ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች መንስዔ የሆኑ አደንዛዥ እፆችን ስርጭት መግታት አዳጋች እንደሆነ ለቀጣይ ሁለት ዓመታት የሚሠራበት ሐገር አቀፍ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ መርሐ ግብር ሰሞኑን ይፋ ሲሆን ተገልጿል፡፡
መርሐ ግብሩ ይፋ በሆነበት ወቅት እንደተመለከተው፣ ጫት ሲጋራና የመሰሉ አደንዛዥ እፆች ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ዋነኛ መንስዔ ቢሆኑም ስርጭታቸውን መግታት አልተቻለም፡፡ አደንዛዥ እፆች የሚያስገኙት ገቢ ላይ ትኩረት እየተደረገ ምርቶቹ ስለተስፋፉ የሕብረተሰቡ ጤና አደጋ ላይ መውደቁም ተገልጿል፡፡
መርሐ ግብሩ ይፋ የሆነው የዓለም ካንሰር ቀን የካቲት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ‹‹ከእኛ አያልፍም›› በሚል መርህ በሒልተን አዲስ አበባ በተከበረበት ዕለት ሲሆን፣ የማሕፀን ጫፍ ካንሰርን መከላከልና መቆጣጠር ላይ የሚያተኩር ሠነድም ይፋ ሆኗል፡፡ ሠነዱ ያተኮረው ከጊዜ ወደ ጊዜ የበርካታ ሴቶችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ቅድመ ጥንቃቄና ምርመራ ላይ ነው፡፡
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከልና ቁጥጥር ተጠባባቂ ዳይሬክተር ዶ/ር ማህሌት ክፍሌ እንደተናገሩት፣ የእቅዱ ተቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ የሚሆነው በሽታዎቹን የመከላከል ሥራ ነው፡፡ ይህም ተላላፊ ላልሆኑ ካንሰር፣ ስኳርና ሌሎችም በሽታዎች መንስኤ የሆኑትን ለይቶ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ ከአደንዛዥ እፅ መታቀብ፣ አመጋገብና አጠቃላይ አኗኗርን ማስተካከልን ያካትታል፡፡ በሽታው ከተከሰተ በኋላ ለማከምም የሕክምና ባለሙያዎችና መሣሪያዎች ሥርጭት ማስፋፋትን ያለመ ነው፡፡
ዶክተሯ እንዳሉት፣ የካንሰር ሕክምናና መድሐኒትን በዝቅተኛ ዋጋ ለማቅረብ የሚደረገው ጥረትና የካንሰር ማዕከል መቋቋም በዘርፉ ከተሠሩ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ሲጋራ ማጨስን አስመልክቶ የተደነገገው መርህ መጽደቁ የኅብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ከተሠሩ ሥራዎች ተጠቃሽ ቢሆንም አሁንም ሲጋራና ጫትን ከመሰሉ አደንዛዥ እፆች የሚገኘው ገቢ ከፍተኛ መሆኑ ሙሉ በሙሉ እንዳይታገዱ አድርጓል፡፡ ለበሽታዎቹ ዋንኛ መስንኤ የሆኑትን አደንዛዥ እፆችን ማስቆምም አልተቻለም፡፡
በመድረኩ የተገኙት ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ፣ የዶክተሯን ሐሳብ ተጋርተዋል፡፡ የአደንዛዥ ዕፆቹ ስርጭት በገንዘብ የታጀበ በመሆኑ አደንዛዥ እፆቹን የማስቆም ጥረት ከባድ ይሆናል ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት የሰጡት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ እንዳሉት፣ በጫትና በሺሻ ላይ ያተኮረ መመርያ በፍትህ ሚኒስቴር እየተረቀቀ ሲሆን፣ በቅርቡም ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር በመተባበር አገር አቀፍ ውይይት ይደረግበታል፡፡
ተላለፊ ያልሆኑ በሽታዎች የመቆጣጠጠርና መከላከል በቅርቡ የተጀመረው የጤና ፖሊሲ ክለሳ ከሚካተቱ አንዱ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ማኒስትሩ፣ ካንሰርን በተመለከተ በርካታ የካንሰር ሕክምና ማዕከሎች መገንባትና ያሉት የበለጠ አገልግሎት የሚሰጡበትን መንገድ መቀየስ አስፈላጊ ነው፡፡
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ሕይወቱን የሚያጣ ሰው ቁጥር በታዳጊ አገሮች ይበዛል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2010 ባደረገው ጥናት መሠረት፣ በአፍሪካ 40 በመቶው የሞት መንስኤ የማይተላለፉ በሽታዎች ናቸው፡፡ በተመሳሳይ ድርጅቱ እ.ኤ.አ. በ2010 ባደረገው ጥናት እንደተመለከተው ኢትዮጵያ ውስጥ 40 በመቶ ያህል ሞት የሚከሰተውም በነዚሁ በሽታዎች ሲሆን፣ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ካንሰር ግንባር ቀደሙን ቦታ ይይዛል፡፡
ዕለቱ ፒንክ ሪበን ሬድ ሪበን የተሰኘ በማሕፀን ጫፍ ካንሰር ላይ የሚሠራ ድርጅት በኢትዮጵያ እንቅሰቃሴውን የጀመረበትም ነው፡፡ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ፈንድ ትብብር የተመሠረተው ማዕከሉ፣ በአፍሪካ ቦትስዋና፣ ዛምቢያ፣ ታንዛኒያ፣ ናምቢያና አትዮጵያ ውስጥ በበሽታው ቅድመ መከላከልና ሕክምና ላይ ይሠራል፡፡
ማኅበሩ በዕለቱ በቀጣይ ለሚኖሩት ሥራዎች የሚውል ከ7.8 ሚሊዮን ዶላር በላይ እርዳታ አግኝቷል፡፡
ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ሮማን እንዳሉት፣ አሁን ካለው የካንሰር ማዕከል በተጨማሪ አምስት ማዕከሎች ተገንብተው አገልግሎት እንደሚሰጡ ጠቁመው የፒንክ ሪበን ሬድ ሪበን እገዛ የማሕፀን ጫፍ ካንሰርን በመከላከል ሁነኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ በተለይም ቅድመ ምርመራ ማድረግ ስላለው ጠቀሜታ የኅብረተሰቡ አመለካከት መለወጥና ሕክምናውም በስፋት መሰጠት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
በመድረኩ ከተሳተፉ ባለሙያዎች አንዳንዶቹ፣ የማሕፀን ጫፍ ካንሰርን ለመከላከል የሚያግዝ ክትባት እንዲሁም ልዩ ልዩ መድሐኒቶች በአግባቡ የሚዳረሱበት መንገድ እንዲኖርና በባለሙያና በሕክምና መሣሪያዎች አለመሟላት የሚጠፋ ሕይወት እንዲቀንስ ተገቢው ዕምርጃ መወሰድ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