Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ኧረ ይኼ የተሽከርካሪ አደጋ አንድ ይባል፡፡ እኔ በበኩሌ ከወባም ሆነ ከኢቦላ፣ ከኤችአይቪም ሆነ ከጠኔ የበለጠ ሕዝብ ሊፈጅ የተቃረበ አደገኛ መቅሰፍት እየሆነብኝ ነው፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ የምናየው ጥድፊያና ውክቢያ ከመሠረታዊ የአነዳድ ሕግጋት ውጪ እየሆነ ነው፡፡ ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ ውስጥ ያሉ ሕሙማን ይዞ ከሚጋልበው አምቡላንስ ጀምሮ፣ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን ተሸክሞ እንደ ልቡ ከሚያጓራው ሲኖትራክ (ቀይ ሽብር) ድረስ የሰው ሕይወት እየተቀጠፈ ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ለእግረኛ ቅድሚያ ባለመስጠትና የእግረኛ መንገድ ላይ ወጥቶ መግደል ወይም አካል ማጉደል የተለመደ ክስተት ሆኗል፡፡ ዜብራ ማቋረጫ ቅድሚያ ለማን እንደሆነ የማያወቁ አሽከርካሪዎች የበዙበት አገር ውስጥ ነው ያለነው፡፡

ከቀናት በፊት ሥራ አምሽቼ ወደ ቤቴ ስጓዝ ከፊቴ ቪትዝ መኪና የያዘ ጎረምሳ የመንገዱን መሀል ይዞ እየነዳ ይጓዛል፡፡ አንዴ ወደ ቀኝ አንዴ ወደ ግራ መኪናውን እየጠመዘዘ እንደ ሕፃን ልጅ ሲጫወት ላየው ጤንነቱ ያጠራጥራል፡፡ ቢቸግረኝ በመብራት ምልክት መስጠት ጀመርኩ፡፡ ወይ ፍንክች፡፡ ሲብስብኝ የማይደረገውን በጥሩምባ ምልክት ሰጠሁት፡፡ ግራ እጁን አውጥቶ የመሀል ጣቱን አሳየኝ፡፡ ከዚህ ጋር እልህ መጋባቱ ጥሩ ስላልሆነ ፍጥነት ቀንሼ መንዳት ጀመርኩ፡፡ ካበደ ጋር ማን ያብዳል?

ቫቲካን ኤምባሲን አልፌ ትንሽ እንደተጓዝኩ ባለቪትዙ ከሚኒባስ ታክሲ ጋር ተጋጭቶ መንገድ ዘግቶ ደረስኩ፡፡ የታክሲው የኋላ ክፍል በተለይ የግራ ፍሬቻውና አካሉ የተጎዳ ሲሆን፣ የቪትዙ የፊት ክፍል እንዳልነበረ ሆኖ ኮፈኑ መስተዋቱን ጋርዶታል፡፡ መኪናዬን ጥግ አቁሜ ወደ ተሰበሰቡት ሰዎች ሳመራ የቪትዝ አሽከርካሪው መሬት ላይ ቁጭ ብሏል፡፡ ተንጠራርቼ ሳየው አስመልሶታል፡፡ ዙሪያውን የከበቡ ሰዎች መስከሩን ነገሩኝ፡፡ በእርግጥም የጠጣው አልኮል አፍንጫ ይጋረፋል፡፡ አንድ የትራፊክ ፖሊስ ባልደረባ መጥቶ ሥራውን ሲጀምር እኔም እንደምንም ብዬ ሾልኬ ከአካባቢው ርቄ ሄድኩ፡፡ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ሳይሆን አንድ ሰካራም ያደረሰው አደጋ በሕይወት ላይ ጉዳት ባያደርስም፣ መንገዳችን ግን በእነዚህ መሰሎች ሞትን ይተፋል፡፡ አካል ያጐድላል፡፡ ንብረት ያወድማል፡፡

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ዕድሜያቸው አካለ መጠን ያልደረሱ ታዳጊዎች ተሽከርካሪ ይይዛሉ፡፡ የመንጃ ፈቃዱን ከየት አገኙት? ትናንት ሞፈርና ቀንበር አስቀምጦ የመጣ አርሶ አደር በአንዴ አራተኛና አምስተኛ ፈቃድ ይዞ ሲኖትራክ ወይም ባለተሳቢ መኪና ይነዳል፡፡ ለምን? ድሮ የምናውቀው ከሁለተኛ ተነስቶ አምስተኛ መንጃ ፈቃድ ለመያዝ ቢያንስ ከስምንት ዓመታት በላይ ይፈጅ ነበር፡፡ አሁን 18 ዓመት ያልሞላው ጎረምሳ እንዴት ሆኖ ነው ሲኖትራክ የሚነዳው? በለብለብ ሥልጠና መንገዱን የጦር ሜዳ የሚያደርጉ ሰዎች መብዛታቸው ካላሳሰበ ምን ያሳስባል?

