Tuesday, February 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየልብስ ፖለቲካ

የልብስ ፖለቲካ

ቀን:

ገዢና ተገዢ፣ መሳፍንት መኳንንት እንዲሁም ንጉሣውያን ከተራው ሕዝብ ጋር አንድ ዓይነት ልብስ እንዲለብሱ የማይፈቀድበት ጊዜ ነበር፡፡ የመሳፍንቱ የመኳንንቱ ልብስ የተለየ ይሆን ዘንድ በተዋረድ ልዑል፣ ራስ፣ ቢትወደድ፣ ደጃዝማች፣ ፊታውራሪ፣ ቀኛዝማች፣ ግራዝማች፣ ባላምባራስ ወዘተ እየተባለ የአልባሳት ልዩነት ብቻም ሳይሆን የገዢና ተገዢ መጠጥና ምግብ፤ ፅዋና ማዕድም የተለየ ነበር፡፡ ይህን የልዩነት መስመር መጣስ የሚያስቀጣ እንደነበርም ታሪክ ያወሳል፡፡

ጠጅ የመሳፍንቱና የመኳንንቱ መጠጥ ብቻ ተደርጎ ይታይ በነበረበት ጊዜ ጠጅ አስጥሎ በመደገስ አስጨፈረ ተብሎ ተከስሶ ከፊታቸው የቆመን ‹‹ተርታ›› ሰው ሰውየው ራሱ አንብቶ ራሱ ማር ቆርጦ ባስጣለው ጠጅ ለምን ገደብ ይጣልበታል ሲሉ አፄ ዮሐንስ አራተኛ የመሳፍንትና የመኳንንቱን መጠጥ እንደተራ ጠጣም አስጠጣም የተባለውን ሰው በነፃ ማሰናበታቸውም በታሪክ ሰፍሯል፡፡

በአፄ ኃይለ ሥላሴ የንግሥና በዓል ላይ ማን ምን ይልበስ የሚለው ተለይቶ እንደነበርም በዝክረ ነገር ተቀምጧል፡፡ በፖለቲካው በሃይማኖቱ እንዲህ እንዲህ እያለ በየዘርፉ ማን ምን መልበስ አለበት እየተባለ ገዢና ተገዢ፣ ተራው ከተመረጠው ይለይ ዘንድ ተቀምጧል፡፡ ይህ በተለይም የኢጣሊያን ወረራን ተከትሎ ንጉሡ ከአገር እስከወጡበት ጊዜ ድረስ የሚስተዋል የአለባበስ ሥርዓት ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ባለሥልጣናትና ሹማምንትን ቀሪው ሕዝብ በአልባሳት የማለያየት ነገር በደርግ ሥርዓትም መቀጠሉን የሚገልጹ ምሁራን በኢሕአዴግ ደግሞ በተለይም በትልልቅ መድረኮች፣ ባለሥልጣናት ሕዝቡም አንድ ዓይነት እንዲለብሱ የማድረግ ባህላዊ ልብሶችን ለገጽታ ግንባታና ለድጋፍ መሠረት ማጠንከሪያ የመጠቀም ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ጊዜው ከመቼውም የበለጠ ባህላዊ ልብሶች በብዙ ዓይነት መንገድ አደባባይ የወጡበት ነው፡፡ በታዋቂ ዲዛይነሮች ተሠርተው ለዕይታ ከዚያም ለገበያ ከበቁ ባህላዊ ልብሶች ባሻገር በትልልቅ ብሔራዊና ክልላዊ ስብሰባዎች፣ ባህላዊ ክብረ በዓላት ላይ በባለሥልጣናትና በበርካታ የስብሰባ ታዳሚዎች በቀሪው ሕዝብም መለበስ የባህላዊ ልብሶቹ ሌላ ገጽታ እየሆነ ነው፡፡

