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤና የተፋሰስ ልማት ይኼንን በማረጋገጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ ይኼ ደግሞ የራሱ የሆነ ጠቀሜታ አለው፡፡ ከዚህ አንፃር፣ አንፃራዊ የኢኮኖሚ ብልጫ በመጠቀም የአገሮቹን ትስስር የአገሮቹን ቀረቤታ ማጠናከር የራሱ የሆነ ጉልህ ፋይዳ አለው፡፡ 85 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ የነዳጅ ፍላጎት የሚሟላው ከሱዳን ነው፡፡ ስለዚህ በየወሩ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከኢትዮጵያ ታገኛለች ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ የእንስሳት ሀብትን አብዝታ ወደ ሱዳን በመላክ የህዳሴ ግድብ ከሚሰጠው ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ተመጣጣኝ ገቢ ማግኘት ትችላለች፡፡ በተጨማሪም ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ከካርቱም፣ ጁባ፣ አዲስ አበባ የኃይል ሦስት ማዕዘን ትስስር ለመፍጠር ምቹ ሁኔታ አለ፡፡ ይኼ ግንኙነት ነዳጅ ከሱዳን፣ ከውኃ ኃይል ከሚገኝ ኤሌክትሪክ ደግሞ ከኢትዮጵያ በማግኘት ሁለቱ አገሮች አንድነትና ትስስርን በመፍጠር ወንድማማችነታቸው እየጠነከረ እንዲመጣ ማድረግ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያና ሱዳን በነዳጅና ከውኃ በሚገኝ ኃይል አማካይነት ትስስር መፍጠር ችለዋል፡፡ ከግብፅ ጋርስ?

አቶ ጌታቸው፡- ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር ታሪካዊ ግንኙነት አላት፡፡ ሃይማኖታዊ ትስስርም ነበራቸው፡፡ የድሮዎቹ የኢትዮጵያ ጳጳሳት እየተቀቡ የሚመጡት ከግብፅ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም በቋንቋና በባህል ከፍተኛ የሆነ ትስስር አለ፡፡ በአሁኑ ጊዜም የግብፅ መንግሥት ለኢትዮጵያ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል፡፡  በአሁኑ ወቅት በእነዚህ ጉዳዮች ትስስር ፈጥረዋል ማለት ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ጥናቱ በሚጠናቀቅበት ጊዜ የተለየ ውጤት ይዞ ይመጣል ብሎ መናገር ይቻላል?

አቶ ጌታቸው፡- የአስዋን ግድብ በደለል የመሞላት ዕጣውን ያስቀራል፡፡ ግድቡ ግብፅን ደለል በማስወገድ ተጨማሪ ወጪ የማይጠይቅበት ደረጃ ላይ ያደርሳል፡፡ ግብፅንና ሱዳንን ለጎርፍ ይዳርግ የነበረውንና በትነት የሚባክነውን ውኃ ያስቀራል፡፡ ይኼንን ነው ባለሙያዎች በመላምት ደረጃ የሚያስቀምጡት፡፡ በዚህ መሠረት የግብፅ ፖሊሲ ተቀይሮ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ካነጣጠረ፣ እነዚህ የጥናት ውጤቶች ይፋ በሚሆኑበት ጊዜ ሁሉም በአንድነትና ሁሉም በስምምነት ተጠቃሚ የሚሆኑበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በናይል ወንዝ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንፈታለን የሚል አቋም እንዳላቸው ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ይኼንን ጉዳይ እንዴት ያዩታል?