ለዚህ እንደ አብነት የምጠቅሰው ምሳሌ ይኖረኛል፡፡ የቀላል ባቡር መስመሩ ከሚሠራባቸው ቦታዎች አንዱ የሆነው የኃይሌ ገብረ ሥላሴ ጎዳና ነው፡፡ ሃያ ሁለት ማዞሪያ ሳይደርስ ዘሪሁን ሕንፃ አካባቢ አንድ ጎረምሳ ሲኖትራኩን እየጋለበ (እየነዳ አይባልም) በፍጥነት ይገሰግሳል፡፡ የባቡር ፕሮጀክቱ ሠራተኛ ቀስ በል እያለው በእጁ ምልክት ያሳየዋል፡፡ ጐረምሳው ሾፌር እያፌዘበት አልፎት ሰላሳ ሜትር ሳይጓዝ በአፍ ጢሙ የተቆፈረ አነስተኛ ጉድጓድ ውስጥ ሲኖትራኩን ይተክለዋል፡፡ የተናደደው ሠራተኛ እየሮጠ ሄዶ በሩን ከፍቶ ሾፌሩን ጐትቶ እያወጣው፣ ‹‹ሰው ሲነግርህ ለምን አትሰማም?›› ሲለው ጎረምሳው ሾፌር፣ ‹‹እባክህ አታካብድ!›› እያለ ማፍጠጥ ጀመረ፡፡ ይህንን ምን ይሉታል? እንዲህ ዓይነቱ ደንታ ቢስ ነው መንገዳችንን ሞት የሚዘራበት፡፡

ባለፈው ሳምንት ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ ከኤርፖርት ከውጭ የመጡ ጓደኞቼን ተቀብዬ ወደሚያርፉበት ቀበና አካባቢ ስወስዳቸው፣ ቀበና አደባባዩ ላይ አስገራሚ ነገር ገጠመኝ፡፡ የአንድ የታወቀ ሆቴል (የሆቴሉን ስም መጥቀስ አልፈልግም) የሠራተኞች ሰርቪስ ሚኒባስ ከጀርመን ኤምባሲ አቅጣጫ ይመጣል፡፡ እኔ ዋናውን መንገድ ይዤ አደባባዩን ሳቋርጥ በጣም ይጠጋኛል፡፡ በጣም ተናድጄ ስለነበር የሐዛርድ መብራቱን ብልጭ ድርግም ሳደርግበት መቆም ሲገባው፣ አደባባዩን በተቃራኒ መንገድ (በሕገወጥ መንገድ) ዞሮ ወደ መገናኛ አቅጣጫ በረረ፡፡ እሱ ይህንን ሕገወጥ ድርጊት ሲፈጽም ከአራት ኪሎ አቅጣጫ የሚመጣ ፍጥነት ያለው መኪና ቢኖር ኖሮ የሆቴሉ ሠራተኞች አይተርፉም ነበር፡፡ ለታወቀ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል የሚሠራ ሾፌር እንዲህ ካበደ ከሌላው ምን ይጠበቃል?‹‹አደባባዩን በመዞር ላይ ያለ ተሽከርካሪ ቅድሚያ ይሰጠዋል›› የሚለው ሕግ ቀረ? ወይስ በደመነፍስ ነው የምንኖረው?

ሰሞኑን እያየነው ያለው ሌላው ትዕንግርት ደግሞ ያሳስባል፡፡ የከተማ ቀላል ባቡር የሙከራ እንቅስቃሴ በጀመረበት አካባቢ አደጋዎች እየታዩ ነው፡፡ ለባቡሩ መስመር ማገጃ የተሠራውን አጥር እየጣሱ ተሽከርካሪዎች አደጋ እያደረሱ ነው፡፡ ያኔ የቀለበት መንገዱ ሥራ ሲጀምር ስንትና ስንት ዜጐቻችን እንዳለቁ አንዘነጋውም፡፡ አሁን ደግሞ አንዴ ፒክአፕ ሌላ ጊዜ የጭነት መኪና የባቡሩን አጥር ጥሰው ገብተዋል፡፡ ባቡሩ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የሚደርሰውን አደጋ ሳስበው እሳቀቃለሁ፡፡ ይህንን ሥጋቴን የነገርኳቸው አዛውንት ጎረቤቴ፣ ‹‹መኪናውም ባቡሩም ቀርቶብን በበቅሎና በፈረስ ብንጠቀም አይባል ጥሩ አይደለም፡፡ እኔ መንግሥትን ብሆን ኖሮ ግን መንጃ ፈቃድን ዲግሪ አድርጌ ከዚያ በኋላ የአዳሜ ጉዱ ይታይ ነበር፤›› አሉኝ፡፡ ምራቁን የዋጠ ሰው እንዲህ አርቆ ሲያስብ የሚመለከተው አካል ምን ነካው?

(ሮቤል ጉግሳ፣ ከጀሞ)  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...