የእነዚህ ልብሶች በስካርፍ፣ ሸሚዝ፣ ኮትና በሌላም መልክ እየተሠሩ በተለያዩ መድረኮች ባለሥልጣናትን ጨምሮ በብዙዎች መለበስ ልብሶቹ የዚህ ብሔር የዚያኛው ብሔረሰብ እያለ እንዲለይና እንዲታወቁ እያደረገ ነው፡፡ የባህላዊ ልብሶቹ ባህላዊ መሠረት፣ የቀለማት ህብር መነሻ ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ግን በብዙዎች ይነሳል፡፡

ባለ ጥቁር፣ ቀይና ቢጫ ህብር ቀለም የጋሞ ሕዝብ የባህል ልብስ ‹‹ድንጉዛ›› ቀለሙ፣ ድሩ በጥቅሉ የልብሱ አሠራር ትርጉም እንዳለው የአርባ ምንጭ ከተማ ምክትል ከንቲባና የባህል፣ ቱሪዝምና መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሴፍ፣ ኩማ ይናገራሉ፡፡ ይህንን ባህላዊ ልብስ በሚመለከት መጽሐፍ ያሳተሙት አቶ ዮሴፍ ድንጉዛ በዘፈቀደ የሚለበስ ሳይሆን የባህል አባቶችና አለቆች በተለየ ሁኔታና ቦታ የሚለብሱት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

በባህል ድንጉዛ የክብር እንጂ በዘፈቀደ የማይለበስ ቢሆንም ዛሬ ላይ በተለያየ ዲዛይን በኮት፣ ሸሚዝና ስካርፍ መልክ ተሠርቶ በብዙዎች በሌላ ብሔረሰብ አባላትና በውጭ አገር ዜጎች ጭምር መለበሱ ባህሉን እንደሚያስተዋውቅና በአንድ ቦታ ላይ ተወስኖ እንዳይቀር እንደሚያደርግ ያምናሉ፡፡

የተሠራ ሰፊ ጥናት ባይኖርም የባህላዊ ልብሱ ከሌላ ጋር ተቀላቅሎ የመለበስ ነገር አንድ ሊታይ የሚገባ ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ ምንም እንኳ በምክር ቤት ደረጃ በጋሞ ባህላዊ ልብስነቱ የፀደቀ ቢሆንም ድንጉዛ በወላይታም የባለቤትነት ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ ‹‹ድንጉዛ የጋሞ ነው የወላይታ›› የሚለው ክርክር በተወሰነ መልኩ ከድረ ገጾችም ዘልቋል፡፡

ቀደም ሲል ልብሱን ሁለቱም ሕዝቦች ይለብሱት እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ዮሴፍ በወላይታ በኩል ድንጉዛ የእኛ ነው የሚል ነገር እንደሚነሳ ቢያውቁም ጥያቄው ግን በቢሮ ደረጃ ተነስቶ አያውቅም ይላሉ፡፡

ባለ ደማቅ ሰማያዊ፣ ነጭና ቡኒ (ጉበታማ) ቀለም ህብር የከንባታ ጠንባሮ ብሔረሰብ ባህላዊ ልብስ መነሻው ባህል፣ የአካባቢው መልክዓ ምድራዊ እውነታ እንዲሁም የብሔረሰቡ ባህላዊ እሴት መገለጫ እንደሆነ የከንባታ ጠንባሮ ዞን ባህል ቱሪዝምና መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የባህል ጥናትና ምርምር ባለሙያ አቶ ወንድሙ ዳምጠው ይናገራሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት ሰማያዊው፣ ብሔረሰብ ‹‹ይሁን ወይም ይኼን እናደርጋለን›› ካለ በቃሉ የሚቆምና የሚፀና መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ጥንት አባቶችና እናቶች የሚለብሷቸው ነጠላዎች ጥለትም በብዛት ሰማያዊ መሆንም ከግምት የገባ ሌላ ነገር ነው፡፡

