Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የዓይን አውጣነት ዘመን!

ሰላም! ሰላም! የጓዳችን ሰበር ዜና ተወርቶ ሳያልቅ ግን ምንድነው ‘ቢቢሲና አልጄዚራ’ በሰበር ዜና የሚያስጨንቁን? ዝም ትላላችሁ? እኔ የማልወደው ይኼን ካሉት ወይ ከሞቱት የማያስመድብ ዝምታችሁን ነው። ውዷ ማንጠግቦሽን ይንሳኝ! ቱ ምን አልኳችሁ? ይኼውላችሁ ይህቺን መሃላ ያለቅጥ እየደጋገምኩ ማንጠግቦሽን አስገኝቻት ነበር። ሰሞኑን እጅግ ታማብኝ የምይዝ የምጨብጠውን አጥቼ (መብራት እየጠፋብን ሦስት አራት ቀን ባናድር እኮ ኮረንቲ እየጨበጥን የምናልቀው ብዙ ነበርን) ብታዩኝ አታውቁኝም። “መቼስ ሰው ቆሞ ሲሄድ ስታየው የሚወድቅ አይመስልም፤” ስለው የባሻዬን ልጅ፣ “እንኳን አንድ ሰው 120 ሆነው አብዮት የጠለፉትም ወድቀዋል፤” እያለኝ ጭንቀቴን ሊያለዝብ ሲጣጣር በጣር ሰነበትን። ውይ! ውይ! ጤና ከምታጡ ኮሙዩኒስቶች ተመልሰው ይምጡ! እሱስ መቼ ቀረልን ስትሉኝ አልሰማሁም አሉ! 

ታዲያ ማንጠግቦሽ ያው እንደምታውቋት እንኳን በሽታ ፌሽታም በመጠኑ ካልሆነ እስከ ጥግ የሚሄድ ማንነት የላትም። የእሷን ተፈጥሮ ሳይ ከአንዳንድ ጫንቃቸው ሰፊ ከሆኑ ሰዎች ጋር እያስተያየኋት እገረማለሁ። (አንድ ጓደኛ አለኝ ይህቺን ‘ጫንቃ ሰፊ’ የሚሏት አባባል አብዝቶ የሚጠቀም) እንዲያው ድህነት፣ በሽታና ግራ መጋባቱን ትታችሁት ኃፍረትና ይሉኝታን ብታስቡ ዘመኑ ብዙ ያነጋግረናል። በጓደኛዬና በእኔ መዝገበ ቃላት ጫንቃቸው ሰፊ የሆኑ ሰዎች ማለት ‘ምን ይሉኝ?’  ብሎም ‘ሼም’  የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል ያልፈጠረባቸው ማለት ናቸው። እናም ፈርዶብኝ በየሄድኩበትና በድለላ ሥራዬ ሳይቀር ሲያጋጥሙኝ ይገርመኛል። አንዳንዴ በክፉም በደጉም ብዙ ሊሸከሙ፣ ብዙ ሊራመዱ ነፍሳቸው ከነሐስ የተሠራችች ይመስሉኛል።

የማየውን እኮ ነው ‘ላይቭ’ የማወራችሁ! ‘ባይ ዘዌይ’ የባሻዬ ልጅ “ይኼን ያየሁትና የሰማሁት እያልክ ‘ላይቭ’ መዘገብ ቀነስ አታደርግም? በ‘ኢንቨስትጌቲቭ ጆርናሊዝም’ ያበደ እንጂ ያሳበደ ዓይተን አናውቅም፣ ልብ አድርግ!” እያለ ያስፈራራኛል። እኔ ግን ወይ ፍንክች ብያለሁ። ሸቤ ፈርቼ ዓይኔን ልጨፍን? ይቀልዳል እንዴ! ከዓይን በላይ ምን አለ? ቅንድብ ነበረ እሱንም ትምህርት ቤት በነሲብ ምርጫ ስንሞላ ነጭተን ጨርሰነዋል። ይኼው ከዚያን ጊዜ ጀምረን ከዓይን ይልቅ ነሲብ፣ ከማስረጃ ይልቅ አሉባልታ አፍቅረን አለን። ተሳሳትኩ? አይዟችሁ ከተሳሳትኩ ተሳስተሃል በሉኝ፡፡ ሄድ መለስ ቢልብንም ዘመኑ የዴሞክራሲ ነው!

