Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅባንክ ጎራ ያለችው ታክሲ

ባንክ ጎራ ያለችው ታክሲ

ቀን:

በካዛንቺስ መናኸርያ መንገድ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካዛንቺስ ቅርንጫፍ፣ የካቲት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ከእኩለ ቀን በኋላ መንገዷን ስታ የገባችው ታክሲ

ፎቶ በመስፍን ሰሎሞን

**************

ተስፋና ቁዘማ

በረባ ባልረባው ፡ ተስፋ እየቆረጡ
ተስፋ አትቁረጥ ሊሉኝ ፡ እኒያውና መጡ።
ባወቁት
ተስፋቸውን ቆርጠው ፡ ተስፋ አትቁረጥ ሲሉ
ያኔ ነው ተስፋዬን ፡ መንግለው የጣሉ።

የኔውስ የኔ ነው ፡ ግን ለመጪው ሁሉ
እንደኔ አይንገሩ ፡ ወይ እንደኔ አይበሉ
ምክንያት
ምን ቢሟጠጥ እንኳ ፡ ቢያጣ እንጥፍጣፊ
ከ”አይዞህ!” ይወለዳል ፡ አዲስ ተስፋ ጣፊ።

  • ደመቀ ከበደ ፡ መሀል ሸገር

*****

ተስፈንጣሪው ሸረሪት

ተስፈንጣሪው ሸረሪት (ጃምፒንግ ስፓይደር) የሚዘለውን ርቀት በትክክል ለማስላት የሚያስችል ለየት ያለ እይታ አለው። ሸረሪቱ ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው?

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ይህ ሸረሪት ዘሎ የሚያርፍበት ነገር ምን ያህል እንደሚርቅ ለመለካት ሁለቱ ዋነኛ ዓይኖቹ ያላቸውን ልዩ ችሎታ ይጠቀማል፤ የእነዚህ ዓይኖች ሬቲና ንብርብር ሆኖ የተሠራ ነው። ንብርብር ከሆኑት ክፍሎች አንደኛው አረንጓዴ ቀለምን ጥርት አድርጎ የሚቀበል ሲሆን ሌላኛው ክፍል ደግሞ ብዥ አድርጎ ይቀበላል። ምስሉ በጣም ብዥ ያለ መሆኑ ሸረሪቱ የሚያየው ነገር በጣም ቅርብ መሆኑን ለማወቅ ያስችለዋል። ይህ ደግሞ የሚዘልበትን ርቀት በትክክል ለማስላትና የሚያድነውን ነገር ለመያዝ ያስችለዋል።

ተመራማሪዎች ይህ ሸረሪት የሚጠቀምበትን ዘዴ በመቅዳት የአንድን ነገር ርቀት በትክክል መለካት የሚችሉ ባለ ሦስት ጎንዮሽ (3-D) ካሜራዎችን አልፎ ተርፎም ሮቦቶችን ለመሥራት አስበዋል። ሳይንስናው የተባለው በኢንተርኔት ላይ የሚገኝ የዜና አውታር እንደገለጸው ከሆነ ‹‹ግማሽ ሴንቲ ሜትር ርዝመትና ከዝንብ አንጎል ያነሰ አንጎል ያላቸው እንስሳት፣ ውስብስብ የሆኑ የእይታ መረጃዎችን ተቀብለው በዚያ መሠረት ዕርምጃ መውሰድ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ›› ለማሳየት የተስፈንጣሪው ሸረሪት እይታ ‹‹ግሩም ምሳሌ›› ነው።

*********

ጎርፉና ሐይቁ

ወቅቱ የዝናብ ወቅትና በጣም ብዙ የሚዘንብበት ጊዜ ስለሆነ ብዙ የጎርፍ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ ጎርፉም እያደር በየቦታው በመዳረስና በየአካባቢው እየተዥጎደጎደ ዛፎችን በመገንደስ፣ እንስሳትን እየጠራረገ እያደር ጉልበቱ እየበረታ ሄደ፡፡

በሃያልነቱም ምክንያት በጣም፣ በጣም ትምክህተኛ ስለሆነ በታሪክ ታላቁ ጎርፍ የሆነ መሰለው፡፡

ጎርፉም አንድ በጣም ቆንጆ ወንድ ልጅ ነበረውና ልጁን ሊድረው ፈልጎ ሃይቁ ደግሞ በጣም፣ በጣም ቆንጆ ሴት ልጅ ነበረውና ጎርፉ ልጁ ይህችን የሐይቁን ልጅ እንዲያገባት ፈለገ፡፡

እናም በባህሉ መሠረት ጎርፉ ያገር ሽማግሌዎችን ወደ ሐይቁ ቤት በመላክ ልጁን እንዲድርላቸው አስጠየቀው፡፡ ሽማግሌዎቹም ወደ ሐይቁ ቤት ሄደው ልጁን ለጋብቻ ጠየቁት፡፡

በዚህ ጊዜ ሐይቁ እጅግ በጣም ተቆጥቶ ‹‹ይህ ጊዜያዊና ነገ የሚያልፍ ወቅታዊ ክስተት እንዴት ልጄን ለጋብቻ ይጠይቃል?›› ብሎ በመቆጣት በንዴት ጥያቄውን አሻፈረኝ ብሎ ሊመልስ ሲል ከእርሱ ወገን ያሉት ያገር ሽማግሌዎች ‹‹ቆይ፣ ጎርፉን አሁን ልታሳዝነው አይገባም፡፡ እስኪ ጉዳዩን እንያዘውና ከራሳችን ጋር እንማከር፤›› ብለው አረጋጉት፡፡

ከዚያም የሐይቁ ሽማግሌዎች የጎርፉን ሽማግሌዎች ‹‹ተመልከቱ፣ እኛ ስለሙሽራው፣ ስለ አባቱና ስለዘመዶቹ ብዙ ነገር ማወቅ እንፈልጋለንና በባህላችን መሠረት ቀጠሮ እንስጣችሁና በቀጠሮው ቀንም ሁላችሁም ትመጡና ተቀባይነት ካገኛችሁ ልጃችንን ልንሰጣችሁ እንችላለን፤›› አሏቸው፡፡

የጎርፉም ሽማግሌዎች በዚህ ተስማምተው የሐይቁም ሽማግሌዎች እንዲህ አሏቸው፣ ‹‹እንግዲያው ቀጠሮአችን በፓርሱስ 26 ቀን እንዲሆን ቆርጠናል፤›› የፓርሱስ ወር በደረቁ ወቅት አማካይ ላይ የሚውል ወር ሲሆን በዚህ ወር ምንም ዝናብ የለም፡፡ ስለዚህ በግልፅ ማየት እንደሚቻለው ይህ ወር ሲገባ ምንም ዓይነት ጎርፍም ሆነ ዝናብ ስለማይኖር ማንም ሰው በቀጠሮው ቀን አልመጣም፡፡

የዚህ ታሪክ መልእክትም በጊዜያዊ ስኬት መታበይ እንደሌለብንና ሁሉም ጌዜውን እንደሚጠብቅ የሚያሳይ ነው፡፡

  • በይስሃቅ አልዳዴ የተተረከ የወላይታ ተረት

**********

እንቆቅልህ

እንቆቅልህ ወይም እንቆቅልሽ ማለት ከቀን ብዛት አነጋገሩ ተለውጦ ነው እንጂ ዕንቁላል አለህ ወይም እንቁላል አለሽ ማለት ነው፡፡ ዕንቁላል ድፍን በመሆኑ በውስጡ ያለው ጫጩት ወንድ ይሁን ወይም ሴት ትሁን ከቅፍቀፋው ወይም ከፍልፈላው በፊት ሊታወቅ ባለመቻሉ የተሰወረና የተደበቀ ምስጢር መጠያየቂያና መፈታተኛ ሆኖ ሲያፋትን ይኖራል፡፡

(ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ፤ ከሥራ በኋላ ሥራ ስትፈቱ እንቆቅልሽ ተጫወቱ፣ 1943)

***************

ፈተና

በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ አንድ ሰው ለተፈለገበት መደብ ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ወጥቶ በርካታ ሥራ ፈላጊዎች ይመዘገባሉ፡፡ ከብዙዎቹ ግን በመጨረሻው ዙር የደረሱት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ከጥቂቶቹ ደግሞ በተለያዩ መስፈርቶች ተጣርተው ሁለት ይቀራሉ፡፡