በ2000 ዓ.ም. በዞን ምክር ቤት የከንባታ ባህላዊ ልብስ ሆኖ መፅደቁን የሚናገሩት አቶ ወንድሙ፣ ዛሬ ላይ በአካባቢው የሙሽራ ልብስ እንኳ በዚህ ባህላዊ ጨርቅ እየተሠራ መሆኑን የልብሱ ተቀባይነት የማግኘት ውጤት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ልብሱ በምክር ቤት የፀደቀው በከንቲባ ያለው ከሦስት መቶ በላይ ጐሳ ተስማምቶ መሆኑንና በባህላዊ ልብሱ መሀል ላይ የሦስቱም ቀለሞች ተጠላልፎ መታየትም የጎሳዎቹ ትስስር መገለጫ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

ከተለያዩ ባለሙያዎች ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ረዥም ዘመን ወደኋላ ሄደው በአያት ቅድመ አያቶች ለብዙ ዓመታት የተለበሱ ባህላዊ ልብሶችን ዛሬ ላይ አጉልተው የማንነታቸው መገለጫ ያደረጉ እንዳሉ ሁሉ አዲስ መገለጫ ይሆነናል ያሉትን ባህላዊ ልብስ የፈጠሩም አሉ፡፡ በዚህ መንገድ ውስጥ አልፈው በቀለም ምርጫ፣ በአሰፋፍ አልያም በሌላ ምክንያት ተቃውሞ የገጠማቸውም ባህላዊ ልብሶችም አይጠፋም፡፡

እንደ አዲስ መገለጫ ሊሆን ይችል ዘንድ አዲስ የባህል ልብስ ይዘው ብቅ ካሉ መካከል ስልጤ ብሔረሰብ አንዱ ነው፡፡ ቀለም እንዴት ተመረጠ? ልብሱ መገለጫችን ይሆናል ነው የሚለው መግባባት እንዴት ተፈጠረ? የሚሉና ሌሎችንም ጉዳዮች በሚመለከት የ10 ብሔረሰቦችን ተሞክሮ በማጤን በሰፊ ጥናት ልብሱ ዕውን መሆኑን የስልጤ ዞን ባህል ቱሪዝምና መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ መሐመድ የሱፍ ይናገራሉ፡፡

እሳቸው እንደገለጹት የተሠራው ጥናት ከሁለት ዓመት በላይ የወሰደ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤትና ሌሎች ምሁራንም በጥናቱ እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ በጥናቱ ብዙ ነገሮች የተዳሰሱ ሲሆን፣ ሕዝቡ አብዛኛውን ጊዜ ቤቱን ለማሳመር የሚመርጣቸው ቀለሞች፣ የልብስ ቀለም ምርጫ፣ የአካባቢው የአፈር ቀለም፣ ገበያ ሲወጣ የሚታየው ገዢ ቀለም፣ ሰው ለሥራ፣ ለሐዘንና ደስታ የሚመርጠው ልብስ ቀለም ከግንዛቤ ከገቡ ነገሮች የተወሰኑት ናቸው፡፡

በ2003 ዓ.ም. በምክር ቤት የፀደቀው ባለ ጥቁር፣ ነጭና ቡርትካናማ (ሚጥሚጣ) ቀለም ህብር የስልጤ ባህላዊ ልብስ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በትልልቅ መድረኮች ላይ በብዙዎች ተለብሷል፡፡ ነገር ግን ከመፅደቁ በፊት ልብሱን ሕዝቡ የኔ ብሎ ሊቀበለው የግድ ስለነበር የብሔረሰቡ አባላት የተሳተፉባቸው ሰባት ዙር የትችት መድረኮች ተዘጋጅተው እንደነበር አቶ መሐመድ ያስታውሳሉ፡፡

ብሔረሰባዊ ማንነት እንዲገለጽ ከማድረግና ከሌሎች ነገሮች አንጻርም የልብሱ ሚና ከፍተኛ እንደሆነ እምነታቸውን የሚገልጹት አቶ መሐመድ፣ ዕርምጃው ባህላዊ ነገሮችን ለመንከባከብና ጠብቆ ለመቆየትም አስተዋጽኦ እንዳለው ያመለክታሉ፡፡ ‹‹ለምሳሌ በገጠር እንኳ የቀሩ የቤት ቀለሞች አሁን በከተማ ሁሉ ተመራጭ እየሆኑ ነው›› በማለት የባህላዊ ልብሱ ቀለሞች ከመታወቅና ከመለመድ አልፈው የብዙዎች ምርጫ እየሆኑ መምጣታቸውን ያስረዳሉ፡፡