 ወደ ዋናው ቁምነገር ስመለስ . . . ምን ነበር የማወራው?  . . .  እ . . . አዎ፣ በውርደታቸው የሚመኩ፣ በውድቀታቸው የሚታበዩ፣ በማጭበርበር ሥልታቸው የጀግነት ካባን አጥልቁልን ብለው ዓይናቸውን በርበሬ ስለሚያስመስሉ ጫንቃቸው ሰፊ ስለሆኑ ሰዎች ነበር የማጫውታችሁ። አይ ‹ሚሞሪ!› የነፃነትና የዴሞክራሲ ‹ቮካቡለሪ› ነው እንጂ የቸገረን እንጂ የታሪክ ‹ሚሞሪ›ማ ነበረን። ምን ዋጋ አለው? (ምንድነው ዛሬ ደርሶ ነገር ነገር የሚለኝ ፀሐዩ ነው እንዴ?) ታዲያ የባሻዬ ልጅ፣ “እነሱ ባይኖሩማ በእኛ ዓይነ አፋርነት፣ ፍርኃት፣ ፈራ ተባ ማለት ኢኮኖሚውና ውድድሩ መቼ ይደምቅ ነበር?” ብሎ ዓይና አውጣዎችን ደግፎ ባላሰብኩት አቅጣጫ እየመጣ ያስጨንቀኛል። ‹‹When There is Blood on the Street, Buy!›› (አይዟችሁ እኔ እፈታላችኋለሁ፤ ቱ ደሞ ይህቺን? በአጭሩ ‘ግርግር ለሌባ ያመቻል’ ማለት ናት! ሳትጨመር ሳትቀነስ) ይላሉ ፈረንጆቹ።

‹‹አንበርብር ምንተስኖት በዚህ ዓለም ላይ በየዋህነት አንገቱን ያቀና ምጣኔ ሀብት ፈጽሞ የለም፤” ብሎ ይጨምርልኛል። መጨመሩ ሳያንሰኝ እንግሊዝኛው ብቻ ራሴን ያዞረኛል። እናም የጎዳናው ጭብጥ ‘በቀደመ ብቻ ሳይሆን በአፈጠጠም ዓይን ባወጣም ነው’ ሆኖ ቋንቋውን ስታዞሩት፣ በጠራራ ፀሐይ ከልጅ እስከ አዋቂ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በፈጣጣው ስንዘረፍ እንውላለን። መቼም ሲፈጥረን ‘ሼመኞች’ ነን ብያችሁ አይደል? ሙሰኛ ለቁርስ፣ ምሳና ራት ሥጋ ቤት ሆዱን ሲያሽ እያዋለ፣ እኛ ሆዳችን እየጮኸ መሰንበትም ተስፋ ነው እያልን እንኖራለን። መቼስ በእውነት መኖር ደግ ነው!   

እናላችሁ ሰሞኑን ማንጠግቦሽኝ እያስታመምኩ ትኩሳቷ ሲያተኩሰኝ የአንዳንዱ ሰው ከብርሃን ፍጥነት በሚልቅ ፍጥነት መተኮስ ፊቴ ድቅን ይልብኛል። “ወይ አገር! ወይ ሰው መባል?” እያልኩ ብርግግ ስል ማስታመሜ ቀርቶ እኔ ራሴ አስታማሚ ሊያስፈልገኝ ሆነ። ውዷ ማንጠግቦሽ ሁኔታዬ ግራ ገብቷት፣ “ምን እያሰብክ ነው እንዲህ ብንን ብንን የምትለው?” ስትለኝ፣ “የእኔን ነገር ታውቂው አይደል ቤት ተቀምጨ ውዬ አላውቅ!” እያልኩ እተጣጠፍባታለሁ። እሷም ነገሩ ያልገባት መስላ ግን ገብቷት ታልፈኛለች። ተፈጥሮዬ ሆኖ የተሰማኝን መደበቅ ያሰብኩትን መሰወር ተሳክቶልኝ አያውቅም። ይኼን ማንነቴን ባሻዬ በደንብ ስለሚያውቁ፣ “ለምንድነው ግን አንዳንዶች የሚሳካላቸው እባብነት ለአንዳንዶቻችን የማይሆንልን? ሐሰት በደረቷ እየተሳበች ይኼን ያህል ከገነነች ሀቅ እንደ ንስር ከደመና በላይ የምትበርበት ዘመን መቼ ነው የሚመጣው? ፅድቅ፣ ፍትሕ፣ እውነት የት ናቸው?” ይሉኛል። ‘እንጃ ባሻዬ! እንጃ!’

        አያያዜን ዝም ብዬ ሳስበው ማንጠግቦሽን በማስታመም ከገፋሁ እንደማያዋጣኝ ገባኝ። ቁጭ ብዬ በነገር እህህ ስል እኔ ራሴ አልጋ እንደምይዝ ታወቀኝ (ተያይዞ መውደቅ እንጂ መነሳትማ አልታደልንም)፡፡ ስለዚህ አልኩና አንዲት ቁንድፍት ልጅ ፈልጌ ቀጠርኩ። ‘ወይ ቁንድፍት እቴ’ ያልኩት በኋላ፤ ምን ዋጋ አለው? ልነግራችሁ እኮ ነው! ዕቃ ብታነሳሳ ውኃ ብታቀብላት ብዬ ብቀጥራት ልጅት ጠዋት 12 ሰዓት ተነስታ ቴሌቪዥን መክፈት ነው። ማታ “ኧረ አጥፊው እንተኛበት” ብለን ስንገስፃት ስልኳን አውጥታ በፌስቡክ ግድግዳዋ ላይ “ቴሌቭዥን ብርቅ ነው እንዴ?” ብላ ስትለጥፍ አጮልቀን ማየት ነው። ደግሞ  የማታውቀው የፊልም አክተር፣ የማታውቀው ሙዚቀኛ፣ መነሻ መውደቂያቸውን የማትተርክላቸው የሚዲያ ሰዎች የሉም። ማታ ቤቴ እንደገባሁ ማንጠግቦሽን “ተሻለሽ?” ብዬ በመጠየቅ ፈንታ “ክላስ’ እንዴት ነበር?” ማለት ይቀለኛል። ማንጠግቦሽ እየሳቀች የተጋተችውን ‘የሚዲያ ሌክቸር’ ለእኔ ትከልሳለች። ባሻዬ ስለማንጠግቦሼ ጤና መሆን ሲጠይቁኝ የልጅቷን ታሪክ ባጫውታቸው፣ ‹‹ወይ ስምንተኛው ሺሕ! ደግሞ ብለው ብለው ሽንኩርት መክተፍ፣ ዕቃ ማነሳሳት፣ ቤት ማፀዳዳትንም በስክሪን ተች ሊተኩት ነው?” ብለው ፈገግ ብለው አዩኝ። ወይ ‘ተች ስክሪን’ አያ!

ጨዋታ ነው የያዝነው መቼስ። አዎ! ደጅ ተፍ ተፍ ባልኩባቸው ጥቂት ቀናት ደግሞ ሁለት ‘ከዓይኔ አላጣሽ’ መኪኖች እጄ ላይ ነበሩ። ‘ከዓይኔ አላጣሽ’ ያሉዋቸው ‘ቪትዞችን’ ነው። ስም እናውጣ እንጂ ድሮስ ራስን ማውጣትማ አልተቻለም እኮ? እናም ‘መኪኖቹን አሻሽጨ የማገኛትን አግኝቼ በዚያውም ለእኔ ዕረፍት ይሆናል ቤቴ ከማንጠግቦሽ ጋር እመሽጋለሁ’ እያልኩ ስሳነፍ ስልኬ ጠራ። ‘አቤት!’ አልኩ። (አቤት ባይና አሜን ባይ ስለተመናመነ አይመስላችሁም አንዳንዱ ችግር እያደር እንደመለዘብ የሚከረው? ወይስ እንዴት ነው?) 50 ሚሊዮን ብር የሚሸጥ ቤት እንዳለ ተጠቆምኩ። አቤት ሲያመጣው! በቃ ምርጫ እስኪያልፍ ‘ቫላንታይንስ ዴይን’ አስታክኬ ከቤቴ ላልወጣ ነው አልኩላችሁና የመኪኖቹን ድለላ ለጠረረበት ወዳጄ አስተላልፌ እኔ ወደ ሚሊዮኖቹ ሮጥኩ። ላይ ታች ዥዋዥዌ ተጫውቼ በግፊ የሚነሳውን ገፍቼ ሃሞቱ የፈሰሰውን፣ ሞተሩ የነከሰውን አለስልሼና አባብዬ ቤቱን ወደማሻሻጥ ስቃረብ አንድ ወዳጄ፣ “ስምንት ሺሕ ብር ይዘህ ታጥፈህ ተዘርግተህ ቶሎ ድረስ፤” ብሎ ደወለ። “የሆንከውን በስልክ ንገረኝና ልምጣ፤” ስለው፣ “የለም በቶሎ ካልመጣህ” ብሎ አስጨነቀኝ። ከሚሊዮንና ከአንድ ለችግሩ ጊዜ ድረስልኝ ከሚለኝ ወዳጄ ማንኛቸውን ማስቀደም እንዳለብኝ ሳወጣ ሳወርድ ራሴን ታዘብኩት።

ይኼውላችሁ ጊዜው እንዲህ ነው። “‘ወደፈተና አታግባኝ’ ብሎ ፀሎት የሚሠራለት ሰው፣ ያውም እንዲህ ገንዘብና ፍቅር ጉረሮ ለጉረሮ በተያያዙበት ዘመን ጥቂት ነው፤” የሚሉኝ ባሻዬ ትዝ እያሉኝ ‘ለእኔ ካለው የት ይሄዳል’ ብዬ ወደ ወዳጄ ሮጥኩ። ደርሼ የሆነውን ሳጣራ እናቱ በጠና ታመው ሆስፒታል መግባታቸውን አጫወተኝ። ገቢዎች ገቢ ማድረግ ያለበት ስምንት ሺሕ ብር የቅጣት ገንዘብ ስላለ ሄጄ ጉዳዩን እንዳስፈጽምለት ዶክመንቶቹን አቀብሎኝ ወደ ሆስፒታል ሮጠ። መቼስ ምን አደርጋለሁ?  እጄ ላይ ያለችውን አንድ አሥር ሺሕ ብር  ይዤ ከአሁን አሁን ከፍዬለት ወደ ድለላዬ እከንፋለሁ እያልኩ ስጣደፍ ገቢዎች ደረስኩ። የሚያስተናግደኝ ወጣት “ሦስት መቶ ብር!” አለኝ። “ወደ ስምንት ሺሕ ብር እኮ ቅጣት አለበት” ስለው “ቅጣቱ ተነስቷል።” አለኝ። “ምንም የምቀጣው የለም?” ስለው ጆሮዬን ማመን ከብዶኝ ሳለ፣ ‹‹ይልቁንስ ሄደው ለመምረጥ ይመዝገቡ …›› ብሎኝ አረፈው። እንደ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሁለት እጆቼን አንስቼ “8100! A! A!” እያልኩ ስጨፍር ሠራተኛውን በሳቅ ገደልኩት። ምን እንደሚሻለኝ እንጃ!

በሉ እንሰነባበት። ፈጣሪ የልቤን ዓይቶ በሌለኝ ገንዘብ ሳልቀጣ ቅጣቱን አስነስቶ እጅ በእጅ ሲከፍለኝ ሳይ፣ “ምነው እንዲህ ቅርብ ነህ እንዴ?” ስል ዋልኩ። ከገቢዎች ስከንፍ ወደቤቱ ጉዳይ ስመለስ ቀደም ብዬ ከቤቱ ባለቤት ጋር ስልክ ያለዋወጥኳቸው ደንበኞች ቤቱን ሲጎበኙት ደረስኩ። ለመወሰን አንድ ቀናት እንደሚፈልጉ ተናግረው የሻይ ጥቂት ብሮች ሸጉጠውልኝ በይደር ተለያየን። ይኼ ሥራ ከተሳካልኝ የዓመቱን ዝግ ዘጋሁ እያልኩ ወደቤቴ ሳመራ ስልኬ ጮኸች። አነሳኋት። ደግሞ አንድ በቅርብ የማውቀው ሰው “አንበርብር እባክህ ውለደኝ!” ብሎ ያለቃቅስብኝ ያዘ። ‘እንዴ አንበርብር ‘ዩኒሴፍ’ ነው ተብሏል እንዴ? ሰው ዛሬ?’ እያልኩ በልቤ፣ “ምን ሆንክ ደግሞ?” ብዬ ብጠይቀው “አንድ ያሰብኩት ነገር ነበር ሳይሳካ ቀርቶ ይኼው በፍቅረኞች ቀን ገንዘብ የሚባል የለኝም። ያስለመድኳት ቢቀርባት ጥላኝ መሄዷ ነው። እንዴት እንደምወዳት ታውቃለህ። ‘ፕሊስ’ ለ‘ቫላንታይንስ ዴይ’ ለፍቅረኛዬ ስጦታ የምገዛዛበትና የምጋብዝበት በቅርቡ የምመልስልህ አሥር ሺሕ ብር አበድረኝ፤” ብሎኝ ሳይጨርስ ጉና ተራራ ድረስ የሚሰማ የተጠራቀመ የብሶት ሳቄን ለቀቅኩት። ስልኬንም በዚያውም ጥርቅም አድርጌ አጠፋሁት። ወዲያው አጠገቤ ካለ አበባ መሸጫ ሱቅ አንዲት ዘለላ አበባ ገዛሁና ወደ ማንጠግቦሽ ሮጥኩ።

ስደርስ ተሽሏት ሰውነቷ ምልስ ብሎ ጠበቀችኝ። ምንም ሳትሠራ ቴሌቭዥን ላይ ተተክላ የከረመችውን አልምጥ የቤት ሠራተኛ አሰናብታ ጉድ ጉድ ትላለች። እቅፍ አድርጌ ሁሌም እንደምወዳት ነገርኳት። ቤት ያፈራውን ክሽን አርጋ የሠራችውን ወጥ እየተጎራረስን የአሥር ሺሕ ብሩን ጉድ አጫወትኳት። እሷም እስከ መራቤቴ ከት ብላ ስቃ፣ “ወርቅ፣ አልማዝ፣ ቶፓዝዮን፣ በአጠቃላይ ገንዘብ  እውነተኛ ፍቅርንና ሰላምን የሚገዛ ቢሆን፣ ሀብታም የተባለ ሁላ ባላንጣ የሚባል መቼ ይኖረው ነበር?” አለችኝ። ምን አባቴ ላድርግሽ አልኳታ! እኔ የምለው በፍቅር ሕግ ሥፍራና ጊዜ ይቆጠራል እንዴ? የፍቅረኛሞች ቀን በደንብ ከሚያውቁትና ከሚግባቡት የልብ ወዳጅ ጋር ጊዜ የሚያሳልፉበት እንጂ ዕዳ እያዘፈቀ፣ በሬ እያሳረደ፣ እንቁ እያሸመተ፣ ያልሆኑትን የሚያስሆን ‘ባላንጣያንስ ዴይ!’ የሆነው ከመቼ ወዲህ ነው? ‘ቫላንታይንስ ወይስ ባላንጣያንስ ዴይ?’ የዓይን አውጣነት ዘመን! መልካም ሰንበት!  

  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት