Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፖርት‹‹ዳኝነትን በአገራችን ሁኔታ ስናየው አንድ ሰው መደበኛ ሥራ ኖሮት በተጨማሪነት የሚሠራው ሙያ...

  ‹‹ዳኝነትን በአገራችን ሁኔታ ስናየው አንድ ሰው መደበኛ ሥራ ኖሮት በተጨማሪነት የሚሠራው ሙያ ነው›› ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ

  ቀን:

  እንደ እግር ኳሱ ሁሉ በአገሪቱ የእግር ኳስ ዳኞች ደረጃና ብቃት ቀድሞ ከነበረው አኳያ ዕድገት አለማሳየቱ ይነገራል፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት ሲነሳ የሚደመጠው ደግሞ ከአምስት ዓመታት በፊት የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) የአገሪቱ እግር ኳስ ከማንኛውም አህጉራዊም ሆነ ከዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ተሳትፎ እንዳይኖረው ለሁለት ዓመት ያህል ማገዱ ነበር፡፡ የእግር ኳስ ዳኞችም በተመሳሳይ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዳይዳኙ መደረጉም ይጠቀሳል፡፡ ያም ሆኖ ግን በአሁን ወቅት በአገሪቱ የሚገኙት የእግር ኳስ ዳኞች ብቃታቸውን ቀደሞ ወደነበረው መመለስ የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመራቸው እየታየ ነው፡፡ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ከአገሪቱ የእግር ኳስ ዳኞች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ዳኝነት ፈቃድ (ባጅ) ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ አግኝቷል፡፡ ይሁንና በወቅቱ የአገሪቱ እግር ኳስ በፊፋ ቅጣት የተላለፈበት በመሆኑ ምክንያት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የመምራት (የመዳኘት) ዕድል አልገጠመውም ነበር፡፡ በአገሪቱ ላይ የተላለፈው ዕገዳ ከተጠናቀቀ በኋላ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ግን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ወጣት ባለተሰጥኦ የዳኝነት ሥልጠናን እንደወሰደ፣ እንደገናም በ2005 ዓ.ም. የአዋቂዎች ‹‹ቢ›› ሥልጠና ከወሰደ  በኋላ በዚያው ዓመት ደግሞ አልጄሪያ ላይ በተደረገው ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የማጫወት ዕድል አግኝቷል፡፡ በ2006 ዓ.ም. ወደ አዋቂዎች ‹‹ኤ›› የእግር ኳስ ዳኝነት ደረጃ ተሸጋግሮ በደቡብ አፍሪካ በተደረገው የቻን ውድድር ላይ ተካፋይ እንደነበረም ይናገራል፡፡ በቅርቡ በኢኳቶሪያ ጊኒ አስተናጋጅነት በተከናወነው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይም አንድ ጨዋታ በዋና ዳኝነት አጫውቷል፡፡ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ከእግር ኳስ ዳኝነቱ ጎን ለጎን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሜዲካል ጥናትና በሶሺዮሎጂ የመጀመርያ ዲግሪ አግኝቷል፡፡ ይህም ለሙያው ትልቅ እገዛ እያደረገለት እንደሚገኝም ይናገራል፡፡ ደረጀ ጠገናውና ዳዊት ቶሎሳ አነጋግረውታል፡፡

  ሪፖርተር፡- የእግር ኳስ ዳኝነት ሥራ (በአማተርነት) የሚሠራ ከመሆኑ አኳያ እንዴት ትገልጸዋለህ?

  አቶ ባምላክ፡- የእግር ኳስ ዳኝነት ሙያ በኢትዮጵያም ሆነ በተቀረው ዓለም የሚሠራው በትርፍ ጊዜ ሥራ (በአማተሪዝም) ነው፡፡ አማተር ሲባል ደግሞ ለስፖርቱ ፍቅር ሊኖር ግድ ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን በተወሰኑ አንዳንድ የአውሮፓ አገሮች እግር ኳስ ዳኝነትን እንደ አንድ የሥራ ዘርፍ (ሙያ) አድርገው የሚሠሩት አሉ፡፡ ዳኝነትን በአገራችን ሁኔታ ስናየው አንድ ሰው መደበኛ ሥራ ኖሮት በተጨማሪነት የሚሠራው ሙያ ነው፡፡ ስለዚህም እኔም ስፖርቱን በተለይ እግር ኳስን በጣም ስለምወድና በልጅነቴም ምንም እንኳ ትልቅ ደረጃ ባልደርስም እጫወት ስለነበር በዚያው ፍላጎቱና ፍቅሩ ስላደረብኝ በዳኝነቱ ልቀጥልበት ችያለሁ፡፡

  ሪፖርተር፡- በልጅነትህ እግር ኳስን የመጫወት ሕልም እንደነበረህ ነው መረዳት የሚቻለው፡፡ እንዳትቀጥልበት ምን አገደህ?