ከ2006 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ በብዛት የስልጤ ልብስ ዲዛይን እንዳደረገ የሚናገረው አርቲስት ዴልታ መሐመድ ጀማሪ ዲዛይነር ነኝ ይላል፡፡ ልዩነት ውበት ነው የሚባለው እውነት በቋንቋና በሌላም መንገድ ከመገለጹ ባሻገር በደማቅ ቀለማት ህብር እንዲገለጽ የባህላዊ ልብሶቹ ሚና ከፍተኛ ነው ብሎ ያምናል፡፡

በተለያየ ዲዛይን ከ500 በላይ የሚሆኑ የስልጤ ባህላዊ ልብሶችን እንደሠራ የሚናገረው ዴልታ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለወራቤ ሆስፒታል ምረቃ በተመሳሳይ መልኩ ብዙ ልብሶችን ሠርቷል፡፡ ‹‹ልብሱ ታይቶ ይኼ ልብስ የዚህ ብሔር የዚያኛው ብሔረሰብ ነው ሲባል ለባህል ልብሱ ባለቤት ዕውቅናና ክብር መስጠት ነው፡፡ የልብሶቹ በዚህ መልኩ መታወቅ ጥሩ ስሜት ይፈጥርብኛል፤›› ይላል፡፡

ምናልባትም በዞን ምክር ቤቶች እየፀደቁ ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ በብዛት እየታዩ ያሉት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልብሶች ቢሆኑም በአንድም ይሁን በሌላ ዲዛይን በሰሜኑ፣ በምዕራቡና ምሥራቁ የአገሪቱ አካባቢ ባህላዊ ልብሶችም በስፋት እየወጡ መሆኑ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ የጎንደር ከተማ ባህልና ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ የቅርስና የባህል እሴቶች ዋና የሥራ ሒደት አስተባባሪ አቶ ዘውዱ በላይ፣ ምንም እንኳ በምክር ቤት ደረጃ ይኼ ተብሎ የፀደቀ የባህል ልብስ ባይኖርም ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ነጭ ልብስ የአካባቢው ኅብረተሰብ የተቀበለው የባህል ልብስ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹ነጭ ልብሱ ጥንድ፣ ድርብ፣ ሸማ ወይም ካባ ሊሆን ጥበብ፣ ባለጥለትና ጥልፍም ሊሆን ይችላል፤›› የሚሉት አቶ ዘውዱ ባለሥልጣናትና ታዋቂ ሰዎች በሚገኙባቸው ስብሰባዎች ላይ ባህላዊ ልብሱ በተለያየ ዲዛይን የአፄ ፋሲል ቤተ መንግሥት የተጠለፈበት፤ ጎንደር ‹‹ወርቃማ ከተማ›› መሆኗ ይንፀባረቅ ዘንድ በቢጫ ሀር ተውቦ ታዳሚዎች እንዲለብሱት እንደሚደረግ ይናገራሉ፡፡ የፋሲል ቤተ መንግሥት ጥልፍ ብቻም ሳይሆን የራስ ግንብንና ሌሎቹንም የሚጠቀሙ ሲሆን ብዙ ጊዜም ስብሰባዎች ላይ ለሚደረጉ ኮፍያዎች ቢጫ ቀለም እንደሚመረጥ ይገልጻሉ፡፡

የሰቆጣ ከተማ የባህል ቱሪዝምና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መስፍን መኰንንም፣ በእነሱ አካባቢም ይህ የባህል ልብስ ነው ተብሎ የፀደቀ ነገር እንደሌለና ይልቁንም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ባህላዊ ልብስ የተለያዩ መድረኮች ላይ ባለሥልጣናትን ጨምሮ በብዙዎች እንዲለበስ እየተደረገ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ኮርቶ ቁምጣና ሸሚዝ፣ ሳሪያን ልብስ፣ ወንዝ አይፈሬና ሌሎችም እንደ ሁኔታው ሴትና ወንዶች እንዲሁም በተለያየ የዕድሜ ክልል የሚገኙ የሚለብሷቸው እንደሆኑና ባለሥልጣናትን ሳሪያን ኮት እንደሚያለብሱ ይናገራሉ፡፡