የመጨረሻዎቹ ተፈታኞች ወንድና ሴት ነበሩና አንድ ላይ ፈታኙ ፊት እንዲቀርቡ ይደረጋል፡፡ ፈታኙ ቀድሞውኑም ቀልባቸው ልጅቱ ላይ አርፎ ኖሮ መጀመሪያ ሴቷን፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ስንት ነው›› አሏት፡፡ ልጅቱም ሳትቆይ ‹‹75 ሚሊዮን›› ትላለች፡፡ ቀጠሉና ወንዱን ተፈታኝ ‹‹አንተ ደግሞ ስማቸውን ጥራ›› ብለው ለዩት፡፡

(ዘመን መጽሔት መጋቢት 2001)

****************

 

ጨረቃ ላይ ናቸው የተባሉ ቁሶች በምድር ተገኙ

የሰው ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃ ላይ ባረፈበት ወቅት ከመሬት ወደ ጨረቃ ተወስደው እዛው እንደተተዉ የታመኑ ቁሳቁሶች ባለፈው ሳምንት ኒል አርምስትሮንግ ቁም ሳጥን ውስጥ ተገኝተዋል፡፡ የተገኙት ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃን የረገጠው አርምስትሮንግ ጨረቃን ከመርገጡ አስቀድሞ እግሩን የደገፈበት ገመድና ጉዞውን የቀረፀበት ካሜራ ናቸው፡፡ አርምስትሮንግ ያረፈው እ.ኤ.አ. በ2012 ሲሆን፣ ሮይተርስ እንደዘገበው ባለቤቱ ቁምሳጥኑን በምታፀዳበት ወቅት ነበር ቁሳቁሶቹን ያገኘችው፡፡

የህዋ ሳይንስ ታሪክ ኪውሬተር የሆነው አለን ኒደል እንዳለው፣ ቁሳቁሶቹ እስከዛሬ ጨረቃ ላይ እንደሚገኙ ይታሰብ ስለነበር እጅግ የሚያስደስት ግኝት ነው ብሏል፡፡ ቁሳቁሶቹ አሁን በናሽናል ኤየር ኤንድ ስፔስ ሙዚየም በመታየት ላይ ናቸው፡፡

***************

ማንዴላ የጠፉበት ወቅት

ኔልሰን ማንዴላ ከቪክተር ቮርስተር እስር ቤት የካቲት 4 ቀን 1982 ዓ.ም. ሲለቀቁ የደቡብ አፍሪካ መዲና ኬፕ ታውን የማንዴላን ንግግር ለመስማት በጉጉት በሚጠብቁ ሰዎች ቢሞላም ማንዴላ በሰዓቱ አልደረሱም፡፡ ማንዴላ በወቅቱ ከእስር ቤቱ እንደወጡ ከእስር ቤቱ አቅራቢያ ወዳለ መዝናኛ ነበር ያመሩት፡፡ የማንዴላ ፋውንዴሽን በቅርቡ እንዳስታወቀው በዕለቱ፣ ማንዴላን ለሰዓታት ማግኘት አልተቻለም ነበር፡፡

የቀድሞው የአገሪቱ ገንዘብ ሚኒስትር ማኑዌል ትሬቨር ‹‹ማንዴላ ነፃ እንደወጣ ዓለም ሊያየው ጓጉቶ ነበር፤ ለሰዓታት ከፈለግነው በኋላ መጨረሻ አንድ ፀጥ ባለ መዝናኛ ውስጥ ጫማውን አውልቆ ሻይ ሲጠጣ አገኘነው፤›› ብለዋል፡፡ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው ማንዴላ ጠፍተው ቢቆዩ ኖሮ ኬፕ ታውን ትርምስምሷ ይወጣ ነበር፡፡ ማንዴላ ወደሚጠብቃቸው ሕዝብ ሲመለሱ በጣም ጨልሞ ስለነበር ንግግሩን ያደጉት በእጅ ባትሪ ታግዘው ነበር፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...