  አቶ ባምላክ፡- በወቅቱ እኖር የነበረው መገናኛ አካባቢ ነበር፡፡ ከሠፈር ልጆች ጋር ለመጫወት ተጠራርተን በምንሄድበት ጊዜ በጣም ስለማልቀራረባቸው ጨዋታ ላይ ኳስ አይሰጡኝም ነበር፡፡ በዚያ ሁኔታ ደግሞ መቀጠል ስለማያዋጣ ትኩረቴን ሁሉ ወደ ትምህርቱ አድርጌ አንዳንድ ጊዜ ግን የሠፈር ልጆች የመሐል ዳኛ ሲፈልጉ የመሐል ዳኛ እየሆንኩ ጨዋታው እዳኝ ነበር፡፡ ቀስ በቀስም የእግር ኳስ ዳኝነት የሚለው ነገር ወደ ውስጤ ገባ ማለት ነው፡፡ ልጆቹ በጨዋታ ወቅት ገንዘብ እያስያዙ ይጫወቱ ስለነበር ከአሸናፊ ቡድን የማገኘው ገንዘብም ሙያውን እንዳዘወትር ከማድረጉም በላይ በውስጤ አድሮ ለሙያው ይበልጥ ትኩረት መስጠት እንድጀምር አስገድዶኝ ገባሁበት፡፡

  ሪፖርተር፡- ዳኝነት የትርፍ ጊዜ ሥራ ነው፡፡ ታዲያ እንዲህ ከሆነ ሙያውን ከማሳደግ አኳያ ችግር የለውም?

  አቶ ባምላክ፡- በእርግጥ መደበኛ ሥራና ዳኝነትን አብሮ ማስኬድ ይከብዳል፡፡ እንዲያም ሆኜ እዚህ ደርሻለሁ፣ አሁንም ደግሞ ትምህርቴን ስለጨረስኩ መደበኛ ሥራየንና ዳኝነቱን እኩል ለማስኬድ ብዙም አልከበደኝም፡፡ ሆኖም የዳኝነት ሙያ ልምምድ ይፈልጋል፣ ጨዋታዎችን መገምገም ይፈልጋል፣ ዋናውና ትልቁ ነገር ደግሞ ማንበብን ጨምሮ ትኩረትም ስለሚፈልግ በጥንቃቄ መንቀሳቀስ የግድ ነው፡፡ በትኩረት ለመሥራት ወይም ለመዳኘት በበቂ ሁኔታ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ በአግባቡ የዝግጅት ሰዓትን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ለዳኝነቱ ብዬ ማኅበራዊ ነገሮች ላይ ብዙውን ጊዜ አልሳተፍም፡፡ ያም ሆኖ ግን በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ተፅዕኖ ባያመጣብኝ ትኩረት ግን እሰጠዋለሁ፡፡

  ሪፖርተር፡- ዳኝነትን ወደ ተሻለ ደረጃ ወይም ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሻሻል የትርፍ ጊዜ ሥራ ተደርጎ መታየቱ ተፅዕኖ የለውም?

  አቶ ባምላክ፡- የግሌን አስተያየት ከተባልኩ ዳኝነትን የምሠራው በፈቃድና በፍላጎት እስከሆነ ድረስ ፕሮፌሽናል ከሆኑት ዳኞች አሳንሼ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አማተርም ሆነ ፕሮፌሽናል እንቅስቃሴውን የሚቆጣጠሩበት የአመለካከት ልዩነቱ ያለው ጊዜን መቆጣጠሩ ላይ ነው፡፡ እርግጥ አማተር የሆነ ዳኛ ፕሮፌሽናል ዳኛ የሚሰጠውን ጊዜ ሰጥቶ ላይሠራ ይችላል፡፡ የሁለቱም መለኪያዎችን ስናይ ግን አንድ ነው፡፡ ዋናው ነገር ስህተትን ማረምና የሙያውን ሥነ ምግባር በመጠበቅ በትኩረት መከታተልና መመልከት ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ከእግር ኳስ ዳኝነት ጋር ተያይዞ በአገሪቱ ያልተለመዱ፣ ለዳኝነት ሥራ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ከሌሎች በተለየ መልኩ ስትጠቀም ትታያለህ፡፡ ለምሳሌ  ኤሌክትሮኒክስ ፍላግና ቾክ የመሳሰሉት መሣሪያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህን በኢትዮጵያ ደረጃ በሰፊው ለማግኘት ያስቸግራል፡፡ አንተ ግን ስትጠቀምባቸው ይታያል፡፡