አቶ ጌታቸው፡- የእያንዳንዱ አገር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በመሪው የሚወሰን ነው፡፡ የግብፅን ቀደም ያሉ መሪዎች ለአብነትም አንዋር ሳዳት፣ ሆስኒ ሙባረክና መሐመድ ሙርሲ፣ እንዲሁም የግብፅ ምሁራን (ልሂቃን) ግብፅ የ‹‹ናይል ስጦታ›› ስለሆነች ከግብፅ ውጪ ማንም አገር ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም የሚል የበላይነት አስተሳሰብ ሲያራምዱ ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር ዓባይን ለመገደብ በሚሞክር አገር ላይ ኃይል የተቀላቀለበት ዘመቻ (ወረራ) ለማካሄድ የሚያስችል አመለካከት ያስተጋቡ ነበር፡፡ አሁን ፕሬዚዳንት አልሲሲ በትብብርና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ችግሮቹን አስወግዶ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመረኮዘ አዲስ አስተሳሰብ ይዘው ነው የመጡት፡፡ ይኼ የሚበረታታ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ የግብፅ ሕዝብ የሚደግፈው ነው፡፡ ይኼንን የፕሬዚዳንት አልሲሲ አስተሳሰብ ዕውን እንዲሆንና እንዲረጋገጥ ምን አስቻይ ሁኔታዎች ተደርገዋል? ብለን ስንመለከት የመጀመሪያው የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ ነበር፡፡ አሁንም በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ እየተሠራበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በታችኞቹ የተፋሰስ አገሮች ላይ የሚሳድረውን አሉታዊ ተፅዕኖ መቆጣጠርና ሁሉንም ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችል የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ነው፡፡ ነፃና ገለልተኛ ኤክስፐርቶችም ይኼንኑ ይደግፋሉ፡፡ የእርስዎ አቋም ምንድነው?  

አቶ ጌታቸው፡- በአፍሪካዊ ወንድማማችነትና አንድነት፣ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ በተለይ ደግሞ በዓለም አቀፍ ውኃ ሕግ መሠረትና ባሉት የተለያዩ አደረጃጀቶችና ‹‹ናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ›› የትብብር ማዕቀፍ መሠረት አገሮች በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያነጣጠረ መርህ ቢከተሉ የተሻለ ነው የሚል አቋም አለኝ፡፡ ይኼ እያደገ የመጣውን የሕዝብ ቁጥርና ከዚያ ጋር ተያይዘው የሚመጡትን ችግሮች ለመቅረፍና የሁሉንም አገሮች ችግር ያስወግዳል የሚል አስተሳሰብ አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- በሦስቱ የተፋሰስ አገሮች ካለው የናይል ወንዝ አጠቃቀም መርህ ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ ምን ይላል?

አቶ ጌታቸው፡- መጀመሪያ ስለዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ ከማየታችን በፊት ተቀባይነት ስላላቸው ዓለም አቀፍ መርሆች ማየቱ የተሻለ ነው፡፡ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን አጠቃቀም በተመለከተ የተለያዩ ተቀባይነት ያላቸው መርሆዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ግዛቱ ላይ ያለው ፍፁም ሉዓላዊነትarmon Doctrined HaHahHhAharmon   mvmvkfkfofkf ሲሆን፣ ሁለተኛው የአንድ መንግሥት ፍፁም መብት፣ ሦስተኛው ገደብ ያለው ሉዓላዊነትና አራተኛው የኅብረት ጽንሰ ሐሳብ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ አራቱ መርሆዎች ኢትዮጵያ የምትከተለው የኅብረት ጽንሰ ሐሳብ ተጠቃሚ መርህ ላይ ያነጣጠረና ከዚያ የሚመነጭ ነው፡፡ ኃይድሮ ዲፕሎማሲያችንን ከዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ ጋር አስተሳስሮ የሚሠራ አካል የለንም፡፡ በአጭሩ የውኃ ሕጎችን በተመለከተ በስፋት ያልተዳሰሰና መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት አገራችን ታላላቅ ግድቦችን እየገነባች ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1997 ዓለም አቀፍ የውኃ ኮንቬንሽን እንዲፀድቅ ተደርጓል፡፡ ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ድረስ ስምምነቱን አላፀደቀችም፡፡ ምክንያቱም በኮንቬንሽኑ አምስተኛውና ሰባተኛው አንቀጾች መካከል የጠራ ልዩነት ባለመኖሩ፣ እንዲሁም ኮንቬንሽኑ በጋራ ተፋሰስ አገሮችን አስመልክቶ አገሮች ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መስጠት እንዳለባቸው እንደ ግዳጅ በማስቀመጡ ነው፡፡ አንቀጽ 5 አገሮች በግዛታቸው የሚፈሰውን ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ምቹና ዘለቄታ ባለው የሌሎችን ጥቅም በማይፃረር መልክ፣ እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃን ለማስጠበቅ ግዳጅ ይጥላል፡፡ አንቀጽ 7 ደግሞ በውኃ የሚጠቀም ማንኛውም አገር በሌላ አገር ላይ ዓብይ ጉዳት ያለማድረስ ግዴታ አለበት የሚሉ ናቸው፡፡ በእነዚህ ሁለት አንቀጾች መካከል ግልጽና አገራችንን ተጠቃሚ የሚያደርግ ድንጋጌ ባለመኖሩ ኢትዮጵያ ጉዳዩን ገና እያጤነች ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ምሁራን በበለጠ መከራከር ያለብን ይመስለኛል፡፡ ግብፆች በውኃ ዲፕሎማሲ፣ በዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ ላይ ብዙ ምሁራን አፍርተዋል፡፡ ተፅዕኖ ሊያደርጉ ከሚችሉባቸው ነገሮች አንዱ በምሁራኖቻቸውና በተመራማሪዎቻቸው ነው፡፡ እኛ እስካሁን ድረስ ኃይድሮ ዲፕሎማሲ የሚለውንና ዓለም አቀፍ የውኃ ሕግን በአንድ ላይ አስተሳስሮ የሚያጠና ቡድን አልፈጠርንም፡፡ ለምሳሌ በአፍሪካ ደረጃ እንኳ ይህን የሚሠራ አደረጃጀት የለም፡፡ አገር አቀፍ ኃይድሮ ዲፕሎማሲውን ከዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ ጋር አስተሳስሮ የሚሠራ አካል የለንም፡፡

ሪፖርተር፡- የህዳሴው ግድብ ግንባታ 56 በመቶ እንደ ደረሰ መንግሥት በቅርቡ ይፋ አድርጓል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የግድቡ ግንባታ እንደዘገየ የሚያወሱ ወገኖች አሉ፡፡ ይኼንን እንዴት ያዩታል?

አቶ ጌታቸው፡- በእርግጥ ይኼ መዘግየቱና መፍጠኑ ሳይሆን ለምንድነው የዘገየው? ለምንድነው የፈጠነው? የሚለውን ማየት ግን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በእኔ ግምት የዘገየበት ምክንያት ጥራቱን የጠበቀና አስተማማኝ የሆነ ግድብ ለመገንባት የማቴሪያል አቅርቦት፣ የባለሙያ ዕይታና ዕውቀት መፍሰስ ስላለበት ነው፡፡ ጥራት ያለው የግብዓት አቅርቦት መምጣት ስላለበትና ተያያዝ ጉዳዮች መሠራት ስላለባቸው፣ በዚህ ምክንያት በተፈለገው መጠንና በታቀደው ጊዜ ላያልቅ ይችላል፡፡ በልዩ ጥንቃቄ የሰው ኃይሉም፣ የግብዓት አቅርቦቱም ጠቅላላ ያለው የአገሪቱ ማክሮ አኮኖሚም መታሰብ አለበት፡፡ በዚህ ምክንያት በሚፈለገው ጊዜና ሰዓት ባይጠናቀቅም አሁን ያለበት ደረጃ ጥሩና የሚያበረታታ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአንድ ወገን የሕዝቡ ተሳትፎ ተቀዛቅዟል፣ በሌላ ወገን ደግሞ የበለጠ ተነሳስቷል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ከየትኛው ወገን ነዎት? ምንስ ነው መሆን ያለበት ይላሉ?

አቶ ጌታቸው፡- መጀመሪያ ፋይዳውን መገንዘብ ነው ቁም ነገሩ፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው የታላቁ ህዳሴ ግድብ መሠረት ሲጣል በአራቱም አቅጣጫ ሕዝቡ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተነሳስቷል፡፡ ገና ሀ ብለን ባሳየነው ስሜትና አንድነት ነው ውጤቱንም መጠበቅ ያለብን፡፡ አለበለዚያ ግድቡ ዘግይቷልና በኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለውን ጫና የምንመዝን ከሆነ ዓባይ አንድ ዓመት፣ ሁለት ዓመት የግንባታ ጊዜው ከተቀመጠለት ጊዜ ጨምሯል ብለን የምናስብ ከሆነ ተሳስተናል፡፡ ግን ደግሞ ዘመናትን የምንከርምበት ከድህነት መውጫ መንገድ ስለሆነ ረጋ ብሎ ማየትና ውጤቱን መጠባበቅ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚዲያዎች ሚና ምንድነው? የሚለውን ነገር መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ሕዝብን ለመቀስቀስ፣ ለማስተማር፣ ለማሳወቅ፣ የመንግሥት ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ የሚዲያዎች ሚና ሰፊውን ቦታ ይይዛል፡፡ እኔ ተቀዛቅዟልም፣ አልተቀዛቀዘም ለማለት ያስቸግረኛል፡፡ ይኼን ለማለት ትክክለኛ መረጃ ያስፈልጋል፡፡ የሚዲያዎች (የመንግሥትም ሆነ የግሉም) አሁን እያደረጉት ያለው ጉዳይስ ምንድነው? የሕዝቡ ስሜት እንዲጨምርም ሆነ እንዲቀዛቀዝና ወደፊት ምን ማድረግ እንዳበት ሚዲያዎች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ሚዲያዎች ግን ይኼንን ሲያደርጉ አይታይም፡፡ በዚያኛው ወገን ያለውን እኩይ ሥራና ደባ የማጋለጥ ሚና ነበራቸው፡፡ በእኔ አስተያየት ግን በሚገባ አልሠሩም የሚል አቋም አለኝ፡፡ የግሉ ሚዲያ አንባቢን ለመሳብ ርዕስ በመምረጥና የጦርነት ወሬ ይዞ ከመጋለብ ርቆ የበሰለና የሰከነ ሥራ ይዞ ለብሔራዊ ጥቅም የሐሳብ ክርክርና መፍትሔ ወደ ማመንጨት ገና አልሄደም፡፡ ብሔራዊ ጥቅምን ከዓባይ ጋር አስተሳስሮ ቀጣይነት ያለው የሐሳብ ልውውጥ፣ የዕውቀት ሽግግር ማድረግ ቢቻል ነው የተሻለ የሚሆነው፡፡ ይኼን እስካሁን ልንሠራ አልቻልንም፡፡ የታላቁ የህዳሴ ግድብ አንድ ተብሎ መሠረት ከተጣለበት ዕለት ጀምሮ ሚዲያዎቹ አስደሳች ዜና ይዘው የሚወጡበት ሁኔታ አይታይም፡፡ በአጠቃላይ አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች የዓረቡን ዓለምና ሌላውን በመወገን ፀረ ኢትዮጵያ ፕሮፓጋንዳቸውን እያካሄዱ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሚዲያ ግን ፀጥታን መርጦ እየተመለከተ ያለ ይመስለኛል፡፡ ግብፆች በየትኛውም ልሳን የሚታተም ከዓባይ ጋር በተያያዘ አንድም ጽሑፍ አያመልጣቸውም፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ያለውን የፕሬስ አታሼ እያስተረጎሙ ወደ ግብፅ ይልካሉ፡፡ ሥራውም ይኼ ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያና ሕዝቧ ሐሳብና አቋም ምን እንደሚመስል ጨዋና ተጨባጭ በሆነ መንገድ እንዲያውቁት ማድረግ የሁላችንም ግዴታና ኃላፊነት እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ግድቡ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያ የሚያስገኘው ነገር ምንድነው? በናይል ፖለቲካ ላይስ ምን አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል ብለው ያስባሉ?

አቶ ጌታቸው፡- ቅድም ለመግለጽ እንደሞከርኩት ለኢንቨስትመንት የሚሆን የኃይል አቅርቦት ችግራችንን ይፈታል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል፡፡ ለቱሪዝም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ለአካባቢ የአየር ንብረት ለውጥም መቀነስ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም በሺሕ ለሚቆጠሩ ዜጎቻችን የሥራ ዕድል አመቻችቷል፡፡ ከዚህ ባለፈም የዕውቀት ሽግግር ያመጣል፡፡ በናይል ፖለቲካ ላይ ያለው አዲስ ነገር ደግሞ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውን መንፈስ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ የጎረቤት አገሮችን የኢኮኖሚ ትስስር ዕውን ያደርጋል፡፡ በአጠቃላይ ሰላምን ያሰፍናል፣ ድህነትን ይቀርፋል፣ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ አዲስ አጋርነት ለሕዝቦች የመቆርቆርና ለጋራ ልማት አዲስ ምዕራፍ ይፈጥራል፡፡                                

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -