Monday, April 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለካንሰር ታማሚ የሳንባ መድኃኒት አይታዘዝም!

አገርኛው ብሒል ‹‹ሕመሙን የደበቀ መድኃኒት አያገኝም›› ይላል፡፡ ሕመምን መደበቅ ብቻ ሳይሆን አለማወቅም በሕይወት ለመኖር ጠንቅ ነው፡፡ ይህንን ከፍ አድርገን ወደ አገር ስናመጣው የሚያጋጥሙ ችግሮችን መሸፋፈን ወይም በጊዜያዊ መፍትሔዎች ለመገላገል መሞከር መዘዙ የከፋ ይሆናል፡፡ ችግርን ማወቅ የመፍትሔ አካል ነው፡፡ መፍትሔው የበለጠ የሚጎመራውና አስተማማኝ የሚሆነው ግን ዘለቄታዊ ሲሆን ነው፡፡ አሁን በአገሪቱ የሚታዩ ጥናት የጎደላቸው ድርጊቶች ግን በእንጭጩ ካልተቀጩ የሚያስከትሉትን ጥፋት ለመገመት ያዳግታል፡፡ በጥናት ላይ ያልተመሠረቱ የይድረስ ይድረስ ውሳኔዎች ለጊዜው ፋታ ቢሰጡም፣ ውለው አድረው ግን የማይድን ፅኑ ደዌ ይሆናሉ፡፡ የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሁን በሚወሰዱ ግብታዊ ዕርምጃዎች ደስታ ቢፈጠርላቸውም፣ ከአጠቃላይ ሕዝብ ፍላጎት አንፃር ግን ሌላ ችግር እንደሚከሰት አለማሰብ ከባድ ነው፡፡ ችግሩ ሌላ መፍትሔው ሌላ፡፡ መድኃኒትና ሕመም አልገናኝ ሲሉ ቀውስ ይፈጠራል፡፡

በቅርቡ ከኦሮሚያ ክልል ጀምሮ ወደ ሌሎች ክልሎች እየተዛመተ ያለው ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የማድረግ ዕርምጃና በፌዴራል መንግሥት ለወጣቶች የተዘጋጀው ፈንድ በአዎንታዊ ጎኑ ይደገፋል፡፡ ወጣቶች የሥራ ዕድሎችን ሲያገኙና እነሱም ነገ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ጥረት መጀመሩ የሚያስመሰግን ተግባር ነው፡፡ ነገር ግን ይህ በጎ ጥረት በጥናት አልባ የዘመቻ ሥራዎች ገጽታውን ሲቀይር ሰከን ማለት ተገቢ ነው፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የወጡ ሥራ ፈላጊዎች በመንግሥት ድጋፍ እርሾ የሚሆን ካፒታል አግኝተው ወደ ሥራ ሲሰማሩ፣ የሚደረገው ድጋፍ ጥገኝነትን ማበረታታት የለበትም፡፡ ወጣቶች በአፍላ ጉልበታቸውና በቀሰሙት ዕውቀት ጥርሳቸውን ነክሰው መሥራት ሲገባቸው፣ ዕርባታ ጣቢያ ውስጥ እንዳሉ አዞዎች የተቀላቢነት ሥነ ልቦና ሊፈጠርላቸው አይገባም፡፡ የነገ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች በጥናት ላይ የተመሠረተ ቢዝነስ ሞዴል ኖሮዋቸው አስተማማኝ የንግድና የኢንቨስትመንት ኩባንያ መመሥረት ሲኖርባቸው፣ በጥናት ላይ ባልተመሠረቱ የሽንገላ ድጋፎች ጥገኛ እንዲሆኑ ማድረግ ጊዜያዊ መፍትሔ ላይ ብቻ ማተኮር ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ለአገር አይጠቅምም፡፡

መንግሥት የሕዝብን ጥያቄ መመለስ አለበት ተብሎ ተወጥሮ ከተያዘባቸው ጉዳዮች መካከል ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንደኛው ነው፡፡ ሕዝብን ለማስደሰት በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ አላስፈላጊ የሆኑ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ፣ ከታሪክ መረዳት እንደሚቻለው ውጤታቸው አጥፊ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ሕዝብን ማስደሰት የሚቻለው ሕግን የሚቃረኑ ድርጊቶች በመፈጸም አይደለም፡፡ በቅርቡ በአሜሪካ አሁን ደግሞ በአውሮፓ በአንዳንድ አገሮች የሚታዩ ‹‹ፖፑሊስት›› እንቅስቃሴዎች ምን ያህል አደገኛ እየሆኑ መምጣታቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በ1930ዎቹ በአውሮፓ የ‹‹ፖፑሊስት›› እንቅስቃሴ እነ ቤኒቶ ሙሶሎኒንና ሒትለርን ነበር ያፈራው፡፡ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጠባሳን የሚያስታውሱት  እነዚህ ሁለት ግለሰቦች የፈጸሙዋቸው ጥፋቶች አውዳሚ ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ ደርግ በሰፊው ሕዝብ ስም በጥናት ላይ ያልተመሠረተ የንብረት ውርስ ፈጽሞ አገሪቱን እንዴት እንዳንኮታኮታት ይታወቃል፡፡ በሕዝብ ስም በጥናት ላይ ያልተመሠረቱ ውሳኔዎች ዳፋቸው ለመጪው ትውልድ ሳይቀር ይተርፋል፡፡

ዕቅዶች ግብታዊና ጊዜያዊ ችግርን ማስተንፈሻ ሲደረጉ ከልማታቸው ይልቅ ጥፋታቸው ይከፋል፡፡ ለወጣቶች የሥራ ዕድሎች ሲፈጠሩ በጥናት ላይ መመርኮዝ ተገቢ ነው፡፡ ጥናቶች ከታች ከቤተሰብ ጀምሮ የአገርን አጠቃላይ ሁኔታ በጥልቀት ሲዳስሱ፣ ለዘለቄታዊ መፍትሔ የሚበጁ ድምዳሜዎች ላይ ይደረሳል፡፡ በለብ ለብ የኮሚቴ ጥናት ላይ በመመሥረት ዙሪያ ገባውን ያልፈተሸ የተሳሳተ ውሳኔ ላይ ሲደረስ ግን ከላይም ከታችም የሚያመረቅዝ ችግር ይፈጠራል፡፡ ሀብትና ዕውቃቸውን ይዘው ላባቸውን እያንጠፈጠፉ የሚሠሩ ሰዎችን ሕገ መንግሥታዊ መብት በመጋፋት መሥሪያቸውን መንጠቅ መቼም ቢሆን ፍትሐዊ አይሆንም፡፡ ለወጣቶች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማምጣት የሚደረገው ጥረት በኢፍትሐዊ ዕርምጃዎች ሲመራ መደናገር ይፈጠራል፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠው በመላ አገሪቱ ተዘዋውሮ ሀብት የማፍራት መብት ተጥሶ ተገቢ ያልሆነ ዕርምጃ ሲወሰድ፣ የአገሪቱን መልካም ስምና ገጽታ ያጎድፋል፡፡ ኢንቨስትመንትን ያዳክማል፡፡ በሽታው ሌላ መድኃኒቱ ሌላ ሆነ ማለት ነው፡፡ ውጤቱም አይረቤ ይሆናል፡፡

መንግሥት በሕገ መንግሥቱ ከተጣሉበት ኃላፊነቶች አንዱ ለሕዝቡ ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር ማስፈን እንዳለበት ነው፡፡ በተጨማሪም ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ማንኛውም ተግባር ተቀባይነት እንደሌለው ነው፡፡ በስመ ሕዝብ ማስደሰት የሚወሰዱ የዘፈቀደ ውሳኔዎች ተቀባይነት የማይኖራቸው የሕግ የበላይነትን ስለሚጋፉ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎች መቼም ቢሆን መልስ ሆነው አያውቁም፡፡ ይልቁንም ለሌላ ዙር ግጭትና ቀውስ ይዳርጋሉ፡፡ በሕግ የበላይነት ጥላ ሥር ሲሆን ግን በአመዛኙ ሁሉንም የሚያስማሙ ውሳኔዎች ይገኛሉ፡፡ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በጥናት ላይ ተመሥርቶ ተግባራዊ ሲደረግ ውጤቱ ለአገር ይጠቅማል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በጥናት ላይ ያልተመሠረቱና በጊዜያዊነት ችግሮችን ለማርገብ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ‹‹ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ›› ናቸው፡፡ ራዕይ አልባና ጥገኛ መንፈስ ከድህነት አረንቋ ውስጥ መውጣት ያለበትን ወጣት ኃይል ያሰንፋል፡፡ ይህ ደግሞ በፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡

አገር የምትለማው፣ የምታድገው፣ የምትበለፅገውና በዴሞክራሲያዊ ጎዳና ላይ በኩራት መረማመድ የምትችለው ከጊዜያዊ መፍትሔዎች በመላቀቅ ለዘለቄታው ማሰብ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ አስተማማኙ መድኃኒትም ይኼ ብቻ ነው፡፡ አንድ ሕመምተኛ ከሚያሰቃየው ፅኑ ደዌ የሚድነው በሚገባ ተመርምሮ ፈውስ የሚሆነው መድኃኒት ሲታዘዝለትና በአግባቡ ሲወስደው ነው፡፡ አገርም የሚያስፈልጋት እንዲህ ዓይነቱ አሠራር ነው፡፡ ከምንም ነገር በላይ ኢትዮጵያ ለምትባለው ትልቅ አገር ምሥል ልዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በተሳሳተ መንገድ ትልቁን ምሥል በማሳነስ ጠበብ ያለ ነገር ላይ ብቻ ማተኮር የሚጎዳው መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ የአሁኑ ትውልድ ለመጪው ትውልድ ማስረከብ ያለበት ምን እንደሆነ ማወቅ ይኖርበታል፡፡ አሁን የሚታዩ ችግሮች ከአገር ፍቅርና ከመጪው ትውልድ ፍላጎት አንፃር ዘለቄታዊ መፍትሔ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ይህንን አለማድረግ በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ ትርፉም መቆጨት ይሆናል፡፡ አገርን የምታህል ትልቅ የጋራ ቤትና ይህንን ጀግናና ኩሩ ሕዝብ ይዞ ወንዝ የማያሻግር ነገር ውስጥ መዘፈቅ ይብቃ፡፡ ችግሩ ከታወቀ መፍትሔውም አስተማማኝ መሆን አለበት፡፡ መሸፋፈንና ማድበስበስ ይብቃ፡፡ ለዚህም ነው ለካንሰር ታማሚ የሳንባ መድኃኒት የማይታዘዘው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

ስለዘር ፖለቲካ

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ  ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይዳፈን ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አሁንም ጤና አልባ ሆኖ የተለመደው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ሊሻሻል ያልቻለው የፖለቲካ ምኅዳር ሰሞኑን አዲስ...