  አቶ ባምላክ፡- በዚህ የሥራ ዓለም ውስጥ ሆኜ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ዳኞች ጋር የመገናኘቱ ዕድል ገጥሞኛል፡፡ በዚህ ምክንያት ከሰዎቹ ጋር በመግባባትና በመጠየቅ እንዲመጣልኝ አደርጋለሁ፡፡ በዚህ መሠረት እንደ ስፕሬይና ሌሎችንም ዓይነት ኦርጂናል የሆኑ ዕቃዎችን በማስላክና በመግዛትም ጭምር ለማግኘት ጥረት እያደረግኩ እጠቀማለሁ፡፡ በተጨማሪም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ራሱ የሚያደርግልኝ እገዛዎች አሉ፡፡

  ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ስትካፈል አንተ በዛ ውድድር ላይ አልተጋበዝክም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን  ተካፋይ በሆነበት የእግር ኳስ ዋንጫ በዳኝነት አለመጋበዝህ የፈጠረብህ ስሜት የለም?

  አቶ ባምላክ፡- በወቅቱ በነበረው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በዳኝነት ከተሳተፉት ዳኞች መካከለ ወደ አዋቂ (ኤሊት) ‹‹ኤ›› ደረጃ በተሸጋገርኩበት ጊዜ አብረውኝ ያደጉ ዳኞች ነበሩ፡፡ ከዚህ በመነሳት እመደባለሁ የሚል ተስፋ ስለነበረኝ ሥልጠናውንም ወስጄ ነበር፡፡ ምርጫ ውስጥ ግን መካተት አልቻልኩም፡፡ ምክንያቱም ማሻሻልና ማስተካከል ያለብኝ ነገሮች ነበሩ ማለት ነው በሚል ተቀብየዋለሁ፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተሳተፈበት በዚያ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ አለመገኘቴ በጣም በጣም ከሚቆጩኝ ነገሮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ምክንያቱም የአገሬ ቡድን በሚሳተፍበት ትልቅ ዝግጅት ላይ አለመገኘት እውነቱን ለመናገር ያስቆጫል፡፡

  ሪፖርተር፡- በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከዳኝነት ጋር በተያያዘ ምን ጠንካራና ደካማ ጎን ተመለከትክ?

  አቶ ባምላክ፡- ጨዋታው ሁሉም ሰው እንደተከታተለው አልፎ አልፎ ከታዩ አላስፈላጊ ችግሮች በስተቀር በግሌ ብዙ ነገር ተምሬበታለሁ ማለት እችላለሁ፡፡ በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ጭምር ትምህርት ወስጄበታለሁ፡፡

  ሪፖርተር፡- በካፍ ውስጥ ከዳኝነት ምደባ ጋር አድሎ እንዳለ የሚያምኑ አሉ፡፡ እንዲያውም ኢትዮጵያውያን ዳኞች በአህጉራዊው መድረክ ተከታታይ ምደባ የማያገኙበት ምክንያት ካፍ ውስጥ ኢትዮጵያን የሚወክል ሰው ስለሌለ ነው ብለው የሚያምኑ ሰዎች አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለህ አስተያየት ምንድን ነው?

  አቶ ባምላክ፡- ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት፣ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሳልመደብ የቀረሁት በእኔ በኩል የሚጎድለኝ ነገር ወይም ያላሟላሁት ነገር እንደነበረ ነው፡፡ በወቅቱ ለተከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ የተሟላ ብቃት ላይ ተገኝቼ ቢሆን ኖሮ ምደባው እንደማያልፈኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ከዚህ አኳያ በሚባለው ነገር አላምንም፣ ምክንያቱም ከሠራሁና የተሟላ ብቃት ላይ ነኝ ብዬ ካመንኩ የማልመረጥበት ምክንያት ይኖራል ብዬ ስለማልገምት ነው፡፡ ለማጠቃለል ብቁ ሆኖ ለመገኘት ሙያው የሚጠይቀውን አሟልቶ መሥራት ያስፈልጋል፤ እምነቴም ይኼ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- በአህጉር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ መታየት ጀምረሃል፡፡ የሚቀርህ ዓለም ዋንጫ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የምትለው ይኖርሃል?

  አቶ ባምላክ፡- በየትኛውም መመዘኛ ቢሆን ለዓለም አቀፍ የዳኝነት ደረጃ ለመብቃት ብዙ ችግሮችን ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ እኔም እነዛን ችግሮች በመቋቋምና ጠንክሬ በመሥራት ዓለም አቀፍ ደረጃ የዘንድሮውን የአፍሪካ ዋንጫ አንድ ብዬ ጀምሬያለሁ፡፡ ከዚህ አኳያ ቀጣይ ዕቅዴ አንድ ዳኛ ዓለም አቀፍ ዳኛ የሚያስብለውን፣ ቢያንስ በትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ለመምራት መብቃት አለብኝ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ለዚያ ደረጃ ለመብቃት የቀሩኝን ጉድለቶች ለማሻሻል ጠንክሬ መሥራት የምፈልገው፡፡

  በዳዊት ቶሎሳ

   

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...