መንግሥታት አልባሳትን ለገጽታ ግንባታና የድጋፍ መሠረት ለመፍጠር በተለያየ መንገድ እንደሚጠቀሙ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በታሪክ፣ ሁለተኛውን ደግሞ በባህል ጥናት የሠሩት አቶ ስንታየሁ ኪዳኔ ያስረዳሉ፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የመሳፍንትና የመኳንንት ልብስ ከቀሪው የኅብረተሰብ ክፍል ልብስ የተለየ እንደነበር፣ በደርግ ሥርዓትም የኢሠፓ አባል የነበሩ እንደየደረጃቸው ውኃ ሰማያዊ፣ ደማቅ ሰማያዊና ካኪ ቀደም ያለው ልብስ ይለብሱ እንደነበር በማስታወስ በሥርዓቶቹ አልባሳቱ ሥልጣን ያለውን ከሌለው፣ በመለየትና ደጋፊት በማብዛት ጥቅም ላይ መዋላቸውን ይገልጻሉ፡፡

በኃይለ ሥላሴና በደርግ ሥርዓት ልብሶቹን ሊለብስ ከሚገባውና ከተፈቀደለት ውጪ መልበስ ይቻል እንደማይቻል የሚያስታውሱት አቶ ስንታየሁ፣ በኢሕአዴግ ነገሮች መቀየራቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹በፊት ገዢውና ተገዢው አንድ ዓይነት አይለብስም፡፡ እንደየደረጃው ሁሉም ሥልጣኑን በአለባበሱ ያሳይ ነበር፡፡ አሁን ግን ባለሥልጣን የሕዝቡን ልብስ እየለበሰ እንዳንተ እየለበስኩ፣ እየጠጣሁና እየበላሁ እያገለገልኩህ ነው እየተባለ ነው፤›› ልብሶቹ ለመንግሥት ገጽታ ግንባታና ድጋፍ ማሰባሰብ እየዋሉ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

በሌላ በኩል እሳቸው እንደሚሉት ለዚሁ ገጽታ ግንባታና ድጋፍ ማሰባሰብ የዚህን ሕዝብ ወይም አካባቢ ልብስ እንልበስ ሲባል የዚያ ማኅበረሰብና አካባቢ ባህላዊ ልብስ ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ወጥ ነገር ሲጠፋ ደግሞ አዲስ የማንነት መገለጫ ባህላዊ ልብስ እየተፈጠረ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ለዚህ በምሳሌነት ካነሷቸው የስልጤ ባህላዊ ልብስ አንዱ ነው፡፡

ከተለያየ ቀለም ህብር ተጨማሪ የማንነት መግለጫ ይሆን ዘንድ አዲስ ባህላዊ ልብስ ለመፍጠር ሸማ የተመቸ ሆኖ መገኘቱንና በተለያዩ አካባቢዎች የኔ ነው የኔ ነው አለመግባባቶች መስተዋላቸውን ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የካቲት አብዮት – ጥያቄዎችሽ ዛሬም እየወዘወዙን ነው!

በበቀለ ሹሜ አጭር መግቢያ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከ1960ዎች ወጣቶች ርዝራዦች አንዱ...

የሰሞኑ የ“መኖሪያ ቤቶች” የጨረታ ሽያጭ ምን ዓይነት ሕጋዊ መሠረት አለው?   

በዳዊት ዮሐንስ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አየር ላይ ከሚንሸረሸሩ ዜናዎች...

ሁለቱ ወጎች፡ ከሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! እስከ በዓሉ ቤርሙዳ

በተክለ ጻድቅ በላቸው ሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! ከሁለት ሦስት ዓመት...

ለትግራይ ክልል ድርቅ ተፈናቃዮች አፋጣኝና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ...